‹‹አሻም አሻም!›› የኢትዮጵያዊነት ካባ ለብሶ የኖረ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ!

Views: 77

የእግዚአብሔር ስስት አይጣል፤ ገራገር ፍጡር ይወዳል፤
ዙሪያችን ደምቆ ሲያበራ፣ አምላክም እንደ ሰው ይቀናል፤
ቀን ከሌት እየለሰነ “ሰው ይሁን!” ብሎ ሲያቀና፣
እንደገና መልሶ መውሰድ፣ የአምላክነት ድርቅና!
አልበዛም እንዴ አሁንስ? ተወቀስ ዛሬ ፈጣሪ፤
ምነው እንደሰው ሆንክሳ ማልዶ መርዶ ነጋሪ፤
እያሳዩ መመለስ ካጠገብ እየመዘዙ፣
በ”ሁሉን መቻል” ዕልቅናህ ይሁን ብሎ ማዘዙ።
እስኪ ውረድና ና፣ አለኝ የምጠይቅህ ፤
እስኪ ተገልጠህ ቅረብ፣ አለ የምሞግትህ፤
መውደድ ለራስህ ብቻ ከቶ ማን ፈቀደለህ??????
ወይ ቀድሞ አለመፍጠር ነው አወይ አጨካከንህ!
አሁን ምን ይሳንሃል? እሱን መውደድ ብትተው፤
እዚህ እኮ እልፍ ወዳጅ አለ፣ የሱ መኖር ግድ አለው።
አልችልህ ነገር ሞግቼህ አጉል መከራከር ነው፤
ግዴለም ለዛሬ ብቻ – እኛ መካከል አኑረው፤
ይዞ የሄደው ደግነት፣ ፈጣሪ ላንተ ምንም ነው፤
ለኛ ግን ፀሐይ ነውና ተውልንና እንሙቀው፤
ለኛ ግን ጸበል ነውና ፈቅደህ እንጠመቀው!

እንዲህ ነው … አንዳንዴ ከፈጣሪ ጋር የሚያሟግት ሰው አለ። ሞቱ ቋሚውን ከአምላኩ ጋር የሚያቃቅር። ‘ኧረ ባይሆን’ የሚባል ነገር ሆኖ ሲገኝ ከፈጣሪ ጋር ያሟግታል። እገሌ ሞተ ሲባል የተቆረጠለት ቀን ስለሆነ ነው እየተባለ የሚነገረው ይትበሃልና እምነት በቀላሉ የማይመልስለት ሰው አለ። ህልፈተ ሕይወቱ ሲሰማና ድንገት ዘመም ሲል ብቻውን የማያዘም እኮ ጥቂት ነው።
ከሳምንት በፊት በአካለ ሥጋ ያጣነው ጋዜጠኛ ካሳሁን አሠፋ እንዲህ የሚያስብል፣ ተለቅሶ የማይወጣ፣ ታዝኖ ቶሎ የማያልፍ ነው። ጋዜጠኝነትን በፍቅር ተሸክሞ ሲባትል የኖረ፤ ያየውንና የሰማውን ሁሉ ከእናት አገር ጋር ካላስተሳሰረ የማይሆንለት የሬድዮ ሰው ነበር። ድምጹ በአፈጣጠሩ የተሞረደ፣ ጆሮ ሳይወጋ ከልቦና የሚያርፍ ለዛ ያዘለ ነው። የሬድዮ ብዙኀን መገናኛ ይዘቱ ከአቀራረብ ጋር ካልተዋሃደ ለዛቢስ ነው። ስልት ይፈልጋል። ባልታሰበ ወቅት ያጣነው ካሳሁን በጋዜጠኝነት ሕይወቱ ኢትዮጵያዊነትን ለብሶ የኖረ ብርቅ የአገር ልጅ ነው።

የቅዳሜና እሁድ ማለዳዎች በብስራት ኤፍ ኤፍ 101.1 ሲደመጡ ‹አሻም አሻም› የሚል ማሟሻ ጎላ ብሎ ይሰማባቸዋል። በዚህ ሰላምታ ውስጥ የጋዜጠኛ ካሳሁን ድምጽ ቀድሞ ወደ ጆሮ ይደርሳል። አዲስ አበባ የሰንበት ቀናት ማለዳዎቿ ሬድዮ ላይ ከሆነ በአመዛኙ በዚህ የሬድዮ ድምጽ ጠዋቷን ታሟሙቃለች ‹‹… አሻም አሻም!››

