ተወርዋሪ ኮከብ -ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ

Views: 330

ተወርዋሪ ኮከብ ይሏቸዋል፣ ድንገት ታይተው፣ አብርተውና አድምቀው፣ ደምቀውም በቅጽብት ጥፍት የሚሉትን። ብዙ የሚጠበቅባቸውና ብዙ እንደሚሰጡ ተስፋ የታየባቸው፣ የሚያሳሱ፣ ተፈጥሮንና ፈጣሪን የምናመሰግንባቸው፣ ሙያንና ሙያተኛን የምናከብርባቸው በብዙ መልኩ ሊገለጹ የሚችሉ ሰዎች እንደ ተወርዋሪ ኮከብ በፊታችን ብልጭ ብለው ከፊታችን ተሰውረዋል።

ካሳሁን አሰፋ በጋዜጠኝነቱ በይበልጥ ይታወቃል። የሥራ ባልደረቦቹ ጓደኝነትና ተጫዋችነቱን፣ ለሥራው ያለውን ፍቅርና መሰጠቱን፣ የቅርብ ቤተሰቡም ሰው ወዳጅና አክባሪ እንደሆነ እየጠቀሱ ሥሙን ያነሱታል። እየቀረቡት በሄዱ ቁጥር ሁሉም ይህን ጋዜጠኛ የሚገልጹበት የየራሳቸው መንገድ አላቸው። ለብዙኀኑ ካሳሁን ጋዜጠኛ፣ በብስራት ኤፍ ኤም ራድዮን የአሻም መሰናዶ አዘጋጅ እንዲሁም ከኢካሽ ፕሮሞሽን መሥራቾች መካከል ነው።

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት ጋዜጠኛ ብርሃን ፈይሳ ስለ ካሳሁን መለስ ብላ የልጅነት ጊዜዋን ታስታውሳለች። ይልቁንም በመደበኛ ትምህርት ቆይታዋ ካሳሁን ያስተምርበት በነበረበት ወይራ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በሚገኘው የማነብርሃን የመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውን የመምህርነቱን ነገር አንስታለች። ካሳሁን በትምህርት ቤቱ የአማርኛ መምህር ሆኖ ለዓመታት አገልግሏል።

‹‹ጊቢው ውስጥ ካሉ መምህራን ተወዳጅና ቀልደኛ፣ በዛው ልክ ቁምነገረኛ ነበር። ብዙ ጊዜ አማርኛ ትምህርት እንደ ቀልድ የሚታይ ነበር። እርሱ ግን እንደ ሒሳብ ትምህርት ነው በትኩረት ያስተምር የነበረው። ትምህርቱ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የሚደፍን ሰው አይገኝም ነበር።›› ስትል ታወሳለች። ‹‹ፈተና ፈትኖን ውጤት ሲሰጥ ሥማችንን ይጠራና ውጤታችንን ሁሉም ተማሪ እንዲሰማ አድርጎ በይፋ ይናገር ነበር። ከሌሎች መምህራን ይልቅ ከእርሱ ጋር ቅርበት ነበረን።›› ስትል አክላለች።

ከትምህርት ቤቱ ሥያሜ ውስጥ ብርሃን የሚለውን ቃል ነጥሎ ወስዶ ሚኒ-ሚድያ ያስጀመረው ካሳሁን ነበር። መምህርም ሆኖ በትምህርት ቤቱ የጋዜጠኝነትን ሙያ ለተማሪዎቹ አሳይቷል ማለት ነው። ተማሪዎችም ወደ ሚኒሚድያ እንዲገቡ በማድረግና በማስተማር ብዙዎችን ያሳትፍ እንደነበር ብርሃን ጠቅሳለች።

ታድያ ሚኒሚድያው ላይ ለልጆችና ለአዳጊዎች እንደሚሠራ ሰው፣ ነገሮችን ቸል ብሎና አቅልሎ የሚሠራ አልነበረም። ለዚህም ማሳያ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ ትላለች፣ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የሆኑ ኹለት ተማሪዎች ወንዝ ሊዋኙ ሄደው፣ አንዱ ሰምጦ ይሞታል።

በማግስቱ ታድያ ስለልጆቹ በሚኒሚድያ የቀረበው የማስታወሻ መሰናዶ፣ የትምህርት ቤቱን አባል ሁሉ እንባ ያራጨ ነበር። ‹‹በጣም አስለቅሶናል። ራድዩ ጣቢያ እንጂ የትምህርት ቤት ሚኒሚድያ የምንሰማ አይመስልም ነበር።›› ስትል ከሕሊናዋ ያልጠፋውን ኹነት ታነሳለች።

