የእለት ዜና

የጋዜጠኝነት ኃላፊነትና ሥነ ምግባሩ

ጋዜጠኝነት የሕዝብ ዐይን እና ጆሮ እንደመሆን ነው፣ እንደባለሞያዎች አስተያየት። ታድያ መገናኛ ብዙኀን ያዩትንና የሰሙትን፣ የታዘቡትና የቃኙትን ሲተነትኑ በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል። ካልሆነ ግን ትልቅ ጥፋት ያደርሳሉ የሚሉት አብርሐም ፀሐዬ፣ በሩዋንዳ የተከሰተውን ዓይነት የጎሳ ግጭት ፈጥረው እረፍት የማይሰጥ እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭትን ማፋፋሚያ እሳት፣ አራጋቢም ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል። ይህ እንዳይሆን ኃላፊነት የሚሰማውና የሙያ ሥነምግባር ያለውን ጋዜጠኝነትን መለማመድ ወሳኝ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያም ከመገናኛ ብዙኀን ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ያሉትን አካሄዶች ቃኝተዋል።

ኢትዮጵያችን የመገናኛ ብዙኀን ፖሊሲ የላትም። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ረቂቁን ገና እያወያየሁበት ነው እያለን ነው። ፖሊሲው የተወያዮቹን ማንነት አልፎ ወይም ከመንግሥት ረጅም እጅ አምልጦ፣ የፓርቲዎችን ይሁንታ በማግኘት፣ በበሰሉ እና በሰሉ ባለሙያዎች የመታየት ዕድል አግኝቶ መሬት ይወርድ ይሆን? መሬት ቢወርድ እንኳን አፈጻጸሙ ስለመሳካቱ እንጃ። የቀደመውን የፕሬስ ነጻነት ውድቀት ላየ፣ በዚህኛውም ተስፋ ባያደርግ አይገርምም። የጎሳ ፖለቲካ እግር ከወርች እስርስር ያደረጋት አገሬ፣ ርዕይዋ ከወረቀትና ከግለሰቦች አፍ አልወርድ እያለ እስከዛሬ ድረስ ይተናነቃታል።

የብዙኀን መገናኛው ረቂቅ ፖሊሲ ከተሳካልን እሰየው ነው። ምናልባት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ከጋዜጠኝነት ትምህርቱ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲያስተምሩ ስለነበረና የሚዲያ ፖሊሲ አለመዘጋጀትና የፕሬስ ነጻነቱ ጉዳይ የሚያስቆጫቸው ስለነበሩ ተስፋ እናድርግባቸው። የእርሳቸውን ትምህርት አሁን ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በኃላፊነት በተሾመችው መምህሬ አማካይነት ተጋብዘው ስለሚዲያ ሕጎች የመማር ዕድል አግኝቼ ነበር። ከዚያ ባሻገርሞ ከዩኒቨርስቲ ውጪም ያቀረቡትን ስልጠና ለመካፈል ችዬ ነበር።

ምሁሩ ያላቸው ዕውቀትና ልምድ ተስፋ እንዲደረግባቸው ዋስትና ይሆናል። ይህ ሳይሆን ቢቀርና እንደ አብዛኞቹ ምሁራን ዱክትርናን የኋላ ኪስ አድርገው የፓርቲ ቲሸርት ከለበሱ ግን እንደተለመደው አሳዛኝ ይሆናል። የዶክተሩ ምሁራዊ ስብዕና ግን ባየሁባቸው መድረኮች ይህንን ስህተት የሚፈጽሙ እንዳልሆኑ እርግጠኛ አድርጎኛልና፣ አንድ ተጨባጭ ፋይዳ የሚሰጥ ነገር እንደሚያሳዩን ተስፋ እያደረግን እንቆይ።