አሻም የሬድዮ ፕሮግራም በጋዜጠኛ ካሳሁን አሠፋ፣ ሚካኤል ዓለማየሁና (የእናኑ ልጅ) እና ምሥክር ጌታነው ኢትዮጵያዊነትና ባህልን በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብሩ አየር ላይ ሲውል አዲስ አበባ ከነአጎራባች ከተሞቿ ትነቃለች። የሰኞና ረቡዕ የአሻም ዝግጅት የአፍሪካ ጉዳዮችና ቢዝነስ ላይ እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል። ካስሽ መዲናችን ውስጥ እስካለ ድረስ አራቱም ቀናት ላይ ከኹለቱ ባልደረቦቹ መካከል ሆኖ ከነድምቀቱ አየር ላይ ብቅ ይላል።

በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በሬድዮና ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ላይ ፕሮግራም መምራት የዋዛ አይደለም። በተለይ የቀጥታ ስርጭት ሲሆን ጊዜ ጀት ነው። ብዙኀን መገናኛ ላይ የሠራ ለጊዜ ልኬት አዲስ አይደለም። የሚዲያ ሰዓት ልጓም የለውም። ጎንበስ ብለው ቀና እስኪሉ ድረስ ብን ብሎ እንደሚያልፍ ነፋስ ዓይነት ነው። ለዚህ ነው ደቂቃዎችን ከሚቀርበው ይዘት ጋር ማጣጣም፣ ቅደም ተከተልን ማስጠበቅ፣ የማስታወቂያን ሰዓት በቦታው እያስገቡ ማስኬድ የፕሮግራም መሪው ጥብቅ ኃላፊነት የሚሆነው።

በአንድ ሰዓት ውስጥ ለሦስት ሆኖ ጥንቅቅ ያለ መሠናዶ ማቅረብ ይከብዳል። በዚህ ውስን ሰዓት የጀመሩትን ርዕሰ ጉዳይ በውስን ጊዜያት ውስጥ አብቃቅቶ መጨረስ ዕውቀትና ክህሎት ብቻ ሳይሆን ልምድም ይጠይቃል። በአሻም መርሃ ግብር የካሳሁን የጋዜጠኝነት ዕውቀትና ልምድ ከባልደረቦቹ የበሰለ ማንነት ጋር በብቃት ይከወናል።
በጋዜጠኝነት ሙያ ስቱዲዮ ውስጥ ወይም ማይክ ላይ ነኝ ብሎ እንደፈለገ የመናገር ሳይሆን የአድማጮችን ስሜት የጠበቀ ስብዕና ይዞ ወደ ጆሮ መድረስ መቻል መታደል ነው። ይህ ዓይነቱ ሙያዊና ተፈጥሯዊ ማንነት ከተሳካላቸው ጥቂቶች አንዱ እርሱ ነው። የካስሽ ሙያዊ አቅም የሚያውቁትንና የሰሙትን ወይም ያዩትን ሁሉ ስቱዲዮ ውስጥ ገብቶ እንደወረደ መጻፍና መናገር የጋዜጠኝነት ልክ ነው የሚሉትን ባለሙያዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረገ ጋዜጠኛ ነው።

ከምስል ከሳች ንግግሩና አቀራረቡ ባሻገር የድምጹ ቅላጼ ትሁትነቱን ያሳብቅበታል። ጋዜጠኝነት ማለት በምንናገረው ጉዳይ ላይ ከሙያ ባለቤቶቹ ባለፈ ባለዕውቀት ነን ማለት አይደለም። ርዕሰ ጉዳዩን በአግባቡ ተረድቶ ከግራ ቀኝ ምልከታዎች ጋር አሰናስሎ በጨዋ ደንብ ወደ አድማጭና ተመልካች ማድረስና ማስረጽ መቻል ነው። ካስሽ በዚህ በኩል የታደለ ነበር።

