የአያት የገበያ ማእከል ሰቆቃ መቼ ነው የሚያበቃው?

Views: 201

አዲስ አበባ መልኳን እንደ ሥሟ ለማደስ ደፋ ቀና በምትልበት ጊዜ፣ በተለያየ መልክ የሚነሱና በተለያዩ አካላት የተፈጸሙ ድርጊቶች ወደኋላ እየጎተቷት ይታያሉ። በተለይ እውቅና ተሰጥቷቸው በልማት ሥራ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ያሉ አካላት፣ በብልሹ አሠራር ውስጥ ሲጠመዱ፣ ለከተማ ልማት ሊመጡ የሚችሉ እድሎች ጭምር ይታጣሉ። ዮሐንስ አይናለምም ይህን ጉዳይ ነቅሰው በማውጣት ለበርካታ ዓመታት በሰበብ አስባቡ ሲጓተት ስለቆየው የአያት የገበያ ማእከል ጉዳይ በሰፊው አንስተዋል።

የአያት ሪል ስቴት ሕገወጥ አካሄድን የሚያስቆመው ማን ነው?
በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ መላ ቅጡ እየጠፋ የመጣው ከመንግሥታዊ ድርጅት እስከ ማኅበራት ከፖለቲከኞች እስከ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአክቲቪስቶች እስከ ፀጥታ አስከባሪዎች ሥርዓተ አልበኝነት ማቆሚያ ያጣ ችግር ሆኖ ይታያል።

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲስ አበባን ‹‹ለነዋሪዎቿ የተመቸች ለጎብኚዎች የደመቀ ከተማ›› አደርጋለሁ እያሉ ችግኝ በሚተክሉበት፣ ከንቲባ ታከለ ዑማ የነዋሪውን ችግር እቀርፋለሁ እያሉ አረጋውያንን ደግፈው ፎቶ በሚነሱበት መድረክ፣ ከመድረኩ በስተጀርባ በርካታ አፀያፊ እና አሳፋሪ ድርጊት በመንግሥት ሹሞችም ሆነ ማኅበራት ሲፈፀም በግልፅ እየታየ ይገኛል።
አዲስ አበባን አዲስ አበባ ለማድረግ ፓርኮች የተሟሉባት፣ ወንዞቿ ቆሻሻ ሳይሆን ጀልባ የሚንሳፈፍበት በአረንጏዴ ልምላሜ ያሸበረቀች፤ ነዋሪዋ ከሥራ በኋላ ‹‹ዎክ›› የሚያደርግበት፣ ስፖርት የሚሠራበት፣ ብስክሌት የሚነዳበት ወዘተ ታላቅ የህልም ከተማ ታቅዶ በ3ዲ ምትሃት ምስል በኮምፒዩተር ቅዠት የምናብ ገነት ልትሆን ዋዜማ በሚሰበክበት ጊዜ፣ እውነታው ነዋሪዎቿ የሚያለቅሱባት እንግዶቿ የሚዋከቡበት፣ ቱሪስቶቿ የሚታዘዙበት አድሏዊ አሰራር የነገሠበት ሆኖ እያየነው ነው።

ላቡን አንጠፍጥፎ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አይለፉ ለፍተው፣ አይሆኑ ሆነው፣ ወገባቸውን ለህመም፣ ኩራታቸውን ለዘመናዊ ባርነት ከፍለው ቆጥበው ‹‹አገሬ ላይ ያልፍልኛል›› ብለው መንግሥትን አምነው እንደ ታማኝ ታታሪ ገበሬ ገንዘባቸውን የዘሩት ዲያስፖራዎች፣ አመድ አፋሽ ሲሆኑ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የህልም ከተማ ምስል ጀርባ የሚታይ እውነት ነው።

ይህን ሁሉ ያስባለኝ ሰሞኑን በተከታታይ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በህብር ሬድዮ እና በዘሐበሻ ሚዲያ የተሟሟቀ ዜና ሆኖ በሰነበተው የአያት ሪል ስቴት ጉዳይ እና በአስራ ስምንት ወራት ወይም በዓመት ከስድስት ወራት ሥራው ተጠናቅቆ የሱቅ ባለቤቶች ተረክበው አገልግሎት ይጀምራሉ ስለተባለው የአያት የገበያ ማእከል ጉዳይ አንድ ለማለት ነው።
ለመሆኑ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባን እንለውጣለን›› ያለን መንግሥት፣ የከተማ አስተዳደር በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የታየውን ፈጣን ዕድገት መቼ ይሆን በአያት ሪል ስቴት ‹‹በአስራ ስምንት ወራት ያልቅላችኋል›› ተብለው አንድ መቶ አርባ አራት ወራት የሚጠብቁትን ግፉአን መፍትሄ የሚሰጣቸው? ብለን በምንጠይቅ ሰዓት፣ አስገራሚ ነገር ከአያት ሪል ስቴት በመስማታችን ነው ጉድ ያስባለን።

