ሀጫሉ ሁንዴሳ

Views: 131

እኩለ ሌሊት አካባቢ ነው። ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎች ይልቁንም ፌስቡክ ግን እኩለ ቀን የሆነ ያህል ብዙዎች ሲመላለሱበት ነበር። ሁሉንም ያስደነገጠ፣ ያስጨነቀና ያሳዘነ ጉዳይ በዜና ተሰራጭቷል። ‹ውሸት አድርገው! ሕልም ይሁን!› ብሎ የሚጸልየውም ጥቂት አይመስልም። ዜናው በእርግጥም ልብ የሚሰብር ነበር። ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ በጥይት መመታቱንና ጳውሎስ ሆስፒታል ቢገባም ሕይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ነው።

ይህን ጉዳይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጠቅሶ እውነት እንደሆነ አረጋገጠ። ከዛች ቅጽበት ጀምሮ የነበረው ሁሉ እንዳልነበር ሆነ። የአዲስ አበባ ብሎም የመላው አገሪቱ ሰላም ተናጋ። የወጣቱ ድምጻዊ ኅልፈት ሐዘን የተሰማቸው ሰዎች ሐዘናቸውን የሚያስተናግዱበት ፋታ አላገኙም። ሞቱን ምክንያት ያደረጉ አለመረጋጋቶች ተከተሉ።

ወደ አዲስ አበባ መግቢያ የሆኑ የተለያዩ አቅጣጫዎች ቁጣና ሐዘንን በተመሉ ወጣቶች ተጥለቀለቀ። በሌሊቱ ከሰባት ሰዓት ጀምሮም ወጣቶች በብዛት አዲስ አበባ ተገኙ። በርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና አዲስ አበባም ጭምር ታወኩ። ‹ሀጫሉን ማን ገደለው፣ ለምን ተገደለ› በሰዓቱ ለዚህ መልስ የሚሰጥ አልነበረም። በማግስቱ ከረፋድ ጀምሮ ለጸብ አጫሪነት የተሰማሩ የሚመስሉ መገናኛ ብዙኀን ‹እነ እገሌ ናቸው የገደሉት› አሉ።

ይህን ተከትሎ ብጥብጥና አለመረጋጋት ባሰ። በአዲስ አበባ የተለያዩ ቤቶች በድንጋይ ናዳ መስታወቶቻቸው ሲረግፍ፣ በየስፍራው ንብረት በእሳት ወደመ። ብዙዎቹ ዘነጉ፣ ስለእነርሱ ፍትህ ማግኘትና ነጻነት ባመነበት መልኩ ሲታገልላቸው የነበረውን ሰው፣ የፖለቲካቸው መጠቀሚያ አደረጉት። በሞቱ እንደመዘባበት ባለ መልኩ ተቀባበሉት። ሰላም በአንድ ጊዜ ሸሸች። ‹ጂራ ጂራ ጂራ!› ሲል ያቀነቀነው ድምጻዊ፣ የ36 ዓመቱ ሀጫሉ ሁንዴሳ ወደማይመለሱበት ሄደ።

ሀጫሉ ሁንዴሳ (1976-2012)
ሀጫሉ ትውልድና እድገቱ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ ነው። በ1976 ይህቺን ዓለም የተቀላቀለው ሀጫሉ በ1981 ትምህርት ጀምሮ አንደኛ ደረጃ እንዲሁም ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአምቦ የመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። ከምንም በላይ ታድያ ከእጁ ክራር ተነጥሎ እንደማያውቅ በሕይወት ታሪኩ ላይ ከቤተሰቦቹና ጓደኞቹ እማኝነት ተጠቅሶ ሰፍሯል።
ወላጅ እናቱ ጉዲቱ ሆራ እና አባቱ ሁንዴሳ ቦንሳ ከወለዷቸው ዐስር ልጆ መካከል ሀጫሉ አምስተኛ ልጃቸው ነው። ከእርሱ ጋር ስድስት ወንድ ልጆችን እና አራት ሴቶችን ወልደዋል። ልጃቸው ሀጫሉ ታድያ ገና በለጋነት ነበር ፖለቲካው ትኩሳትና ግለት፣ ተቆርቋነትም ተሰምቶት የቀረበውን ትግል የተቀላቀለው።