የብስራት ኤፍኤሙ መሠለ መንግሥቱ ‹እግር ኳስን በሬድዮ ተመልከቱ› ከሚለው ንግግርሩ ውስጥ አንደበታዊ ነገርን እንደ ቴሌቪዥን መመልከት ስለመቻል የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው። ማንም የሬድዮ ጋዜጠኛ መለኪያው ይሄ ሊሆን ይገባል። አነጋገሩና አቀራረቡ በአድማጭ አእምሮ ውስጥ ምስልን ሊከስት ይገባዋል። ካሳሁን ይህ ነው! በጎንዮሽ ከባልደረቦቹ ጋር፣ አየር ላይ ከአድማጮቹ፣ ከመስታወት ወዲያ ደግሞ ከቴክኒሻኖቹ ጋር፣ ከራሱ ሲሆን ርዕሰ ጉዳዩን ከማስታወቂያዎቹ ጋር በማጣመር እያግባባ አንዲቷ የአሻም ሰዓት ታልፋለች።
ጋዜጠኛ ካሳሁን አሠፋ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ባቋቋሙት ኢካሽ የተሰኘው ድርጅት ውስጥ ከሚሠራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል የአሻም ሬድዮ ወደ ብዙኀኑ በመድረስ በኩል አኩሪ ሥራ እየተሠራበት ያለ ነው። ኢካሽ ፕሮሞሽን በማማከርና በማስታወቂያ ሥራዎች ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል።

በዚህ ዓመትም ጋዜጠኝነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የበለጠ እንዲዳብርና ክብር እንዲያገኝ እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃኑ ግብዓት ማቅረብ እንዲቻል ሲባል ብዙዎችንም ከህልማቸው ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሙያ ሥልጠና ማእከል በትብብር በማቋቋም ተጨማሪ የሥራ ዘርፍ ፈጥሯል። በዚህ ሥልጠና ውስጥ ሥልጠናውን በመስጠት ጭምር ተሳትፎው የላቀ ነው። በተለይ ስለዜና አዘገጃጀትና አቀራረብ ማስተማር ልምዱ ለብዙዎች ደርሷል።

ካሳሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው። ከዚያ ቀደም ብሎ ከኮተቤ (መምህራን ኮሌጅ በሚባልበት ጊዜ) በቋንቋ ዲፕሎማ ተቀብሏል። ስለዜና ሲያስተምር ግን ከዩኒቨርስቲው በላይ ፋና 98.1 ቀርፆኛል ባይ ነው። የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ቤት ረግጠው የሚወጡ ጋዜጠኞች ውስጡ ሳሉ ባላውቅም ቤቱን ከለቀቁ በኋላ ግን ለጣቢያው ያላቸው ምሥጋና አይጣል ነው።

ፋና ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በአግባቡ ያዋሃዳቸው ስለመሆኑ ደረታቸውን ነፍተው ከሚናገሩት መካከል ጋዜጠኛ ሰሎሞን ኃይለየሱስ፣ ካሳ አያሌው ካሳ እና ይሄው ካሳሁን አሰፋ ናቸው። እነዚህን የጠቀስኩት በኢካሽ የጋዜጠኝነት ሥልጠና ላይ ባለን የሥራ ግንኙነት ከአንድም ኹለት ሦስት ጊዜ አብረን ስላወጋን ነው። የነገረ ሙያቸው ከፍታም በገሃድ የሚታይ ነውና የሚያውቃቸው ሁሉ ያሉትን ያምናል። አንዳንድ ድርጅት እንዲህ ነው፤ ያለስስት ሙያዊ መንገድ ያሳያል። ከዚያ ከተወጣ በኋላ ደግሞ ያልሆነውን ትቶ የሚሆነውን አበጃጅቶ የራስን መንገድ መያዝ የባለሙያው ጉዳይ ነው።

ካስሽ አሻም የሬድዮ ፕሮግራም ላይ የራሱን ተከታይ አፍርቶ ስኬታማ የሬድዮ ሥራ ከጀመረ ስድስተኛ ዓመቱን መጪው ጳጉሜ ላይ ይደፍናል። እሱ ግን የማይጋፉት ባላጋራ ገጠመውና ስድስተኛ ዓመቱ ለማክበር አይገኝም። ሥራው ግን እንዳይቆም ሆኖ የተመሠረተ ነውና እኛ ባልደረቦቹን ጨምሮ የሚያውቁትና የሰሙትን ሁሉ ይመለከታል። ሞት ቀጠሮ የለውም፤ የደራሲና የጋዜጠኛ ሕይወት ውጭ ውጭውን ሲባል የሚኖርበት ነውና የቤቱ አይሞላም።

