ተስፋ ፈንጣቂው የውሃ ሙሊት ጅማሮ

Views: 285

የአባይን ወንዝ መሰረቱ አድርጎ፣ ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የጉባ ተራራ ታክኮ እና ሱዳንን በቅርብ ርቀት እየገረመመ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኘው ሕዳሴ ግድብ፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ የውሃ ሙሊት ተጀምሯል። እንደ ዓይናቸን ብሌን የምንሳሳለት እና የእያንዳንዳችን አሻራ ያረፈበት ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ልባችን በሐሴት እንዲሞላ እና በልበ ሙሉነት ቀና እንድንል አድርጎናል። ግድቡ ዘመነኛ የሥልጣኔ ሙከራዎቻችን ማሳያ ትዕምርት በመሆን በትውልዱ ልብ ላይ ታትሟል።
ምንም እንኳን የሳምንቱ መጀመሪያ ለኢትዮጵያውያን የምሥራችን ማብሰሪያ ቢሆንም በተለይ ለግብፃውያን መርዶ ነጋሪ ሆኖባቸዋል ማለት ይቻላል። ግድቡ በመንግሥት ደረጃ በከፍተኛ ምስጢር ተይዞ፣ አመቺ በሆነ ጊዜ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ መሆኑ ነጋሪ ባያሻውም ግንባታውን ከተቻለ ለማደናቀፍ ካልሆነ ለማዘግየት ብዙ ሴራዎች ተጎንጉነዋል፤ በተለይ በግብጽ።
የግንባታው ጅማሬ ለሕዝብ ይፋ የተደረገበት ወቅት በተለይ ከግብጽ ሊመጣ የሚችለውን ጫና በሚቀንስ ሁኔታ በደንብ የታቀደበት በመሆኑ ሰምሯል። ወቅቱ የግብጽ መንግሥት ቅቡልነት ፈተና ላይ የወደቀበት እና የሕዝቡም አንድነት የላላበት፤ በአጠቃለይ ግብጽ የተዳከመችበት በመሆኑ ሊመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ጫና አስቀርቶላታል።
ይሁንና ግንባታው ተጀምሮ ግብጽ ወደ መረጋጋቱ፣ መንግሥቷም ወደ መጠናከሩ ደረጃ ሲደርስ እጅግ አታካች፣ ምህዋሩ ወዴት ሊወስድ እንደሚችል በውል ወዳልታወቀ ድርድር አይሉት ውይይት ተገብቷል። አብዛኛውን ጊዜ ድርድሩ ኢትዮጵያን፣ ግብጽን እና ሱዳንን የሚያሳትፍ የሦስትዮስ ሲሆን የግብጽ ቀዳሚ አጀንዳ ግን ኢትዮጵያን በማዘናጋት ግንባታውን ከተቻለ ማስቆም ካልሆነ ማዘግየትን ታሳቢ ያደረገ ነበር። ለዚህም ማሳያው ግብጽ በተደጋጋሚ ድርድሩ አቋርጣ መውጣቷ፣ ተያያዥነት የሌላቸው አጀንዳዎችን በተደጋጋሚ ማቅረቧ እንዲሁም ሰሚ አላገኘችም እንጂ አልፎ አልፎም ማስፈራራቷ ተጠቃሽ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአባይ ወንዝ ውሃ የጋራ አጠቃቀም በተመለከተ የግብጽ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አይሎ የነበረ ሲሆን በድርድሩ የአሜሪካ መንግሥት እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ማድረግ መቻሏ እንዲሁም የአባይ ወንዝ ጉዳይ ከሦስቱ አገሮች በዘለለ የዓለም የሰላም እና ደኅነንት ጉዳይ ነው በማለት አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ጸጥታው ምክር ቤት ማቅረቧ ተጠቃሽ ናቸው። የኋላ ኋላ ኹለቱም ሙከራዎቿ አልተሳኩላትም።
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ የግድቡን ግንባታ አጠናክራ የቀጠለችው ኢትዮጵያ፣ ከግብጽ ለሚደርስባት ጫና ምላሽ ፈርጠም ያሉ የማያወላዱ ምላሾች መስጠት ጀመረች። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ከእንግዲህ ወዲህ ግብጽ እንደለመደችው ድርድሩን አቋርጬ እወጣለሁ ብትል ኢትዮጵያ ፈጽሞ ለድርድር በድጋሜ እንደማትቀርብ ማሳሰባቸው እና በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ግድቡን የገነባነው ውሃ ለመሙላት በመሆኑን በዕቅዱ መሰረት የውሃ ሙሌቱ እንደሚካሔድ አረጋግጠዋል፤ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን በገዛ ፈቃዳችን ግድቡን እንዳፈረስነው ይቆጠራል የሚል አንድምታ ያለው ጠንካራና የማያወላዳ ግልጽ መልዕክትም አስተላልፈዋል። እነዚህ መልዕክቶች ለኢትዮጵያውያን በአገር የመተማማን ብርታትን ሲጨምሩ፣ ለግብፃውያን ግን የእስከዛሬ የማደናቀፍ ባተሌነታቸው ላይ ውሃ ቸልሰውበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በይፋ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ባልሰጠችበት ሁኔታ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በርካታ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመርን በልዩ ትኩረት የሳተላይት ምስል በማስደገፍ የዘገቡ ሲሆን በሌላ በኩል ወደ አፍሪካ የተመለሰው አታካቹ የሦስትዮሽ ውይይት እንደልማዱ ያለስምምነት መቋጨቱም እንዲሁ ተሰምቷል።
የኢትዮጵያውያንን ቀልብ ሰሞነኛው የብዙ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው፣ አካል ያጎደለው እና ንብረት ያወደመው ኹከት እና ግርግር ሰቅዞ የያዘ ቢሆንም የግድቡ ውሃ ሙሊት መጀመር ደስታ አብሳሪ፣ ተስፋ ፈንጣቂ ከመሆን ግን አላገደውም።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com