‘‘የአህያ እና የፈረስ’’ ፖለቲካ ሳምንት

Views: 117

ሰሞኑን የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ብረቱ የመከራከሪያ፣ መነታረኪያ እና መዘላለፊያ የሆነው ርዕሰ ጉዳይ ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረገው ቆይታ በተለይ ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ጋር በተያያዘ አምልጦት ይሁን አውቆ የሰነዘራቸው ቃላት ነበሩ። ሃጫሉ ብዙዎች የቀደመውን ሕወሓት መር መንግሥት በመታገል ለእስር የተዳረና የተንገላታ፣ በለውጡ ዋዜማም በሚሊኒየም አዳራሽ በባለሥልጣናት ፊት ወኔ ቀስቃሽ ሽለላ እና ቀረርቶ በማሰማቱ ከብዙዎች አድናቆት ጎርፎለታል፤ ብዙ ወጣቶችንም ለተቃውሞ ማነሳሰቱ ደጋፊዎቹ ሁል ጊዜ በበጎ ያነሱታል፤ ያወድሱታልም።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ቴሌቪዥን ቀርቦ ከሰጠው ቃለ ምልልስ በተለይ ዳግማዊ ምንሊክን ጭካኔ ለማንኳሰስ የተጠቀማት ተረክ የብዙዎች ቀልብ ስባለች፤ የድጋፍም የተቃውሞም ድምፆች እንዲሰሙ ሰበብ ጭምር ሆናለች። ዩሐንስ መኮንን የተባሉ የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚ የቃለ ምልልሱን ፍሬ ነገር ዘርዝረው ወደ አማርኛ መልሰው ብዙዎች ተጋርተውታል።

‘‘ይኼ ምንሊክ የተቀመጠበት [ፒያሳ፣ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘውን ሐውልት] የተሰረቀ ፈረስ ነው። ገላን አካባቢ ከሚኖር ሲዳ ደበሌ ከተባለ ገበሬ ነው የተሰረቀው። . . . አስፈላጊ ከሆነ ይህ ትውልድ የተሰረቀውን ፈረስ ሊጠይቅ ይችላል። . . . ምንሊክ ወደ ኦሮሚያ ሲመጣ በአህያ ላይ ተቀምጦ ነበር የመጣው። . . . ፈረስ ላይ መቀመጥ የት ያውቅና ነው? ምናልባትም ሰው እየጎተተለት ፈረስ ላይ ተቀምጦ ይሆናል። ዛሬም በየዓመቱ የዓድዋን ድል እናከብራለን የሚሉ ሰዎች ፈረስ ላይ እንደ ንጉሥ [ሰው] አስቀምጠው ሌሎች ፈረሱን ሲጎትቱ አያለሁ።’’
ሃጫሉ፣ ድፍረት በተሞላበት መንፈስ ምኒሊክን አሳንሶ መናገሩን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን አቅላቸውን ሊስቱ ምንም ያልቀራቸው ሰዎች በማኅበራዊ ትስስር አድናቆታቸውን ለመግለጽ ቃላት ሲያጥራቸው ተስተውለዋል። አንድ የፌስቡን ተጠቃሚ ‘‘ዕድሜ ይስጥህ አቦ! የልቤን ነው የተናገርክልኝ’’ ሲል ድጋፉን የገለጸ ሲሆን፤ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ‘‘ፍዝዝ ያለውን ፌስቡክ አነቃቃቀው’’ በማለት አድናቆቱን ከመግለጽ ባሻገር ‘‘ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! የምትል እንግዲህ ተንጫጫ’’ ሲልም አላግጧል። ቀላል የማይባሉ የሐሳቡ ደጋፊዎች የፌስቡክ ምስላቸውንም በሃጫሉ ተክተዋል።

በሌላ ወገን ደግሞ ቀፎው እንደተነካ የንብ መንጋ ብዙዎች የሃጫሉን ቃለ ምልልስ አጣጥለውታል። ‘‘ድሮስ ሃጫሉ ታዋቂ እንጂ መች አዋቂ ሆነና’’ በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል፤ እንደ ጥበብ ባለሙያ በሕዝቦች መካከል መጠራጠር ከመፍጠር መተማመን፣ መለያየትን ከመዝራት አንድነትን፣ ከቁርሾ ይልቅ ፍቅርን መስበክ ሲገባው በተቃራኒው ማድረጉ ነገ የሚጸጸጥበትንና የሚያፍርበትን ተግባር ፈጸመ ሲሉ የኮነኑተም ነበሩ።

ከዚህ በተለየ ግን በአቻምየለህ ታምሩ የፌስቡክ ገጽ ላይ ‘‘ወሬ ሲነግሩህ ሐሳብ ጨምርበት’’ በሚል ርዕስ የታሪክ ድርሳናትን ዓርዕስት እና ገፆች በማጣቀስ የተለጠፈች መጣጥፍ የብዙዎችን ቀልብ ስባለች።

መጣጥፏ ከበቂ በላይ በአመክንዮ እና በማስረጃ የተደገፈች የፈረስ ግልቢያን ባህል ከኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት አንጻር በመተንተን የሃጫሉ ክብረ ነክ ገለጻ መሻሪያ አድርገው በሰፊው ተጋርተዋታል፤ ለጸሐፊውም ያላቸውን ምስጋና እና አድናቆትም አንቆርቁረውለታል።

እንዲሁም በሌላ በኩል ደግሞ ዘመቻ በሚመስል መልኩ ደግሞ በርካቶች የእምዬ ምንሊክን የምንሊክ አደባባይ ሐውልት ምስል በገፆቻቸው ላይ ከመለጠፍ አልፈው የራሳቸውንም ምስል በንጉሱ ተክተዋል።

ሃጫሉ ላይ የተቃውሞ ዶፍ ያወረዱት የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች፣ ሃጫሉ የሰነዘረው ክብረ ነክ ንግግር ከሳምንታት በፊት አምሳሰደር ሱሉማን ደደፎ ከጻፉት ጋር በማዛመድ ዳግማዊ ምንሊክን በውሸት የማጠልሸት ትርክ ቀጣይ ፕሮጀክት አድርገው ወስደውታል።

በዚህ ሳምንት ሐሙስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰዓት 80 ሺሕ ዳቦ የሚያመርተውን የሸገር ዳቦ ፍብሪካ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው “ሁሉም ሰው የትላንታና እና የታሪክ ተንታኝ ከሆነ ወደ ፊት መጓዝ አይቻልም” በማለት ያሰሙት ንግግር በማኅበራዊ ትስስር ለሚካሔዱት ንትርኮች ማላሽ ነው ሲሉ አንዳንዶች ጠርጥረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com