ካስሽም ከዚህ የተለየ ሕይወት አልነበረውም። በተለይ ሥልጠናውን በጥምረት ለመሥራት ካቀድን ጀምሮ ወደ ትልቅ ተቋምነት ለማሸጋገር በተደጋጋሚ እየተገናኘን ውጥናችንን ስናሰላ የየግል ሕይወታችንንም ማውጋታችን አልቀረም። ካስሽ ባለራዕይ ነበር። ሕጻናት ልጆቹን በባንዲራ አልባሳት እያስዋበ ፎቶ ማንሳት የሚወደው ካስሽ ጥሩ የኑሮ መንገድ ይዞ እንደነበር አውቃለሁ። ስለነሱ ያስባል፣ ቢያንስ በመኖሪያ ቤት በኩል ከኪራይ ለመውጣት ያልማል። ከዚያ በፊት ልተው ቢልም የማይተወው የደግነት እጁም ለብዙዎች ይዘረጋል። ለእህት ወንድሞቹ ሙት ነው። ከዕቅዱ ውስጥ እነሱን አውጥቶ አያውቅም። ካስሽ እንዲህ ነው! የብቻ ሰው አይደለም፤ ዙሪያው በመስጠት፣ ልቦናው በማገዝ፣ ሐሳቡ ሁሉ በአብሮነት የተከበበ ነው።

ሁሉም ነገር ግን በዚህ መልኩ ይቀራል ያለ አልነበረምና ይቺን ምድር ከሕልሙ ስኬት በፊት ተለያት። በለሆሳስ ሰው እየጣለ ያለው ዝምተኛው ገዳይ እጅ ገባ። ብዙም ነገሬ ባላለውና አብሮት በቆየው ደም ብዛት ድንገት ሕይወቱ አለፈ። የሰማ ሁሉ “እንዴት ተደርጎ?!” በሚል ድንጋጤ የካስሽን ሞት ያላመነበት ምክንያት አለው። ሁሌ እንደሮጠ፣ እንደሳቀ፣ ቆሞም ይሁን ቁጭ ብሎ ከጋዜጠኝነት ፈቀቅ ሳይል እንደባተለ በደስታ የኖረ እንጂ መቼ ጤና የጎደለው ይመስል ነበር?!

ከሚወደው ሙያ ጋር እንደተጣበቀ እዚያው አለፈ። ሲያዩት ሺሕ ዓመት የሚኖር ይመስላል። ለዚያ ነው የሚያስደነግጠው። ከላይ ያለው ግጥም ፈጣሪን በመሞገትና በመማጸን መሐል የቆመውም ለዚያ ነው። መልስ ልጃችንን የሚያስብል ህልፈተ ሕይወት ነውና! እሱ በመኖሩ አምላክ ቀናበት ወይ የሚያስብል፤ አልቅሰው የሚቀብሩት ሳይሆን ህልፈቱ ቅር የሚያሰኝ ነው። ቀና ሰው ግን ለምን ያልፋል?

ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የሐያሲ አብደላ እዝራ ህልፈተ ሕይወትን ተከትሎ በዋቤ ሸበሌ ሆቴል በተዘጋጀ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የተናገረው ትዝ ይለኛል። ሐያሲው ለዓለማየሁ ወዳጁ ነው። ሥነ ጽሑፍን በመሔስ ዘርፉን እያገዘ የነበረው ይህ ብርቱ ሰው ድንገት ዘንበል አለ፤ ዘንበል ብሎ አልቀረም። በአካለ ሥጋ ከሚያውቁትም ከሚያውቃቸውም ተለይቶ በዚያው መቅረቱ እውነት ሲሆን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በአንድ ቦታ እንዳዘመመችው ሁሉ የአንዳንድ ጸሐፍት ስሜት ውስጥ ቁጭት ቦታውን ያዘ።

ዋርካ ሲወድቅ የዋርካው መንደር ሰው ሁሉ ይደነግጣል። ስለመጪው ዘመን ሐሳብ ይገባዋል። ዋርካ ሲወድቅ ከለላው ከመንደሩ ይገፈፋል። እንደዚህ ያሉ የሰው ዋርካዎች አሉ! እነሱ ከመኖር ላይ ዞር ሲሉ የሚጋለጥ ነገር አለ። የዓለማየሁ ሐዘን ገጽታውን ሸፍኖት የታየውም ለዚህ ነበር።

