ስመኘው እና ያልታዩ ገፆቹ!

Views: 361

እለተ ሃሙስ ሃምሌ 19 ቀን 2010 ማለዳ ላይ ነበር በአዲስ አበባ እጅግ አሰደንጋጭ እና ልብ ሰባሪ ኹነት የተከሰተው ፤ የኢትዮጲያውያውን የዘመናት ህልም እና ምኞት የሆነው የታላቁ ኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎለት የግንበታው ሂደት ተጀምሮ 60 ከመቶው የተሻገረ እስኪሆን ድረስ እንደ አደራ ልጅ ተቀብሎ አጠቃላይ ክንውኑን በበላይነት ሲመራ የነበረው መሃንዲስ ህልፈት ተሰማ።

ታላቅ አደራን የተሸከመው እሱነቱ በርትቶ አመታትን እንዳልተሸገረ ሁሉ በእዚያች ቀነ ጎደሎ ግን መስቀል አደባባይ ላይ ቆማ ከተገኘችው ወርቃማ ቀለም ያላት v8 መኪና ውስጥ አንገቱ እንደዘመመ ላይነቃ እስከወዲያኛው አሸልቦ ተገኘ።

ታዲያ በእንዲህ መልኩ ባልተጠበቀ ኹነት እና አጋጣሚ ግርታን በሚፈጥር መልኩ መሃንዲሱ በእዛች ተሸከርካሪ ውስጥ ህይወቱ አልፎ የመገኘቱ ነገር የበረከቱ መላ ምቶች ከግራ ቀኝ እንዲናፈሱ አደረገ።

እነዚህ መላምቶች እና ጥያቂ አዘል ነበሩ ፤ ለምን በእንዲያ መልኩ በምን ምክንያት መሃንዲሱ ህይወቱ አልፎ ሊገኝ ቻለ ? ማን ገደለው ? በምንስ ምክንያት ? የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ከግራ ቀኝ በብዙ ይናፈሱ ጀመር።

ከእዚህ አስደንጋጭ እና ልብ ሰባሪ ያልታሰበ ክስተት በኋላ ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው ፌደራል ፖሊስ በወቅቱ ኮሚሽነር በነበሩት ዘይኑ ጀማል እና በሌሎችም ጉዳዩን ሲከታተሉ በነበሩ የምርመራ ቡድን አባላት በኩል በተሰጠው መግለጫ ፤ በተደረገው የፎረንሲክ ምርመራ መሰረት ‹‹መሃንዲሱ በነበረበት ጭንቀት ምክንያት በገዛ ሽጉጡ እራሱን አጥፍቶ መገኘቱን አረጋግጠናል›› የሚል ነበር።

ለእዚህም ማረጋገጫ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ያለው የፌደራል የፖሊስ የምርመራ ውጤት እንደሚያስረዳው ከህልፈቱ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ቢሮው ደብዳቤ ፅፎ መገኘቱ ነው ሲል ፖሊስ አስረድቶ ነበር።

ይህ አሳዛኝ ክስተት ከተፈጠረ ጊዜያት ነጉደው ኹለት ድፍን አመታት ተቆጥረዋል ፤ ኢትዮጲያ ባላት የውሃ ሃብት ተጠቅማ የእድገት ጉዞዋን አደላድላ እንዳትሄድ የሚደርጉ እልፉ ጥልፍልፍ እና ፈተናዎች ቢገጥሟትም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ግን እነዚህን ፈተናዎች መሻገር ችላ እንዲሁም በአይበገሬው እና የበርሃ አንበሳ የሆነውን የስመኘውን አደራ ሳትሰንፍ በተባበረ ክንድ ተቀብላ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በታላቅ ድል አጠናቃዋለች።