የፖሊሲው አስፈላጊነት
ፖሊሲው ባለቤት አልባው የአገራችን ጋዜጠኝነት የመመሪያ ቋት እንዲያገኝ ያደርገዋል። ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው ብዙኀን መገናኛና ባለሙያ ሲኖር ጋዜጠኝነት ፈር ይይዛል። ሥነ ምግባርን የጣሰ ጋዜጠኝነት እንደደነበረ የጋሪ ፈረስ ነው፣ ጥፋቱ ጥቂት አይደለም። ከጉዳቱ የተረፉትን ሰዎች አስበርግጎ ብቻ አይመለስም። መርህ አልባና ሥነ ምግባር የሌለው ብዙኀን መገናኛ አገር ያፈርሳል። ብዙዎቻችን የምናውቀውን የሩዋንዳ እልቂት በሚዲያ በኩል ሆኖ ሲመራ የነበረው ወንጀለኛ ፈረንሳይ ውስጥ ስለመያዙ በቅርብ ሰምተናል። ሩዋንዳውያንን የካጋሜ ጦር ደርሶ ከመታደጉ በፊት ‘ሚዲያ’ የሚባል ጦር ሠራዊት ሺዎች እንዲወድቁ ምክንያት ሆኗል።

ጉዳዩ ሞት ብለን የምናቀለው ሳይሆን ፍጅት ነበር። ኤፍ ኤሞቹ ጎራ ለይተው በሁቱና ቱትሲ ተቧድነው ለጊዜው የበላይ የሆነው ቡድን መሣሪያውን ሚዲያ አድርጎ ጀሌውን ለገዳይነት ጠራበት፤ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳሳ ስያሜ እየሰጠ አነሳሳ። ወገን በወገኑ ላይ ለሰሚ በሚዘገንን መልኩ ጨከነ፤ ውጤቱ ከፍቶ እልቂት ነገሠ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ብዙኀን መገናኛዎቹ ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው። በሕግና ሥነ ምግባር እየተገራ ያልቆየ ባለሙያና የብዙኀን መገናኛ ተቋም ልጓሙን ከጣሰ መመለሻ የለውም። ‹‹ዕውቀት የትም የሚያደርስ ፈረስ ሲሆን፣ ልጓሙ ግን ሥነ ምግባር ነው›› የሚባለውስ ለዚህ አይደል?!

በሙያ ደረጃ ጋዜጠኝነት በሥነ ምግባር የሚገዛና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ጠበቅ ያለ ብርቱ ሥራ ነው። ነገሩን ከሌሎች ሙያ ለማመዛዘን ሳይሆን ከላይ እንዳስተዋልነው ጋዜጠኝነት ዘንበል ያለ ጊዜ የገዳይነት መርዝ የተሸከመ በመሆኑ ጥፋቱ የከፋ ስለሚሆን ነው። የሚያጠፋው ደግሞ ጥቂት ሰዎችን ሳይሆን ሕዝብና አገርን በመሆኑ ነው።

የሙያ ሥነምግባሩ እንደሚያዘው ማንኛውም ዘገባ ትክክለኛና ፍትሃዊ እንዲሆን ይፈለጋል። ዘጋቢው ባለሙያ ስሜትና አድሎ ሳያሸንፈው በታማኝነት የሚሠራ እንዲሁም መረጃ ሲሰበስብና ሲመረምር ከዚህ ጋር ተያይዞ ሚዛናዊነትን ለመተግበር ሲል የማይታክት መሆን ይኖርበታል። ጋዜጠኛ ጽኑ ባለሙያ ካልሆነ የሚገኘው መረጃ በተሳሳተ መልኩ ሊተላለፍ ከመቻሉም ባሻገር በቀላሉ የማይታጠፍ ስህተት ሊሠራ ይችላል።

አሁንም እንደምናየው ዓለም ከሥነ ምግባር በራቁ ድርጊቶች እየተሞላች ነው። ኢ-ሰብዓዊነት ሰልጥኗል። እጅግ የተከበሩ ምሁራንና ባለሥልጣናት ክህደትና ዋሾነትን የእውነት ያህል ይናገሩታል። ጽንፈኞች ሚዲያን ከጦር መሣሪያ በላይ እየተጠቀሙበት ነው። በዚህ ግብረ ገብን በተወች ዓለም ውስጥ የሚሠራ ጋዜጠኛ ያለበትን ፈተና ማሰብ ነው። ለዚህም ነው የቱም ክስተት ወደ ዜናነት ከማደጉ በፊት ጥልቅ ዕይታን የሚፈልገው። በእውነትና ውሸት መካከል ያለችው መስመር እምብዛም አትታይምና የጋዜጠኝነት አጉሊ መነጽር ትፈልጋለች።