‹‹አብደላ ዕዝራን ከሚወስድ እንደኔ ዓይነት ሰው ነበረለት አይደለ ወይ?” አለ ዓለማየሁ፣ ለእግዜር ቅሬታውን ሲነግር። ‹‹እግዜርን እንደመቀየም አልኩት›› ሲል አከለ። ከእንግዲህ ሥነ ጽሑፍን ማን ይሔሰዋል? በሚል ቅሬታ ከአምላኩ ጋር እስከመቀያየም ያደረሰው ወዳጅም የሥራ አጋርም ሆኖ አብሮት ለዓመታት ያሳለፈውን፣ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትልቅ አበርክቶ የነበረውን ሐያሲ በማጣቱ ምክንያት መሪር ሐዘን ስለተሰማው ነው። እንደዚህ ያለ መድረክ ኖሮ ሀዘንን ከብዙኀኑ ጋር መወጣትም እሰየው ነው። የጋዜጠኛ ካሳሁን አሠፋም እንዲያ ነው። ሞት ባይኖር የሚያስብል!
በጥቅሉ በወርሃ ሠኔ አገር ጉዳት ላይ ናት። ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ያጣችው ኢትዮጵያ ሀዘኗ አልወጣ ብሏታል። አንዳንድ የጥበብ ሰዎች ሥራዎቻቸው በተከታዮቻቸው ልብ ውስጥ ቦታ አግኝቶ ሲቆይ ህልፈተ ሕይወታቸው በቀላሉ የሚታመንም፣ የሚቀበሉትም አልሆን ይላል። በሞት መለየት ያውም የሚወዱትን ሲሆን ያማል! ያለፈው ሳምንት እንዲህ ባለ ስሜት ያለፈ ቢመስልም አሁንም ድረስ ከሐዘናቸው ያላገገሙ በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያዬ ሆይ የሞት ጥላሽ ይገፈፍ! ኹለት ወጣቶችን አጥተናል።

የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም በመጠቃቱና ጉዳቱም እየከፋ በመምጣቱ ይህንኑ አስመልክቶ በተዘጋጀው መርሐ ግብር የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ባህር ዳር አቅንቶ ነበር። ጋዜጠኛ ካሳሁን አሠፋም የቡድኑ አካል ነው። ካስሽ እንዲህ ባለው አገራዊ ጉዳይ ተሳትፎው ላቅ ያለ ነው። የካሜራ ባለሙያ ጭምር ይዞ ያልተጓዘበት ስፍራ የለም። በኢትዮጵያ ባህል ላይ የቴሌቪዥን መሠናዶ ለማዘጋጀት ውጥንም ስለነበረው መረጃ እየሰበሰበ በመሆኑ ለቱሪዝሙና ተያያዥ ጉዳዮች ቅርብ ነው።

ለኢትዮጵያዊነትና ባህሏ ስሜቱ ስስ ነው። ውልደቱ ከወደ ደቡብ ነውና እያየ ያደገው ተፈጥሮና የባህል ስብጥሩ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ሳያደርገው አልቀረም። አመጋገብ፣ የዕደ ጥበብ ሥራ፣ ባህላዊ ሽምግልና እና የመሣሠሉት የማኅበረሰቡን አኗኗሮችና ቱባ ባህሎችን በቻለው ገጽ ሁሉ ያለመሠልቸት ተናግሯል፤ ጽፏል፤ ተርኳል።

ከባልደረቦቹ ጋር በአሻም ሬድዮ ላይሆን አቅርቧል። አሻም በዚህ ረገድ ያለመሠልቸት በወጥነት የሠራ የሬድዮ ፕሮግራም ነውና ምስጋና ይገባዋል። የሬድዮ ፕሮግራሙ አሰናጆች ካሳሁን፣ ምሥክርና ሚካኤል ከኮተቤ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ድረስ አብሮ ተምሮ በሥራው ዓለምም በጋራ እስከመሥራት የደረሱ ናቸውና ለብዙኃኑ የአብሮነት ምሳሌ ናቸው። የሥራም ሆነ የወዳጅነታቸው ዋርካ ደግሞ ካሳሁን እንደነበር እነርሱም በምስክርነት የሚናገሩት ነው።

