የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት – ከ‹ነበር› እስከ ‹ነው›

Views: 344

ወደ ዊንጌት በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ይገኛል፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት። ብዙዎች ‹ፓስተር› በሚል ሥም ይጠሩታል። ለዚህም ምክንያት አላቸው። ይህንንም ምክንያት በኢንስቲትዩቱ የ‹ነበር› አምድ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኛለን።

ከታሪክ ማኅደር
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ1914 ነበር የተለያዩ የኅብረተሰብ እና የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን በመስጠት አሁን ተቋሙ በሚገኝበት ጉለሌ አካባቢ ሥራ የጀመረው። ያቋቋሙትም የበጎ ፈቃድ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ የተገኙት አሜሪካዊው የሕክምና ባለሞያ ዶክተር ቶማስ ላምቤ ነው። ይህም ሆስፒታል ጣልያን ኢትዮጵያን እስከ ወረረችበት ጊዜ ማለትም እስከ 1928 ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

ኢትዮጵያን በጣልያን ወረራ እጅ ላለመስጠት በአርበኞቿ ትግልን ስታደርግ በቆየችባቸው አምስት ዓመታት፣ ሆስፒታሉ ‹ሚኒስትሮ-ዴላ ሳኒታ› እየተባለ ይጠራ ነበር። ታድያ ተመሳሳይ አገልግሎት ይስጥ እንጂ በአምስቱ ዓመታት መገኛው እዛው ጉለሌ ሳይሆን ወደ አራት ኪሎ ተቀይሯል። ይህም ደግሞ አሁን የሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝበት ቦታ ነው።
ከአምስት ዓመት በኋላ በ1933 ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ነጻነቷን ስታስመልስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆስፒታሉን የመቆጣጠር ኃላፊነትን ሙሉ ለሙሉ ተረክቦ ሥያሜውንም ወደ ኢምፔሪያል የሕክምና ምርምር ተቋም ቀይሮታል።

ተቋሙ ታድያ ሥያሜውን ብቻ ሳይሆን መገኛውንም በተመሳሳይ በተደጋጋሚ ሲቀያይር ቆይቷል። ለምሳሌም ካዛንችስ አካባቢ እንዲሁም ሜክሲኮ መገኛዎቹ ነበሩ። በመጨረሻም ተቋሙ አሁን ወደሚገኝበት ወደ ጉለሌ የተመለሰው በ1943 ነበር። በዚህ ጊዜም የሆስፒታሉ ሥም ተፈሪ መኮንን ሆስፒታል የሚል ነበር።

በ1944 ከዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በፓሪስ ከሚገኘው ፓስተር የተባለ ማእከል ጋር የኹለትዮሽ ስምምነት አካሄዱ። ከዚህ በኋላ ነው የተቋሙ ሥያሜ ዛሬ ድረስ ወዳልተዘነጋው ወደ ‹የኢትዮጵያ ፓስተር ኢንስቲትዩት› የተለወጠው። ሆኖም በዛም ጸንቶ አልቆየም፣ በ1957 የኹለትዮሽ ስምምነቱ አበቃ። ተቋሙም ዳግም ወደ መንግሥት እጅ ሲመለስ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሚኒስቴር ተረከበው። ሥያሜውም ተቀይሮ ‹የንጉሠ ነገሥት ማእከላዊ ቤተሙከራና የምርምር ተቋም› ተባለ።

በጊዜው ታድያ ጥናትና ምርምር ይካሄድባቸው የነበሩ ወይም በሌላ አገላለጽ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድባቸው የተቋቋሙ መምሪያዎች የባክቴሮሎጂ፣ ፓራሳይቶሎጂ እና ሴሮሎጂ፣ የኬሚካል አናሊሲስ እና የታይፈስ ክትባት ማዘጋጃ መምሪያዎች ናቸው። በተጨማሪም የቲቢ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ የታይፎይች፣ የቢጫ ወባ እንዲሁም የጉንፋን በሽታ ክትባቶች በተቋሙ ይመረቱ ነበር።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን በሚመለከት በጊዜው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ችግር ይስተዋል ነበር። ለዚህም ተገቢና በቂ ምላሽ ለመስጠት በ1959 የጥናት መድረክ የተካሄደ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ በ1962 የኢትዮጵያ መንግሥት ከስዊድን መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ የሕጻናት ምገባ ዩኒት ወይም መምሪያ በተቋሙ ስር ተመሠረተ።

የዛሬው ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲህ እንዲህ እያለ 1968 ላይ ደረሰ። በዚሁ ዓመት ሥያሜው ‹የኢትዮጵያ የሥነ ምግብ ተቋም› ተባለ። ይህ ተቋም በተለይም ከ1968 እስከ 1973 በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ መፍትሄ አመላካች እቅዶችን በመንደፍና ድርቁን ለመቋቋም በተደረገ እንቅስቃሴ በኩል ትልቅ ሚና የነበረው እንደሆነም ይነገርለታል።

