የበይነ መረብ ጥቃት ‹አራተኛው የውጊያ ሜዳ› ወይስ…?

Views: 121

ዓለም በየጊዜው ለውጦችን ታስተናግዳለች፤ አስተናግዳለችም። የሰው ልጅም የኑሮ ውጣ ውረድን ለማቅለልና ለመቀነስ በፈጠራ ሥራዎች እየታገዘ፣ ቴክኖሎጂንም በየጊዜው እያስተዋወቀና እያሻሻለ፣ ዘመናትን ተሻግሮ ከዛሬ ደርሷል። ከጎረቤት ጋር በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም አልያም በድንበር ካልሆነ፣ በሩቅ ካለ አገር ጋር ግጭት መስማት እምብዛም የነበረበትና የኖሩትን የየብስ፣ የባህርና የአየር ጥቃት አልፎ አሁን የበይነ መረብ ጥቃት ጊዜ መጥቷል። ይህም ሌላ የግጭት ማስተንፈሻ እየሆነ ይመስላል።
ይህ በቀደመው ጊዜ ደሃ የተባሉ አገራትን አያሳስብም ነበር። ይልቁንም በሠለጠኑና ቴክኖሎጂን አስቀድመው በተዋወቁ አገራት ይበልጥ ጎልቶ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ሆኖም አሁን ግን የበይነ መረብ ጥቃትና መጎሻሸም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራትም የሚሰማ ዜና ሆኗል። ይልቁንም ከኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ፣ ከግብጽ በኩል በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ የሳይበረ ጥቃቶች መጠን ከፍ እንዳሉ በየጊዜው የሚወጡ ዘገባዎች ይነግሩናል።
እነዚህ ጥቃቶች ምን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው? ዓላማቸው ምንድን ነው? ይህን ለመቋቋም ኢትዮጵያ ምን እያደረገች ነው? እና የመሰሉ ሐሳቦችን በማንሳት፣ ባለሞያዎችን በማነጋገርና መዛግብትን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ዳር ድንበርን የሚጥስ እና ሰላምን የሚነሳ የውጭ ወራሪ ኃይል ሳታስተናግድ ቀርታ አታውቅም። በአልበገር ባይነት፣ የሞት ሽረት ትግል ያልተዋደቀችበት ጊዜያትን ለማግኘትም የሚቸግር ጉዳይ ነው። ከጣልያን የአምስት ዓመት የአርበኞች የተጋድሎ የታሪክ አሻራ እስከ ካራማራ አሸዋማው ምድር፤ ከዘመቻ ጸሐይ ግባት እስከ ዛላንበሳ እና የትግራይ ሰንሰለታማ ተራሮች ድረስ በተደረጉ ተጋድሎዎች፣ በርካቶች ከሰንደቅ አላማቸው አስቀድመው ራሳቸውን ሰጥተው በደማቸው እና በአጥንታቸው አገር አቁመዋል።

ዛሬም ድረስ ድንበሯ ተከብሮ ወሰኗ ታፍሮ ለመኖሩ ምክንያቶች እና የኋላም ጠንካራ ታሪኮች ለመሆናቸው፣ ኢትዮጵያውያን የልብ ኩራት ያላቸው እና ጠንካራ የሥነ ልቦና መሠረት ባለቤት መሆናቸው ማረጋገጫ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም።

በእነዚህ ተጋድሎዎች ታዲያ ከአመዛኙ የእግረኛ ወይም ተሽከርካሪ ጦርነት (የየብስ ውጊያ) ባለፈ በጥቂት የአየር ላይ ወጊያ እና ምንም በሚባል ደረጃ ደግሞ የባህር ላይ ውጊያዎች ተከናውነዋል። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራው የኢሕአዲግ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ወዲህ፣ ባህር በር እና ባህር ኃይል እስከ ወዲያኛው ያሸለበ ጉዳይ መሆኑን ለማወቅ የታሪክ ድርሳናት እና ሕያው ሰነዶች ምስክር ናቸው።