ይህም በሕይወቱ ቀላል የማይባልን መስዋዕትነት እንዳስከፈለው ዛሬ ካለፈ በኋላ ብዙዎች ተረድተዋል። በተለይም የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በተቀላቀለው ትግል የተነሳ እርሱና ሌሎች ጓደኞቹ ለእስር ተዳርገዋል። ይህም በ1995 የሆነ ሲሆን፣ ሀጫሉ አምቦ በሚገኝ እስር ቤት አምስት ዓመታትን አሳልፏል። ይህ ከእድሜው፣ ከሕይወቱ፣ ከትምህርቱ፣ ከነጻነቱ የተነጠቀውን አምስት ዓመት በማረሚያ ቤት እንዲሁ ያሳለፈው አልነበረም።

እንዲህ ነው፤ ይልቁንም በእስር ቤቱ ትምህርት እንዲጀመር ከማረሚያ ቤቱ አመራር ጋር ተነጋገረ። ያንንም ሊያሳካ ቻለ። አልፎም ለጥሞና የረዳው ይመስላል፣ ከእስር ከተፈጣ ስድስትና ሰባት ወር ገደማ ቆይቶ ያወጣው የመጀመሪያ አልበሙ ‹ሰኚ ሞቲ› የግጥምና የዜና ሥራዎችን በዛው በእስር ሳለ ነው ያሰናዳቸውና በሐሳቡ የጨረሰው።

ሀጫሉ አዲስ አበባ እንደመጣ ከታምራት ከበደ ጋር ተገናኝቶ በእስር ቤት ሳለ የወጠነውን የመጀመሪያ አልበሙን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቀቀና ለአድማጭ አደረሰ። ይህ አልበሙ ነበር ከአድማጩና ከሕዝብ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው። ይሄኔ ሀጫሉ የአምቦ ልጅ ብቻ እንዳይደለ ታወቀ፣ የአገር ልጅ ነውና፣ የኢትዮጵያ።

ከአልበሙ ውስጥ ሰኚ ሞቱ የተሰኘው ሙዚቃ የሙዚቃ ቪድዮ ተሠራለት። ቀጠን ያለ፣ ከገጹ ፈገግታ የማይጠፋና በአፋን ኦሮሞ የሚያንጎራጉረውን ሙዚቃ ቋንቋውን መረዳት ለማይችሉ ቅንጥስጥስ እያለ በእንቅስቃሴው የሚተርክ ዓይነት ሙዚቀኛ ነው። በተለይም ‹ሰኚ ሞቲ› የተሰኘው ሙዚቃ ቪዲዮ ተሠርቶለት ለእይታ ከቀረበ በኋላ ሀጫሉ ለጆሮ ብቻ ሳይሆን ለዐይንም እንግድነቱ አበቃ።
ሀጫሉ ጽናቱን ያሳየበትን አንድ ድርጊት የፈጸመው ከዚህ በኋላ ነው። አቋርጦ የነበረውን ትምህርት ቀጠለና አጠናቀቀ። በሙዚቃ ሥራውም ከእለት እለት እያደገ ከጃምቦ ጆቴ ጋር ስብስብ ሥራዎች አሳተሙ። ሕልሙም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነበር፣ በተለይም ከጃምቦ ጆቴና ሌሎች ድምጻውያን ጋር በመላው ኦሮሚያ የሙዚቃ ድግስ ወይም ኮንሰርት የማቅረብ ፍላጎት ነበረው።

ሕይወት ለዚህ ወጣት የሙዚቃ አፍቃሪና ላመነበት ሐሳብ ተሟጋች የሆነ ሰው ተረጋግታ አልሄደችም። አንድ የሙዚቃ ሥራ ለማቅረብ በጉዞ ላይ ሳለ የመኪና አደጋ አጋጠመው። ለሞት ግን አልዳረገውም፣ ሆኖም በደረሰበት ጉዳትና ከዛ በማገገም በወሰደበት ጊዜ ለበርካታ ዓመታት ከሙያው እንዲርቅ ግድ አለው። አልተሸነፈም፣ ደግሞ ተነሳ። ‹ዋኤ ኬኛ› የተሰኘ ኹለተኛ አልበሙን ሠራ። ከዚህ በኋላ አሜሪካ ሄደ። በአሜሪካ የመጀመሪያ ኮንሰርቱን አቀረበ። ጥሪ በተደረገለት ሁሉ በአረብና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሙዚቃውን አቅርቧል። ባቀረበበትም ከፍተኛ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ፣ ‹እዚህ ቆይ! አትሂድ› ያሉት አልጠፉም። እርሱ ግን ለሙያው ፍቅርና ለቤተሰቡ ክብር፣ ወገኑና አገሩም ማገልገልን መርጦ አገሩ ተመልሷል።

