ሦስቱ ሠኔዎች፤ የከሸፉት የኹከት መንገዶች

Views: 77

ኢትዮጵያ የለውጥ ንፋስ ከነፈሰበት ጊዜ ጀምሮ በርከት ያሉ እና ከዚ ቀደም ታይደተው በማይታወቅ ሁኔታ አገር ውስጥ የተከወኑ ድርጊቶች ቀላል አይደሉም። ከአገር ውስጥ መፈናቀል እስከ ተቅላይ ሚንስትር ግድያ ሙከራ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት የኹለት ዓመት ተኩል እድሜ ባለው የለውጥ ኃይል የአስተዳደር ዘመን የተከወኑ አስደንጋጭ ኹነቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
የክልል መንግስታትን በአገሪቱ የጦር ከፍተኛ መኮንኖች ደርቦ መግደልም የሰሚን ጆሮ ጭው ካደረጉ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን በመፍጠርም ምንም ይሁን ምን ተራ ሽብርተኝነት ጉዳይ ሳይሆን አገርን ወደ ማተራመስ እና ወደ ለየለት የብጥብጥ ቀጠና ለመክተት ያልተወጣ ጋራ እና ይልተወረደ ቁልቁለት እንደሌለ በርካቶች የሚስማሙበት እና በገሀድ ወጣ እውነት ነው።
በአገር ውስጥ ከተከናወኑት ከፍተኛ የአደጋ ጣይ ጥቃቶችም ደግሞ እንደ አጋጣሚም ይሁን ታስቦበት ብቻ በሰኔ ወር መከሰታቸው ደግሞ ግርምትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው። እነዚህን እና መሰል ያልተሳኩ ግን ደግሞ ተቃጥተው የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈው በአጭር የተቀጩትን የኹከት መንገዶችን በተመለከተ የአዲስ ማለዳ ኤርሚያስ ሙሉጌታ የደኅንነት ባለሙያዎችን፣ የሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ ተመራማሪዎችን እና ፖለቲካ ተንታኞችን በማነጋገር የዚህ ሳምንት የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በቀደሙት ዓመታት በተለይም ከሦስት ኣመታት በፊት ሠኔ ሲባል ለኹሉም ኢትዮጵያዊ ከአስረኛ ወርነቱ ባለፈ ለመንግስት ሠራተኛው የበጀት መዝጊያ፣ ለነጋዴው የግብር መክፈያው፣ ለተማሪው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ የደከመበትን እና የለፋበትን ውጤት የሚያይበት እና ከአንድ ክፍል ወደ ሌላኛው ከፍል ያጠናው በማዕረግ የሚተላለፍበት ዓመቱን ሙሉ ያሾፈው ደግሞ ባለበት የሚደግምበት ወርሃ ሠኔ የኹሉም መለያ ወር።

ታዲያ ይህ ለኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ስፍራ ያለው ወር ለአርሶ አደሩም ሰማዩን በተስፋ እየተመለከተ ከበሬው ጋር እያወጋ እርሻውን የሚከውንበት ወርም ነው። ይሁን እንጂ ይህ ብዙዎችን የሕይወት ኡደት ቀያሪው ወር ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በኢትዮጵያ ከባባድ ኹነቶችን በማስተናገድ የ13ቱን ወራት ቁንጮነት የያዘ እና ሠኔ ሲባል የቦምብ ጥቃት፣ ሰኔ ሲባል የጀነራሎች እና ክልል መንግስታት ሙት ዓመት፣ ለሦስተኛ ጊዜ ሰኔ ሲባል ደግሞ የዝነኛው ኦሮምኛ ሙዚቀኛው ሐጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈት የተሰማበትም ሆኖ ተመዝግቧል።

በእነዚህ ሰኔዎች ዕጅግ ከበዱ የኹከት መንገድ የሚመስሉ ግን ፍጻሜያቸው የከሸፉ ኹነቶች በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር ተፈጽመዋል። እውነት እንደታሰበው ቢሆን እና የተቃጡት ሙከራዎች ግባቸውን መተው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ መልኳ ይህ ይሆን እንዳልነበር ብዙዎች ይስማሙበታል።

ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን ሰጡ እና ለበርካታ ኣመታ በደኅንነት መስሪያ ቤት ያገለገሉ እና አሁንም በኃላፊነት ስፍራ ላይ የሚገኙ ግለሰብ እንደሚሉት፤ ‹‹በተደጋጋሚ ሙከራዎች ይካሔዳሉ ግን አሁንም የኢትዮጵያን ጉዞ ከግስጋሴ ሊገቱ ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም ደግሞ እንዲህ በሦስቱ ሰኔዎች ከተከሰቱት እና ገነው በወጡ ወደ ሕዝብም በደረሱ ሙከራዎች በላቀ ውስጥ ለውስጥ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ኢትዮጵያን ወደ ኹከት የሚመሩ እና አገረ መንግስትን አናግተው ሰላማዊ የመንግስት ሒደትን የሚነቀንቁ ይሆኑ ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚንስትሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተወረወረው የቦንብ ጥቃት እና የአንድን ሰው ክቡር ሕይወት ከቀጠፈው እስከ የዓይን ማረፊያ እና ሕዝብና አገርን ቀን ከሌት የሚያገለግሉ ታላላቅ የስራ ኃላፊዎችን የቀተፈው ኹከቶች ጅምር መንገድ ታዲያ በአንድም በሌላም በኩል ያሰቡትን ዓላማ ሳይመቱ መክነው ቀርተዋል ሕዝብም ለዚህ ምስክር ነው።

ደኅንነት ባለሙያው ሲናገሩ ለሙከራዎች ከሽፈው መቅረት በየደረጃው ያለው የደኅንነት እና የጸጥታ መዋቅር ቀን ከሌት በመስራት እና የተዘረጋውን ክፋት መረብም እየበጣጠሰ እንደሚገኝ እና ይህም ለሙከራዎች መክሸፍ አይነተኛ አስተዋጽኦ መሆኑን ለማወቅ ይቻላል። ‹‹በየጊዜው በአገር ደረጃ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ከመስመር ለማውጣት እና ኢትዮጵያንም ወደ አልታሰበበት መንገድ ለመምራት የተሞከሩት ሙከራዎች ለቁጥር የሚያዳግቱ መሆናቸውን መናገር እችላለሁ›› ይላሉ።

በሦስት ተከታታይ ሰኔዎች የተሞከሩት ሙከራዎች ታዲያ እንዴት ይታያሉ ግባቸው አንድ የመሆኑን ያህል ይዘታቸው እና አካሔዳቸው ግን ከዚህ በተለየ መሆኑ ቅርጹን እየቀያየረ ወደ አንድ ግብ ለሚሄደው የኹከት መንገድ ዋነኛው መገለጫ ለመሆኑም አስተያየት ሰጪው ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። ‹‹ከአንድ ወገን ብቻየሚሰነዘር ጥቃት አይደለም። ከኹሉም ብሔር ብሔረሰቦች ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ እና ሕገ ወጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች የመኖራቸውን ያሕል ሕገ ወጥ ተግባሩም በዚሁ ደረጃ በኹሉም አካባቢ በስፋት የሚፈጸም ጉዳይ ሆኗል››። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአገር ውስጥ መፈናቀል ማጋጠሙን የሚጠቅሱት ደኅንነት ባለሙያው፤ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር እና ወደ የትኛውም አቅጣጫ ቢጓዙ የእርስ በርስ ትስስርን ለማየት በማያዳግተውን አገር፣ ሰዎች ወልደው ከብደው በኖሩበት ቀየ፣ አንዱ ከአንዱ ጋር በጋብቻም ሆነ በጉርብትና ተሳስሮ በኖረባት ኢትዮጵያ የመፈናቀል እና ሐብት ንብረትን መዘረፍ ከሕዝቡ የሚመጣ እንዳልሆነ እና ሰው በሰው ላይ እንዲነሳ አድራጊዎች መኖራቸውንም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደኅንነት ባለሙያ ይናገራሉ።

ሰኔ 23/2012
ከጥቂት ዓመታት በፊት የለውጡ አመራር ወደ ስልጣን ለመምጣት በቀረበበት ዋዜማ ላይ ነበር ከሀጫሉ ሁንዴሳ ጋር በአካል የተገናኘነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ወደቀችበት፤ ኦሮሚያ እና ከመሐል ከተማ ራቅ ያሉ የአዲስ አበባ ክፍሎችም የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋረጠበት እና ኹሉም ነገር የተወጠረበት የጭንቅ ጊዜ ነበር።
እኔም በአንድ የቅርብ ሰው የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ለመታደም ወደ ኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ከተማዋ ጊንጪ አቅንቼ ነበር ፤ በዚህም ወቅት ነበር ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ጋር በአካል ለመገናኘት የቻልኩት። በታደምኩበት የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ታዳሚውን እና ሰርገኞችን ለማዝናናት ወደ መድረክ በወጣበት እና ገና ጉሮሮውን በሚሞርድበት ወቅት ግን ሰርግ ቤቱ በሀጫሉ አድናቂዎች እና ወዳጆች ተደበላለቀ።