ይህ ታላቅ የስኬት ጅማሮ ሲታወስ ለእዚህ ከፍታ ትልቁን ሚና የተጫወተው ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መነሳቱ የግድ ነው ፤ ለታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ‹‹ዛሬነት ትላንትና ላይ ከህይወቱ ቆርሶ ብዙውን ያካለፈለው ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ለስራው ታማኝ እና የጠለቀ አገራዊ ፍቅር ያለው ሰው ነበር›› ሲሉ የሚያነሱት አመታትን ከእርሱ ጋር ያሳለፉት የስራ ባልደረቦቹ እና እርሱን በቅርብ የሚያውቁት ናቸው።

ኢንጅነር ስመኘው የታላቁ ኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ትልቅ ምልክት ሆኖ ዘመናትን ከዘለቀ በኋላ ላይነቃ ያሸለበው ላይመለስ ያንቀላፋው እርሱ እና ግድቡ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገፅታ ሆነው በእኛነታችን ውስጥ ይዘልቃሉ እርሱን ማጣት ማለት መጥፎ ሰቀቀን ነው ሲሉ የሚያነሱት እነዚሁ ወዳጆቹ ናቸው።

ስመኘው ሚስጥሩን አውጥቶ የማያካፍል የበዛውን ጊዜም ከስራ ውጪ አንዳንዴ ካልሆነ በብቸኝነት ተጨምቶ ማሳለፍን የሚያዘወትር ነው ሲሉ የሚያነሱት ጥቂት የማይባሉት የሙያ አጋሮቹ እና በስራ አጋጣሚ ከእርሱ ጋር አብረው ያሳለፉት ናቸው።

በኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ጉዞ ከለውጡ በፊት እና በኋላ በነበሩት ጊዜያት በስራቸው ላይ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶች ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥረውበት እንደነበር፤ የሚያነሱት ከእርሱ ጋር በእጅጉ የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያነሱት አጋሮቻቸው ምንአልባትም ከለውጡ በፊት በስራቸው ላይ የነበረው አስተዳደራዊ ጫናዎች ከለውጡ በኋላ መታየታቸው በፈጠረበት ስሜት ከበቂ በላይ ጭንቀት ውስጥ ገብቶ እራሱን አጥፍቶ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል።

‹‹ስመኘው ሙሉ ህይወቱን ለስራው የሰጠ በስራውም ታማኝ የነበረ ሰው ከመሆኑ በላይ በጣም ተቆጪ እና አልፎ አልፎ የሚለዋወጥ ባህሪ አለው›› ሲሉ የሚያነሱት ከግልገል ግቤ አንድ አንስቶ እስከ ህልፈታቸው ጊዜ ድረስ በነበሩት 11 ዓመታት አብረዋቸው ያሳለፉት ያሬድ ግርማ የተባሉት በሲቪል መሃንዲስነት አሁንም በህዳሴው ገድብ እየሰሩ የሚገኙ ግለሰብ ናቸው።

ከኢንጅነር ስመኘው ጋር ከሌሎች ሰራተኞች በተለየ የላቀ ቀረቤታ እንዳላቸው እና ከስራ ውጪም ባሉት ጊዜያት አብረዋቸው እንደሚሳልፉ የሚያነሱት እኚሁ ግለሰብ ስመኘው ከህልፈቱ አንድ ወር በፊት ከእዚህ ቀደም የሌላቸውን እንግዳ ባሪያት ይመለከቱ እንደነበር አስታውሰው ይገልፃሉ ፤ ይህም እንግዳ ባህሪ ከህልፈታቸው አንድ ወር በፊት በጣም ረዥም ጊዜ ቀን እና ሌሊትን ጨምሮ ለብቻቸው በመሆን በጭንቀት ያሳልፉ እንደነበር ያነሳሉ።