ቆይቶ በ1977 ‹ብሔራዊ የጤና ምርምር ተቋም› የሚል ሥያሜን ይዞ በአዋጅ ዳግም በአዲስ መልክ ተቋቋመ። በዚህ ጊዜም የተቋሙ ድርሻና ኃላፊነት በኢትዮጵያ በጤና ዙሪያ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ የሆነ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከተለያዩ ሆስፒታሎች የሚላኩ ሕክምናዎችን በማከናወንና የቤተሙከራ አገልግሎት የሚሰጥበት ሆነ።

በ1979 በጤና ሚኒስቴር በኩል፣ በጊዜው እውቅና የተሰጠው የባህላዊ መድኃኒት ጥቅም እንደ አማራጭ የጤና ምንጭ በከተማ እንዲሁም በገጠር አስፈላጊነቱን በመረዳት፣ የባህል መድኃኒት መምሪያ በውስጡ ተቋቁሟል። የጤና ዘርፍ ላይ ጥናቶችን በተቀናጀ መልኩ ማድረግ የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን መረዳት የመጣውም በጊዜ ሂደት ይመስላል።
ስለዚህም በተቋሙ ውስጥ በተለያዩ ጊዜ የተመሠረቱ የሥራ ክፍሎችና መምሪያዎች፣ በአንድ ላይ የተካተቱበት ብሔራዊ የጥናትና ምርምር ተቋም መመሥረት አስፈላጊ መሆኖ በጊዜው ታመነበት። እናም በ1987 የኢትዮጵያ ጤና እና ምግብ ስርዓት የምርምር ተቋም ተመሠረተ። የኅብረሰተብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን የሚመለከት ክፍል ተመሥርቶ በቀደሙት የተቋሙ ተግባራት ላይ መታከሉና የተለያየ ቦታ ሆነው ሲሠሩ የነበሩ ተግባራት በአንድ ላይ መጣመራቸው፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኅብረሰተብ ጤና ቤተሙከራ ስርዓት በድምሩ ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ምክንያት ሆነዋል።

ይህም ተዳምሮ በመጨረሻም በ2006 የተቋሙ ሥያሜ አሁን ወደሚጠራበት ‹የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት› ደረሰ። ተቋሙም ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት ተቋም እንዲሁም የራሱ ሕጋዊ ሰውነት ያለውም ሊሆን ቻለ። በዚህም ማቋቋሚያ አዋጅ የተቋሙ ድርሻና ኃላፊነቶች በሦስት ዋና በተባሉ ተግባራት ተቀነበበ።
አንደኛው በአገር ዐቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ምርምር አጀንዳ ላይ ተመሥርቶ ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የጤናና ሥነ ምግብ ችግሮች ላይ ምርምር ማድረግ ነው። ኹለተኛው የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥርን በተመለከተ ከሚመለከታው ጋር በመጣመር ስጋቶችን ቀድሞ መለየትና በቂ ዝግጅት ማድረግ ሲሆን፣ ሦስተኛው የተቋሙን ቤተሙከራዎች በሠለጠነ የሰው ኃይልና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በማጠናከር ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄድ ነው።

በጉዞ መካከል
ተቋሙ የፌዴራል ጤና ሚኒስትርን በቴክኒካዊ እንዲሁም ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ዓላማው ነው። ለዚህም አራት ስልታዊ ግቦች ያሉት ሲሆን፣ የጤና እና ስርዓተ ምግብ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ለእውቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲውል ማድረግ፣ ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር፣ ጥራት ያለው የቤተ ሙከራ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም የኅብረተሰብ ጤና ተመራማሪዎችን ማሠልጠን የሚሉ ናቸው።

ስለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ አጠር ያለ ታሪክ እንደተጠቀሰው፣ ተቋሙ በአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና ብቃት ላይ መድረስን የቅርብ ርቀት እቅዱ አድርጓል።
በትንሹ በሚመስል ሥራ የጀመረው ይኸው ተቋም ሥያሜውንና ስፍራውን እየቀያየረና የሚሰጠውን አገልግሎት በየጊዜው እየጨመረ፣ መቶ ዓመታትን ሊሞላ ኹለት ብቻ ቀርተውታል። በኢትዮጵያ የሕክምና እና የጤና አገልግሎት ከነድክመቱ ደረሰበት ለሚባለው ደረጃም ሊደርስ የቻለው በዚህ ተቋም መኖርና መንቀሳቀስ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

