ኮቪድ 19 እና የኪነ-ጥበብ ምሽቶቻችን

Views: 279

በሰው ልጅ የእለት ተእለት የሕይወት መስተጋብርና ውጣውረዱ ውስጥ ልማትና ጥፋቱን፣ ሰናይና እኩይ ሀሳቡን፣ ተግባሩንም ሳቢና ማራኪ በሆነ መንገድ መልሶ ለሰው ይቀርብበታል፣ ኪነጥበብ። በዚህም ምክንያት ክስተትን፣ ኹነትን፣ ታሪክንም ጭምር በማይጠፋ አሻራ ለቀጣይ ትውልድ የማስቀረት አቅም ካላቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሆኗል። በኪነ-ጥበብ የማይዳሰስ እሳቤ የማይነካ ጉዳይ የለም።

ታድያ በጥበብ ሀብት በታደለችው በኢትዮጵያ፣ ኪነጥበብ በክውን ጥበባት በባህል ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች እንዲሁም ወቅትን ጠብቀው ከሚደረጉ ትውፊታዊ ክዋኔዎች አልፎ፣ በአዳራሽና በድንኳን ጥላ ስር መካሄድ ጀመረ። ለዚህም ጥንስስ የሆኑ የጥበብ ወዳጆችና የጸሐፍት ደራስያን መጠነኛ ስብስብና ማኅበር እንደሆነም ብዙዎች ይናገራሉ።

ይህንንም ጊዜ ተሻግሮ በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እነዚህን መድረኮች በማጠናከር፣ የተወሰኑ ሊቃውንት የሚሰባሰቡበት የነበረውን ብዙኀኑም የሚታደምበት ጭምር እንዲሆን አደረጉ። እኚሁ የጥበብ ሰዎች እርስ በእርሳቸው መማማሪያ ይሆነናል ብለው የፈጠሩትን መድረክ አሳድገው፣ ለብዙዎች ሥራቸውን የሚያቀርቡበት፣ መልእክት የሚያስተላልፉበት አውድ አደረጉት።

ጦቢያ ግጥምን በጃዝ፣ ብራና የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ ሰምና ወርቅ የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ ማምሻ (በነረድኤት ተረፈ)፣ ትዝብት (በኪነ-ዘንባባ አዘጋጅነት)፣ በምስክር ጌታነው የሚዘጋጅ ወርሃዊ የዲስኩርና የሥነ ጽሑፍ መድረክ…ሌሎችም እውን ሆኑ። አልፎም በትዕይንተ መስኮቶች ብቅ ብለው በአካል ላልታደሙ ‹አለን› አሉ። እያደረ ባለሙያውንም ከተደራሲው ጋር እንደ ድልድይ ሆነው ሲያገናኙና የብዙዎችን የጥበብ መሻት ሲያረኩ መመልከትም የተለመደ ጉዳይ ሆነ።

እነዚህ የኪነ-ጥበብ ምሽቶች ለወጣቱ ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ ከመሆናቸውም በላይ የሐሳብ አድማሳቸውን እንዲያሰፉና መልካም ያሉትን በማወደስ የሚቀበሉበት፤ የሚነቅፉትን በሀያሲ መነፅር የሚገመግሙበት መድረክ ነው። ይህን የመሰለ መድረክ ነው እንግዲህ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ታጉሎ ለወራት ሳይከናወን የቀረው።

ገጣሚት ምሥራቅ ተረፈ የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ዋና አዘጋጅ ናት። ለዐስርት ዓመታት በመድረክ የቆየው ጦቢያ ግጥምን በጃዝ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ታዳምያንን እያስተናገደ አይደለም። ነገር ግን ፕሮግራሞችን ያለታዳሚ እያዘጋጁ እንደሚገኙ እና መደበኛ የግጥም ምሽቶች አለማቋረጣቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸችው።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከዐስር በላይ የሚሆኑ የኪነጥበብ ምሽቶች ይከናወኑ እንደነበር ያወሳችው ምሥራቅ፣ እንደ ጦቢያ ያሉ እንዲሁም ተመሳሳይ በሆኑ መድረኮች ላይ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ የሚተዳደሩ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የሚባል ችግርን አስከትሎባቸዋል ትላለች። አቅራቢዎች ብቻ ሳይሆኑ እነዚህንም ምሽቶች ይታደም የነበረው የኅብረተሰብ ክፍልም በዛው ልክ ተጎድቷልም ባይ ናት። መድረኮቹ ሐሳብ ለመቀባበልና ለማንሸራሸር ሲያገለግሉ ኖረዋልና፣ ይህ ሁኔታ የመረጃ ክፍተትንም ይፈጥራል ስትል ገልጻዋለች።