‹ማላን ጅራ› የተሰኘ ሙዚቃው አሁን ላይ ብዙዎች ደጋግመው የሚሰሙትና ቋንቋውን የማይረዱ ሳይቀሩ አብረው የሚወዘወዙበት ድንቅ የሙዚቃ ሥራው ነው። የጥበብ ሰዎችና ሙዚቀኞች ለሰብአዊ ድጋፍና ኅብረት ባስፈለገበት ጊዜ አቤት ለማለት ፈጣን፣ አጋዥና ምን እንታዘዝ ባይ ናቸው። የፖለቲካው ነገር አልጥም ሲላቸው፣ ነገሮችን መቃወም ሲፈልጉና ድምጻቸውን ማሰማት ሲሹ ፍጥነታቸው በዛ ልክ አይደለም። ጥቂቶች ግን በስንኞች ይቀኛሉ፣ ሕዝቡም መፍትሄ እንዳገኘ ሁሉ አብሮ ያዜማል።

ሀጫሉ እንዲህ ካሉት ሙዚቀኞች መካከል ነው። በዚህ ዘርፍ እንዲደነቅ ያደረገውም የሚያምንበትን በድፍረት ስለሚናገርና ዝም በተባለበት፣ ወይም ሐሳብና ጭኝቀትን ሰው በለሆሳስ በሚነጋገርበት ጊዜ እንኳ እርሱ ድምጽ ማጉያውን አንስቶ፣ ግጥሞቹን ከዜማ አጣምሮ ስለፍትህ የሚዘምር መሆኑ ነው።

‹ማላን ጂራ› የሚለውን ሙዚቃውን በድምጽ ብቻ ሳይሆን በምስል ሲያቀርብ፣ የሙዚቃውን ጭብጥ ቋንቋውን የማይረዳ እንኳ በቀላሉ እንዲገባው አስቻለ። መለያየት፣ በትውልድና በነገ ውስጥ የሚገኝ ተስፋ፣ እምነትና ጽናትን በዚህ የሙዚቃ ስንኝ ቀለምነት በብዙ ሰው አእምሮ ሸራ ላይ ሳለ። ጥበብ ስለራሷ ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበረሰብ ልትሰጥ በምትችለው አገልግሎት ውስጥ ልትታይ ቻለች።

‹ማላን ጂራ› የወጣው በ2007 ነው፣ ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት። ይህም የኦሮሞ ወጣቶች ጥያቄ ጎልቶ የተነሳበት ወቅት ነው። እርሱም ቢሆን ሙዚቃውን የሠራው በወቅቱ የነበረው ሙቀት መነሻ ሆኖት እንደሆነ መናገሩን የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን አብሮን አደረገው ካሉት ቆይታ ጠቅሰው ገልጸዋል።

‹ማላን ጅራ› ምኑን አለሁት እንደማለት ነው። በኋላ ታድያ ይህን ሙዚቃ ተከትሎ በሠራቸው ሥራዎች የፖለቲካውን ሂደትም አብሮ የሚተርክ ይመስላል። ይልቁንም በ2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ፣ የተመኙት ለውጥ ሲመጣ፣ ‹ጂራ ጂራ!› ወይም ‹አለን አለን!› የተሰኘ ሙዚቃን ሠራ።