ጉድ አንድ
በአገራችን ከቀደምት ሪል ስቴቶች አንዱ ነው፣ አያት ሪል ስቴት። በምሥራቅ አዲስ አበባ ጫፍ ያለው ሰፈርም ሥያሜውን ያገኘው ከሪል ስቴቱ ነው። አያት መንደሮችን ቆርቁሮ መኖሪያ ቤቶችን ለመሥራት ከደንበኞች ጋር ተዋውሎ እና ተፈራርም ሥራ መጀመሩ ይታወቃል። ጅምሩ ያስመሰግናል። ደንበኞችን ለዓመታት ማጉላላት ግን ያስወግዛል።
የአያት ሪል ስቴት በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ2000 የከተማችንን ትልቁን እና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን 632 ሱቆች ያሉትን 10 ሺሕ ካሬ ሜትር ያለው የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ያለው ዘመናዊ የገበያ ማእከል በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ግንባታውን አጠናቅቄ ውሃ መብራት እና አሳንስር ገጥሜ ለአገልግሎት ዝግጁ አደርጋለሁ ብሎ ሙሉ ክፍያ ተፈፀመ። ከዋ በኋላ እነሆ ሱቆቹ አገልግሎት ሳይሰጡ አስራ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ምን ይሄ ብቻ! የገበያ ማእከሉ አገልግሎት ሳይሰጥ አርጅቶ በመፈራረስ ላይ ይገኛል።
የአያት ሪል ስቴት የሱቅ ባለቤቶቹን ገንዘብ ቅርጥፍ አድርጎ ወስዶ ሠራሁ ያለው ሕንፃ ውሃ እና መብራት የሌለው አንድ ተራ ህንፃ ሊያሟላ የሚገባውን መሰረተ ልማት ሊያሟላ ያልቻለ፣ ባይጀምር በሚያስብል ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ሪል ስቴቱ ግንባታውን በሰዓቱ ጨርሶ ባለማስረከቡ ምክንያት ቦታው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ የወንጀል መፈፀሚያ፣ አደገኛ ዕፅ ማጨሽያ፣ ሴቶች የሚደፈሩበት፣ በርካታ አፀያፊ ድርጊት የሚካሄድበት ስፍራ ሆኗል ተብሎ ተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦበታል። ሆኖም አያት ሪል ስቴት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል።
የአዲስ አበባ መስተዳደር ዝምታም ግራ ያጋባል። የቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለእነዚህ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በየደረጃው ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም።

የአያት ገበያ ማእከል 632 ሱቆች ለአስራ ኹለት ዓመታት ያለ መብራትና ውሃ መቀመጣቸው አገልግሎት መስጠት ስላቃታቸው የባለ ሱቆቹ ኪሳራ ሲሰላ ከአንድ ቢሊዮን ኹለት መቶ ሰማንያ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው። ወደ ሃምሳ ሚሊዮን የሚገመት የመንግሥት ገቢ አሳጥቷል።
ይህ ስሌት ከኪራይ እና አገልግሎት የ15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ እና የአራት ሺሕ ሠራተኞች የሥራ ግብርም እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ ኪሳራ እንደሆነም ይታወቃል። አያት ሪል ስቴት ታዲያ ይህንን ትልቅ አገራዊ፣ ኅብረተሰባዊ እና ግለሰባዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳጣት እንዴት ድፍረት ሊያገኝ ቻለ? የመንግሥት አካላትም እንዴት ይህንን አገራዊ ሻጥር እና ወንጀል ሊታገሱ ቻሉ? ያሰኛል።

ጉድ ኹለት
የአያት ሪል ስቴት የኮንትራት አስተዳደርና ደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ሰይድ ይመር፣ ከአበሻ ወግ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ለዚህ ሁሉ ግፍ፣ በደል እና ብሶት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው ሌላው አስገራሚ ጉድ ነው።

ጥያቄውን ስንመልክት እንደዘምኑ ፖለቲከኞች ሁሉ ድርጅታችው በቀድሞ መልካም ሥራዎቹ ላይ በመመስረት አያት አክስዮን ማኅበር ከተመሰረተ ከ1989 ጀምሮ ከምንም በመነሳት ጫካ የነበረውን ቦታ መንጥሮ በመለወጥ አኩሪ ተግባር የፈፀመ መሆኑን አወሱ።