ከ1400 በላይ ሰዎች ይታደሙት የነበረው ጦቢያ ግጥምን በጃዝ፣ መሰናዶውን ወደ መገናኛ ብዙኀን በመውሰድ በየሳምንቱ እሁድ በ8 ሰዓት አርትስ ቴሌቭዥን ላይ እንዲተላለፍ ሆኗል። ቀረጻውም ተመልካች በሌለበት ነገር ግን ቀንና ሰዓቱን ጠብቆ እየተደረገ ይገኛል።

‹‹በቀጥታ ለመታደም እና ፕሮግራሞቹን በአካል ተገኝቶ ለመመልከት የሚፈልግ ሰው ግን እየመጣ አይደለም። ይህም [በቴሌቭዥን መታየቱ] ስሜቱ ሰው እንዳለበት አይሆንም። ባዶ አዳራሽ ውስጥ ነውና ቀረፃው እየተከናወነ የሚገኘው፣ የገጣሚው ወይም የኪነ-ጥበብ ሥራ አቅራቢው ስሜት ከታዳሚው ጋር አይጋባም።›› በማለት የተፈጠረውን ክፍተት ታስረዳለች።

ከዚህ ባለፈም ወቅታዊ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚፈለግው የስሜት ጠርዝ መልእክቶችና ሐሳቦችን ለማስተላፍ ሁኔታው ከብዷል። ምሥራቅ ደግሞ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገችው ቆይታ ነገሩን እንዲህ ስትል ገለጻዋለች፤ ‹‹የአባይ ጉዳይ መሰረታዊ ጉዳያችን ነው ብዬ አምናለሁ። አሁን ትላልቅ የኪነጥበብ መድረኮች ያስፈልጉን ነበር። በተለያዩ መድረኮችም ስለአባይ ጉዳይ መነሳት ነበረበት። ይህም በኮቪድ 19 ምክንያት ማድረግ አልተቻለም። ስለአባይም በፈለግነው መጠን እንዳንጮህ አድርጎናል።››

ሌላው ደግሞ ምሽቶቹ ወጪ የሚወጣባቸው እንደመሆናቸው፣ በአንጻሩም ገቢን ያስገኛሉና በዝግጅት ሥራው ተሳትፎ ለነበራቸው ለብዙዎች ገቢን ማንጠፉ አይቀርም። ምሥራቅም በዚህ ላይ ያለችው አለ። ይልቁንም እያንዳንዱ የጦቢያ ግጥምን በጃዝ መሳናዶዎች ስፖንሰሮች ነበራቸው ያለች ሲሆን፣ አሁን ግን ስፖንሰሮች መክፈል ስለማይችሉና የፕሮግራሙ አዘጋጆችም ሥራቸውን ለሚያቀርቡ ባለሞያዎች የሚከፍሉት ባለመኖሩ፣ ክዋኔውን መቀጠሉ ከባድ ሆኗል።

‹‹ከዚህ በፊት እየሠራን የነበረው በስፖንሰር እና በትኬት ገቢ ነበር። አሁን ግን ስፖንሰርም ሆነ የትኬት ገቢ የለንም። ስለዚህ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ በማይፈልጉ ሰዎች በተለይም የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ቤተሰቦች እንዲሁም አርትስ ቲቪ የራሱን ግማሽ በመቶ በመስጠትና ለአቅራቢዎቹ በመክፈል፣ ሥራው እንዳይቋረጥ ሆኗል። ተጋድሎ እያደረግን ነው የምንገኘው።›› ስትል አስረድታለች።

‹ብራና የኪነ-ጥበብ ምሽት› በጉዞ ሚድያ እና ማስታወቂያ የሚዘጋጅና ለኹለት ዓመታት በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ሲከናወን የቆየ ወርሃዊ የሥነ ጽሑፍና የዲስኩር ምሽት ነው። የዚህ መሰናዶ አዘጋጅ በፍቃዱ አባይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሰዎች መሰብሰብ እና አዳራሽ ውስጥ ዝግጅቶችን ማከናወን ሙሉ ለሙሉ ስለማይቻል ምንም ሥራ እየሠራን አይደለም። በአጠቃላይ ሥራው ቆሟል ማለት ይቻላል ብሏል።