የዛን ቀን አንድ ነገር ታዘብኩ፤ ሀጫሉ በኦሮሞ ወጣት እና በኢትዮጵያዊያን ሙዚቃ ወዳዶች ልብ ዘንድ ላይፋቅ መታተሙን። ሙዚቃ የአለም ቋንቋነቱንም ምንም እንኳን የሚናገረውን ቋንቋ በውል ባይገባቸውም ቅሉ አብረውት ሲያቀነቅኑ የታዘብኳቸውን ሰዎችም አይቼ አረጋግጫለሁ።

የሰርግ ቤቱን ታዳሚ በወኔ ሲወዘውዝ ነበረው ድምጸ መረዋው ሀጫሉ ወጣትነትን በችሎታ አጅቦ ከቆራጥነት እና ልበ ሙሉነት ጋር በአደባባይ ኪነ ጥበብን ለነጻነት በአግባቡ የተጠቀመ ምጡቅ ባለሙያ ለመሆኑም በቅርበት ለማየት ከቻልኩት አንዱ ነው። ይህ በአካል ያገኘሁበት አጋጣሚ ሀጫሉን ከኹለት ዜማዎች ባለፈ መስማት አላስቻለኝም ነበር። ነገር ግን በስራ ምክንያት በተዘዋወርኩባቸው ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች የሀጫሉን ዜማ ያልሰማሁበት ከተማ፤ ያልጨፈርኩበት የምሽት ክበብ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ። የሀጫሉ ጥዑመ ለዛ ያላቸው ሙዚቃዎች በኢትዮጵያ ጋራ እና ሸንተረሩን እየተጋጩ ከአድማስ አድማስ ሲያስተጋቡ ውለው ሲያስተጋቡ ያድራሉ። ሀጫሉ ተወዳጅ ነው፣ ሀጫሉ ተመራጭ የኦሮምኛን ሙዚቃ እና አሳድጎ የኦሮሞን ወጣትንም ለማንቃት እና ለነጻነቱ እንዲቆምም አይነተኛ አስተዋጽዖ የተጫወተ የኦሮሞ ፈርጥ፤ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።

ሩቅ ለማደር አስቦ ሲሰራ የኖረው እና ቅርብ ያደረው ሀጫሉ በዚች ምድር ላይ በኖረባቸው ጥቂት ዓመታት የማያልፍ ስራዎችን በሕዝብ ዘንድ ቀርጾ ያለፈ ድንቅ ጥበብ ሰው ነበር። በጀግንነት እና በወኔ የተቃኙት የሀጫሉ ሙዚቃዎች ዛሬም ሆነ ነገ ከሀጫሉ እልፈት በኋላም እተደመጡ ተተኪውን ትውልድ ሲያንጹ እና ሙዚቃን እንዴት ለተገቢው ዓላማ ማዋል እና ሀሳብን ማስተላለፍ እንደሚቻል ብሎም ለውጥን ማምጫ መንገድም እንደሆነ ማሳያ መሆኑን ይማሩበታል።

ሰኔ 23/2012 ለልበ ሙሉው እና ለከያኒው ሀጫሉ እንደማንኛውም ቀን የስራ እና ባተሌነት ቀን ነበር። ነገር ግን ጠዋት በቀኝ አውለኝ ላለው ሀጫሉ ማታ መሽቶ ግን በተደጋጋሚ እንደሚገልጸው በትልቅ ናፍቆት ለሚጠብቁት ልጆቹ ግን ሊበቃ ሳይችል ከመንገድ ቀርቷል። የፌደራል ፖሊስ ስለ ድምጻዊው አሟሟት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ገላን ኮንዶሚኒየም በተባለ ስፍራ ሀጫሉ የሚያሽከረክራትን ተሸከርካሪ አቁሞ ወርዶ ተመልሶ ወደ ተሸከርካሪዋ በገባበት ወቅት ገዳይ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የተሽከርካሪውን በር በመክፈት በጥይት እንደመቱት አስታውቋል። ህይወቱን ለማትረፍም በተደረገው ርብርብ ወደ ጥረነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስዶ የነበረ ቢሆንም መጥፎ አጋጣሚ ሀጫሉን ከሚወደው ሙዚቃ፣ ከአድናቂዎቹ እና ከሚወዳት ኢትዮጵያ ነጥቃዋለች።

