የእለት ዜና

ይቅርታ ጠያቂ ይኖር ይሆን? ኃላፊነት የሚወስድስ?

በተደጋጋሚ በአገር ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ከመፍታት እንዲሁም በዘላቂነት ከማቆም አንጻር በመንሥት ዘንድ በሚወዱ እርምጃዎች የጎንዮሽ ጉዳቶች በሕዝብ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተግዳሮቶች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። በዚህም ረገድ በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነትን ወስዶ ይቅርታ የሚጠይቅ ባለመኖሩ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ይስተዋላሉ።

ጉዳዩ የተፈጠረው ከወደ ፀሐይ መውጫዋ አገር የትጉሀን መንደር በሆነችው የሩቅ ምሥራቋ አገር ጃፓን ነው። በጃፓን መዲና ቶኪዮ ታዲያ መነሻቸውን አድርገው ወደ ተለያዩ ጃፓን ከተሞች የሚወነጨፉ እጅግ ፈጣን እና ምቹ፣ ዘመናዊ ባቡሮች አሉ። በቅንጡ ባቡሮች ታዲያ ጃፓናዊያን በርካታ መቶ ኪሎሜትሮችን በየቀኑ እየተጓዙ ሠርተው መግባት የለመዱት እና የዕለት ተዕለት ተግባራቸውም ነው። እነዚህ ባቡሮች ታዲያ ጃፓናዊያን በራሳቸው ስብዕና የፈጠሯቸው እስኪመስል ድረስ ሽራፊ ሰከንዶችን ሳያዛንፉ ነው መንገደኞችን ለማጓጓዝ በእያንዳንዱ ጣቢያ ላይ ከተፍ የሚሉት።

የሆነው ሆኖ ታዲያ በአንድ ወቅት ከጃፓናውያን ቅልጥፍና እና ሰዓት አክባሪነት አንጻር ሲታይ እጅግ እንግዳ የሆነ ነገር ተፈጠረ። ሰርክ በተቀመጠለት ደቂቃ እና ሰከንዶችን ሳያጓድል ከተፍ እያለ መንገደኞችን በጉያው አቅፎ የሚወነጨፈው ባቡር ለሦስት ደቂቃ ያህል ዘገየ። አንድ ደቂቃ ተጠበቀ፤ ለውጥ የለም፣ ኹለተኛው ደቂቃም አለፈ በቃ! ጃፓናዊያን ተጨነቁ። ሦስተኛው ደቂቃ ሞልቶ ሰከንዶች እንዳለፉ ታዲያ ተናፋቂው ባቡር ከተፍ አለ።

ሰዓት አክባሪዎች፣ ሰከንዶች በሕይወታቸው ላይ ያላቸውን ጠቀሜታ ጠንቅቀው የሚያውቁት ጃፓናዊያን ከቅሬታ ወደ ቁጣ የቀረበ ስሜታቸውን መደበቅ ሳይችሉ ቀርተው በአደባባይ በመውጣትም ባቡሩን ለሦስት ደቂቃ የዘገየበትን ጉዳይ እንዲብራራላቸው መንግሥታቸውን ወተወቱ። ሥልጣኔ መቼም ደግ ነው! የጃፓን መንግሥት ሳይውል ሳያድር ነው የባቡሩን የሦስት ደቂቃ መዘግየት ምክንያትን መመርመር የያዘው።

በቀኑ መጨረሻ ለካንስ አንድ ባቡር ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ባቡሮች ነበሩ ዘግይተው ኖሮ፤ የተገልጋዮችም ቁጣ አይሎ ስለነበር ወደ ምክንያቱ የተሮጠው። አመሻሹ ላይ ታዲያ የጃፓን ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ወደ ሕዝብ በይፋ ቀርበው ለሦስት ደቂቃ የዘገየው ባቡር በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት በመሆኑ ሕዝባቸውን ይቅርታ ጠየቁ። ይቅርታ መጠየቁ አስገራሚ ጉዳይ ቢሆንም የጠየቁበት መንገድ ደግሞ ግርምትን የሚያጭር ጉዳይ ነበር። ለሦስት ደቂቃ የዘገየውን ባቡር ታሳቢ በማድረግ ለሦስት ደቂቃ በሕዝባቸው ፊት ከወገባቸው እጅግ ጎንበስ ብለው ነበር ይቅርታቸውን ያቀረቡት።