ሆን ተብለው የሚቀነባበሩ ክስተቶች ስላሉ ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል። እነዚያ ክስተቶች ወደ መገናኛ ብዙኀን በመረጃ ወይም በዜናነት ሲቀርቡ አቀነባባሪዎቹ የሚፈልጉት ውጤት አለ። ስለሆነም ጋዜጠኛም ሆነ ሚዲያ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የአንድ ወገን መረጃ ተሸካሚ መሆን የለበትም። ውጤቱ ሞት ወይም ቀውስ ፈጣሪ ሊሆን ስለሚችል። ይህ ባይሆን እንኳን ኢ-ፍትሃዊነት የፍትሃዊነትን ቦታ ሊተካ ይችላል።

ጋዜጠኝነት ከባድ ኃላፊነትን የተሸከመ ባለአራት ዐይና ሙያተኛ ይፈልጋል። እንደ ጋዜጠኛ ወይም ዘጋቢ ያገኘውን መረጃ እውነትነቱንና ፍትሃዊነቱን ደግሞ ደጋግሞ ማጣራትና መመርመር ይገባል። የሰማውን፣ ያየውንና ያነበበውን ሁሉ እንደትክክለኛ ዘገባ ከወሰደው በስተመጨረሻ የከፋ ስህተት ሊፈጥር ይችላል። በማየት ብቻ እውነት ነው ተብሎ መዘገብ ስህተት ያመጣል። በማየት ከሆነማ ጨውም ስኳር ይመስላል እንደሚሉት ነው። በማየት ከሆነማ የምናያትን ጨረቃ መጠኗ ኳስ ያክላል ብለን ልንዘግብ ነው። ትክክለኛ ዘገባ መጠጋትን፣ ማሽተትንና መቅመስን ይጠይቃል።

በ1909 የተመሠረተውና ተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገው ኤስ. ፒ. ጄ. SPJ (The Society of Professional Journalists) የጋዜጠኞች ማኅበር ነው። ስለዚህ ጉዳይ አጥብቆ ሲመክር ለምሳሌ የመረጃ ምንጮችን ከመጠቀም አንጻር ያስቀመጠው ነገር አለ። እንዲህ ይላል፤ ‹‹በተቻለ መጠን የመረጃ ምንጮች ከትክክለኛው ቦታ ሊሆኑ ይገባል››

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹መረጃን ወደ ሕዝብ ከማድረሳችሁ በፊት ስለ ትክክለኝነቱ ኃላፊነት ውሰዱ፤ ፈትሹ፣ አረጋግጡ!›› ሲል ባለሙያዎችን አጥብቆ ይመክራል። (Take responsibility for the accuracy. Verify information before releasing it. Use original sources whenever possible.)
እዚህ በኢትዮጵያችን መርሁ በየመገናኛ ብዙኀኑ ግድግዳዎች ላይ ባማረ ጽሑፍ ሰፍሮ ልናየው እንችላለን። ዋናው ነገር ግን የሙያው ሥነ ምግባርና ኃላፊነት በልቦና ውስጥ መስረጹ ነው።

በአጠቃላይ ጋዜጠኝነት ስህተት ከፈጠረ የአደጋው ከባድነት ግዙፍ በመሆኑ የተነሳ ኃላፊነቱ የዋዛ እንዳልሆነ ሁሉም የሚስማማበት ሙያ ነው። በዚህ የተነሳ በአንድ አገር ላይ ብዙ ሺሕ ጋዜጠኞች እያሉ ጋዜጠኞች ናችሁ የሚባሉት ግን ከጣት ቁጥር አይበልጡም።
አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmaik.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com