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጠራጣሪ መሆንን ጨምሮ ቁጡነት እና ሌሎችም እንግዳ ባህሪያት ይታዩባቸው እንደነበር፤ የሚያነሱት ያሬድ የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዘለግ ላለ ጊዜ አዲስ አበባ ቆይተው አንደማያውቁ በማንሳት ከህልፈታቸው አንድ ወር በፊት ግን አዲስ አበባ መቆየታቸውን ይገልፃሉ። የሞታቸው እለት ወደ ግድቡ የሚያቀኑበት እና የሙያ ባልደረቦቻቸው እርሳቸውን ይጠብቁ እንደነበርም አስታውሰው አንስተዋል።
ከ1991 ጀምሮ የግልገል ጊቤ አንድ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በነበሩት 21 ዓመታት አብረን አሳልፈናል የሚሉት ሽፈራው ዳምጤ የተባሉት የስራ ባልደረባቸው ‹‹ ስመኘው ማለት ከሰው ጋር ተግባቢ በስራውም ትጉህ ከመሆን ባለፈ አሳታፊ እና ተባብሮ እና ተመካክሮ የሚሰራ ነው። ›› ሲሉ ገልጿቸዋል።
‹‹ከስራ ግንኙት ባለፈ ማህበራዊ ህይወት ላይ ንቁ ተሳታፊ ናቸው›› የሚሏቸው ሽፈራው ‹‹ በስራ አከባቢ የመደጋገፍ እና የመጠያየቁ ነገር ላይ ይሳተፋል ሰውንም ለማገዝ ሁሌም ቀና ልቦና ነው።›› በማለት ስለ በረሃ ጀግናው ኢንጅነር ስመኘው ወደ ኋላ ተጉዘው በመንፈስ እንጂ በአካል ስለ ማያገኙት የስራ ባልደረባቸው፣ ወዳጃቸው እና አለቃቸው ያነሳሉ።

‹‹መረጃዎችን አሰባስቦ በጥንቃቄ የመያዝ እና የማስቀመጥ ልዩ ልምድ አለው›› ሲሉ የሚያነሷቸው ሽፈራው ‹‹ሁሌም መረጃዎች በአግባቡ ተደራጅተው በጥቃቄ መቀመጥ መቻላቸው መጪው ትውልድ ካለበት አንዲያስቀጥል ያስችለዋል ›› ብለው ያምኑ አንደነበር ይገልፃሉ።

‹‹ለስራቸው ከሚታሰብላቸው ወርዊ ክፍያ ባለፈ አበልን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን መቀበል የማይሹ ስለ መሆናቸው ያነሳሉ። ከዛም ባለፈ የማልረሳው ስለእርሳቸው ያሉት ‹‹በአንድ አጋጣሚ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በግድቡ ዙሪያ ዘገባ ለመስራት ወደ እርሳቸው ዘንድ ቀርቦ ቃለ መጠየቅ እያደረገላቸው በነበረበት ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወደፊት ትልቅ ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል ነው ? ብሎ በጠየቀበት አጋጣሚ ስመኘው ቃለ መጠይቁን አቋርጠው ለጋዜጠኛው ‹‹ እንደምታየው በእዚህ ስፍራ ዶዘር እክካቫተር እና ሌሎችም የግንባታ እቃዎች እንጂ ጦር መሳሪያ የለም ምን አይተህ እንደዛ አልክ ብሎ በቁጣ አስቆመው›› ሲሉ ሽፈራው ስመኘውን ምላሽ ይናገራሉ።

ደግሞ በሌላ አጋጣሚ ይላሉ ሽፈራው ከውጪ ከቢቢሲ የተወከሉ ባለሙያዎች ከእርሳቸው ጋር ቆይታ ለማድረግ በመጡበት ሰዓት የካሜራ ባለሙያው አጠቃላይ የግድቡን ሂደት እና እንቅስቃሴ መቅረፅ ሲገባው በግንባታ ላይ ሳሉ በመጀመሪያዎቹ ሰሞናት ላይ የግንባታ ደህንነት መጠበቂያ ጫማ ያላደረጉ በነጠላ ጫማ የሚሰሩ ወጣቶችን እግር ለመቅረፅ ሲሞክር በተመለከቱበት አጋጣሚ በጣም ተበሳጭተው እንዳስቆሙት ‹‹ከእዚህ ግዙፍ እና ሊታይ ከሚገባው ፕሮጀክት ወርደህ ይኼን መቅረፅ ገፅታችንን ለማጠልሸት ካልሆነ ሌላ ምን ይረባሃል›› ብለው እንዳቋረጡት አንስተው አውግተውናል።

የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ቢሆኑ ‹የግድቡ መገንባት ግብፅ አይጎዳትም ወይ ? ታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ላይ ምን አይነት ጫና ይፈጥራል?› የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎችን እንደማይወዱ ከእዛ ይልቅ ‹‹በገዛ ሀብታችን እንዴት እንጠቀም ለህዝባችንንስ እንዴት እናሳልፍ የሚለውን አንሱ ያን ግብፃውያን አሊያም እኛ በሃብታችን እንዳንጠቀም የሚፈልጉ አካላት ይጠይቁ›› ይሏቸው አንደነበርም ሽፈራው ይናገራሉ።

ነገር ግን የሚሉት ሽፈራው እርሳቸውም እንደ ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው የሚሉትን እንደሚጋሩ እና የስራ ጫና ከበቂ በላይ እንደነበረበት፤ ከዛም ባለፈ የግድቡ እንቅስቃሴ መጀመርያ ከመጀመሩ በፊት በታሰበው ፍጥነት እንዳልሄደ ስለሚውቅ ፤ ከዛም በተጨማሪ ጥያቄ ማስነሳቱ ደግሞ እንደማይቀር ስለሚገመት የመሞቱ ዋዜማ ቀናቶች ከወትሮው ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ይስተዋልባቸው እንደነበር በትዝታ አንስተዋል።

‹‹ በስራ ላይ ጠንካራ እና ሁሉንም ኃላፊነት መውሰድ መገለጫው ነው››ሲሉ የሚያነሱት ለበርካታ ዓመታት በሹፌርነት ሙያ ከእርሳቸው ጋር ያሳለፉት አሸናፊ ነጋሽ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ እርሳቸው እንደሚሉት በቀደመ ጊዜ በጣም እርጋታ እና ብርቱ የስራ መንፈስ ይታይባቸው የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው የኋላ ኋላ ግን የበዛ እና ጎልቶ የሚታይ ጭንቀት እና መረበሹ ይገርመኝ ነብር ሲሉ ያነሳሉ።አብዛኘውን ጊዜ በስራ ሰአት ከስመኘው ጋር እንደሚያሳልፉ እና በዛም ለውጦቹን ላቅ ባለ ሁኔታ መታዘባቸውን አንስታዋል።

ከህልፈታቸው ኹለት እና ሦስት ወራት በፊት ባሉ ጊዜያት የመረጋጋት እና አእምሮን የመሰብሰብ ነገር ይታይባቸው እንዳልነበር፤ የሚያነሱት አሸናፊ በተለይ በመኪና ሲጓዙ እጃቸውን የማወራጨት ፤ ቴፕ ከፍተው በከፈቱበት ቅፅበት የመዝጋት ወይ መቀየር የመኪና መስኮት ከፍተው ድምፃቸውን ከፍ አድገርው የመጮህ እና ሌሎች እንግዳ ባህሪያት ይታዩበቸው እንደነበር አስታውሰው ተናግረዋል።

ስመኘው ባለፉበት ዕለትም ጠዋት ላይ ከሰዓታት በፊት ተገናኝተው እንደነበር የሚያነሱት አሸናፊ በሜቴክ ጉዳይ ላይ ስብሰባ እንደነበረ አስታውሰዋል። ሌሎች ሰዎችን ይዤ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ወደ ሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ሄድኩኝ ፤ እዛ ከደረስን ከጥቂት ደቂቃ በኋላ መስቀል አደባባይ ችግር እንደተፈጠረ እና መምጣት እንዳለብን ተነገረን። ከዛም ኹሉንም እንደ ቀሪው የኢትዮጲያ ህዝብ የሆነውን መስማት ጀመርን ይላሉ።

