ፍቅር – በዘመነ ኮቪድ 19

Views: 286

‹‹ሰርጋችንን ጥር ውስጥ እናድርገው ወይስ ሚያዝያ በሚለው ትንሽ ተከራክረን ነበር። የእኔ ሐሳብ አሸንፎ ሚያዝያ ውስጥ ልናደርግ ተስማምተን ለቤተሰብ አሳወቅን። ይኸው በወረርሽኙ ምክንያት ግን ድግሱ ቀረ። ኹለታችን ብቻ ግን ጋብቻችንን ፈጽመናል።›› አለች፤ በ2012 ልትመሠርት ያሰበችውና የወጠነችውን ትዳር በሰርግ ለማጀብ አስባ ያልተሳካላት የአዲስ ማለዳ ባለታሪክ።

ሳሮን (ሥሟ የተቀየረ) ሰርግ ብዙ ትጓጓለት ያልነበረ ክዋኔ እንደነበር ጠቅሳለች። ‹‹ወጪና ድካም ነው። የተወሰነ ሰው ሰብሰብ አድርጎ እወቁልኝ ማለት ይበቃል ብዬ ነበር የማስበው። በቤተሰብ ግፊትና በሂደት ግን ሐሳቤን ቀይሬ ነበር።›› ስትልም ታስታውሳለች። ሳሮን ከአሁን ባለቤቷ ጋር ሦስት ዓመት በእጮኝነት ያሳለፉ ሲሆን፣ ሰርግ የመደገስ ፍላጎታቸው ግን እምብዛም እንደነበር ነው አያይዛ ያነሳችው።

‹‹በወረርሽኙ ምክንያት እንደማይከናወን ሳውቅ ነው መሰለኝ፣ የሚፈልገውን እንደተከለከለ ሕጻን በጣም ነበር የከፋኝ (ሳቅ)። ቢሆንም ሕይወትና መኖር ይቀድማል። ሁሉም ነገር ጤና ካለ ይደርሳል። እኛም በጤና ካለፍን ኻያ እና ሃምሳ ዓመት የትዳር ዓመታችንን ደግሰን እናከብራለን።›› ስትል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ፣ ፈገግታ በሞላው ገጽታ ትናገራለች።

‹‹በእርግጥ በእኛ አገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ሆነ የእንቅስቃሴ ገደቡ ላይ በጣም ጫና አልተደረገም። እንጂ ውጪ አገር እንደምንሰማው ጥብቅ ቢሆንና በተለይም ከባለቤቴ ጋር ሳንጋባ በፊት ይህ ቢሆን ኖሮ፣ በየቀኑ መገናኘት ለምደን ይከብደን ነበር። እንዴት ሊያልፍ እንደሚችል መገመትም ይከብዳል።›› ስትልም ታስረዳለች። ያም ብቻ አይደለም፣ የእንቅስቃሴ ገደቡ ጥብቅ ቢሆን ኖሮ፣ አዲስ ወዳጅነቶችን መመሥረት፣ የፍቅር አጋር መያዝና መተዋወቅ በራሱ ፈተና ውስጥ ይወድቅ ነበር።
አዲስ ማለዳ ይህን ታሪክ ከሰማች በኋላ የተለያዩ ድረገጾችን አገላብጣለች። በተለይም ‹ፍቅር በኮሮና ዘመን› ስትል ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ በተለይም የእንቅስቃሴ ገደብ ፍጹም ጥብቅ በነበረባቸው አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ምን ታየ፣ ምን ተሰማ የሚለውን ቃኝታለች።

ፍቅር እስከ መቃብር
በትዳር 71 ዓመታትን ቆይተዋል። ‹ዓመት ዓመት ያድርስልን፣ ያዝልቃችሁ!› ሲባልና ሲመረቅ የቆየ ትዳራቸው፣ ሰባ አንድ ዓመታትን ተሻግሯል፣ መዳረሻው ግን ከኮሮና ወረርሽኝ ዘመን ላይ ሆነ። በአምስት ቀናት ልዩነትም ጥንዶቹን ሞት አከታትሎ ወሰዳቸው። የኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም መገናኛ ብዙኀንም ይህንን ዜና አሰምተው ተናገሩ።

