የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በሙሉ ይሁን በከፊል በገንዘብ ለመርዳት በሚሞክር ማንኛው ሰው ላይ የ15 ዓመት ፅኑ እስራትና አንድ መቶ ሽሕ ብር ቅጣት የሚጥል አዲስ አዋጅ ሊፀድቅ ነው።
ከጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ በገንዘብ ከመርዳት ባሻገር በቁሳቁስ፣ በንብረት፣ በኢኮኖሚያዊ ሀብቶች እና በቴክኒክ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግንም በጥብቅ የሚከለክለው አዲሱ አዋጅ ድርጊቱን ፈጽሞ በሚገኝ ማንኛውም ወገን ላይ እስከ 15 ዓመት እስር እንዲያስቀጣ ይደነግጋል። ሆኖም መንግሥት የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ መደገፍን በተመለከተ ያሉበትን ግዴታዎች ከመፈፀም አንፃር የሚወስዳቸውን አስፈላጊ እርምጃዎች አዋጁ እንደማይከለክል ረቂቁ በግልጽ አስቀምጧል።
ኢትዮጵያ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶችን ማፅደቋ ይታወቃል። ሆኖም ከመንግሥት እዉቅና ውጭ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊካሔዱ ወይም ሊያልፉ የሚችሉ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን የሚደግፉ ማናቸውንም አካላት ለመቆጣጠር የአዋጁ መውጣት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ረቂቁ ያስረዳል።
የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት እና ተግባሩን በገንዘብ መደገፍ ዓለም ዐቀፋዊ የደኅንነት ስጋት በመሆኑ፣ ሁሉም አገራት ይህን ለመከላከል እና ለመግታት በጋራ እና በትብብር እንዲሰሩ ሁኔታዎች እንደሚያስገድዱም ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ያስገድዳል ሲልም ረቂቁ ስለአስፈላጊነቱ ያብራራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በገንዘብ መደግፍ አስመልክቶ የንዋይ ቁጥጥር እርምጃ ግብረ ኃይል የተባለ ቡድን አቋቁሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህን ግበረ ኃይል በአገር ውስጥ ተግባራዊ ባለማድረጓ እና ሕግ ባለማውጣቷ ከእነ የመንና ኢራቅ ተርታ ለሕግ ተባባሪ ባለመሆን ተሰልፋለች። ይህም ለአዲሱ አዋጅ መውጣት ትልቅ ጫና አሳዳሪ ሆኗል ተብሏል።
‹‹ጅምላ ጨራሽ›› የሚለው ቃል ኑኩሌርን ጨምሮ ሌሎች የሥነ ሕይወት ወይም የኬሚካል ሕጎችን የሚጣረሱ እና ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መሣሪያዎችን የሚያጠቃልል እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ‹‹የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ፀረ ብዜት ብሔራዊ ኮሚቴ›› የሚል እና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ኮሚቴ እንደሚቋቋም አቅጣጫ አስቀምጧል። የሰላም ሚኒስቴር ደግሞ የኮሚቴው ሴክሬታሪያት ሆኖ ያገለግላል። ኮሚቴው 10 አባላት የሚኖሩት ሲሆን ለጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ ከመደገፍ ጋር ተያይዞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሚወሰኑ ቅጣቶችና ማዕቀቦች በአገር ውስጥ መፈፀማቸውን መከታተል አንደኛው የኮሚቴው ኃላፊነት ይሆናል።
በሌላ በኩል ኮሚቴው ኢትዮጵያን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም የሚፈፀሙ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ መደገፍን ለመቆጣጠር የሚያስችል አመራሮችን መስጠትና መመሪያዎችን የማውጣት ተግባር ይከውናል። ይህን አዋጅ ለማስፈፀም የሚረዳ ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማውጣት እንደሚችልም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበ ሲሆን፣ ይመለከተዋል ለተባለው ቋሚ ኮሚቴ ተጨማሪ ውይይት መመራቱም ታውቋል። ተጨማሪ ውይይቶች ከተደረጉበት በኋላም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላላ ስብሰባ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011