ይህ የእኔን አንድ አጋጣሚ ለመግቢያነት ተጠቀምኩ እንጂ ሀጫሉ አዲስ ማለዳ ያጋገረቻቸው እና ሀጫሉን ከልጅነት እስከ እውቀት አብረውት የኖሩ ደግሞ ተናግረው የሚያቆሙ አይመስሉም። ስለ ጀግንነቱ፣ ስለ ቆራጥነቱ፣ ልበ ሙሉነትን ስለተላበሰው ስብዕናው እና መሰል ጉዳዮች ሀጫሉን አንስተው አይጠግቡም።

የሙዚቃ አቀናባሪው እና በርካታ ስራዎችን ከሀጫሉ ጋር ሰርቻለሁ የሚለው የአዲስ ማለዳ አስተያየት ሰጪ ጂቅሳ በላይ ነው። ‹‹ከሀጫሉ ጋር በተደጋጋሚ በስራ አማካኝነት የመገናኘት ዕድል ገጥሞኝ ያውቃል። ስብዕናው እና ሰው አክባሪነቱ ልዩ ሰው ነው። ሀጫሉ ጭምት የመሆኑን ያህል ትዕግስቱ ገደቡን አልፎ አይቸውም አውቃለሁ እጅግ ቁጡ እና ሌላ መልክ የሚይዝ አይነት ፍጡር ነው›› ሲል ስለ ሀጫሉ የሚያስታውሰውን ለአዲስ ማለዳ ይናገራል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳም በሀጫሉ ሑንዴሳ ድንገተኛ ሞት ከገቡበት ድንጋጠየ እና ብስጭት በወጉ ሳይወጡ ነበር ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫቸውን ያስተላለፉት። ‹‹በፊንፊኔ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጀግናው ወንድማችን፣ ደማችን፣ የትግል የለውጥ ምልክት የሆነው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በመሳሪያ መመታቱን ሰማሁ›› ሲሉ ጀምረው ‹‹በሀጫሉ ሕልፈተ ሕይወት እንደ አንድ አብሮ አደግ እንደ ትግል ጓድ እና እንደ ጀግና የተሰማኝ ሀዘን ከፍተኛ ነው፤ ለእኔ ደግሞ ወንድሜ አማካሪዬ ነው፤ ይህን ጀግና ነው ያጣነው›› ሲሉም ሀዘናቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም ርዕሰ መስተዳደሩ በሀጫሉ ላይ የተፈጸመው ግድያ ታስቦበት ተፈጸመ ግድያ እንደሆነ እና እንደ ተራ ነገር የሚታለፍ እንዳልሆነም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚሁ በተመሳሳይም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርብ የሚያውቁት እና የትግል አጋራቸው የሆነውን ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው እንደሰሙት ተናግረዋል። የሀጫሉን ታጋይነትንም በተመለከተ ‹‹የእኛ መታወቂያ አይኑረው እንጂ ወይም ዩኒፎርም አይልበስ እንጂ እንደኛው ታጋይ ነበር›› ሲሉም ተናግረዋል። በሦስቱ ሰኔዎች የተካሔዱትን አገራዊ አስደንጋጭ ክስተቶችን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ በቀዳሚ ኹለት ሰኔዎች የተደረጉትን ግድያዎች እና በሦስተኛው ሰኔ ማለትም በሀጫሉ ግድያ ዙሪያ ‹‹ምንም ጉዳዩ የማይመለከተውን ›› ሲሉም ጠቅሰዋል።

ሰኔ 15/2011
ከኹለት ሳምንታ በፊት አንደኛ የሙት ዓመታቸው የተከበረው የኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ባልንጀራቸው ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ከአዲስ አበባ እንዲሁም በተመሳሳይ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ተጨማሪ ኹለት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም በተመሳሳይ ግድያ ተፈጽሞባቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጆሮ ጭው ያደረገ ክስተት የተፈጸመበት ጊዜ ነበር።