‹‹በአንድ አጋጣሚ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ይገኙ ከነበሩ የክልሉ የስራ ሃላፊዎች ጋር የነበረውን የስራ ቆይታ ካገባደደ በኋላ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ ጉዟችንን ወደጉባ ማድረግ ጀመርን›› እኚሁ አሽከርካሪ ያን አጋጣሚ አንስተው ይናገራሉ‹‹ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ የጀመርነው ጉዞ ጥቂት እንዳስኬደን ሸርኮሌ እየተባለ የሚጠራ ስፍራ ጋር ሰንደርስ የማሽከርክራት መኪና አንደኛው ጎማ ይተነፍሳል፤ በዚህ ጊዜ አጋጣሚው የተፈጠረው በእኔ የማሽከርከር ስህተት እንደሆነ የተረዳው ስመኘው እኔ ላሽከርክራት በማለት ተቀብሎኝ ጉዞ ጀመርን ጥቂት እንደተጓዝን ግን ሁለቱም ጎማ በመተንፈሱ ተደናገጥን ስፍራው ለደህንነት ምቹ ካለመሆኑ በላይ ምንም አይነት መኪና እንኳን የምናገኘት አልነበረም፤ የኋላ ኋላ ግን ቀርከሃ የጫነ የጭነት መኪና ሲመጣ እንዲያቆምልን ጠየቅነው፤ የነበረውን ነገር ለአሸከርካሪው ካስረዳነው በኋላ እንድንሄድ በፈቀደልን ቅፅበት ስመኘው እዛ ቀርከሃ ላይ ተንጠላጥሎ ወጣ ››ሲል ሳቅ በተሞላበት ድምፀት አጋጣሚውን ያጫውተን ጀመር ከእዛም የመኪናው አሽከርካሪ ‹‹ይህ ሰው አዲስ አልሆነብኝም አውቀው ይሆን ብሎ ሲጠይቀኝ የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪጅ እንደሆነ ስነግረው ረዳቱን አስወርዶ ቀርከሃው ላይ እንዲወጣ አድርጎ ስመኘውን ገቢና እንዲቀመጥ በማድረግ በስፍራው 14 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ወሰደው ለእኔም ቅያሪ ጎማ ተልኮኝ ከእዛ ስፍራ ልንቀሳቀስ ቻልኩ ›› ሲል ያጫወተን አሸናፊ ታዲያ ከእዚያ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በስራ ጫና እያሉ ሲያማርሩ ሲመለከት ‹‹እናንተ ስራ በዛ ጫናው አደከመን ትላላችሁ እኔና አሸናፊ ቀርከሃ ላይ ተጭነን ከባድ መንገድ ተጉዘን አልፈናል›› ሲል እያሳሳቀ ያቺን አጋጣሚ ያነሳት ነበር ሲሉ አጫውተውናል።
‹‹ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ትጉህ እና ታታሪ የስራ ሰው ከመሆኑ ከእዛም አለፍ ሲል ሳቅ ጨዋታ ወዳድነቱ በላይ ከፍ የሚለው ሰዋዊ እሱነቱ ለእኔ ትልቅ ቦታ እንድሰጠው ያስገድደኛል ›› ሲሉ ስለ እርሳቸው መናገራቸውን የሚቀጥሉት በአሽከርካሪነት የስራ ዘርፍ ከእራሳቸው ጋር የሰሩት አሸናፊ ባለቤት የመውለጂያ ጊዜዋ ደርሶ ሆስፒታል በገባችበት ሰዓት ፍቃድ አግኝቼ ወደ እርሷ መሄድ አለመቻሌ አስጨንቆኝ ነበር። እርሱን ሄጄ ሳማክረው በኔ ሃላፊነት ይሁንና ሄደህ ባለቤትህ ጎን ሁን ብሎ የሚያስፈልገኝን ሰጥቶ ከመሸኘት አልፎ ልጄ አድጎ ትልቅ እስኪሆን እንኳን ባለው ጊዜ ሁሌም እያስታወሰ ይጠይቀኝ ነበር ሲል በቅሬታ ስሜት ተውጦ ትዝታቸውን አካፍለውናል።