ባለትዳሮቹ ፓት እና ሮን ውድን ይባላሉ። ፓት የ91 ዓመት ወይዘሮ ሲሆኑ፣ ሮን ደግሞ 94 ዓመታትን በምድር ቆይተዋል። አንዲት ብቸኛ ሴት ልጅ ያፈሩ ሲሆን፣ ሴት ልጃቸው በእናትና አባቷ ተከታትሎ መሞት ዙሪያ በሐዘኗ መካከል ወርዚንግ ሄራልድ ለተባለ በጣልያን የሚገኝ ጋዜጣ አስተያየቷ ሰጥታ ነበር።

እንዲህም አለች። ‹‹ሕክምና ይሰጧቸው የነበሩ የሕክምና ባለሞያዎችንና ሆስፒታሉን አመሰግናለሁ። እማዬና አባዬ ኹለቱ ብቻ በአንድ ክፍል በተቀራራቢ አልጋ ላይ እንዲሆኑና እጅ ለእጅ እንዲያያዙ አድርገዋል፤ ፈቅደዋል። ይህም እናታችን እንቅልፍ ይዟት በነበረበት በዛው ከመሞቷ አራት ቀን በፊት ነው። እርሷ ከሞተች በኋላም አባቴን ሲንከባከቡት ነበር።›› ብላለች።

ጥንዶቹ እንዲሁ በተፈጥሮ ሞት አልፈው ቢሆን፣ ዜናቸው በዚህ መልክ ሊሰማ ባልቻለ ነበር ያሉም አልጠፉም። በኮሮና ዘመን ግን የእነዚህ ጥንዶች የፍቅርና የትዳር ታሪክ ለመነገርና ለመሰማት በቃ። ትውውቃቸውም ተተረከ።

ሮን የ22 ዓመት እንዲሁም ፓት ደግሞ የ19 ዓመት ወጣት ሳሉ ነው የተዋወቁት። እኚህ ጥንዶች ኹለት የልጅ ልጅ ሲያዩ፣ ለአራት ልጆች ቅድመ አያት መሆን ችለዋል።

ፍቅር በዐይን ይገባል!
ፒውፕል ዶት ኮም የተሰኘ ድረ ገጽ በዘመነ ኮሮና ስለተከሰተ አንድ የፍቅር ታሪክ እንዲህ አስነበበ። በጣልያኗ ቬሮና ከተማ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ ታውጆ በነበረበት ወቅት ኹለት ወጣቶች አሻግረው በመኖሪያቸው ሕንጻ መስኮት በኩል ተያዩ። ዘገባዎች እንደ ሮሚዮ እና ጁልየት ያለ ታሪክ ተደገመ ሲሉ ነው በገጾቸው ላይ ይህን ታሪክ ያወጡት።

እንዴት ተያዩ? የሚለውን የሚጠይቁ ሰዎች አሉ። እንዲህ ነው፤ እርሱ ማይክል አልፓዎስ ይባላል፤ እርሷ ፓውላ አግኔሊ። የፓውላ እህት ቫዮሊን ተጫዋች ናት። ታድያ ከኮቪድ 19 እለታት በአንዱ ቀን፣ ቫዮሊኗን ይዛ በመስኮት ወጥታ ለአካባቢው ሰው ሙዚቃውን ማሰማት ጀመረች።