በቀደሙት ጊዜያት ዳር ድንበር ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች እና ውጊያዎችን በማካሔድ በሰው ልጅ መስዋዕትነት የሚከበር እንደሆነ የሚታወስ ነው። ይህም የእግረኛ ጦር፣ አየር ኃይል እና ባህር ኃይል በመባል የሚጠቀስ ሲሆን፣ በብዙኀን ዘንድም የሚታወቅ እንደሆነ እሙን ነው።

ይሁን እንጂ ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ በሚዘምነው የሰው ልጅ የሕይወት ዑደት ውስጥም የጦርነት ቀጠናዎች ከገሃዱ ዓለም ርቀው በቴክኖሎጂ የሚካሔዱበት ዘመንም ብቅ ብሎ ብዙዎቻችንን ለማስደመም በቅቷል። የሰውን ልጅ የውትድርና ተሳትፎ በሰው ሠራሽ ሮቦቶች (አሻንጉሊቶች) በመተካት ለውጊያ መዘጋጀት በአደጉት አገራት ከረጅም ዓመታት በፊት ቀድሞ የታሰበበት ጉዳይ መሆኑ ከዓመታት በፊት ሲሰማ አጀብ ተብሎ እንደነበርም አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ የዘመን ፍሰት ሂደቱን በቀጠለ ቁጥር ቴክኖሎጂም መዘመን እና ከቴክኖሎጂም ጋር ተያይዞ ለእኩይ ተግባር የሚውልበት መንገድም በዛው ልክ እየሰፋ እና እየተለጠጠ በመምጣት አሁን የደረስንበት ሁኔታ ላይ አድርሶናል። ለዚህም ነባራዊ እውነታን መቃኘት ብቻ በቂ ማስረጃ ነው። ይህም ደግሞ አራተኛው የውጊያ ሜዳ በመሆን እየሠራ እና ዓለምን በማስጨነቅ አገራትን የለየለት የበይነ መረብ ምዝበራ ተጠቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ የበይነ መረብ ጥቃት ነው።

ይህም ታዲያ በአደጉት አገራት ከባድ የሆነ ጥቃትን ከማድረሱ በተጓዳኝ፣ ጥቃቱ በተለይም ደግሞ በዋና ዋና መሠረተ ልማት እና አገራት ቁልፍ ስፍራዎች ላይ የሚካሔድ ነው። በዚህም ከፍተኛ የሆኑ ጉዳቶችም ያጋጠሙባቸው ክስተቶች ጥቂት አይደሉም። በተለይም ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር በመዘመን ቀዳሚውን ረድፍ የሚይዙት የአደጉት አገራት፣ የአገራቸውን ጠቅላላ የእንቅስቃሴ ስርዓት ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ፣ የሚደርስባቸው ጉዳትም ይህ ነው የማይባል እንደሆነ በቅርብ የምናውቀው ጉዳይ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም በበይነ መረብ ደኅንነት ዙሪያ የኹለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ የሠሩት ሰዒድ ነጋሽ እንደሚሉት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የበይነ መረብ ደኅንነት ስጋት የዓለም ቀጣዩ የውጊያ ሜዳ ለመሆኑ የማያጠራጥር ኹነት እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የበይነ መረብ ደኅንነት ስጋቶች አሁን ለደረስንበት እና በቀጣይም ለሚደረስበት የዓለም ደኅንነት ስጋት ከፍተኛ አመላካች ጉዳዮች ለመሆናቸው ማረጋገጫም እንደሚሆን ይተነትናሉ።

በድንበር የማይገናኙ አገራት ነገር ግን በተነኮስከኝ እና ተነኮስሽኝ ዓይነት እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ መመልከትም የበይነ መረብ ጥቃትን ሌላኛው የውጊያ ሜዳ ማድረጋቸው መገለጫው እንደሆነ ማወቅ ይቻላል ሲሉ ይናገራሉ።