በእነርሱም በኩል ታድያ ወደ ሕዝቡ ለመድረስ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀማቸውን ያነሳው በፍቃዱ፣ ‹‹አንዳንድ ሥራዎችን በዩ-ቲዩብ እና በሌሎች ቻናሎች ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ሞክረን ነበር። እሱንም በኢንተርኔት አገልግሎት መቆም ምክንያት ምንም አይነት እንቅስቃሴን ማድረግ አልቻልንም።›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ለኪነ-ጥበብ ምሽቱ ዝግጅት በብዙ መንገድ የሚሠሩ የነበሩም በተመሳሳይ ከኪነ-ጥበብ ምሽቶች መቋረጥ ጋር አብሮ ሥራቸው መረበሹን የጠቀሰው በፍቃዱ፣ ‹‹እኛ ጋር የሚሠሩ ገጣሚያን፣ ዲስኩር አቅራቢዎች፣ የሙዚቃ ባንዱ፣ አዳራሽ ኪራይና በአጠቃላይ ከስራችን የሚሠሩ ሰዎች በሙሉ፣ ሁላችንም ቢያንስ ለአምስት ወራት ሥራ ፈት ሆነን ነው ያለነው።›› ብሏል።

ሌላው ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን የሰጠው የሰምና ወርቅ የሥነ-ጽሑፍ ምሽት አዘጋጅ ጌታቸው ዓለሙ ነው። እርሱም ‹‹ኮቪድ 19 በመላው ዓለም የተከሰተ የጋራ ችግር፣ የጋራ ሕመማችን ነው።›› በማለት ንግግሩን ይጀምራል። አንድ ዓመትን የዘለቀው የሰምና ወርቅ የኪነ-ጥበብ ምሽት ሥራ ሲቆም፣ ከባላገሩ ቴሌቭዥን ጋር ሥራውን ለመሥራት ወጥነው እንደነበርም ጌታቸው ያወሳል።

‹‹ከባላገሩ ቴሌቭዥን ጋር ልንሠራ የነበረው ሥራ በጣቢያው ስርጭት ማቆም ምክንያት ቢቋረጥም፣ አሁን በአሀዱ ቴሌቭዥን እሁድ እሁድ ሰምና ወርቅ በባህል በኪነጥበብ እንዲሁም በንባብ ባህል ላይ ፕሮግራሞችን ለመጀመር እየሠራ ነው።›› ሲል ያሉበትን ሁኔታ ተናግሯል።

ከመድረክ የራቀ ከመጻፍ እንዳይርቅ!
አዲስ ማለዳ ለእነዚህ የተለያዩ ኪነጥበባዊ መሰናዶዎች አዘጋጆች ያቀረበችው ሌላው ጣያቄ፣ እነዚህን መድረኮች ታሳቢ አድርገው የሚጽፉ የኪነጥበብ ሰዎች ካሉ፣ ይህ ኹነት የመጻፍ አያርቃቸውም ወይ? አያናጥባቸውም ወይ? የሚል ነበር።

ምሥራቅ በዚህ ላይ አስተያየቷን ስትሰጥ እንደውም በተቃራኒ ነው የማስበው አለች። መጥፎ ጎኑ አይታየኝም ስትልም እንደሚከተለው አስረዳች፤ ‹‹እንደውም ደራሲ ትንሽ ሰብሰብ ብሎ ከራሱ ጋር የመሆኛ ጊዜ አግኝቷል። አሁን እኔ ለምሳሌ ለረጅም ጊዜ ውጪ ነበር የምውለው። ብዙ እንቅስቃሴዎች ነበሩኝ። አሁን ግን ሰብሰብ ብዬ ቤቴ ውስጥ ነው ያለሁት። በዚህ ምክንያት ተጠቃሚ ሆኛለሁ።›› ስትል ትገልጻለች።

አልፎም ይህ ዝምታ ጭር ያለ ጊዜ በደንብ ማስጻፍ ካላስቻለ፣ ጸሐፊነትንም ጭምር ያጠራጥራል ብላለች። ራስንና ዙሪያን እንደማዳመጫ ጊዜ ተወስዶ ደራሲን የማብቃት፣ የማንበብና የመጻፍ ክህሎቱን ለመጨመር ትክክለኛው ሰዓት ነው ስትልም ሐሳቧን ገልጻለች።

በፍቃዱ በበኩሉ፣ ይህ ነገር እንደ ሰዉ ይለያያል ባይ ነው። ‹‹ለማንበቢያ እንዲሁም ከራሱ ጋር መነጋገሪያ አልፎም ለመጻፊያ ጊዜ ያገኘ አለ። በዛው ልክ ደግሞ በኮቪድ 19 ምክንያት ትኩረቱን መሰብሰብ ያቃተውና ለመጻፍ ወይም ለመግጠም፣ ሥራዎችን ለመሥራት የተቸገረ ሰው ይኖራል። እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስዶት መጸሐፍ እስከማሳተም የደረሰ ሰው አለ። በንባብ ያሳለፈ እንደዛው ይገኛል።›› ሲልም ጥቅምና ጉዳቱ እንደ ግለሰቡ ነው በማለት ልዩነቱን አስረድቷል።