ያለፈውን የትግል እና የድል ዓመታት ከገለጹ በኋላም ከ2001 እስከ 2008 የድርጅቱ መሥራች የቦርድ ሰብሳቢ ሥራ አስኪያጅ፣ የኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ፣ የፋይናንስ ሥራ አስኪይጅ በመታሰራቸው ችግር መፈጠሩንና አንጸባራቂው ድል መደብዘዙን ይነግሩናል። የግንባታው መዘግየት ምክንያት ይህ እንደሆነ ገልፀው ኃላፊው እስር ቤት የገቡበትን ምክንያት ባለፈው አንፀባራቂ የአያት ግንባታ ድል ቀባብተው ያልፉታል።

ነገር ግን ኃላፊው በእስር እያሉ የራስ ሆቴል ግዢ መፈፀሙን የነገሩን ሰይድ፣ ኃላፈዎቹ ባልተገለፀው ወንጀላቸው ቢታስሩም ድርጅቱም አብሮ የታሰረ ይመስል ለምን ይህን እንዳልነግሩን ጉድ አስብሎናል።

የአቶ ስይድ ነገር በዚህ ብቻ አላበቃም። ዛሬ በአስራ ሦስትኛው ዓመት ስለ መብራት ጉዳይ እያጠናቀቁ እንደ ሆነ ሲነግሩን፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለሥልጣን የምሥራቅ ዲስትሪክት ኃላፈው አቶ ገብሬ፣ አቶ ሰኢድ የሚፎክሩበትን አያት ሪል እስቴት 632 ሱቆች ላሉበት ግንባታ የ40 ቆጣሪ ብቻ መክፈሉ ‹‹አያት ሪል ስቴት አይመለከተውም። ሂዱና መብራት ኃይልን ጠይቁ›› ማለታቸውን እንዴት ያስታርቁት ይሆን?

12 ዓመታት ያለ መታከት እና ያለ መሰልቸት የሚሰነዘሩ የሚወረወሩ የሐሰት ምላሽ መቼ ይሆን የሚያቆመው? ያሰኛል። ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይላል የአገሬ ሰው። ከሁሉም የሚገርመው የአቶ ሰይድ ከመለሱት ደንበኞች ካቀረቡት ችግር ባሻገር እርሳቸው ስለ ሥራው መቀላጠፍ በምናባዊና በድራማዊ ልማት ካቀረቡልን ሁሉ ጉድ የሚያሰኘው መልሳቸው እንሆ፤
‹‹ለመሆኑ ቦታው የአደንዛዥ ዕፅ የሚጨስበት፣ ሴቶች የሚደፈሩበት፣ ልጆቻችን የሚበላሹበት ሆነ›› ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሱ ‹‹ፀጉር ቤት ልትሠራ የመጣች ልጅ ጓሮ ዞራ ዕፅ ብታጨስ አያት ምን ያድርግ?›› ማለታቸው ከዚያ ውጪ ተደፈሩ ስለሚባሉ ሴቶች ተጨባጭ ማስረጃ አለማግኘታቸውን ሲናገሩ፣ ዕፅ ያጨሰችው ልጅ ፀጉር ልትሠራ መምጣቷን ምን ተጨባጭ ማስረጃ አግኝተው ነው? ወይስ አብረው አጭሰው?

አያስብልም ትላላችሁ? ለዚህ ሁሉ ማህበራዊ ቀውስ ወንጀል መበራከት ተጠያቂው አያት ሪል እስቴት ነው አያሰኝም? የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት በክፍለ ከተማው የሚገኘውን ሕገ ወጥ ድርጊት መቆጣጠር መከታተል ሲገባው፣ አያት ሪል እስቴት እንደልቡ ዜጎችን እንዲበዘበዙና እንዲጨቆኑ ሲያደርግ የሱቅ ባለቤቶችን መብት ሊያስከብርላቸው አልቻለም።