ካሳሁን ከተማሪዎቹ ጋር ያለውን ግንኙት ለማስረዳት ቃላት ያጠራት ብርሃን፣ ደጋግማ ይህንን ነጥብ አንስታለች። በተለይም ተማሪዎቹን ሁሉ ለይቶ እንደሚያውቅ አስታውሳ፣ ትምህርት አጠናቅቃ በሥራ ገበታ ላይ ሳለች በማኅበራዊ ሚድያ ፌስቡክ የቀደመ መምህሯን ‹እንዴት አለህ?› ስትለው ከበርካታ ዓመታት በኋላም ቢሆን እንዳልረሳትና እንዳስታወሳት ጭምር በአድናቆት አውስታለች።
ካሳሁን ወጎችና መጣጥፎችን ጽፎ ለተማሪዎቹ ያቀርባል። ታድያ የማይነጥላቸውን መልእክቱን የሚያስተላልፍባቸው አንድ ገጸ ባህሪ ነበሩት፣ እትዬ አስካለ ይባላሉ።

በሥነ ጽሑፉም ሁለገብ ሥራን ይሠራ የነበረውና በጊዜው መምህር ካሳሁን፣ ወግና ልብወለድ አልያም መጣጥፍ ሲያቀርብ ሁሉም ጸጥ ረጭ ይላል። ጆጎ ገብ ድምጹን፣ ሳቢ አተራረኩንና ተማሪዎች አዲስ ነገር የማያጡበትን ጽሑፉን ሁሉም በጉጉት ይሰማል።

‹‹ካሳሁን ኳስ ይጫወታል። የአርሰናል ደጋፊም ነበር። ትምህርት ቤታችን ውስጥ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ግጥሚያ ሲያደርጉ እርሱም ይጫወት ነበር። ደግሞም አሪፍ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል ነበር›› ብርሃን እንዳለችው ነው። ታድያ የአማርኛ መምህሩ ካሳሁን የጋዜጠኝነት ሙያንም በልቡ አስቀምጦ ኑሮ፣ የፋና ኤፍ ኤም ሬድዮ ሥራ ሲጀምር የመምህርነት ሙያውን ገታ አድርጎ ጋዜጠኝነቱን ጀመረ።

እንደዛም ሆኖ ከትምህርት ቤቱ ቢለይም በየጊዜው እየሄደ ይጠይቃቸውና ተማሪዎቹን ያገኛቸው ነበር። በኋላም ብርሃን በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጋዜጠኝነት እየሠራች መሆኑን ስትነግረው፣ ሐሳብ ያካፍላት እንዴት መሥራትም እንዳለባት ይመክራት እንደነበር ታወሳለች። ተማሪዎቹ ወደ ሙያው እንዲቀርቡም በተቻለው ያግዛቸው ነበር።

የመጀመሪያ ዲግሪውን በአርክቴክቸር እና የከተማ ፕላኒንግ ያጠናቀቀው ልዑልሰገድ ገብረሚካኤል፣ እንደ ብርሃን ሁሉ የካሳሁን ተማሪ ነበር። በበኩሉ በሚኒሚድያው የነበረውን ተሳትፎ አስታውሶ፣ ካሳሁን ያኔ እንኳ ይሠራው የነበረውን ሥራ ምን ያህል ከልቡ እንደሚሠራና እንደሚወድ ያወሳል።

‹‹አጥፍተን ከሆነ መግረፍም ካለበት ይጋረፋል። ግን መትቶሽም የምትወጂው ዓይነት መምህር ነበር። አማርኛ አስተማሪ ይሁን እንጂ፣ አማርኛን ከማስተማርም ከፍ ያለ/የሚልቅ ሰው ነበር።›› ሲል ካሳሁንን ይገልጸዋል። ታድያ እንደ ልዑል ገለጻ ካሳሁንን ሲያነሳ ሁሌም የሚገርመው ስለአገር ያለውን ስሜት ነው። ‹‹መረጃ ለማቅረብ ብቻ አይደለም ካሳሁን የሚሠራው›› ይላል። ይልቁንም ከልቡ በመነጨ ስሜት፣ ተረድቶትና የራሱ ጉዳይ አድርጎት ነው።

ብዙዎች በብስራት ኤፍኤም አሻም የራድዩ ፕሮግራምን የሚከታተሉ፣ በተለያየ አጋጣሚ ካሳሁንን የሚያውቁ ይህን ይመሰክሩለታል። በምልዐት የተሰጠውና ሳይሰስት የሰጠ እንደሆነም ያነሳሉ። ተጫዋችና ተግባቢነቱ ከልባቸው ያልጠፋም፣ ከዚህ በኋላ በአካል የማይገኝ መሆኑና ወደማይቀርበት ዓለም የመሄዱን ነገር ለማመን ተቸግረዋል።

አብርሐም ፀሐዬ የካሳሁን የቅርብ ጓደኛና የሥራም ባልደረባ ነው። ኢካሽ የጋዜጠኝነት ሥልጠና ሥራ ከአንድ ዓመት በፊት ሲጀምርና በጋራ እንዲሠሩ ሲወስኑ፣ የካሳሁንን የሥራ ፍቅር በጉልህ እንደተመለከተና በይበልጥ ደግሞ አብሮ ለመሥራት የተመቸ ሰው እንደሆነ ያነሳል። ማሠልጠኛውንም ከሚሰጠው የአጭር ጊዜ ሥልጠና ባለፈ በቅርንጫፍ ለማስፋፋትና ጊዜም ለመጨመር ታስቦ ነበር።

