የእለት ዜና

ሀብታም አያነብም ያለው ማነው?

ስለንባብ ጥቅም ብዙዎች ይናገራሉ። ይልቁንም አመለካከትንና እይታን የሰፋ፣ አነጋገርን የሚረታ፣ አሠራርን በብልሃት የተቃኘ ለማድረግም ማንበብ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ብዙዎች ይናገራሉ፣ ይመሰክራሉም። እንዲህ በኮሮና ሰበብ ቤት መቀመጥ ግድ ያለውም ጊዜውን በንባብ እንዲያሳልፍ የሚመክሩ ጥቂት አይደሉም። አብርሐም ፀሐዬ ይህን ሐሳብ አንስተው፣ ንባብን ባህል ማድረግን በዘላቂነት መሥራትና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችም በተግባር ተከታዮቻቸውን ሊመሩበት የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ። ለዚህም በአረአያነት የሚጠቀሱ ሰዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ቢነበቡ መልካም ነው የተባሉና የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችንም አስቀምጠዋል።

የእኛም አገር ሀብታሞችና ባለሥልጣናት ወደ ትውልዱ ቀርበው ያነበቡትን መጽሐፍና ከውስጡ ስላገኙት ፋይዳ እያጫወቱን በንባብ እንገናኝ።
ባለጸጋዎች ይደመጣሉ። በሥልጣን ከፍ ያሉም፣ በሕይወት ዘመናቸው አንዳች የታሪክ ጡብ ያስቀመጡ ተደማጭነታቸው ከፍ ያለ ነው። ሥራቸው ጎልቶ የወጣ ፖለቲከኞች፣ ስፖርተኞች፣ ደራሲያን፣ ጋዜጠኞች የየራሳቸው አድናቂና ተከታይ አላቸው። የሚሉት ይደመጥላቸዋል፤ የሚያደርጉት ይታያል። ትውልድ እነሱን እየተመለከተ መንገዱን ያቀናል። በግልባጩ ያልሆነ ሐሳብና ድርጊት ከእነርሱ ከመነጨም ሕዝብ መንገዱን ይስታል።

ታላላቆች የሚያደርጉት እያንዳንዱ ድርጊት የታላቅነታቸው ግብዓት ነው ተብሎ ስለሚታመን ነገረ ሥራቸው በሕዝብ ዘንድ እንደ አርአያ ይወሰዳል። ያነባሉ ከተባለ አንባቢያን ይፈጥራሉ፣ ትጉህ ሠራተኝነታቸው ሲወሳ የአገሬው ሰው ሥራ ይወዳል። ስፖርት ሲሠሩ ካየ የስፖርት ሠሪው ቁጥር ከፍ ይላል። ሲሰርቁ ከታየም ሰራቂዎች ይበዛሉ። እንዲህ ነው ቅብብሉና ተጽእኖው!
በተለይ ወደ ፈረንጆቹ ካየን ማንበብ ብቻ ሳይሆን አንብቡ እያሉ መጻሕፍት የሚጠቁሙ ባለጸጋዎች አሉላቸው። ወደታች ወረድ ብለን በዚሁ ርዕስ ስር የቱጃሩን የቢል ጌትስን የመጻሕፍት ጥቆማውን እንመለከታለን። ከዚያ በፊት ግን አንዳንድ ሐሳቦችን እናንሳ።

አሜሪካንን እንደ ታላቅ አገር በመገንባት በኩል አሻራቸውን ካሳረፉ ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ ነው የሚባልለት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ድንቅ አባባል አለው። ‹ታሪክ ጻፍ ወይም የሚጻፍ ታሪክ ሥራ›› ይላል። ለጊዜው ከኹለት አንዱ ያልሆንን ደግሞ ሦስተኛ አማራጭ አለን፤ ማንበብ የሚባል።

የተሠሩ ታሪኮችን ብናነብ በጎ ነገር እንወርሳለን። በዚያ ተነስተንም ታሪክ እንሠራለን። የንባብ ፋይዳው ቀላል አይደለም። ንባብ እይታን ያሰፋል፣ መጻሕፍት እንቅፋቶችን እየከረከሙ መንገዶችን ያቀናሉ። ብርቱ ጸሐፍት በምናብ ሠረገላ የሚመላለሱ ናቸውና ቀድመው ያያሉ፤ ይተነብያሉ። ያንንም ይጽፉታል። ለዚህ ነው ዘመን በየጊዜው ሲቀያየር መጽሐፍት ግን ከተነባቢነታቸው የማይቀየሩት፣ ቀያሪ ናቸው እንጂ የሚቀያየሩና የሚጠፉ አይደሉም።