ሰኢድ በገለጻቸው እንዲህ አሉ፤ ‹‹ከቅርቡ የዋናክራይ የበይነ መረብ ላይ ጥቃት ሰንዛሪ የመደራደሪያ ጥቃት አሜሪካ ከሩቅ ምሥራቅ አገራት ለመላካቸው እና በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የሆኑ የደኅንነት ተቋማት እና ሌሎች ቁልፍ መሥሪያ ቤቶችን ለማሽመድመድ የተቃጣው ሙከራ፤ ለሕዝብ ይፋ ባይሆንም፤ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሶ ነበር። እኛም አገር ይኸው ጥቃት በጥቂቱም ቢሆን ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው። በተለይም ደግሞ በግለሰቦች ደረጃ የግል መጠቀሚያ ኮምፕዩተሮቻቸውን በመጥለፍ እና በድንገት እንዲዘጋ በማደረግ ከዛም በኢሜይል መልዕክት ልከው በክፍያ መደራደር እና የመሳሰሉ በሙያዊ አጠራራቸው ራንሰምዌር የሚባል ጥቃት እንደሚያደርሱ የሚታወስ ነው።››

በተለያዩ ጊዜያት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሚያወጣቸው የበይነ መረብ ጥቃቶች በኢትዮጵያ በዋናነት ታላላቅ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች ማእከል ያደረጉ እና በገንዘብ ተቋማትም ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት እና ዝርፊያ ለማካሔድ የታቀዱ እንደነበር ከመግለጫዎች ለማወቅ ተችሏል።

እነዚህ ጥቃቶችንም በሚመለከት ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፤ በየዓመቱ እጅግ እየጨመሩ እንደመጡ እና በቀዳሚው ዓመትም 691 ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ጠቁሟል። እንደ ኤጀንሲው ገለጻ የተመዘገቡት እና ተሰንዝረው ያልተሳኩት ጥቃቶች ከሞላ ጎደል በመሰረተ ልማት ተቋማት ማለትም በመብራት እና በቴሌኮም ላይ የተቃጡ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በገንዘብ ተቋማት የተገነቡ ለመሆናቸው ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ቁጥር ታዲያ ከስድስት ዓመታት ከነበረበት ዓመታዊ ቁጥር (59) በአጭር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር እና ጭማሪ በማሳየት፣ በአሃዝ ሲሰላ ከነበረበት በ13 እጥፍ በመጨመር 691 ደርሷል ማለት ነው። ይህ አሁን የደረሰበት ደረጃም የመጪውን የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ አመላካች እና ወደፊት የዓለም አገራት ኃያልነት ባላቸው የጦር ኃይል መሆኑ የሚያበቃበት ወቅት ሩቅ እንደማይሆን ማሳያ ነው በሚለው ሐሳብ የዘርፉ ልቃንም ይስማሙበታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የበይነ መረብ ደኅንነት መምህር እና በዘርፉ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ የሚታወቁት ለማ ላሳ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲናገሩ፣ የሰዒድን ሐሳብ በመጋራት የበይነ መረብ አውድ አራተኛው የውጊያ ሜዳ ነው በማለት ይጀምራሉ።

አያይዘውም ‹‹ዓለማት ከዚህ በኋላ በድንበር ግጭት የሚጣሉበት እና በገሃዳዊ ሉአላዊነት አለመረጋጋት ውስጥ የሚገቡበት ወቅት ያበቃ ይመስለኛል። እንዲያውም ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ እንኳ፣ በቨርቹዋል እንጂ በቀጥታ እና የሰው ልጆችን ደም በማፍሰስ የሚካሔድ እንደማይሆን በርካታ አመላካች ጉዳዮች አሉ›› ሲሉም ያብራራሉ። በተለይም ደግሞ በአገራት መካከል ያለው የሥነ ምህዳራዊ ርቀት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሩቅ አገራት መካከል ያሉ ችግሮች ይበልጥ የሚካረሩ ከሆነ፣ ከአገር ምጣኔ ሀብትም አንጻር ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ስለሚያስከትል፣ የበይነ መረብ ጥቃቶች እና ጦርነቶች ማካሔድ ቀላል መሆኑ የጦርነት አውድማውን ወደ ቨርቱዋል እንደሚስበው ይናገራሉ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ እና አሁንም ድረስ በስፋት በኢትዮጵያ እየተሰነዘሩ ያሉ የበይነ መረብ ጥቃቶችን ለመገደብ እና ይባስ ብሎም በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ገጽ ለገጽ ውይይት ከመቋረጡ ጋር ተዳምሮ፣ በቪዲዮ ኮንፍረንስ እየተካሔዱ እንደሚገኙ የሚታወስ ነው። በዚህም ረገድ ከተለመዱት የበይነ መረብ ጥቃት ለመዳን የቅድመ ዝግጅት ማድረጉ ታውቋል።