በመካከል ወጣቱ ማይክል ይህን ድምጽ ተከትሎ አንገቱን አቀና። አስቀድማ ዐይኗን ጥላበት የነበረችውን ሴትም ተመለከተ። ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ቫዮሊን ከምትጫወተው አጠገብ ውብ የሆነች ሴት ተመለከትኩኝ። እንዳየኋት ነበር የወደድኳት።›› አለ። እናም ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ፈልጎ አገኘኛት፣ መልእክት ላከላት። ታድያ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት አክሎ አለ፤ ‹‹‹ፍቅር በኮሮና ዘመን› የሚል መጽሐፍ ሳልጽፍ አልቀርም!›› የሚገርመው ታድያ ፓውላም እህቷ ቫዮሊኑን ስትጫወት አጠገቧ በቆመችበት ሰዓት ማይክልን ከርቀት ተመልክታ ‹‹እንዴት ያለ መልከ መልካም ሰው ነው›› ብላ ለአፍታ አስባው እንደነበር አልደበቀችም።

ታድያ በጣልያን የእንቅስቃሴ ገደቡ ላላ ማለቱን ተከትሎ እነዚህ ጥንዶች ተገናኝተዋል። ሲገናኙም በርቀት በመተያየት ውስጥ አንዳቸው ሌላቸውን ሲጠብቁ በነበሩበት ሁኔታ እንዳገኙ ነው ዘ ታይምስ ለተባለ አውታር ያስረዱት። ከቤተሰቡ ጋር ይኖር የነበረው ማይክል፣ ከእህቷ ጋር የቆየችው ፓውላም አሁን በጋር ኑሮ ለመመሥረትና ጎጆ ለመውጣት ወስነዋል። በሳምንታት የዐይን ለዐይን ትውውቅ ብቻ።

የአንደኛ ዓመት ትዝታ
ይህ ደግሞ በኢንግሊዝ የተከሰተ ታሪክ ነው፤ ታሪኩን አውጥቶ የዘገበው ደግሞ ሲኤንኤን ነው። ጄምስ ማርሽ እና ፍቅረኛው ኬይራ ሊፐር የተገናኙበትንና የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩበትን የመጀመሪያ ዓመት ሊያከብሩ ነበር። ከእለቱ ቀድመው የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚችል ቢያውቁም፣ በፍጥነት ይሆናል ብለው ግን እርግጠኛ አልነበሩም።

ግን ሆነ። አንደኛ ዓመታቸውን ሊያከብሩ በሚገባቸው እለት፣ እንግሊዝ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች። በየቀኑ በአካል የአብሮነት ጊዜን የሚያሳልፉ የነበሩት ፍቅረኛሞች፣ አሁንም በማኅበራዊ መገናኛዎች ነው ግንኙነታቸውን የቀጠሉት። በተገኘው አማራጭም እየተያዩ ያወራሉ፣ ይነጋገራሉ።

‹‹ምን ያደርጋል ኢንተርኔት ኔትወርኩ ቢያመጣ
መገናኘት ነበር ናፍቆት የሚያወጣ›› ቢሉም፣ የተገኘውን እድል ሁሉ ከመጠቀም ግን ወደኋላ አላሉም። አንደኛ ዓመታቸውንም እንዲህ ባለ መልኩ አሳልፈዋል።
ታድያ ጄምስ እንደሚለው ከሆነ፣ እንደውም እንዲህ ተራርቀው ጊዜን ማሳለፋቸው ግንኙነታቸውን እንደሚያጠነክረው ያምናል። በፈተና እና መከራ ጊዜ ፍቅር ይበረታል የሚል እምነትም አለው። እናም ‹ዋናው ጤና ነው› ያሉት እነዚህ ጥንዶች፣ የአንደኛ ዓመት ትዝታቸው ኮቪድ 19 መሆኑን ተቀብለዋል።