የሆነው ነገር ባለፈው ሳምንት ማለቂያ ሚዲያውን ጥቁር ያለበሰ ክስተት ነበር። የነገሬ ማጠንጠኛም ይህ ነው። ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ በድንገተኛ ሕመም ሕክምና ሳያድነው፣ የኹለት አዳጊ የሕጻናቱ አባትነት እስትንፋስ ሳይሆነው፣ የእልፍ ወዳጆቹ ምኞት እውን አልሆን ብሎ እንደዋዛ አለፈ። የባለቤቱ ራሔልን ሐዘን ላየ የካስሽ ቤተሰባዊ ፍቅርና የኃላፊነቱን ጥግ ይረዳል። እህትና ወንድምቹን እንደወላጅ አባት አብሮነቱን በተግባር ያሳየ ሩህሩህ ነው።

አባቴ ብለው ሲያለቅሱ፣ ሐዘናቸውን መቋቋም አቅቷቸው ሲወድቁ ለተመለከተ ጋዜጠኛው ውስጥ ሰብዓዊነትም ነበር ለካ ይላል። ከደራሲና ጋዜጠኛ ካሳ አያሌው ካሳ ጋር እያወራን የነገረኝ አለ ‹‹ሰው እንዴት ሰው ሆኖ እከሌ እንዲህ አደረገኝ፣ እንዲህ ሆንኩ፣ በደሉኝ፣ ጎዱኝ አይልም?! ካስሽ እኮ እንዲህ ነበር።›› አለኝ ከሰበብ የራቀ ስብዕና!

ከኔ ጋር በጓደኝነትም በሥራም ቅርብ ነበርን። የካስሽ ህልፈት እከሌ ሞተ ሲባል ክው ከሚያደርጉ ሞቶች እንደ አንዱ የሆነ ነው። ሥራው ላይ ኖሮ ሥራው ላይ ሳለ ያረፈ ጋዜጠኛ ነው። አራት ዐስርተ ዓመታት ገና የሕይወት ወግ የሚጀመርበት፣ ወደ ራስ መስመር የሚገባበት፣ መስመር የለሽ ባተሌነት ተቀንሶ በአንድ ዘርፍ ውስጥ ለመከተት የሚወሰንበት አማካይ ዕድሜ ነው። አርባ ኹለት ዓመት ማለት ሰብሰብ ተብሎ አሀዱ የሚባልበት ጊዜ ነው።

ክው የሚያደርገውና የሚያሳዝነውም ለዚህ ነው። በጋዜጠኝነቱ ታታሪ የነበረ የኢትዮጵያ ልጅ ግን አረፈ። የመድረክ ዝግጅት ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ መልበስን ይሻል። በአንደኛው የኢትዮጵያ የባህል ልብስ መታየት ይቀናዋል። በደንብ ላስተዋለው የእርሱ ኢትዮጵያ ትለያለች፤ ይዟት ዞሯል፤ አቅፏት ኖሯል። ከስሯ አልተለየም። እየወደዳት፣ እየሰሰተላት፣ እየሳሳላት፣ እየጸለየላት አለፈ። ኢትዮጵያን በጋዜጠኝነት ካባ እንደለበሳት ከነአገራዊ ኩራቱ ዐፈሯ ውስጥ እስከወዲያኛው አረፈ። የኢትዮ አምላክ ነፍሱን በገነት ያኑረው። የቀሩትን የሕይወት ዘመን አጋሩና የአብራኩ ክፋዮች መጪ ዘመን ብሩህ ያድርግ!

ጋዜጠኛ ደራሲና ተርጓሚ ነብይ መኮንን በስውር ስፌት የግጥም መጽሐፉ ላይ ይመስለኛል አንድ ያስቀመጣት ውሃ የምታነሳ መልዕክት አለችው። ቃል በቃል ባይሆንም እንዲህ ትላለች፦
“በዚህ እየሄደ ባለው ዕድሜዬም ቢሆን የመጻፌ ምክንያት ምናልባት የሞት መላዕክት ቢመጣና ነብይን የት አገኘኸው ተብሎ ቢጠየቅ ከአትሮንሱ ስር እየጻፈ ነበር እንዲልልኝ ነው።” ብሎ ጽፏል። ነገርየው ቀልድ አዘል እውነት ነው! ሰው ከሞቱ አሟሟቱ ማንነቱን የሚናገርበት ጊዜ አለና እየሠሩ ኖረው እየሠሩ የሚያልፉ ሰዎች የታደሉ ናቸው።

