ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

Views: 251

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዋንግ ዪ በኩል አረጋግጣለች።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ ከቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑት ዋንግ ዪ ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በነበራቸው የስልክ ውይይት በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አቶ ገዱ የቻይና መንግስት ”በቤልት እና ሮድ ኢንሸቴቭ” አማካኝነት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስችል የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን እና የሚኒስትሮች ቨርቿል ኮንፍረንስን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የኮቪድ ወረርሽኝን ለመግታት ቻይና ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት ከቻይና ጋር የጀመረችውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሰርል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የተካሄደውን አስቸኳይ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ቨርቿል ስብሰባና ውሳኔ በተመከተም አቶ ገዱ ገለጻ አድርገዋል።

መሪዎቹ የናይልና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው መስማማታቸውን፤ በዚሁ መሰረት በግድቡ ሙሊት እና አሰተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚጠናቀቅ መስማማታቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲገልፅ መወሰኑን አቶ ገዱ አብራርተዋል።

በመሆኑም ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በኩል መታየት በጀመረበት አግባብ እንዲፈታ ቻይና ድጋፏን እንድታደርግም አቶ ገዱ በውይይቱ ወቅት ጠይቀዋል።

ዋንግ ዪ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵየ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ እና ትብብሯንም አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com