የእለት ዜና

በግብርና ምርት አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ማኅበራት 800 ሚሊዮን ብር ብድር ተፈቀደላቸው

መንግሥት በግብርና ምርት አቅርቦት ላይ ለተሰማሩ 65 ሸማቾች እና አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የ800 ሚሊዮን ብር ብድር መፍቀዱን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡

የብድሩ ተጠቃሚ የሚሆኑት በዘጠኙም ክልሎች እና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ በግብርና ምርት አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ሽማቾች እና አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሆናቸው ተገልጿል።

ይህም የሆነው ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ የሚስተዋል ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እንዲሁም አርሶ አደሩን እና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ ለማገናኘት ታስቦ ነው ተብሏል፡፡

ብድሩን የሚሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሆኑን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።ልማት ባንክ ለማኅበራቱ የሚያበድረው 800 ሚሊዮን ብር በአንድ ዓመት ውስጥ የሚመለስ ሲሆን፣ ወለዱም ዝቅተኛ በሚባል የሰባት በመቶ ምጣኔ እንደሚሰጥ ኤጀንሲው አመላክቷል፡፡

65ቱ ብድር የሚወስዱ ማኀበራት የመክፈል አቅማቸው ታይቶ እንደተመረጡም የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃያልሰው ወርቁ ገልጸዋል።
ብድሩ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የግብርና ምርት አምራች እና ሸማች ማኅበራት በሙሉ አቅማቸው ምርት እንዲያሰባስቡ፣ ሰንሰለቱ ባጠረ ግብይት ስርዓት የግብርና ምርትን እንዲያገበያዩ እና ለሽማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ታስቦ እንደተመቻቸ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኡስማን ሱሩር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመንግሥት እንዳቀረበ እና መንግሥት ችግሩን አምኖ በመቀበሉ ሽማቾች እና አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብርና ምርቶችን ማሰባሰብ እንዲችሉ ብድሩን መፍቀዱን ኡስማን አመላክተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት ብድሩ ማኅበራቱ ከእስከዛሬው በተሻለ ሁኔታ አገልግሎታቸውና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ እና የነበረባቸውን የገንዘብ እና ሌሎች ችግሮች በመፍታት የአቅርቦት ችግርን እንዲቀርፉ ያስችላል።

ብድር ከተፈቀደላቸው 65 የግብርና ምርት አምራች እና ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲሆኑ፣ እስካሁን ከ30 በላይ የሚሆኑት ብድሩን ለመውስድ የመጨረሻ ሰነድ ለልማት ባንክ የተፈቀደላቸውን ገንዘብ ለመውስድ የመጨረሻ ሂደት ላይ እንደሆነ ኡስማን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።ቀሪዎቹ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ብድሩን ከሚሰጠው ልማት ባንክ ጋር ቅድሚያ ማለቅ ያለባቸውን የውል ስምምነቶች በማካሄድ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

ማኅበራቱ ብድሩን ማግኘታቸው ደግሞ በኮቪድ-19 ምክንያት እየታየ ያለውን ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን እንደሚያስቀር እና ሽማቾች በቀጥታ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት በተመጣጠን ዋጋ የግብርና ምርቶችን እንዲሸምቱ እንደሚያስችል ይጠበቃል።

ብድር ከተመቻቸላቸው ማኅበራት ውስጥ በአዲስ አበባ የሚገኘው መሰረተ የካ ሽማቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን አንዱ ነው።የዩኒየኑ ቦርድ ስብሳቢ አብርሃም ተክላይ የ20 ሚሊዮን ብር ብድር እንደተፈቀደላቸው እና ብድሩን ማግኘታቸው ግብርና ምርቶችን በተሻለ መጠን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ወዲህ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ የገንዘብ ጫና ማሳደሩን ኡስማን ጠቁመዋል።በተለይ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሌሎች ኅብረት ሥራ ማኀበራት በላይ እንቅስቃሴያቸው በመገታቱ የመቀዛቀዝ ሁኔታ እንደታየባቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ማኅበራት ቀጥሎ ጫና ያደረባቸው የሽማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ አጠቃላይ 21 ሚሊዬን ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኮቪድ-19 ምክንያት የከፋ ነገር ቢከሰት በሚል ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡

ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ እስካሁን ከአባሎቻቸው 48 ሚሊዬን ብር በማሰባሰብ በኮቪድ-19 ተጎጅ ለሆኑና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!