በዚህም መሰረት ደቦ የተሰኘ እና የቪዲዮ በተለይም በአገሪቱ ትላልቅ የሥራ ኃላፊዎች ዘንድ የሚደረጉ የቪዲዮ ውይይቶች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከለላ ለመስጠት የሚረዳ መተግበሪያ እና ጥቃት መከላከያን ይፋ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ከጊዜያት በፊት ይፋ አድርጓል።

ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ የቪዲዮ ኮንፈረንስ መተግበሪያ የተዘጋጀበት ምክንያት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የወቅቱ የመንግሥት ትልልቅ ስብሰባዎች በቪዲዮ አማካኝነት እንዲከወኑ አስገዳጅ ስለሆነ ነው። ይህንንም ተከትሎ ዓለም ዐቀፍ የሳይበር ጥቃቶች እየተበራከቱ ስለመጡ በአገር ምስጢር ላይ የሚከሰተውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል እና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ በሚደረግበት ጊዜ፣ በቀላሉ ከሳይበር ጥቃት ነፃ በሆነ መልኩ መሥራት ለማስቻል ታስቦ መሆኑን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይቨር ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር በኃይሉ አዱኛ ያስረዳሉ።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስትጠቀምበት የነበረው የቪዲዮ መገናኛ ዘዴ የመቆጣጠሪያ ሰርቨሩ በአገር ውስጥ ስላልነበር መተግበሪያውን የሚቆጣጠረው ከአገር ውጭ የሚገኝ ኩባንያ ስለነበር የአገር ምስጢር የተጠበቀ እንዳልነበር ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ የግንኙነት መስመሩ መተግበሪያውን ተጠቅመው ለሚገናኙት ሰዎች መረጃው የሚደርሰው በቅድሚያ በተቆጣጣሪዎቹ አልፎ መሆኑን አስረድተዋል። በዚሁ ምክንያት የመረጃ ልውውጡን የሚቆጣጠሩ የሰርቨሩ ተቆጣጣሪ አገራት የአገራትን መረጃ ቀድመው በመጥለፍ ለተለያዩ የጥቃት ዓላማ እንደሚጠቀሙ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ተሠርቶ አስተማማኝነቱ ተረጋግጦ ለመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የዋለው የቪዲዮ ኮንፍረንስ መተግበሪያ ስርአት፣ የመቆጣጠሪያ ሰርቨሩ በአገር ውስጥ እንደሆነና በሌሎች አገሮች እንዳይጠለፍ ተደርጎ መሠራቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የመተግበሪያውን የመረጃ ደኅንነት በአገር ውስጥ ጠላፊዎች እንዳይጠለፍም የደኅንነት አጠባበቁ ስለሚደረገው የመረጃ ልውውጥ ከግንኙነቱ ዉጭ ለሆነ ሰው መረጃ እንዳያሳይ ተደርጎ ተሠርቷል ተብሏል። በተጨማሪም መተግበሪያው በአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲሠራ ማድርግ እንደሚቻልም ተነግሯል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ከግብጽ መነሻቸውን ያደረጉ 17 የበይነ መረብ ጥቃቶች በሦስት ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ቢሆንም፣ ኤጀንሲው የተቃጡትን 17 ጠቅላላ ጥቃቶች ማክሸፉን አስታውቋል። ይህ ታዲያ ከዚህ ቀደም ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ሲሰነዘር የነበረውን የበይነ መረብ ጥቃት ወደ አፍሪካ ተጠናክሮ መግባቱን ማሳያ እንደሆነ ለማ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።
ከግብጽ የሚነሰዘረው ቀጣዩ ጥቃት – በበይነ መረብ ወይስ በቀጥታ ጦርነት?