አንለያይም?
በውጪው ዓለም በድረገጾች ጓደኛ ማግኘት የተለመደ ነው። ለዚህ አገልግሎት ብቻ የሚውሉም ገጾች ተከፍተው ይሠራሉ። እነዚህም በአገራችን ‹ፍቅረኛና ትዳር አግናኝ› ብለው በአጭር የስልክ ቁጠር ላኩልን፣ ደውሉልን እንደሚሉት ነው። በእርግጥ በውጪው ፍቅርም ትዳርም አገናኝ ነን አይሉም፣ ይልቁንም ተገናኝተውና ቀጠሮ ይዘው የሚተዋወቁበትን አውድ ነው የሚፈጥሩት። ነገሩንም በግርድፉ ስንተረጉመው የመቀጣጠሪያ መተግበሪያ (dating app) ልንለው የምንችል ነው።
ሲኤንኤን የአሜሪካዊቷ ቦሳርት ታሪክ አጋራ። ቦሳርት በወረርሽ ምክንያት ስትሠራ ከቆየችው የሞግዚትነት ሥራ ብትቀነስና ያረፈችበት የአክስቷ ቤትም በአክስቷ ማቆያ መግባት ምክንያት ጭር ቢልም፣ ውሎና አዳሯ ከመተግበሪያው በአንዱ ከተዋወቀችው ሰው ጋር ሆኗል።

ይህን ሰው የተዋወቀችው የእንቅስቃሴ ገደብ ሙሉ ለሙሉ ሳይጣልና ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ሳይባል በፊት ነው። ከዛም በፊት አምስት ጊዜ አካባቢ ተቀጣጥረው ተገናኝተዋል። እርሷም በዚህ ሰው ፍጹም ደስተኛ ሆናለች። እናም ታድያ ከቤት አትውጡ አዋጅ እንደታወጀ በአንድ ቤት ለመክረም ወሰኑ። ትውውቃቸው ቀናት በሚጠብቅ ቀጠሮ ሳይሆን በየቀኑ ሆነ።

አንድ ሳምንት በዚህ መልክ እንዳሳለፉ፣ ቦሳርት በትውውቃቸው መነሻነት በወደፊቷም ውስጥ የሳለችው ሰው ለሥራ ወደሌላ ከተማ መዘዋወሩ ተነገረው። ይህም ለስድስት ወር የሚቆይ ነው። እንደልብ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ጊዜ እርሱ ሊሄድ፣ እርሷ ባለችበት ልትቆይ ግድ አላቸው።

እርሷም በሲኤንኤን እንዲህ ስትል ገለጸች፤ ‹‹እድሜዬ 35 ነው። ለሴት ልጅ ወሳኝ የሚባል የእድሜ ክልል ነው ይባላል። እናም ይህን ሰው እስኪመለስ ልጠብቀው አልጠብቀው የሚለውን ለመወሰን ተቸግሬአለሁ። ፈርቻለሁም።›› ስትል አስተያየት ሰጥታለች።

የቦሳርትን ሰምተው፣ ‹‹አንድ ጊዜ ብቻ ተገናኝተን ብንዋደድም፣ በወረርሽኙ ምክንያት ዳግም መገናኘት ያልቻልንም ስንት አለን! አመስግኚ!› የሚሏትና ያሏት ጥቂት አይደሉም።

ይህ የተወሰነ ታሪክ እንጂ ያልተነገረ ብዙ አለ። በአገራችንም ቤት ውስጥ መቀመጥ ግድ ባለመባሉና የእንቅስቃሴ ገደቡም ላላ ያለ በመሆኑ እንጂ፣ እንደ ሳሮን ያሉና ሌሎችም ለጆሮ የሚስቡ ታሪኮች በኖሩ ነበር።

ፍቅር በኮሮና ዘመን እስከ ሞት ዘልቆ ሲታይ፣ በአስገራሚ አጋጣሚ አገናኝቷል፣ እንገናኛለን ያሉትን አራርቋል፣ ያላሰቡትን ደግሞ አንድ አድርጓል። በአንጻሩ በትዳር በርካታ ዓመታትን ቆይተው፣ ሲዋደዱ ሲፋቀሩ የተባለላቸው ተጣልተውና ተጋጭተው፣ የወረርሽኙን ጋብ ማለት ፍቺ ለመፈጸም የሚጠብቁም ጥቂት አይደሉም። በዚሁ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃትም ተያይዞ የሚነሳ ነጥብ ሆኗል። በድምሩ ግን በኮሮና ዘመን የማይታይና ያልታየ የለም። ወደፊት የሚሰሙ ታሪኮችም ጥቂት እንደማይሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com