መንግሥት እና ሕግ ያለበት አገር ይህ ሲፈፀም ያስገርማል። ሌላው ነገር አያት የገበያ ማእከል ባለሱቆች ማኅበር የሚጠበቅበትን ሥራ እየሠራ አለመሆኑ ይታያል። ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፊት ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ስብሰባ አካሂዶ አያውቅም። ለሱቅ ባለቤቶች ከአያት ሪል እስቴት ጋር የደረሱበትን ጉዳይ አያሳውቅም። እንዲሁ አለሁ ለማለት ያህል ቢሮ አለው እንጂ ተከፍቶ አያውቅም።
ማኅበሩ የቢሮ ፀሐፊ የለውም። የአመራሮቹም ስልክ አይነሳም። ይህ ማኅበር ለተገልጋዩ በየጊዜው የደረሰበትን ደረጃ መስጠት ሲገባው እንደ ማኅበር ከአያት ሪል እስቴትም ሆነ ከአዲስ አበባ መስተዳደር፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከማናቸውም መንግሥታዊ አካል ጋር የባለ ሱቆቹን ሕጋዊ መብት ማስከበር የሚችል ፤ የሱቅ ባለቤቶች አዋጥትው የሚከፍሉት ሕጋዊ ጠበቃ ሊኖራቸው ይገባል።

አሁን ይህ ባልሆነበት ‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም› ሆኗል። በበጎ ፈቃድ ማኅበሩን የሚመሩ አባላት የሥራ ጫና፣ የጊዜ እጥረት ካለባቸው ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ሪፖርታቸውን አቅርባው የደረሱበትን አሳውቀው በአንፃሩ ጊዜ ላላቸው ጉዳዩን መከታተል የሚሆንላቸው አባላትን መምረጥ እና መብታቸውን ጥቅማቸውን ማስከበር ይኖርባቸዋል።
ሌላው ግራ የሚያጋባው መንግሥታዊ አካል ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ያለው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ነው። ይህ ኤጀንሲ ተግባሩ እና ዓላማው ምንድን ነው? ለምን ዓላማ ነው የተቋቋመው? ተብሎ ሲታሰብ ኤጀንሲው በአዋጅ የተቋቋመው በውጪ አገራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከእናት አገራቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ ስለሚያጋጥማቸው አስተዳደራዊ እና ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች በተለይም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉትን መቅረፍ መርዳት እና መተባበር እንዲችል ነው።
በተግባር ሲታይ ግን ኤጀንሲው የዳያስፖራ ቀንን ለማክበር፣ ለፖለቲካ ጉዳይ ደፋ ቀና ሲል ከመዋል በስተቀር ዲያስፖራው በኢንቨስትመንት ጉዳይ ስለሚደርስበት ግፍ እና በደል መስሚያ ጆሮ የሌለው አካል ሆኖ ይታያል።

539 የሚሆኑ የአያት የገበያ ማእከል የሱቅ ባለቤት ዳያስፖራዎች በማኅበራቸው በኩል ለኤጀንሲው ከዓመት በፊት ያስገቡት የአቤቱታ ማመልከቻ ምላሽ በመንፈግ ውሳኔ መስጠት አቅቶት ይህንን ያህል ጊዜ መቆየቱ ምናልባትም የአያት ሪል ስቴት የሱቅ ባለቤቶች ላይ ከፈፀመው ግፍ እና በደል የሚተናነስ አይደለም። እንዲያውም የዳያስፖራ ኤጀንሲ ከእጀ ረጅሙ፣ ሕግ ከማይገዛው፣ መንግሥት ከማያዘው አያት ሪል ስቴት ጋር ጭራ ቆልፏል፤ እጅና ጓንት ሆኗል ያሰኛል።

እነዚህ ዳያስፖራዎች በየሚኖሩበት አገር ንግድ እና ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት የሚችሉ አምባሳደር ናቸው። ሙከራቸውን ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲበጥስባቸው ይህንን ‹‹ሀይ›› የሚል ኃይል አጥተው በከንቱ ትልቅ ዕምቅ አቅም አገራችን ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

አያት ሪል ስቴት በመንግሥት መወቀስ መጠየቅ ካለበት ወደ አገር ሊመጣ የሚችል ኢንቨስትመንትን በመግደል የአገር ገፅታን በማበላሸት፣ መንግሥት እና ሕግ የሌለበት፣ የኢንቨስትመንት መብት የማይከበርበት፣ ሥራ ፈጣሪዎች የሚበደሉበት እና የሚጉላሉበት፣ የኢትዮጵያን ምስል ማበላሸት ነው። ታድያ ይሄ ሁሉ ግፍና በደል፣ የባለሱቆች እሮሮ፣ የዳያስፖራ እንጉርጉሮ ማብቂያ መቼ ይሆናል ያሰኛል። አንድ የሱቅ ባለቤት በተናገሩት ቃል ጽኹፌን ላብቃ፤ ‹‹ከአያት ባርነት ነፃ የምንውጣው መቼ ነው?››

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com