በተለይም ተቋሙ የኢትዮጵያ ፓስተር ኢንስቲትዩት በሚል መጠሪያ በሚጠራበት ጊዜ የፈንጣጣ በሽታን ክትባት ማምረት መቻሉ ተጠቃሽ ነው። የእብድ ውሻ በሽታ ክትባትም ተጠቃሽ ሲሆን፣ በዚህ ውጤታማ እንደነበርም ዛሬ ድረስ ተቋሙ በፓስተር ስም ሲጠራ ቀድሞ ይኸው ትዝ በሚላቸው በርካታ ሰዎች ምክንያት መገመት ይቻላል። አልፎም ክትባቱን በገፍ ማምረት በመቻሉ አስቀድሞ ከውጪ እንዲመጣ ይደረግ የነበረበት አሠራር እንዲቀር አስችሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የተቋሙ ሥም ደጋግሞ በመነሳቱ እውቅና ከቀድሞው ጨምሯል። ሆኖም ግን አስቀድሞም የሚከሰቱ ድንገተኛ የጤና እክሎችንና አገራዊ ወረርሽኞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ሥራ ውስጥ ግንባር ቀደም አስተባባሪ ሆኖ የሚገኘው የኅብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ነበር፤ ነውም።

ለማሳያም ኮሌራ፣ ኢቦላ፣ ፖሊዮ፣ የወባ በሽታና ኩፍኝ መሰል ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ድርሻውን ተወጥቷል። ያም ብቻ አይደለም፣ የተቋሙ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለመንግሥትና በጤናው ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን አመራርና መመሪያ እንዲያወጡ ደጋፊ ሐሳብ ሰጥቷቸዋል። ይህም የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም የጤና አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ድርሻው የጎላ ነው።

የምርምር ቤተሙከራዎችን ማስፋፋት ውጥኑ ያደረገው ተቋሙ፣ በ2020 ቁጥራቸውን ወደ 16 ለማድረስ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል። በተያያዘም በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ጥናቶች ሲኖሩ፣ ትኩረቱ ሁሉ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳይሆን በፊት፣ ተላላፊ ያልሆኑ፣ ቸል የተባሉ ሞቃታማ አካባቢ የሚገኙ እንዲሁም በድንገት የሚከሰቱ በሽታዎችን የሚመለከቱ ነበሩ።
ይህ እድሜ ጠገብና አንጋፋ ተቋም፣ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ለበርካታ ዓመታት የቤተ ሙከራ አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ተቋም በመሆን አገልግሏል። በዘርፉም ባለሞያዎችን በማሠልጠን የመጀመሪያው የአገር ውስጥ ትምህርት ቤት ሲሆን በድምሩም በዘርፉ አሉ ለሚባሉ ጥሩ እርምጃዎች ሁሉ ምስጋናውን የሚወስድ መሆኑን የሚመሰክሩለት ነው። አሁንም ቢሆን ታድያ በተመሳይ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

ተቋሙ በእድሜ ቆይታው ከላይ እንደተጠቀሰው በከፍተኛ ደረጃ ለሚወጡ ጤና ነክ ፖሊሲዎች ቀላል የማይባለውን አስተዋጽኦ እንካችሁ ያለ ነው። በተለይም በብሔራዊ የጤና ፖሊሲ፣ በትንበያ፣ በጤና አገልግሎት ፓኬጅ፣ በጤና አገልግሎት ክፍያ ስርዓት እንዲሁም ተላላፈ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ ሥሙ ይነሳል።
በቅርቡ የነበሩና በዚህ ተቋም ምክንያት የተነሱ ተግባራዊ የሆኑ ሥራዎችን እናንሳ። ለምሳሌ ኅዳር 30/2011 ‹በየወሩ የመጨረሻ እሁድ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ከተሽከርካሪ ፍሰት ነጻ መንገዶች ላይ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በመገናኘት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንከላከል።› በሚል በከተሞች የአካል እንቅስቃሴች ልምድ እየሆኑ ታይተው ነበር።

ይህም የሆነው በ2016 በተደረገ ጥናት 52 በመቶ ሞት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚከሰትና ከዚህም ከግማሽ በላይ የሚጠቁት እድሜያቸው ከ40 በታች የሆኑ ሰዎች እንደሆኑ ተቋሙ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ከአልኮል መጠጦች ጋር በተያያዘም ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ አዳጊዎች የአልኮል መጠጦች እንዳይሸጡና እንዲከለከል የሆነው በዚሁ ተቋም ምክረ ሐሳብ መሠረት ሲሆን፣ በተጨማሪም ሰዎች በሚበዙበት ቦታ ማጨስና የአልኮል ማስታወቂያ በተለይ በብሮድካስት መገናኛ ብዙኀን እንዲታገድ የሆነውም በተያያዘ ነው። በድምሩ የተቋሙ የጥናት ግኝቶች የጤና ዘርፍ ልማት እቅዶችን ለመገምገምና አካሄዶችን ለመቃኘት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ያለበት ደረጃ ከእያንዳንዱ ትላንት የተሻለ ቢሆንም አሁንም ሊጓዝት ያለውና የሚገባው ርቀትና ደረጃ ከፊት የሚጠበቀው ነው። በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍና ስርዓት ለውጥ ለማምጣትም ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ይታወቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com