የእለት ዜና

በአማራ ክልል ከ350 በላይ አዲስ ኢንዱስትሪዎች በኃይል እጥረት ምክንያት ሥራ መጀመር አልቻሉም

የኢትዮጵያን የዘይት ዕጥረት ይቀርፋሉ የተባሉ ፋብሪካዎችም ይገኙበታል

በአማራ ክልል ከ350 በላይ የሚሆኑ አዲስ ኢንዱስትሪዎች በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት የግንባታ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ቢያጠናቅቁም ወደ ሥራ መግባት አለመቻላቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የኃይል አቅርቦት ሳይሟላላቸው ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎችም በዚሁ ችግር በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አለመሆኑ ተጠቁሟል።

በተለይ በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ ዘይት እጥረት እንደሚፈቱና የኢትዮጵያን ፍላጎት አጥግበው ለውጭ ገብያ ይተርፋሉ ተብለው የታሰቡ በክልሉ የተገነቡ ኹለት ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች፣ የዚሁ ችግር ሰለባ መሆናቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይሄነው አለሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በመሆኑም ከፋብሪካዎቹ ከፊታቸው የኃይል አቅርቦት ችግሩ እንደተጋረጠባቸውና ትኩረት እንደሚሹ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የአገሪቱን ችግር ይቀርፋሉ ተብለው ከታሰቡት በክልሉ ከተገነቡት የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅስው፣ ነገር ግን የምርት ሥራ በመጀመር ላይ ለሚገኘው ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ለማምረት የሚስችል የኃይል አቅርቦት ማቅረብ አመቻሉን እና ከሚፈልገው የኃይል አቅርቦት የቀረበልት ግማሽ ያክሉ ብቻ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ይህም ፋበሪካው የታሰበለትን ያክል ምርት ማምረት እንደማይችልና ማምረት ከሚችለው አቅሙ ግማሽ ያክሉን ብቻ ለማምረት እንደሚገደድ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኃይል አቅርቦት እጥረት በአገር ደረጃ ያለ ቢሆንም በአማራ ክልል ግን ችግሩ እጅግ የከፋ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም ምክንያት ያሉትን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ ፣ አንደኛው ምክንያት በክልሉ ያሉ አጠቃላይ ሰብስቴሽኖች (መለስተኛ የኃይል ማከፋፈያዎች) 26 ስድስት ብቻ መሆናቸና ለክልሉ ከሚያሳፈልገው የኃይል አቅርቦት አንፃር አናሳ መሆኑን በኃይል እጥረት የሚወሰድ፣ ሲሆን በሌላ በኩል የግብአት ችግርና የማስተላለፊያ መስመሮች ጥራት መሆናቸውን አመላክተዋል።

መተጨማሪም ለክልሉ ፍትሐዊ የኃይል አቅርቦት እንዳልደረሰው እና ክልሉ ከሌሎች ክልሎች አንፃር ያለው የኃይል አቅርቦት መጠን ክፍተት እንዳለበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ይህ ችግር በክልሉ ላይ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ እና የክልሉ መንግስት በዋና ችግርነት ገምግሞ ቅሬታ ያቀረበበት ጉዳይ አንደሆነና መስተካከል እንዳለበት ይሄነው አክለው ጠቁመዋል።

እንዲሁም በክልሉ ካሉት 26 ሰብስቲትዩሽኖ(ማከፋፈያዎች) 16ቱ የአገልግሎት ጊዜቸው ብዙ አመታትን ያስቆጠረ መሆኑና የኃይል መሸከም አቅማቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት እነዚህ በክልሉ ያሉ 16 ማከፋፈያዎች በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የግንባተ ሥራቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ለመግባት የኃይል አቅርቦት የሚፈልጉ ፕሮጀክቶች ችግር ለመፍታት ጠጨማሪ ኃይል እንደሚስፈልግም ተመላክቷል።
በክልሉ ያለውን የኃይል አቅርት እጥረትን በጊዜያዊነት ለመፍታት ትርፍ የኃይል አቅርቦት ያለበትን አካባቢ እጥረት ወደ አለበት ማዛዋር፣ በቴክኒክ ብልሽት የቆሙ ማከፋፈያዎችን በማስጠገን ወደ ስራ ማስገባት፣ ማከፋፈያዎችን ማስፋፋትን በአጭር ጊዜ መፍትሔ መወሰዱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በግል ባለሀብቱ የሚለሙ ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ጥሬ ዕቃ አስገብተው በመብራት እጥረት ወደ ኪሳራ መግባታቸውም ተገልጿል።

ችግሩን ለመፍታት በክልሉ ካሉት 26 ማከፋፈያዎች በተጨማሪ በደብረ ብርሃን አዲስ ማከፋፈያ በቅርቡ እንደተገነባ እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ተጨማሪ ማከፋፈያዎችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በክልሉ ካሉው የኢንቨስትመንት አንቅስቃሴ አንፃር ወደፊትም ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እንደሚሰፈልግ ተጠቁሟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!