ለግድቡ መጓተት እና ይነሱ ለነበሩ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሻው እኔ ነኝ ብሎ በማሰብ የጥፋተኝነት ስሜት በተደጋጋሚ ይሰማው እንደነበር ያነሱልን አሸናፊ ከእዚህ ባለፈ ከህልፈታቸው አንድ እና ሁለት ወራት አስቀድሞ በነበሩ ጊዜያት ቅያሪ ልብሶችን በመኪና ውስጥ ይዞ ይንቀሳቀስ እንደነበር እነዚያን ታጥበው የተተኮሱ ልብሶቹን በመኪና ውስጥ ይቀይር እንደነበር ይገልፃሉ።

እስካሁን ያናገርናቸው እና የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ከሞቱ ኹለተኛ አመት መሙላቱን አንተርሰን ከጠየቅናቸው ቅርብ የሙያ አጋሮቻቸው የተገለፀልን ፤ትልቅ የኃላፊነት ስሜት እንደሚሰማው እና እያንዳንዷን ነገር በጥንቃቄ ይከውን እንደነበርም ይገልፃሉ።

ሌላው ቢቀር ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል የመጡ ሰዎች በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት በሚያደርጉበት ሰዓት እርሱ ገለፃውን ማድረግ እንደሚመርጥ የተናገሩ ሲሆን የዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ሌሎች መሃንዲሶች ምንአልባት የተሳሳተ መረጃ ቢሰጡ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ከማሰቡ የተነሳ እንደሆነ ይገልፀሉ። የሕዳሴው ግድብ ለስመኘው እንደ ስለት ልጁ ለማንም የማያስነካው፤ በሞግዚት ዕጅ ጥሎት እንደሄደው ልጁ ተመልሶ እስኪያገኘው የሚሳሳለት አገሩ በኃላፊነት የሰጠችው ውድ አደራው ነበር።

ለዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ሙሉ ህይወቱን እንደሰጠ የሚያነሱት የሙያ አጋሮቻቸው በጠቅላላ ከህልፈቱ ኹለት እና ሦስት ወራት በተለይ ደግሞ አንድ ወር አስቀድሞ የቀደመ ሳቅ ጨዋታ አዋቂነቱ ሆነ የነበረው ተስፋ እና ጉጉት እየደበዘዘ ሔዶ ሃዘን ትካዜ እና ጭንቀት ይነበብበት እንደነበር ይናገራሉ። ግድቡ በታሰበለት ልክ ላለመሄዱ በቀደሙት አመራሮች የተፈፀሙ ስህተቶች በሙሉ የእኔ ናቸው ፤ በግድቡ ላይ ብዙ ተስፋ ያደረገው ህዝብ ይኼን ቢያውቅ የታሪክ ተወቃሽ ያደርገኛል በሚል የጥፋተኝነት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በብዙ ይታይበት እንደነበርም አጫውተውናል፡

እውን ሲሆን ይታይ የማይመስለውን እና ያለ ከልካይ ተጓዡን የአባይ ወንዝ ለአፍታ ገታ አድርጎ በእዛ መጠቀም እንዲቻል ታስቦ የተወጠነው ውጥን ዛሬ ላይ ፍሬ እያፈራ ይመስላል ፤ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ እና እስከ አሁን ድረስ ደግሞ 74 ነጥብ 5 በመቶ የግንባታው ሂደት ከግብ መድረሱ ለኢትዮጲያውያን ታላቅ ድል ነው።

ቀሪው ሩብ መሆኑ ደግሞ ሩጫው ላይ መበርታት ግድ እንደሆነ ማሳያ ናቸው ታዲያ እነዚህ ሁሉ ጉዞዎች ሲታወሱ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሚና ከፍ ያለ መሆኑ የቅርብ የሙያ አጋሮቻቸው አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com