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ሰኔ 10፣ 12 ፣ 13 እና 14/2012 መቀመጫቸውን ግብጽ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ያቀዱበትንና በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታውቋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራው የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ (Cyber_Horus Group) ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር (AnuBis.Hacker) እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስድ (Security_By_Passed) በተባሉ የሳይበር አጥቂዎች አማካይነት መሆኑንም ኤጀንሲው ገልጿል።

ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ ሲሆን፣ በይበልጥ አርብ ሰኔ 12/2012 እና ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ኤጀንሲው ጠቅሷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የ13 የመንግሥት፣ አራት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ድረ-ገጽን የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውቋል።
የሳይበር ጥቃት ሙከራው በአገሪቱ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስድ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ኃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን፣ ዋና ዓላማቸውም በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተለይ ከውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን ዐቀፍ ተጽእኖ በአገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደነበር ገልጸዋል።

የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደኅንነታችው ታሳቢ ያላደረጉ ተቋማት፤ በቀጣይነት የደኅንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አረጋግጧል።

ኤጀንሲው አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት እና ይህን መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት መከላከል ባይችል ኖሮ ጥቃቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖሊቲካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር ገልጿል። ኤጀንሲው አያይዞም በመከላከሉም ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ማስወገድ መቻሉን እና ይህንንም ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አሳውቋል።
በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፤ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራ ሊሰነዘር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት .et domain ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደኅንነት አረጋግጠው እንዲጠቀሙ፤ ራሳቸውን ከሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት ለመከላከል እና አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ኤጀንሲው ጥሪውን ማቅረቡንም ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ ገልጿል።

በቅርቡ የተፈጠረውን እና ከግብጽ የተቃጣውን በይነ መረብ ደኅንነት ጥቃትም በተመለከተ ሙያዊ አስተያየታቸውን የሚሰጡት ለማ ላሳ፤ ‹‹ይህ ዓይነት ጥቃቶች እንደሚኖሩ ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ ተናግሬ ነበር። ግን የሚሰማ እና ሰምቶም ወደ ተግባር የሚገባ ሰው የለም ወይም አልነበረም። ግብጾች ካለንበት መልክዓ ምድራዊ ልዩነት እና ርቀት እንዲሁም ከሚያቋርጡበት በርካታ አገራት አየር ክልል ታሳቢ አድርገው የበይነ መረብ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዕሙን ነው። በተለይም ደግሞ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የተያዘለት ቀነ ገደብ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር፣ ከፍ ያሉ ጥቃቶች ለመሰንዘራቸው ምክንያትም ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

ይህ ታዲያ የሚቀጥል እና ወደ ፊትም የሚቆይ ተግባር እንዳልሆነም ጨምረው ገልጸዋል። ‹‹ይህ አካሔድ ግብጾችንም የሚጠቅም አይደለም። ብዙ የሚያስኬድ ባለመሆኑ ለጊዜው ይሞክራሉ። ነገር ግን ከኢትዮጵያ ወገንም የሚገጥማቸው ጠንካራ ምከታ ያስቆማቸዋል። እምብዛም እንዳይገፉበትም ይደርጋቸዋል›› ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ዓለም ዐቀፍ መጻኢ ሁኔታ እና ኢትዮጵያም የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግም፣ ስርዓተ ትምህርቶች በበይነ መረብ ደኅንነት ዙሪያ መቀረጽ እንደሚኖርባቸው እና ጠንካራ የሆነ ሰርቨር በአገር ደረጃ ሊኖር እንደሚገባም ለማ ያስገነዝባሉ። በተለይም ደግሞ የልሕቀት ማእከላት መገንባታቸው ዕውን መሆን እንደሚኖርባቸውም አውስተዋል። ይህንም ተከትሎ ለልሕቀት ማእከላት ግንባታ የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጥናት እያዘጋጁም እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹እስኪ አስበው! የተሰነዘሩት ጥቃቶች በሙሉ ተሳክተው ቢሆኑ ኖሮ እና ቴሌኮሙን ጠልፈውት ቢሆን ኖሮ እኮ እንደ አገር ትልቅ ችግር ውስጥ ገብተን ነበር›› ሲሉም ሁኔታው የፈጠረባቸውን ድንጋጤ ሳይሸሽጉ አንስተዋል።

