ምልሰት – ወደ አባቶች ቀን

Views: 91

ብዙዎች ‹ፍቅር የለም!› ብለው እንደሚያስቡ እንገምታለን። ይህ ነገር ጥናት የተደረገበት አይመስለኝም። ግን በዙሪያችን ደምቀው የምናያቸውና ጎልተው የምንሰማቸው ጉዳዮች የፍቅርን አለመኖር ሲነግሩን በጥቅሉ እንደሌለ እንዲሰማን ይሆናል። በሚያሳዝን ሁኔታ ደግሞ ፍቅር የሚገኝባቸው ስፍራዎች፣ ኅብረቶችና ልቦች አሙቁልኝ ስለማይወዱ ድምጻቸው አይሰማም። ይህም ተደምሮ ፍቅር እንደሌለ እንድናስብ ያደርገናል።

የዚህ ውጤት ግን የሚታየው ፍቅር የለም ብለን እንድናምን ማድረጉ ላይ ብቻ ሳይሆን እንዲኖር መድከም ዋጋ እንደሌለው ከማሰብም ላይ ነው። ይህ ነው እርስ በእርስ እንዳንተማመንና ያም እየባሰ እንዲሄድ እንጂ እንዲሻለው የማያደርገው።

ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሕጻናት፣ ሴቶችም ወንዶችም ላይ የደረሰው ጥቃት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በተለይም ልጆቻቸውን የደፈሩ አባቶች መኖራቸው መነሳቱ ብዙዎችን አስደንግጧል። ያስፈራል። ‹ልጄ በአባቷ ተደፈረች› ያለች እናት ‹ተጠንቀቁ!› ስትል፣ ምን ማለቷ ይመስለናል? ልጆቻችሁን ከአባታቸው አርቁ? ይህ ነው መተማመንን ይፈትናል፣ አለመተማመንን ያብሳል የምንለው።

ወዲህ ታድያ የአባቶች ቀንም ባሳለፍነው ሳምንት ሲታሰብ፣ ለይቼ ባላስታውስም አንዲት ሴት እንዲህ ስትናገር ሰማሁ። ቃል በቃል ባይሆንም ሐሳቡ እንዲህ ነው፣ የልጆቿ አባት በርካታ ሕጻናት በአባታቸው ጭምር የመደፈራቸውን ዜና የሰማ እለት ቤቱ ገብቶ ሴት ልጁን ሰላም ሲል፣ በልጁ ሐሳብ ውስጥ ምን ሊመላለስ እንደሚችል ለአፍታ አሰበ። ያስፈራል።

‹ፍቅር የለም› ወደማለት ያደረሱን ጎልተው የሰማናቸው የመካካድ ዜናዎች፣ የታዩ ወንጀሎች፣ የተሰሙ አሰቃቂ ድርጎቶች ወዘተ ናቸውና። ለዛ ነው የወደቀ ዕቃ አንስቶ መመለስ በዓለም ደረጃ ሳይቀር አነጋጋሪ የሆነው። መልካም ሥራ የጠፋ እስኪመስለን ድረስ አስከፊና ተስፋ አስቆራጭ ዜናዎች ሥልጣን ይዘዋል።

ያም ብቻ አይደለም። እነዚህ የጥፋት ዜናዎች ዜና ብቻ ናቸው። የተሰጣቸው ግብረ መልስ አይነገርም። ይህም የፍትህን መጓደል ይነግረናል። ይህን መደራረብ የአእምሮና የሥነ ልቦና ምሁራን ምን ሊሉት እንደሚችሉ አላውቅም፤ ግን አላወቅንም እንጂ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ደኅና አይደለንም፤ ታመናል።

በደሃ አገር ላይ፣ የቤተሰብ ድምር አገርን እንደሚፈጥር በሚታመንበት፣ አልፎም አባት ብቻውን የቤተሰብ የገቢ ዋስትና በሆነበት ሁኔታ፣ በአባቶች ላይ የሚኖረው ጫና ቀላል የሚባል አይሆንም። በዚህ ላይ ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ የሚቀበሏቸው አመሎችና ጸባዮች ይደረባሉና፣ ‹አባት› ሲባል እንባ የሚቀድመው እንዳለ ሁሉ፣ ክህደት የሚታየው ጥቂት አይደለም።

በዚህ ላይ ይህ የሕጻናት ልጆች በአባታቸው መደፈር የባሰ ቤንዚን እንዳይሆን፣ ለዜናው ማብራሪያ ሊሰጠው የሚገባ ነው። እናት አንደበት አግኝታ ‹ልጄ በአባቷ ተደፈረች!› ስትልና ‹ሌሎቻችሁም ተጠንቀቁ› የሚል መልዕክት ስታስተላልፍ ወይም ‹በእኔ ይብቃ!› ስትል፣ ከምን ዓይነት አባት ነው የምንጠነቀቀው የሚል ጥያቄ ይመጣል።

ነገሩ ግራ ያጋባላ! ልጁን የደፈረ አባት ምን ዓይነት አባት ነበር? ልጁን ትልቅ ቦታ የማድረስ ሕልም ያለው? የልጁ ሕይወት መስመር እንዳይስት የሚቆጣጠር? የምኖረው ስለልጄ ነው የሚል? በስርዓት ለጋብቻ ለሚጠይቅ ሰው እንኳ ልጁን ለመስጠት ጥያቄ የሚያበዛና ሽማግሌ የሚያመላልስ? የምናውቀው አባት እንዲህ ስለሆነ።

ልጁ እንደሆነች የሚያውቅ አይደለም እንጀራ አባት ተብሎ የተጠራ፣ እንዲህ ያለ በደል ሲፈጽም፣ ክስ ማቅለያ ሳይሆን፣ ስለ መልካም አባቶች ሲባል ምክንያቱ መታወቅ አለበት። አለበለዚያ አእምሯችን እንደታመመ ይቆያል። አሁን ላይ ፍትህ የሚጠየቀውም ስለቆሰሉት ሕጻናት፣ በለጋ እድሜያቸው አእምሯቸው ላይ አስከፊ ክስተት ስለተሳለባቸው ስለወንዶቹም ስለሴቶቹም ልጆች ብቻ አይደለም። ዜናውን ስለሰማ ጆሮ፣ አእምሮው ጉዳዩን ማብላላት ስላሳመመው ሰው ሁሉ ነው።
ሊድያ ተስፋዬ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com