ይህን ጉዳይ በተለያዩ መንገዶች ከእኛ አኗኗር ጋር በማነጻጸር ከባድ እና ሩቅ ለሩቅ የሆንን እንደሆንን ለመታዘብ ታሪክ መጥቀስ እና መጽሐፍትን ማገላበጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ይህን ጉዳይ ያጫወተኝ ግለሰብ በሥራ አጋጣሚ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር እና ልዑካቸው በተገኙበት የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ምርቃት ላይ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ባቡር ጉዞ ባደረግንበት ወቅት ነበር።

ከጠዋቱ በኹለት ሰዓት አዲስ አበባ ለቡ የባር ጣቢያ የተነሳው ባቡር በኹለት ሰዓታት የመጎተት ሊባል በሚችል ፍጥነት ተጉዞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አንድ መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አዳማ ከተማ ላይ ተገኝቷል። ጉዞው ከባቡሩ መንቀራፈፍ እና በየደቂቃው እየጠነከረ ከሚሔደው ሙቀት ጋር ተዳምሮ ዝለትን ፈጥሮብን ነበር። ገና ከመጀመሪያውም በ1፡30 ጠዋት ላይ እንደሚጀምር የተነገረን ጉዞ ግማሽ ሰዓታትን እንደ ቀልድ አልፎ ነበር የተጀመረው።

እናም ታድያ ለዚህም ይቅርታ የጠየቀ ካለመኖሩም በላይ በተለይም ደግሞ ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ኢትዮጵያ ተወካይ ከሆኑት ለሰማይ ለምድር የከበሩት ሥራ ኃላፊ በርሳቸው ምክንያት ማርፈዳችንን ከቁብ ሳይቆጥሩት ግማሽ ሰዓታትን አርፍደው መጥተው እንኳን በጊዜ ስለመጡ ውለታ እንደዋሉልን እና ምስጋና እና ሙገሳም እንዲቸራቸው በሚመስል አኳኋን ነበር ሲገረምሙን የነበረው። አጀብ ነው መቼም የእኛ ነገር።

ይህን ጨዋታ ታዲያ ለማንሳት የተገደድኩበት ጉዳይ ከሰሞኑ የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በእኛ እና እነርሱ ፖለቲካ አራማጆች ከፍተኛ ጉዳት ሲከሰት እና ውድመት ሲፈጠር መመልከት አሳዛኝ ነገር ነበር። በዚህ ብቻ ሳይበቃን ጭራሽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላሟ በአንጻራዊነት ስትሞካሽ የነበረችው ሸገርም ሰኔ 23/2012 ስትናጥ ውላ ማደሯም አስገራሚ ጉዳይ ነበር።

ታዲያ ይህን እና ያን ጉዳይ ተከትሎ በርካታ እርምጃዎች ከመንግሥት ወገን ሲወሰድ ታይቷል። እርምጃውም እንደቀጠለ ነው። ከተወሰዱት እርምጃዎች ታዲያ ኢንተርኔትን ጠርቅሞ የትኛውንም አይነት ግንኙነት ማገድ ነበር። በእርግጥ ለአገር ደኅንነት እና ለሕዝብ ሰላም ሲባል የተወሰዱትን እርምጃዎች በመንግሥት በኩል ይበል የሚያሰኙ ጉዳዮች መሆናቸውን ያህል፣ መንግሥት ጥርስ ማውጣት ጀምሯል አስብሎን ልባችንን በተስፋ ሞልቶናል።