የለማን ሐሳብ የሚጋሩት ሰዒድ ነጋሽም፣ በገንዘብ ተቋማት አካባቢም ከፍተኛ የሆነ የበይነ መረብ ደኅንነት ክፍተቶች መኖራቸውን እና ይህም በአፋጣኝ ሊቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ለመሆኑ ጠቁመዋል። ‹‹በአንዳንድ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ ጥቃቅን እና ለውጭ ፍጆታ የማይውሉ የበይነ መረብ ጥቃቶች መኖራቸው ይሰማል። ነገር ግን ለገጽታ ግንባታችን መጥፎ ነው፣ ደንበኞቻችን ይርቁናል በሚል ታፍነው የሚቀሩ ጥቃቶች መኖራቸው ይሰማል›› ሲሉ ይናገራሉ።

ሰዒድ አያይዘውም ከግብጽ የተጀመረው የበይነ መረብ ጥቃት ዘመቻ አዲስ እንዳልሆነ እና ከዚህ ቀደምም በጥቂቱም ቢሆን የሚሰነዘሩ ግን በአጭር ጊዜ ይከሽፉ የነበሩ ጉዳዮች እንደሆኑ ይናገራሉ። ከለማ ሐሳብ በተለየ ሰዒድ አስተያየታቸውን ሲያሰቀምጡ፣ ከግብጽ በኩል የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ከዚህም በላይ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው ባይ ናቸው።

‹‹ምክንያቱም ቀደም ብለን የጦር ኃይላችንን ወደ ማጠናከሩ እንጂ ይህን ያህል የበይነ መረብ ጥቃት ሪኮርድ ያላትን አገር ወደ ቨርቹዋል ፊታችንን አዙረን ጠንካራ ሰርቨር እንዲኖረን የሠራንበትን ጊዜ አላስታውስም›› ሲሉም አስተያየታቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም ሰዒድ አስተያየታቸውን ሲያስቀምጡ፣ መንግሥት ጠንካራ መተግበሪያዎችንም ሆነ መጠበቂያዎችን ገዝቶ በማምጣት እና በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን በማሰማራት ሊመጣ ካለው እና ከሚሰነዘረው ጥፋት አገርን እና መሰረተ ልማቶችን ሊከላከል ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

በሰላም እና ደኅንነት የትምህርት ዘርፍም ቢሆን የድንበር ግጭቶችን እና ሌሎች የተለመዱ የሰላም እና መረጋጋት ዕጦቶችን ብቻ ከማስተማር በተጨማሪ፣ የበየነ መረብ ደኅንነትንም በተመለከተ ትምህርቶች ቢካተቱበት መልካም ነው ሲሉም ለማ ለሳ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን ይደመድማሉ።

የኹለቱ የተፋሰስ አገራት ፍጥጫ እና መጻኢ እርምጃዎች
የላይኛው ተፋሰስ አገራት ተብለው ከተለዩት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የውሃውን ፍሰት በተመለከተ እና የግድቡን ግንባታ ሒደት ተከትሎ ጠንካራ ተቃውሞዎችን የምትሰነዝረው ግብጽ፣ ከአሜሪካ ዋሽንግተን እስከ አዲስ አበባ ብሎም ካርቱም እና ካይሮን ጨምሮ ያልተሰበሰቡበት እና ለድርድር ያልተሔደበት ስፍራ እንደሌለ ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ይሁን እንጂ ከተፋሰስ አገራት ጋር ድርድር እያካሔደች በጎን ደግሞ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የአቤቱታ ደብዳቤዎችን በማቅረብ እና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ የማድረግ ሥራዎችንም እየሠራች እንደምትገኝ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም ከዚህ በኋላ ግብጽ የተፋሰስ አገራትን ድርድር ረግጣ የምትወጣ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ዳግመኛ ለድርድር እንደማትቀመጥ አስታውቋል። አያይዞም ለጸጥታው ምክር ቤትም ኢትዮጵያ በተያዘለት ጊዜ ገደብ የግድቡን ውሃ ሙሌት እንደምታካሂድ አስረግጦ ተናግሯል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ትልቁ የግብጽ ፍራቻ ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌት ከጀመረች የሚፈሰው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ የሚል ነው። በተለይም ለአገሪቷ ደኅንነት ቅርብ የሆኑት የግብጽ ሚዲያዎች ግድቡ ትልቅ ስጋት እንደሆነ በመግለፅ የሚያወጡት ዘገባ ግብፃውያን ስለ ግድቡ እና ስለ ኢትዮጵያ የልማት ግቦች ያላቸው አመለካከት የተንሸዋረረ እንዲሆን አድርጎታል። የግብጽ ፕሬዝደንት የሆኑት አል-ሲሲም ቢሆን ይህንን ክፍተት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ በቅርቡ እስከተነሳው የሕዝብ አመፅ እና ተቃውሞ ለማብረድ፣ ግድቡን ለመቀስቀስ እና የአገራቸውን ፖለቲከ ለማረጋጋት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ምንም እንኳን ከዚህ በኋላ የግድቡን ግንባታ ማስቆም የማይቻል ነገር ቢሆንም፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 አገራቸው ከሱዳን እና ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የስምምነት መርህ መግለጫ ተፈፃሚ እንዲሆን ሲወተውቱ ይስተዋላል።

