ጉዞ ወደ ድል!

Views: 130

ድህነትን በተከፋችና ባዘነች እናት፣ በተጎሳቆለ አባት እንዲሁም በታረዘ ሕጻን መስለው ያስቀምጡታል። ከዚህ ቀደም በሲቄ አምድ እንዳነሳነው ሁሉ እናት በአገር ትመሰላለችና የአገርን ሐዘን በእናት ውስጥ እናያለን። አባት የቤቱ ምሰሶ ይባላልና ዋስትና ማጣትም በአባት መከፋት ውስጥ ይነበባል። ልጅ ወራሽና ተቀባይ ነውና በመታረዙ ውስጥ ከቤተሰቦቹ እናትና ከአባቱ፣ ከአገሩ ይቀበለው ጸጋ እንደሌለው እንደሆነ ሹክ ይለናል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ጉዞዋ ወደ ድልና አሸናፊነት ነበር። ደስታዋ ከአንድ ጀንበር የማይዘልቅ፣ ሻማዋ ከግማሽ ሌሊት የማያሻግር እየሆነ በየመሃሉ ቢጠፋባትም፣ ያለመሰልቸት ትውልድ ጉዞዋን ይቀባበላል። የእናትን እንባ ለማበስ፣ የአባትን ትካዜ ለማስቀረት፣ ልጅንም ከመታረዝ ለመታደግ ተደክሞላታል።

አሁን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቁ ጉዳይ ነው። የውሃ ሙሌት ተጀምሮ ከደረሰበት መድረሱም ቀላል የማይባል እርምጃ ነው። ይህ ወደ ድል የሚደረግ ጉዞ ነው። ነገሮች ሁሉ አበቁ፣ ኢትዮጵያ ዋንጫ ተቀበለች ማለት ግን አይደለም። የማጣሪያ ውድድር እንዳለፈ ሯጭ አንዱን ዙር አጠናቀቀች ነው።

ገና ብዙ ድል ልታደርጋቸው የሚገባ፣ ከግድብ ግንባታ በላይ ያስቸገሯት የአእምሮ ግንባታ ሥራዎች አሉባት። ዛሬም ሰው በብሔር ምክንያት ይሰደዳል፣ ይገደላል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት አገሩን እያፈረሰ ለየትኛው አገር እንደሚታገል ባይታወቅም፣ ወጣቱ በገዛ ቤቱ ላይ ድንጋይ በመወርወር ላይ ነው።

ሴቶችና እናቶች ከማንምና ከምንም በላይ የዚህ ጉዳት ዋነኛ ተቀባይ ናቸው። በራሳቸውም፣ በልጆቻቸውም ላይ መከራውን ደጋግመው ይቀበላሉ።
የሕዳሴ ግድቡ አንድም በጭስ ምክንያት እየተጎዳና እየጠፋ ያለውን የእናቶችን ዐይን መጠበቅና ማዳን፣ ከዛም መገላገል ነው። ከዛ በፊት ወይም ከዛ በተጓዳኝ የእናቶች እንባም መፍሰሱ እንዲቆም ስለሰላም ሊሠራ፣ አጥፊዎች በአደባባይ ፍርዳቸው ሊነገርና ሊገለጽ ይገባል።

የብሔር ግጭትን ለመፍጠር ዓላማ ያደረጉ ድርጊቶች፣ የሃይማኖት ጸብ ለማጫር የሚፈጸሙ የሰዎችን ሕይወት የማጥፋት ተግባራትን የትኛውም ሰብአዊ ነፍስ አትቀበልም። ይህ ድርጊት እንኳን ብሔርና ሃይማኖት ሊኖረው፣ ሰውነት እንኳ የለውም። እንደምናውቀው ደግሞ ሁሉንም ሰውነት ይቀድማል፤ ሰው መሆን ይቀድማልና።

በእነዚህ አጋጣሚዎች ግን በሴቶች ላይ ከባድ ጥቃቶች ይደርሳሉ። አስገድዶ መድፈርም እንዲህ ያሉ አጋጠሚዎችን ጠብቆ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን ብዙ ጊዜ ታዝበናል። እናም አገር እንደ አገር ወደ ድል በምታደርገው ጉዞ ውስጥ እነዚህ ትንንሽ ስብርባሪና እንዲሁ የሚያልፉ የሚመስሉ ችግሮች ስለታማነታቸው ከትልቁ እኩል ቆራጭና አጥፊ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ነገሬን የአቋም መግለጫ አስመሰልኩት! በድምሩ ግን ወደ ድል የሚደረግ የትኛውም ጉዞ እንቅፋት እንደማያጣው ቢታወቅም፣ መከላከል የምንችላቸውን ግን እንከላከል ነው። መንግሥትም በሥልጣኑና ባለው ኃይል ይህን እንዲያደርግ ይጠበቃል። ሕዝብ ቢያንስ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማቀበል በመቆጠብ፣ ባለማዳረስ፣ በጎ በጎውን በማሰብና ምክንያታዊ በመሆን አገሩን ሊያግዝ ይገባል።

ይህ ጊዜ አገርን የምናግዝበት ነው። የድል ጉዞ በአጠራሩ ከ‹ጉዞ› በፊት ድልን ያስቀደመ በመሆኑ እንጂ፣ የአልጋ በአልጋ ጉዞ አይደለም። ቢሆንም ቢያንስ ልናስተካክል በምንችለው ግን ልንጎዳ አይገባም። እናም እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ በአስተሳሰብ ምክንያታዊነት የታነጸ ትውልድን ገንብተን ‹የማያልፍ የለም!› ለማለት ያብቃን!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com