ግን ከኢንተርኔት መዘጋት ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ኪሳራስ ማነው ኃላፊነት የሚወስደው? ማነው እንደ ጃፓናዊው ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ወደ ሕዝብ ብቅ ብሎ ይህን ያህል ጊዜ ኢንተርኔት ያጠፋንባችሁ ለኹላችንም ጥቅም እና አገራዊ ደኅንነት ነው፤ በኢንተርኔት መጥፋት ሳቢያም ለተጋረጠባችሁ ችግር ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ የሚለን ሰው ማን ይሆን?
ኮቪድ 19 ከተከሰተ ወዲህ ሰው በቤት ውስጥ እንዲቀመጥ እና አስገዳጅ ካልሆነ በቀር ከቤት እንዳይወጣ የሚደረግበት አግባብ መኖሩን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ስንታዘብ ቆይተናል። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ይህን ትዕዛዝ የሚተገብሩ ግለሰቦች ወደ ውጭ በመውጣት የሚያስፈልጋቸውን ከመግዛት ይልቅ ኦንላይን ዕቃዎችን በማዘዝ ቤታቸው ድረስ እንዲመጣላቸው የማድረግ ጉዳይ እንዳለ ይታወቃል።

አካላዊ ንክኪን ከማራቅ እና ማኅበራዊ ፈቀቅታን ከመተግበር አኳያ ታዲያ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው ይኸው የኢንተርኔት ላይ ግብይት በአንድ አዳር ማስጠንቀቂያም ሳይሰጥበት ሲቋረጥ የኢሜይል ልውውጦች፣ የተጀመሩ ሥራዎች፣ ግብይቶች፣ ግንኙነቶች በአንድ ቅጽበት እንዲቆሙ ተገደዱ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት ቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረውን ሰው በመሉ ወደ ገበያ ሥራዎች በመውጣት ራሱን ለበሽታ አጋልጦ ግብይት አንዲያካሒድ ማስገደዱም አንደኛው ተግዳሮት ነበር።

እሺ! ታዲያ እንዲህ ላለው ችግርስ ይቅርታ የሚጠይቀው ማነው? በቃ የትኛውንም እርምጃ እየወሰዱ ጭጭ ዝም ማለት እንዴት ነው አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ የምናፋጥነው?

የመልካም ሥራ ጅማሮዎችን በመጥቀስ እና በሌት ተቀን በማሞካሸት ወደ ተሻለ ደረጃ ከማሳደግ ይልቅ የተሠራውን ሥራ እያሞካሹ ምስጋና ይገባናል አይነት ከበሮ ሲደልቁ መዋል አገርን እንደ አገር ሕዝብንም እንደ ዜጋ ጠንካራ አድርጎ ለመገንባት እጅግ ከባድ የሆነ መንገድ እየተከተልን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። መሪ ሕዝብን እንደሚመስል ሁሉ ሕዝብም መሪውን እንደሚመስልም ማሰብ ያስፈልጋል።

በተለይም ደግሞ ጥንካሬን ከመሪ ወደ ሕዝብ በማውረድ ጠንክሮ የሚያጠነክር፣ ተቋማትን ገንብቶ ማኅበረሰብን የሚያንጽ አመራር ያስፈልጋል። ጃፓናውያን ከብዙ መቶ ዓመታት የዝግመታዊ የማኅበረሰባዊ ልማቶች ዕድገትን አልፈው ነው አሁን የደረሱበት እና ያሉበት ደረጃ የደረሱት። የሠለጠነ ሕዝብ የሠለጠነ መሪን መፍጠር አያቅተውም።
ጃፓናዊያንም መብትና ግዴታቸውን በሚገባ ጠንቅቀው የሚያውቁ እና ለሚፈጠረው ችግር እና ለሚያጋጥመው ተግዳሮት ኃላፊነትን ወስዶ ይቅርታ የሚጠይቅ አካልን መፍጠር ችግሮች ተደጋግመው እንዳይፈጠሩ እና ትናንት የተቸገርንባቸው ነገ ደግሞው እንቅፋት እንዳይሆኑብን ማረጋገጫዎች ናቸው።

ይህ ባልሆነበት እና ኃላፊነትን ወስዶ ተጠያቂነትን በማያሰፍን ማኅበረሰብ ውስጥ ስንኖር፣ የዘፈቀደ ምልልስ እና ሕገ ወጥ እና ሀይ ባይ ያጡ ድርጊቶች ማስተናገጃ ሜዳዎች ከመሆን አንላቀቅም። ኢንተርኔት መዘጋት አሁን የተፈጠረ ጉዳይ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ከአንድም ኹለት ሦስት ጊዜ ዘለግ ላሉ ጊዜያት ተጠርቅሞ ቆይቷል።