‹‹የተሔደበት መንገድ ከባድ እና ኢትዮጵያን እንደ አገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚከት ነበር። ነገር ግን ከመንግስት የተወሰዱት አፋጣኝ እርምጃዎች የታሰቡት ውዥንብሮች እና አለመረጋጋቶች ግባቸውን ሳይመቱ ቀርተዋል፤ አገርም ቀጥላለች›› ሲሉ የደኅንነት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

በወቅቱ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው አጋጣሚ ተራው ሕዝብ ‹‹እነዚህን የመሰለ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከተገደሉ የእኛስ የእለት ተዕለት ጥበቃ ከመንግስት ወገን የሚሰጠን ምን ያህል ጠንካራ ነው?›› የሚል ጥያቄዎችንም ያነሱበት አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል። ከተከሰተው አስቸጋሪ ኹነት በኋላ የተለያዩ አካባቢዎች ነባር ሁነታቸውን ለመቀጠል የተቸገሩበትንም አጋጣሚ አዲስ ማለዳ መታዘብ ችላለች።

በተለይም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መዲና ባህር ዳር ከተማ ክልሉ አመራሮቹን ካጣበት ክስተት በኋላ የቀደመው የዕለት ተዕለት ክንውኖች ላይ በጉልህ የሚታዩ ለውጦችን ማየት ይቻላል። በተለይም ደግሞ ባህር ዳርን ከዓመታት በፊት ለሚያውቋት እና ግርማ ሞገሷን ከሰርክ በተሌነቷ ጋር ሳይነጣጥሉ ለሚታዘቡ ባህር ዳር መቀየሯን በሚገባ ለመታዘብ አይቸገርም።
አዲስ ማለዳ ከተፈጠረው አስደንጋጭ ኹነት በኋላ በባህር ዳር እና የአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውራ ለመታዘብ እንደሞከረችው በከተሞች ዋና ዋና መንገዶች ላይ ሙሉ በሙሉ በሆነ የወታደራዊ ትጥቅ የተንቆጠቆጡ የክልሉ ልዩ ኃይሎችን ሲንጎራደዱ እና የትኛውንም አይነት እንቅስቃሴ በሙሉ ወታደራዊ ንቃት ሲታዘቡ ፤ አንዳንዴም አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲያዩ በፍጥነት ወደ ስፍራው በመቅረብ ፖሊሳዊ እርምጃን ሲወስዱ መታዘብ ችላለች። ይህ አይነት እርምጃ በባህር ዳር እና ሌሎች የክልሉ ከተሞች ላይ ለመታዘብ ባለፉት ኣመታት ወይም አንድ ትልቅ ባለስልጣን መጎብኘት ይኖርበታል ወይም ደግሞ በክልሉ የሚካሔድ ትልቅ ክብረ በዓል ሊካሔድ ግድ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታዲያ አሁንም ድረስ ማገገም ያልቻሉት የከተማዋ ፈርጥ ሆኑት የምሽት ክበቦች ናቸው። በባህር ዳር ከተማ ቢፈልጉ ዘመናዊ ቢያሻዎች ደግሞ ለዛ ያላቸው ባህላዊ ጭፈራዎችን እያማረጡ ትክሻዎን ሲሰብቁ ማደር ልማድ ነበር።

ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በባህር ዳር በተገኘችበት ወቅት ከተማዋ በተለይም ነዋሪው ከድንጋጤው ተላቀቀ በማይመስል ሁኔታ በጊዜ ቤቱ መከተት ልማዱ ሆኖ የምሽት ሕይወቱም ቀዳሚ ግርማ ሞገሱን ተገፎ ጨምት ሆኖ ነበር። አንድ ዓመት የሙት ዓመታቸው የተከበረው የመንግስት የስራ ኃለፊዎችን የፍርድ ሒደትም ተከትሎ በርካታ ቅሬታዎች ሲሰማባቸው መቆየቱም የሚታወስ ነው።
በተለይም ደግሞየጀነራል ሰዓረ መኮንን ባለቤት ኮሎኔል ጽጌ ወደ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ብቅ ብለው የባለቤታቸው ገዳይ ነው በሚል ጥርጣሬ ተይዞ በፍርድ ሒደት ላይ የሚገኘውን ጉዳይ እንዳይከታተሉ መደረጋቸውን እና የፍርድ ሂደቱም መንጓተቱን ፤ አጥፊዎችም ተገቢውን ቅጣት አለመቀበላቸውን ጨምረው ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይህን መተከትሎ መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኮሎኔል ጽጌ የባለቤታቸውን ገዳይ የፍርድ ሒደት በቅርብ ሆነው መከታተል እንዲችሉ የተፈቀደላቸው መሆኑንም አስታውቋል። ይሁን እንጂ እንደ ኮሎኔል ጽጌ ገለጻ ይህ ከመንግስት በኩል የሚታየው ለዘብተኝነት ነገ ወደ ባሰ ደረጃ እንደሚያደርስ መጠቆማቸውም ይታወሳል።