አሁንም ታድያ ሥራዎች እንደሚቀጥሉና እንደማይቋረጡ፣ እርሱ በሕይወት ያለ ያህል ቆጥሮ እንደሚሠራ ነው አብርሃም የሚናገረው። ኢካሽ ማሠልጠኛን በጋራ እንደመጀመራቸው፣ ከሥያሜው ጀምሮ የካሳሁን ማንነት ሁሉን እንካ ብለው እንዲሰጡት የሚፈቅድ ሰዋዊ እንደሆነም ሳይጠቅስ አልቀረም። በቢዝነስ ሥራም ብዙዎች ሳይስማሙ ሥራዎች በየጊዜው ይቋረጣሉ ይፈርሳሉ፣ ካሳሁን ካለው ሰውኛ ማንነት የተነሳ ግን ይህ አይሆንም ሲል አያይዞ አውስቷል።

በብሥራት ኤፍኤም በሳምንት አራት ቀን በሚተላለፈውና ስድስት ዓመቱን በተጠጋው ‹አሻም› ከተሰኘው የራድዮን መሰናዶ በተጨማሪ፣ ካሳሁን የተለያዩ ባህልና ታሪክ ላይ ያተኮሩ መድረኮችን በማዘጋጀትና በመምራት፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ በማማከር ጊዜውን ሰጥቷል። ይህም ከቤተሰቡ ጊዜን ቀንሶ ለሌሎች ለብዙዎች እንዲሰጥ ያስገደደው ነበር።

‹‹ካሳሁን አመስጋኝ ነው›› አለ አብርሃም፣ ስለጓደኛውና ባልደረባው ሲናገር። ሲያመሰግን ስለተደረገለት ትልቅ ነገር አይደለም፣ በትንሿ ነገርም ያመሰግናል። ይህም ፈገግታና ትህትና በተሞላበት መንገድ የሚያደርገው ነው። ያም ብቻ አይደለም፣ ቢጎዳ እንኳ ተጎዳሁኝ አይልም። ሁሉን በውስጡ አኑሮ የመጣውን በፈገግታ ያስተናግዳል። ይህ የሚገርም ተፈጥሮውም አብረውት ለመሆን ሳይቀር ያስናፍቃል፣ እንደ አብርሃም አገላለጽ።

‹‹የእርሱ ኢትዮጵያም ትለያለች። ሁሉንም ነገር ከኢትዮጵያ ጋር ያገናኛል። በነገሩም ሁሉ አገሩን ያነሳል።›› ሲልም ገልጾታል። ጋዜጠኝነቱን እንኳ በኢትዮጵያዊነት ዐይን የሚያይ ነው። ለአገር ተቆርቋሪ፣ ስሱ፣ ያገባኛል የሚል፣ ሙያውን አክብሮ ያስከበረ ጋዜጠኛ ነው፤ ካሳሁን አሰፋ።

አብርሃም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቆይታ ከቀረበለት ጥያቄ መካከል አንዱ፣ ‹‹ካሳሁን ታይተው እንደሚጠፉ፣ አብርተው ብዙም ሳይቆዩ ከዐይን እንደሚሰወሩ ተወርዋሪ ኮከቦች አይደለምን?›› የሚል ነበር። እርሱም አለ፣ ‹‹የኤልያስ መልካ ሽኝት ጊዜ ጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ ስለ ኤልያስ ሲናገር፣ ዘመንና ትውልድ እንዳይወቀስ የትውልድንም ወቀሳ የሻረ ባለሞያ ነው አለው። ካሳሁንም ጋዜጠኝነትን በኢትዮጵያዊነት የቃኘ፣ ወቀሳችንን የሻረ ሙያተኛ ነበር።››

ካሳሁን ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት ነበር። ለቤተሰቡም የኃላፊነትን ስሜት ወስዶ እህቶቹን ወንድሞቹን ተንከባካቢም ጭምር። ለዛም ነው ወንድሜ ሳይሆን አባቴ ብለው ያለቀሱለት ይላል አብርሃም። ይህ ሰው ሥራውን ሲል፣ ሲባትል፣ ሲባዝን፣ ለጤናው መስጠት የነበረበትን ትኩረት አልሰጠም፣ አልተንከባከበም። ለራሱ ካደረገው ይልቅ ለሌሎች የሰጠው ስለበለጠ፣ ስለሙያውና ስለአገሩ ስላለው የሚያስቀና ፍቅርም እስከ ወዲያኛው የሚረሳ አይሆንም።

ተግባቢነት፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢነት፣ ለሌሎች መኖር፣ መስጠትና አመስጋኝነት፣ ትህትና የሙያና የአገር ፍቅር፣ በድምሩ ሰውነት የካሳሁን አሰፋ ሥም ሲጠራና ሲታወስ አብረው የሚነሱ ማንነቶቹ ናቸው። ይህ ሰው ሠኔ 26/2012 ላይመለስ ዓለምን ተሰናብቷል። አዲስ ማለዳ ለባለቤቱና ለልጆቹ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹና የሥራ ባለደረቦቹ፣ ለተማሪዎቹና ለሚያውቁት ሁሉ መጽናናትን ትመኛለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com