ንባብን የሙጥኝ የሚሉ የመቀየሪያውን ማሽን ቁልፍ እንዳገኙ ይቁጠሩ። ዓለም ትላንቷን፣ ዛሬዋንና ነገዋን የምትከትበው በመጻሕፍት ነው። አንባቢዎች የሆኑ ደግሞ የዓለምን ዶሴ አገኙ ማለት ነው። ጠቢባን በዓለም ላይ በእግር ከመመላለሳቸው አስቀድመው በንባብ መንገድ ይመላለሳሉና፣ የመጻሕፍት ወዳጆች የሆኑ ከጠቢባን መንደር ራሳቸውን ያገኛሉ ማለት ነው።
መጻሕፍት የነገን መንገድ አጥርተን የምናይባቸው መስታወት ናቸው። የትላንቱን ስበው፣ ዛሬን ፈትሸው፣ ከመጪው ጋር አስተሳስረው የሚያሳዩ የትውልድና የዘመን ካርታ ናቸው። ጥሩ አንባቢዎች ጥሩ መሪዎች ናቸው የሚባለውም ለዚህ ነው። ወደኋላም ወደፊትም ያያሉና።

ጥቂት የዓለማችን መሪዎችና ባለጸጎች ካነበቧቸው መጻሕፍት ውስጥ ይሆናል ያሉትን ይጠቁማሉ። እንደነ ቢልጌትስና ዋረን ባፌት ያሉ ቱጃሮችን መጥቀስ ይቻላል። የተወሰኑ መሪዎችም ይሄ ልማድ አላቸው፤ በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት በመገኘት በዕረፍት ወቅት ተማሪዎችና ሠራተኞች ሊያነቡት ይገባሉ የሚሉትን መጻሕፍት ይጠቁማሉ።

ለማሳያ ያህል ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጥሩ የማስረዳትና ሐሳብ የማካፈል ልማድ ባለቤት ናቸው። አነጋጋሪው ፕሬዝዳንት ትራምፕም እንዲሁ ከማንበብ እስከ መጻፍ ጥሩ የሚባል ልምድ አላቸው። በተለይ በቢዝነስ ጉዳዮች ላይ አመለካከታቸው ይደነቃል። የጀርመኗ አንጌላ ሜርኬልም አንብበው ለሌሎች በማካፈል በኩል ተመሣሣይ ልማድ አላቸው።

በአገራችን
በአገራችን በየጊዜው የንባብ ባህልን ለማዳበርና ይህንኑ ባህል ለማስቀጠል እንዲቻል ልምምድ የማድረግ ብቅ ጥልቅ የሚል እንቅስቃሴ ይደረጋል። አለመታደል ሆኖ ይሄም ጉዳይ እንደ ሌላው ዘመቻ ተጀምሮ ይቀራል። በየመገናኛ ብዙኀኑ እየተሠራ ያለው ንባብ ተኮር ፕሮግራም ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፣ በተደራጀና በዓላማና ግብ የተቀየሰ መሆኑ ግን ያጠራጥራል።

አመራረጡና አቀራረቡ ዥንጉርጉር ነው፤ ወጥነት የለውም። የአገራችንን ጸሐፍትና አንባቢ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን በተጠና አካሄድ መርጦና አዘጋጅቶ ማምጣት ቢቻል መልካም ነው። እንደነ ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ ያሉና ወደ ትውልዱ ቀርበው የሚወያዩ ጥቂት ባለጸጋዎች አይጠፉምና፣ መፈላለግ መልካም ነው። የፍሊንት ስቶኑ ባለቤት ጸደቀ ‘ሾተል’ የሚል መጻሕፍ አበርክተዋል። አንባቢ ትውልድ ያልፈጠረች አገር ለውጥን እያሰበች ከሆነ በአገር ላይ ማሾፍ ነውና፣ የንባብ ባህል እንደቀላል መታየት የለበትም።