ሰኔ 16/2010
ለዓመታ ፍትህ የተጠሙ እና ለውጥን በናፈቁ ወጣቶች እምቢተኝነት ወደ ፊት የመጣው እና ‹‹ቲም ለማ›› በሚል የዳቦ ስም በዋናነት ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልል በተወጣጡ ከፍተኛ የስራ አመራሮች የተጣመረው የኦሮማራ ወደ ስልጣን የመጣበት ኹለተኛ የልደት ዓመቱን ሻማ የለኮሰው ያለፈው መጋቢት ነበር።

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አቀንቅኗል፣ እስረኞችን ፈቷል፣ የናፈቅነው ለውጥ አምጥቷል እና መሰል መልካም ነገሮችን ለኢትዮጵያ በማምጣት መጻኢ አገራዊ ራዕይንም ብሩህ አድርገን እንድንመለከት የተስፋ አድማሳችንን የሰነጠቀልን ብልህ መሪያችን ነው ባሉ ግለሰቦች አነሳሽት ነበር ሰኔ 16/2010 ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ የተዘጋጀው።
ለአራት ኪሎው ቤተ መንግስት አዲስ የነበሩት ዐብይ አሕመድም በመስቀል አደባባይ ለተገኘው ደጋፊያቸው እና ‹‹ከጎንህ ነን›› ላለው ሕዝብ ንግግር ለማድረግ በተገኙበት ወቅት ታላቅ ፍንዳታ ተሰማ።በመጀመሪያ ደረጃ የድምጽ ማጉያ የቴክኒክ ስህተት እንጂ ቦምብ እንደሆነ መለየት ያስቸግር እንደነበርም በስፍራው የነበሩ ሰዎች ያወሳሉ።

የሆነው ሆኖ የአንድ ሰውን ሕይወት በመቅጠፍ እና ለበርካቶች ቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት የዳረገው ክስተትም በዐብይ አሕመድ የጠቅላይ ሚንስትርነት ዘመን የመጀመሪያው አስደንጋጭ ክስተት እንደሆነም ይነገርለታል። ከክስተቱም ተከትሎ በርካታ የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች ፣ የፌደራል ፖሊስ የፖሊስ አባላት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ስራ ኃላፊነት ያላቸው ግለሰቦች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበርም ይታወሳል። በኹነቱ በርካቶች ከአቅም በላይ በሆነ ቁጣ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሲሞክሩም ተስተውለዋል ምንም እንኳን ጉዳዩ በአጭር ሰዓት በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን ቢታወቅም።

በተፈጠረው ክስተት አሁንም መንግስት ከተጠርጣሪዎች መካከል በቁጥጥር ስር ያውላቸው እንጂ ምንም አይነት የፍርድ ውሳኔ እንዳልሰጠም ለማወቅ ተችሏል። ይህም ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የልብ መዛል እና መድከም እንዲሁም በፍርድ ሒደቱ ላይ ይህ ነው የማይባል አመኔታን እንዲያጣም የሚያደርግ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ሐምሌ 19/2010
ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር ያነባችበት ቀን። ለሰራው ስራ እና ላሳረፈው አሻራ ስራው ተጠናቆ መቼ ይሆን በይፋ እናመሰግናለን የምንለው የተባለው የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ዋና መሐንዲስ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በግል ተሸከርካሪው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው እጅግ ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነበር። ራሳቸውን ገድለው ለመገኘታቸው የፖሊስ ሪፖርት አስታውቆ በርካቶች ግን እምብዛም ሳይዋጥላቸው ቀርቶ አልፏል።