ሲዘርፉ፣ ሲተናኮሉ፣ ሲያሴሩስ መሞት አለ አይደል! ካስሽ ሥራው ላይ ሳለ ነው ህልፈቱ። በመምህርነት መንገድ መጥቶ በጋዜጠኝነት ሙያ ኖረ። በዚሁ ሥራ ላይ እያለ ለልጆቹ ጋር የረባ ጊዜ ሳይሰጥ፣ አንገት ማስገቢያ ጎጆ ሳይቀልስ ድንገት ጅምሩን ሁሉ ትቶ መሄዱ ሲታሰብ ያሳዝናል።

የጋዜጠኝነት ፍቅሩ አይጣል ነው። ኢትዮጵያን የሚኮራባትም የሚያለቅስላትም በጋዜጠኝነት ዐይኑ ነው። አንድ ጊዜ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ህንጻ ጉዳት በቀጥታ ከቦታው ሲያስተላልፍ ሳግ እየተናነቀው ነበር። እንዲህ ነው እሱ! አገር ልቡ ውስጥ ናት። አሁን የሕይወቱ የማብቂያ ጊዜ በሆነው የጣና እምቦጭ የዘገባ ሥራ ላይም አገር ምን እየሆነች ነው በሚል የተሰበረ መንፈስ ከጣና ጋር ሲያወጋ ነበር። ነብይ በመጨረሻዬ ቀን ከአትሮኑሱ ስር መገኘት እሻለሁ አለያም ደግሞ እንደጻፍኩ ማለፍን እፈልጋለሁ የሚል አንድምታ ያለው ጽሑፉ ካስሽ ላይ እውነት ሆኗል። በጋዜጠኝነቱ ሜዳ ላይ ሳለ ጊዜውን አጠናቋል።

የህልፈተ ሕይወቱ ክስተት ድንገት በሆነ ምክንያት ነው። እዚያው ከጣና ሐይቅ ሥራ ሳይወጣ ባህር ዳር ሳለ ድንገት ነገር ዓለሙን ያቆመ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። ካስሽ መራመዱ ተገታና እንደመውደቅ አለ። አጠገቡ የካሜራ ባለሙያው ሲሳይ ጉዛይ ነበረና ደርሶ ደገፍ አደረገው። ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ተከታተለ። ሰውነቱ አልታዘዝ እንደማለት ሲል ወደ ሕክምና ተወሰደ፤ ሁኔታው ወደአ ዲስ አበባ ሊያስመጣው ግድ ሆነና ተወሰነ።

ነገ ከነገ ወዲያ ይድናል በሚል ሁኔታው ኢንተርኔትን ጨምሮ ለብዙኀን መገናኛዎች ህመሙ ይፋ አልተደረገም። በሂደት ግን ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ቤተ ዛታ ሆስፒታል እንደተኛ ሳምንት አለፈው። ለማስታወቂያ ጆሮ ገብና ሥሙም የሆነው ድምጹ ቃላት ለማውጣት እንቢ አለው። ለወትሮው ቅልጥፍ የሚለው አረማመዱ፣ ቆሞ ለሚያየው ነቃ ያለ አካሄዱ ቀርቶ ከአልጋ ላይ ዋለ። በዚህ መልኩ ሳምንት አለፈው።

ሰኔ 26 ግን ከቤተ ዛታ መልካም ያልሆነ ዜና መጣ። የተሞከረው ሁሉ ጋዜጠኛውን ለማትረፍ የማይሆን እንደሆነ ተነገረ። ከሕክምና ሰዎቹ ጋር ቀርበው ከተነጋገሩት የቅርብ ሰዎች አንዱ ምስክር ጌታነው ነበርና ጠጋ ብዬ ምን አሉህ አልኩት። እርሱ ግን እንባ ቀደመው። ካስሽ አለፈ። ወንድማችን የኢትዮጵያዊነት ካባ ዝቅ ባለ ቁጥር ከፍ እያደረገ፣ አንድም ቀን ሳይሰለች አገርን የአብሮነት ካባ እንዳለበሰ ያለድካምና መሰልቸታ እንደወደዳት አለፈ። የወንድማችንን ነፍስ ይማር!

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com