የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው

Views: 288

አነስተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ጫናን የሚያቃልል ጥናት አስጠንቶ ለመንግሥት ሊያቀርብ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የመንግሥት ሠራተኞች ለረጅም ዓመታት በምሬት ከሚያነሷቸው ችግሮች አንዱና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ችግር መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኑሮ ውድነቱ ከቤት ኪራይ ዋጋ መናር ጋር ተዳምሮ የዜጎችን ኑሮ መፈታተን ጀምሯል። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ እንደገለጹት በቤት ኪራይ ዋጋ መናር ቀጥተኛ ተጎጂ ከሚሆኑ ዜጎች መካከል ዝቅተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ሠራተኞቹ ገቢያቸውን በሙሉ ለቤት ኪራይ ስለሚያውሉ ለምግብና ሌሎች አገልግሎት ለመሸፈን እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ። ችግሩን ይፈታል የተባለ ጥናት ኮሚሽኑ ከኮንስትራክሽንና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥናት ማስጠናቱንና ጥናቱም በቅርቡ ለመንግሥት እንደሚቀርብ ገልጸዋል።
”ጥናቱ በዋነኛነት ለረጅም ዓመታት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲሰሩ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ደሞዝ የሚኖሩ ሰዎች አሁን ላይ ከተፈጠረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መናርና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ጋር ተያይዞ የሚበሉበትን እስከማጣት የሚደርሱ መሆናቸውን ጥናቶቻችን አሳይተውናል” በማለት ገልጸል። መንግሥት ጥናቱን መሠረት በማድረግ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንደሚያስቀምጥ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
”የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በወረቀት ላይ የተፃፉ የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነዶችን ከማነብነብ ወጥተው የተጨበጡ ውጤቶችን በማምጣት ራሳቸውን የሚያሳድጉበት አሰራር መፍጠር ይገባል” ነው ያሉት። በተለይ የዋስትና ዘዴዎችን በማመቻቸት የፋይናንስ ግኝቶችን በማፈላለግ ዝቅተኛ ደሞዝ ለሚከፈላቸው ሠራተኞች መፍትሄ በመስጠት በኩል የመንግሥት ሚና የጎላ ይሆናል ብለዋል።
”ይሄን ችግር መንግሥት እንደ መንግሥት ሊፈታው ይችላል ብለን እናምናለ ፤እኛም በመንግሥት ወኪልነታችን እዚህ ተቀምጠን የምናያቸው ነገሮች የመንግሥት አደረጃጀት በቅንጅት እስከሰራ ድረስ በሌሎች የማህበረሰብ አካላት ዘንድ በማህበር እየተደራጁ ቤት የሚሰራበትን ሞዴል ወደ መንግሥት ሠራተኞች ማምጣት በፌዴራልም በክልሎችም ደረጃ የሚከብድ ነገር ነው ብለን አናይም” ነው ያሉት ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ። በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com