በሐሩር እና ከቁር ጋር እየታገለ የአገርን እና የወገንን ኃላፊነት ለመወጣት ከልጆቹ ተለይቶ በጉባ በርሃ ውሎ እና አዳሩን ላደረገው መሐንዲስ ከአገሩ የተከፈለው ግን በፍትሕ አልባ የተደመደመ ሞት ነበር። ቤተሰቡን ለብቸኝነት ራሱን ለሐሩር በሰጠበት የስራ ሳይሆን የኃላፊነት ሞራል ዓላማውን ከግብ ሳያደርስ ከመንገድ ቀርቷል። ስመኘው በቀለ በአንድ ዝናባማ ማለዳ አሻግሮ ያያትን ኢትዮጵያን፤ ዜጎች ከመብራት እና ከኃይል ዕጥረት ጋር የስቃይ ሕይወት ሲገፉ እያየ ያደገው መሐንዲስ በትጋት የሚገነባው ግድብ ተጠናቆ እናቶች ሲስቁ፣ ሴቶች ሲፈነድቁ ለመታዘብ ሳይችል አሻግሮ እንዳያት ዘላለማዊውን እንቅልፍ አንቀላፍቷል።

በሜዳ ላይ ስለቀረው መሐንዲስ አሁንም የሚያነሳ እና ከመንግስት ወገን ፍትህን እና መፍትሔን እንዲያገኝ የወተወቱ በርካቶች ነበሩ የሆነው ሆኖ አሁንም ድረስ ‹‹ራሳቸውን አጥፍተዋል›› ከሚለው የፖሊስ ሪፖርት በቀር የቀጠለ ግኝት አለመኖሩን የሚታወስ ነው።

በእነዚህ ክስተቶች ምን ይነግሩናል ?
በሦስት ተከታታይ ሰኔዎች በተፈጸሙት እና አገርን እና ሕዝብ ድንጋጤ ውስጥ የከተቱ ክስተቶች በተፈጸሙ ጊዜ እና መንግስትም ሕግን ለማስከበር በሚል በቁጥጥር ስር ቢውሎም የፍርድ ሒደታቸው ተጠናቆ አጥፊዎችም ላይ ቅጣት አለመጣሉ እና ለሕዝብም ይፋ አለመደረጉ በቀጣይ ለተከሰቱት ሕገ ወጥ ክስተቶች እንደ ማበረታቻ እንደተቆጠረም በሪፖርተር ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት እና ፖለቲካ ተንታኙ ነአመን አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ።

መንግስት እየወሰደው የነበረው እርምጃ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጠንካራ እርምጃ ወስዶ ቢሆን ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ ላንደርስ እንችል ነበር ሲሉ ነአመን ይናገራሉ። ከሀጫሉ ግድያ በፊት የነበሩ ከፍተኛ ባለ ስልጣናት ግድያዎች እና በጠቅላይ ሚንስትሩም ላይ የተሞከረው ግድያ መሰረት ተደርጎ የተወሰደው ምርመራ እና ውጤቱ በአስቸኳይ ለሕዝብ ቢያስታውቁ እና ይፋ ቢደረግ እዚህ ደረጃ ላይ አይደረስም ነበር ሲሉ ያስረግጣሉ።

እስካሁን የተቃጡት እና የተፈጠሩት ክስተቶች ቢሳኩ ምን ይፈጠር ነበር በሚል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ነአመን ሲመልሱ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ፍለጎታቸው ምንድነው ወይም ዓላማቸው ምንድነው የሚል ጉዳይ መነሳት እንዳለበት መለየት ይገባዋል›› ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም የተፈጠሩት ከባባድ ችግር በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ለየለት የዕርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያን ይከታል የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ነገር ግን አገርን ወደ አልመረጋጋት ግን እንደሚከታት እርግጠኛ መሆን እንደሚችሉ ግን አልደበቁም።

አያይዘውም ነአመን በአሁኑ ሰዓት መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚመከር እና ትክክለኛውን የሕግ አግባብ በመከተል የከፋ ችግር በአገር ላይ እንዳይከሰት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል። በአሁኑ ሰዓት አይነኬ ሲባል የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ይበል የሚያሰኝ ተግባራትን እየተገበረ እንደሆነ እና በቀጣይም ሕግን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ የሆኑ ስራዎች ይሰራሉ ተብለው እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com