ዝም ለማይሉ!

Views: 209

የኪነጥበብ ባለሞያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ትልቅ ድርሻ ሊጫወቱ ይችላል። ምንም እንኳ በበቂ ሁኔታ ባይሆንም፣ በአገራችን የተለያየ ጊዜ ይህን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ታዝበናል። በተፈለገ ጊዜ ጥበባዊ ሥራቸውን ከማቅረብ ተቆጥበውና ሰስተው ባያውቁም፣ ከዛም በላይ እውቅናቸው፣ ዝና እና ተጽእኖ የመፍጠር አቅማቸው የበለጠ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉበት እንደሆነ ግን እሙን ነው።

በርካቶቹ የጥበብ ባለሞያዎች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ለተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ንቅናቄዎች አምባሳደር መሆናቸው ይታወቃል። በዚህም እጅግ ሊመሰገኑ የሚገቡ መሆናቸው ያስማማል። እውነት ነው! ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋልና ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በውጪ አገራት ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የኪነጥበብ ባለሞያዎችን ስንመለከት፣ እንደውም ከራሳቸው አልፈው ለአፍሪካና ለተቸገሩ አገራት ድጋ ማሰባሰብ ላይ ይሳተፋሉ።

ከሰሞኑ አዲስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በተለይም በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቤት መቀመጥ ግድ ማለቱን ተከትሎ በሕጻናትና በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ብዙዎችን አስቆጥቷል። ይህንንም ተከትሎ የፊልም ባለሞያዎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ታዝበናል። ጥሩ ነው! እንቅስቃሴ የሚጀምረው ‹አቤት!› ብሎ ከመነሳት ነው።

እስከዛሬ አለመሆኑ በእርግጥ የሚያስከፋ ነው። በአሳዛኝና አሰቃቂ ሁኔታ በደል የደረሰባቸው ሴቶች በጥቃት ሕይወታቸው ሲነጠቅ ታዝበናል። በተጓዳኝ ለሴቶች መብት ጠበቃ ነን የሚሉና የሴቶች ጉዳይ አጀንዳ በሆነበት አውድ ሁሉ የሚገኙ ሰዎችን እናውቃለን። ወይ አልተከታተልኩኝ ከሆነ አላውቅም፣ ግን ምንም ሲናገሩ አይታይም። አስተባባሪ ወይም ጠሪ የሆነ ከጥበብ ዘርፍ ውጪ የሆነ ገለልተኛ ለምን እንደሚያስፈልግ አላውቅም። ግን ብዙ ጊዜ አነሳሽ ይፈለጋል።

አሁን የኪነጥበብ ባለሞያዎች ይልቁንም ሴቶች ‹ዝም አንልም!› ብለዋል። እስከመቼ ዝም ሳይሉ እንደሚቆዩና ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ምን ያህል ለመታገል ጽናት እንደሚኖራቸው መገመት አልችልም። ግን ጸንተው እንዲቆዩ ምኞቴ ነው። ወደድንም ጠላንም ተጽእኖ መፍጠር ይችላል። አድናቂና ወዳጅ አላቸው። ተሰሚም ሊሆኑ ይችላሉ፣ ያላቸውን አቅም ካወቁ።

የፊርማ ማሰባሰብ ሥራዎች ጀምሮ፣ ግንዛቤ ማጨበጫዎች፣ በአረአያነትና በምሳሌነት ሊከወኑ የሚችሉ ተግባራት ወዘተ ቀላል የማይባል ተጽእኖ መፍጠር የሚቻልባቸው መንገዶች ናቸው። ሕዝቡ ጋር ብቻ አይምሰላችሁ፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃም እውቅና ያላቸው ሰዎች የተሰሚ እድል አላቸው። የሚያከብራው ጥቂት አይደለም፣ ያንን አጋጣሚ ለለውጥ ሊጠቀሙበት የሚያስችል እድል ሰፊ ነው።

አሁንም ታድያ የተጀመረውን ዝም አንልም እንቅስቃሴ ከቃልና ከአፍ በዘለለ፣ በተግባርና በጽናት ማሳየት ተገቢ ነው። አንዳች እንከን ሲገኝባቸው ተናጋሪና ተቆጪ፣ ፈራጁ እንዳለ ሁሉ በዛው መጠን በጎ ሥራውንም የሚመለከት አለ። ተከትሏቸው ሊያደርግ የሚሻውም እንደዛው።

አሁን ይህን የሴቶችን ይልቁንም የሕጻናትን ጉዳይ አጥብቀው እንዲይዙ ይጠበቃል። ሴቶችን በሚመለከት ያለው አመለካከት እንዲጸዳ ከሚሠራቸው ፊልሞችና ከሚወክሏቸው ገጸባህርያት ጀምሮ ልብ ሊሉ ይገባል። ያ በሰዎች አእምሮ ላይ የሚያኖረው አሻራ ቀላል አይደለምና። በእውናዊ ዓለምም ሕግ እንዲሻሻል፣ ሴቶችን እንዲጠብቅና ሴት መውለድ የማያስፈራበት አገር እንዲሆን ‹አቤት!› ማለት ይገባቸዋል። እርሱንም በጽናት እንዲያደርጉት እየጠየቅን፣ እንጠብቃለንም።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com