የእለት ዜና

የሩቁ አጥር

በብዙ ስርዓቶች ውስጥ አጥሮች የሚታጠሩት በሩቅ ነው። ይህም የሰው ልጅ ለስርዓት ተገዢ እንዲሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳየው የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ውስጥ ግዴታውን ተወጥቶ መብቱንም አስከብሮና የማንንም መብት ሳይነካ እንዲኖር ለማስቻል ነው።

በሃይማኖት ስርዓት ይህ በስፋት ተጠቅሶ የሚገኝ ሐሳብ ነው። በቅርብ ከማውቀው ስነሳ፣ በክርስትና የእምነቱ አባቶች አብዛኛውን የክርስትና ሕግ በሩቅ ከማጠር ጋር ያመሳስሉታል። ምሳሌ ልጥቀስ። ለምሳሌ ዝሙት ከባድ ኃጢአት ነው። ታድያ በጥንት በሕገ ልቡና እና በኦሪት ዘመንና ስርዓት እንዲህ ያለ በደል የፈጸመ ሰው በደንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ሊፈረድበት ይችላል። በጊዜው የነበረው ስርዓት ያንን ይፈቅዳል።

በኋላ በሐዲስ ኪዳን ግን ዝሙት መፈጸም አይደለም፣ ያየ የተመኘ ራሱ እንዳመነዘረ ይቆጠራል የሚል ስርዓት ተጻፈ። ይህን ታድያ የእምነቱ አባቶች ሲገልጹት ‹በሩቁ ሲያጥረው ነው›› ይሉታል። እንዲህ ነው፤ እንኳን በተግባር መፈጸም ማሰብ በራሱ ጥፋትና ስህተት እንደሆነ የሚያውቅ ሰው፣ በአካል ዝሙት ለመፈጸም አይደፍርም ወይም ራሱን ከዛ ይገዛል፤ ተብሎ ይታመናል።

እንዳልኳችሁ ይህን በክርስትና ያለውን በምሳሌ ያነሳሁት በቅርበት የማውቀው ስለሆነ እንጂ በእስልምናና በሌላው እምነትም ተመሳሳይነት ያላቸው አጥሮች አሉ። ይህ ሁሉ ሰው በስርዓት ይኖር ዘንድ ነው። ታድያ ወዲህ ወደ ነገሬ ስመለስ፣ በሩቁ ማጠር ከወዲሁ ያስፈልገናል ለማለት ወድጄ ነው።

ብዙዎች ሲናገሩ በተለይም በማኅበራዊ ገጾች ላይ ሐሳባቸውን ሲያጋሩና መልስ ሲሰጡ ስመለከት፣ በተለይ ከለከፋ ጋር ተገናኝቶ፣ ነገሩን ቀላል ያደርጉታል። ንቅናቄም ሆነ እንቅስቃሴ የማያስፈልገውም ተደርጎ የተወሰደበት ጊዜ ጥቂት አይመስለኝም። ‹‹ለከፋ ደግሞ ምን ችግር አለ! ውበቷን እያደነቀ ነው!›› ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩም አይታጡም። ‹‹ካልተለከፍን ደስ አይለንም›› የሚሉም አሉ፤ ይባላል።

ይሄ ‹አሉ! ተባለ!› የሚባል ነገር ከአንድ ‹ቧልታይ› ከሆነ የፊልም ገጸባህሪም ሊቀዳ የሚችል ስለሆነ እንተወው። ወዲህ ግን ‹ለከፋ ውበትን ማድነቅ ነው› የሚል ሙግት በግልጽ እንሰማለንና እሱን ያዙልኝ።

ሲመስለኝ ሴትን ማክበር ከዛ ይጀምራል፣ አለማክበርም በአንጻሩ ይገለጣል። የሩቅ አጥሩ ያ ነው፣ መንገድ ላይ ሴትን አለመልከፍ። መንገድ ላይ ነጻነቷን ማክበር። ያንን አጥር ያለፈ አስገድዶ ከመድፈር የሚመልሰው ማን ነው? መንገድ ላይ መቀመጫዋን ቸብ አድርጎ አልፎ በድል አድራጊነት ሲፈግ፣ እርሷ ሰው አየኝ አላየኝ ብላ መሳቀቋን እንደ አሸናፊነት ሲቆጥር፣ ያንን የክብር አጥር ሲጥስ፣ ከዛ ከወዳጆቹ ጋር ተባብሮ ጥቃት እንዳያደርስባት ተው የሚለው ምንድን ነው?

መጀመሪያ የሩቁ አጥር በስርዓት መገንባት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህም ከቃላት የሚጀምረው ነው። ሰዎች የቃላት አጠቃቀምን እንደቀላል ማየታቸውም ትክክል የማይሆነው ለዚህ ነው። የሩቁ አጥር በእነዚህ ጡቦች የተሠራ ነው። በቃላት፣ በተግባርና በንግግር ውስጥ። ፊልሞቻችንና የሙዚቃ ቪዲዮዎቻችንም ‹ሃይ!› ሊባሉ የሚገባው ይህን አጥር ስለሚያስጥሱ ነው።

እናም እነዚህን የሩቅ አጥሮች ማስከበር ላይ በሚገባ መሥራት ከዛ ያለፉ ጥፋቶችን ለመከላከልና ሲፈጸሙም እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል። ሕጉ የሩቁን አጥር ባፈረሰ ላይ አርጩሜ ማሳረፍ ሲችል፣ ገብቶ ሊዘርፍ የሚደፍር አይኖርም። ካለም የበረታው ዱላ እንደሚያርፍበት ይታወቃል። ሕግና ስርዓት ያስፈለጉትም ለዚህ ነው። እናም የሩቁን አጥር ማስከበሩም አይዘንጋ!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com