ቢል ጌትስና ንባቡ
ባለጸጋው ቢል ጌትስ በዚህ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለዕረፍታችሁ ብታነቡት ያሉትን መጻሕፍት ከነመጠነኛ ማብራሪያቸው ብንጋራ ለኛ አገርም ጥሩ ልምድ ይሆናል። አንባቢ መሆናቸው የሚነገርላቸው ባለሀብቱ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በቤታችሁ ስትሆኑ ብታነቡት ያሉትን እነሆ (አንባቢን አንተ እንበልና በሱ እንቀጥል)
1.The Choice (By Dr. Edith Eva Eger)
ይህን የመጽሐፍ ርዕስ ወደ አማርኛ መልሰን ብናየው ‹ምርጫው› የሚል ትርጉም ይኖረዋል። ቢል ጌትስ ስለመጽሐፉ ሲገልጽ ስላለፈ አስቸጋሪ ሕይወት የሚያነሳ ነው ይላል። የመጽሐፉ ደራሲ የሆነችው ኤገር (Eger) በ16 ዓመቷ ወደ ኦሽዊትዝ የመግደያ ካምፕ ከነቤተሰቦቿ ተግዛ በነበረችበት ሰዓትና ከዚያ በኋላ በተዓምር ተርፋ አሜሪካ ውስጥ ሐኪም በመሆን እያገለገለች የጻፈችው ግለ ታሪክ ነው።
ቢል ጌትስ ይህ ዓይነት መጽሐፍ ሰዎች በሕይወታቸው አስቸጋሪ ክስተት ሲገጥማቸው በምን መልኩ እንደሚያሸንፉት የሚያስተምር ነው በማለት አንደኛ ምርጫዬ ነው ብለው ጠቁመዋል።

2.Cloud Atlas (By David Mitchell)
በግርድፉ ‹የአትላስ ደመና› የሚል የአማርኛ ትርጉም እንስጠው። ይህ መጽሐፍ በውስጡ ስድስት ታሪኮችን አስተሳስሮ የሚተርክ ልብ ወለድ ነው። ማንም ሰው ከጨረሰውም በኋላ ማሰቡን እንደማያቆም በተለይ የሰው ልጅ አስቸጋሪና አስደሳች ሕይወት እንደሚያሳልፍ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ መርከበኛ የነበረውን አሜሪካዊ ወጣት በማስታወስ ቢልጌትስ አንብቡትና እንደኔ ተመሰጡበት ሲሉ ኹለተኛ ጥቆማቸው አድርገውታል።

3.The Ride of a Lifetime (By Bob Iger)
‹የሕይወት ዘመን ጉዞ› ብለን የምንተረጉመው ይህ መጽሐፍ ቢል ጌትስ በቢዝነስ መጽሐፍነቱ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ በነበረው ንባቤ ወደር የማይገኝለት ነው ብለውታል። በከፍተኛ አመራር ላይ ሆነው ትልቅ ድርጅት ለሚመሩ ኃላፊዎች ውስብስብ ሥራ እንዴት እንደሚመራ ያስተምራል ካሉ በኋላ፣ መጽሐፉ ከቁምነገረኝነቱ በዘለለም በመዝናኛነቱም ሊነበብ ይችላል በማለት በሦስተኝነት የጠቆሙት ነው።

4.The Great Influenza (By John M. Barry)
‹ታላቁ ኢንፍሉዌንዛ› የሚል ትርጉም ያለው ይህ መጽሐፍ የቢል ጌትስ አራተኛ ጥቆማ ነው። መጽሐፉ በዚህ በቀላሉ ሊተነበይ በማይችል ዓለም ላይ እንደመኖራችን ሊገጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመረዳት ሲባል ወደ ኋላ ተመልሰን ስላሳለፍነው ታሪክ መረዳት እንደሚገባን ያስረዳል።
ይኸው በ1918 ስለተከሰተው ገዳዩ ኢንፍሉዌንዛ የሚተርከው መጽሐፍ፣ የወረርሽኝ አደጋ እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችልና ይህ ዓይነት ክስተት ሲገጥመንም ምን እንደሚከሰት መገመት የሚቻልበት ነው በማለት በአራተኝነት ጠቁመውታል።

5.Good Economics for Hard Times (By Abhijit V. Banerjee and Esther Duflo)
‹ጥሩ የምጣኔ ሀብት ቀመር ለአስቸጋሪ ወቅቶች› የሚል ትርጉም ያለው ይህ መጽሐፍ፣ በኹለቱ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚዎች የተጻፈ ነው። እንደ ቢል ጌትስ ጥቆማ መጽሐፉ ለዚህ ዘመን ምጣኔ ሀብት የሚሠራና በመካከለኛ ደረጃ ላሉ አንባቢዎችም የሚጠቅም ነው።

መጽሐፉ ኢ-እኩልነትና ፖለቲካዊ ክፍፍልን በመዳሰስ ከምጣኔ ሀብት የፖሊሲ ሐሳቦች አንጻር የተጻፈ ሲሆን፣ እንደ አሜሪካ ባሉ የበለጸጉ አገራት ጉዳዮችን የሚቃኝ ስለመሆኑ ቢል ጌትስ ገልጸው፣ በአምስተኛነት ጠቁመዋል።
መጪው ክረምት ነው። እናንብብ! ቸር ያሰማን!
አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com