በስምምነቱ መሰረት ግድቡ ጉልህ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ኢትዮጵያ ቃል ብትገባም በግብጽ በኩል ያለው ፍላጎት በየጊዜው ሲለዋወጥ ተስተውሏል። ከዚህ ቀደም በግብጽ ዲፕሎማት የነበሩት ግርማ፣ ይህንን ከተገነዘቡት መካከል ናቸው። ‹‹ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥቅም ታገኝ ዘንድ በሦስቱ አገራት ስምምነት መሰረት በውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅን በተመለከተ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በገልለተኛው ቴክኒክ ኮሚቴ እንዲፈታ ብትፈልግም፣ በግብጽ በኩል ችግሮቹን በፖለቲካ ዐይን የማየት ችግር አለ›› ይላሉ ግርማ። የግድቡ ግንባታ በተፈጥሯዊ እንዲሁም ሌሎች ሊያመጣቸው የሚችለውን ጉዳት ለማጥናት ከሦስቱም አገሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ፤ ከዚያም ቢ.አር.ኤል እና አርቴሊያ የተባሉ ኹለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች የማጣራት ሥራ ተሰጥቷቸዋል።

ይሁን እንጂ በአገራቱ መካከል ያለው ልዩነት ባለመፈታቱ እና ጥናቱን እንዲከታተል የተቋቋመው የሦስትዮሹ የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እንቅስቃሴ ድክመት ጥናቱ እንደታሰበው የዛሬ ሦስት ዓመት በፊት እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆኗል። በቅርቡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ከሦስቱም አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።

ታዲያ በዚህ መሃል ነበር ግብጽ ያልተጠበቀ ምክረ ሐሳብ ይዛ የቀረበችው። በምክረ ሐሳብ ላይ የግድቡ የውሃ ሙሌት በሰባት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የጠየቀች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮቢክ ውሃ እንድትለቅላት ጥያቄ አቅርባለች። ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምክረ ሐሳቦቿ ይህንን ለየት የሚያደረገው ነገር ቢኖር፣ ግብጽ የግድቡን የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ለመቆጣጠር ጥያቄ ማቅረቧ ነበር። ኢትዮጵያ መልስ ለመስጠት ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) መስከረም 7/2012 መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በግብጽ የቀረበው ምክረ ሐሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ውሃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት የጣሰ ነው አሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያን አላስፈላጊ እና ጎጂ ግዴታ ላይ ይጥላል ሲሉ ስጋታቸው ገልፀው ነበር። በተጨማሪ ግብጽ የግድቡ ዓመታዊ የውሃ ፍስት 40 ቢሊዮን እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል ነው ሲሉም ስጋታቸው አጋርተው ነበር።

የተደራዳሪ ቡድኑ አባል እና የሚኒስትሩ አማካሪ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋውም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በዓመት ልትለቅ የምትችለው የውሃ መጠን ከ29 አስከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው በማለት በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመልቀቅ ግዴታ ውስጥ ብትገባ፤ የአየር መለዋወጥን ተከትሎ በሚከሰት ድርቅ የገባችውን ውል መፈፀም ስለማትችል፤ ሐሳቡን ወድቅ መድረጉን ደግፈው ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com