የጥበብ ሰው ርኅራሔ
ካፒታል ሆቴል የተካሄደን አንድ መድረክ ጥቂት የማይባሉ መገናኛ ብዙኀን ከ‹አንድ አፍታ› ዩትዩብ ቻናል ተውሰው ሲያጋሩት ነበር። በዛም ላይ ድምጻዊው ድምጽ ማጉያውን ጨበጠና ወደ መድረኩ ወጣ። ያደረገው ንግግር ሐሳቡ ሲጨመቅ፣ ቃል በቃል ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በተቀየረ አገላለጽ፣ እንዲህ የሚል ነበር፣ ‹ከያኒያን ሩኅሩህ ናቸው። ለአድማጭ፣ ተደራሲ፣ አንባቢ፣ ተመልካች ወዘተ ያላቸውን ከመስጠት አይቆጠቡም። በማኅበራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም ጭምር የሕዝብን ድምጽ ማሰማት ተገቢ ነው። እንደ ርኅራሄና እንደ ልገሳም የሚቆጠር ነው።›
ያንን እርሱ አድርጓል። ያመነበትን ከመናገር ወደኋላ የማይለው ሀጫሉ፣ በተለያዩ የመድረክ ሥራዎቹም በሽለላና በፉከራ መልክ የሚያቀርባቸው የተቋጠሩ ስንኞች፣ አስደንግጦ ‹ኧረ ጸብ እንዳያመጣ!› የሚያሰኛቸው እንዳሉ ሁሉ፣ አብረውት በቁጭት ሲያቀንቅኑ የሚታዩ ጥቂት አይደሉም።

ካለው ላይ በማካፈልና በመስጠት የሚወደሰው ሀጫሉ፣ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ በተፈናቀሉ ጊዜ ድጋፍና ገቢ ማሰባሰብ ላይ እንዲያግዝ ጥሪ ሲቀርብለት፣ አቤት ወዴት ከማለት ውጪ ደጅ አላስጠናም፣ አላንገራገረም። ሌሎችንም ቀስቅሷል። በ2011 የአድዋ ድል በዓልን በሚመለከት በቀረበ ዝግጅት፣ የኦሮሞ ተዋጊዎች በጦርነት የነበራቸውን ከፍ ያለ ሚና አንስቷል። ለአምቦ የከተማ ልማት ሥራ ካለው ገንዘብ ከመስጠት አልቦዘነም።

በመጨረሻ
ለጥፋት የተሰማሩ እጆች ክፍተትንና አጋጣሚን ይጠቀማሉ። ካልተገኘ ደግሞ ይፈጥራሉ። ሀጫሉ በሕይወት በነበረበት ዓመታት በሐሳቡ የማይስማሙና የሚቃወሙት ጥቂት አይደሉም። የሚደግፉትም እንደዛው በርካታ ናቸው። እርሱም ያመነበትን ከመግለጽ ወደኋላ አይልም፣ አላለም ነበር። በተለይም በታሪክ ዙሪያ በሚነሱ አለመግባባቶች ውስጥ፣ የሚያምንበትን ይገልጻል።
ሰው በዙሪያው ያለ እንቅስቃሴ ውጤት እንደሆነው ሁሉ፣ ገና በልጅነት እድሜ በእስር ያሳለፈው ሕይወት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚንሸራሸሩ ሐሳቦች፣ እድሜው፣ እርሱ ከተገኘበት ሐሳብ በተቃራኒ አቅጣጨ የሚመጡ ወቀሳዎች፣ በመጨረሻም የራሱ ግንዛቤና እይታ ሀጫሉን ሠርተውታል። ወጣት ነበር፣ ራስን በመፈለግ የሰው ልጅ የኑሮ ዑደት ውስጥ እየጎተቱ ጊዜውን የበሉበት ኹነቶች ቢቀናነሱ፣ የኖረው ጥቂቱን ነው።

ይህ ሁሉንም ያሳዘነ ክስተት ነው። ጉዳዩም የሐሳብ ልዩነት አይደለም፣ እውነትና ፍትህ፣ ሰው የመሆን ጉዳይ ነው። ‹‹ኤሰ ጅራ› የተሰኘ ነጠላ ዜማ እየሠራ የነበረው ሀጫሉ፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው። ወላጅ አባቱ የቀብር ስነስርዓቱ ሊፈጸም በአምቦ ስታድየም በተከናወነ የሽኝት ሥነ ስርዓት ላይ አሉ፣ ‹የልጄ ደም በከንቱ ፈስሶ እንዳይቀር ወደ ፈጣሪ ለምኑልኝ!› በሞቱ እናተርፋለን ያሉ ሁሉ እንዳይሆንላቸው ከሕግና ፍትህ ሁሉም እውነቱን ይጠበቃል።

አዲስ ማለዳ ለድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቡ፣ አድናቂና ወዳጆቹ ሁሉ መጽናናትን እንዲሁም ለነፍሱ ዘለዓለማዊ እረፍትን ትመኛለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com