በዚህ ወቅት ታዲያ በተፈጠረው ኢንተርኔት መቋረጥ እንደ መንግሥት ኃላፊነትን ወስዶ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት የደረሱ ኪሳራዎችን አስመልክቶ ኃላፊነትን በመውሰድ ይቅርታ የጠየቀ ባለመኖሩ፣ ይኸው ዛሬም ተመሳሳይ ችግር እየተፈጠረ የማይለቅ አዙሪት ውስጥ ገብተን ስንዳክር እንገኛለን። ለመሆኑ መቼ ነው ይህ ጉዳይስ የሚቆመው? አሁንም ኃላፊነቱን ወስዶ ይቅርታ የሚጠይቅ የሠለጠነ የሥራ ኃላፊ ከሌለ በቀጣይ ይህ ችግር ላለመፈጠሩ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለንም።

በጃፓን ስለ ተፈጠረው አጋጣሚ በተመስጦ ሲያወጋኝ የነበረው የጉዞ አጋሬ ታዲያ የኹለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በጃፓን ዮኮሐማ ከተማ እንደተከታተለ እና ወደ አገር ቤትም ተመልሶ በአንድ የጃፓን ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ለዓመታት መሥራቱን አወጋኝ። እንዴት ነው ግን ከጃፓናዊያን ጋር መሥራት ስልም ጥያቄዎችን ሰነዘርኩለት። በጃፓናዊያን ዘንድ አንድ ደቂቃ የዓመት ያህል ዋጋ እንዳላት ሲነግረኝ በመገረም ነው ሳደምጠው የነበረው።

በተቻላቸው መጠን ችግርን በመጋፈጥ እና መፍትሔ በመቅረጽ የሚያምኑ ሕዝቦች ሲሆኑ ኃላፊነትን በመውሰድ ለሚያጠፉት ነገርም ይቅርታን መጠየቅ እና በአጠፉት ጥፋትም በመጸጸት ከባድ ራስን መጉዳት ደረጃ ላይ በመድረስም የሚታወቁ ሕዝቦች እንደሆኑ አወጋኝ። እኔም ታድያ ምናለበት ባላቆመ እያልኩ ነበር የምሰማው። እንዲያው ጃፓናዊያንን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ በሌሎች አገራትም ላይ ይህን መሰል ይበል የሚያሰኙ ተግባራት አይታጡም።

እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? መቼ ነው የእኛ አመራሮች ወደ ሕዝብ ቀርበው ይህን እና ያንን ስለሠራን ይቅርታ እንጠይቃለን የሚሉን? መቼ ነው ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ የሚል የሥራ ኃላፊ የምናየው?

ኹላችንም በእኔን አይመለከትም ልክፍት ተይዘን የሚፈጠረውን ጉዳይ እንኳን ምን እንደሆነ ሳናውቅ ጉዳዮ እኔን አይመለከትም በሚል ምላሽ ስንቱን ቀላል ችግር መፍትሔ አልባ ጋንግሪን አድርገነው ቁጭ አድርገነው ይሆን?

በአጭር ለመቅጨት የሚያስችሉ ጉዳዮችን ከኃላፊነት በመሸሻችን ምክንያት ለትውልድ ሲተላለፉ ማየት እንዴት የሚያሳቅቅ ጉዳይ እንደሆነ የተረዳነው አይመስለኝም። ካለንበት ድህነት ለመውጣት የሥራን ባህል ለልጅ ልጅ ከማውረስ ይልቅ ባልኖርንበት እና ባልነበርነት ዘመን ወደ ኋላ ሽምጥ ገስግሰን ዘር ስናጠና እና ሀረግ ስንመዝ ለድህነታችን የምናቀርበው ምክንያት ደግሞ ያለፈውን ዘመን አገዛዝ ሲሆን እጀግ ይገርማል። ዛሬም እኛ ትውልድ ላይ ይብቃ ብለን ለሚቀጥለው የልጅ ልጆቻችን እንዳይተላለፍ ለማድረግ እንኳን አልሞከርንም።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com