ከዛ ይልቅ ይህ ወቅት ካለፈ በኋላ በሚኖሩ ክዋኔዎች ላይ የሚቀርቡ ሥራዎችና ይህ ጊዜ ሲያልፍ የሚወጡ ሥራዎች ይህን የወረርሽኝ ጊዜ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ምን ያህል እንደተጠቀሙበት ሊነግረን ይችላል ብሏል። ‹‹ነገር ግን አዳዲስ ሥራዎችን ማግኘት ካልቻልንና አዳዲስ ሥራዎችም ሆነው የበሰሉ ካልሆኑ ጊዜያችንን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም በማለት መፍረድ እንችላልን። አሁን በዚህ ወቅት እንደዚህ ነው ብለን ውሳኔ ለመስጠት ግን የሚያስቸግር ይመስለኛል።›› ሲል ያስረዳል።

ጌታቸውም በዚህ ላይ ሐሳቡን አካፍሏል። በበኩሌ ጸሐፍያን ብዕራቸው አይነጥብም ሲል፣ ከዚህ ቀደም ሥራዎችን አብረውን [ከሰምና ወርቅ የሥነጽሑፍና ዲስኩር ምሽት ጋር] ይሠሩ የነበሩ ግጥሞችን፣ ዲስኩሮችን ወጎችን ያቀርቡ የነበሩ ትላልቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ዛሬም ድረስ አብረውን ነው ያሉት ብሏል። እንደውም እያገዙ በመሆናቸው ምስጋናውን በዚህ አጋጣሚ ቸሯል።

እርሱም እንደ ምሥራቅ ሁሉ ለጸሐፍያን መልካም አጋጣሚ ነው ሲል ገልጾታል። ‹‹ጎበዝ ለሆነ ሰው ይህ ጊዜ የጥሞና ጊዜ ነው። ምክንያቱም አሁን እንደምናየው በአገሪቷ የተለያዩ ጉዳዮች እየተከሰቱ ነው።›› ሲልም ተናግሯል።

‹‹ኮሮና ከነጥፋቱ መልካም ነገር እያሳየን ነው።›› ያለው ጌታቸው፣ አሁን እየታዩ ባሉ የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ ጸሐፊው ቁጭ ብሎ የሚመሰጥበት እና የሚያነብበት እንዲሁም ሥራዎቹን የሚከልስበት አጋጣሚ ነው ሲል ይገልጸዋል።

ለቀናት የተዘጋው ኢንተርኔት
በአካል መሰባሰቦች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት ሲባል ክልክል በሆነበት በዚህ ጊዜ ኢንተርኔትና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለብዙዎች ወሳኝ ሚና ነበራቸው። በአካል ማቅረብ ያልቻሉትን ሥራም ብዙዎች የዩ-ቲዩብ ቻናል በመክፈት ጭምር ለተደራሲያቸው ሲያቀርቡ ተስተውሏል።

ሠኔ 22 ቀን 2012 በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያትና እርሱን ተከትሎ በተፈጠሩ ቀውሶች ኢንተርኔት ተዘግቶ ለጥቂት ሳምንታት ቆይቷል። ይህም አገርን ሰላም ለመመለስ የተደረገ እንደሆነ ብዙዎች ቢስማሙም በተለያዩ ሥራዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል አልነበረም።

ምሥራቅ በዚህ ላይ ሐሳቧን ለአዲስ ማለዳ ስታካፍል፣ ጦቢያ ግጥምን በጃዝ ሙሉ መሰናዶው በማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የሚጫንና ሐሳቡንም በእነዚህ አውዶች ላይ ያደረገ ባለመሆኑ ጉዳቱ ብዙም አልተሰማቸውም። ዜናዎችናን የመሰናዶው መቃረብ ለማሳወቅ እንዳላስቻላቸወ ግን ጠቅሳለች።

በንግግሯም እንዲህ አለች፤ ‹‹ድሮም በምንጠቀማቸው የሚድያ ቻናሎች በሙሉ አሁንም እየተጠቀምን ስለሆነ እዚህ ላይ ብዙም ተግዳሮት አልገጠመንም። ነገር ግን ምናልባት ሌሎች እንደኛ ፕሮግራም የሚያዘጋጁ እና ፕሮግራማቸውን እንደኛ በቴሌቭዥን ማስተላለፍ የማይችሉ ሰዎች ድፍንፍን እንደሚልባቸው እገምታለሁ። ግን በአገር የመጣ ስለሆነ ይህንን እንቀበላለን።››

በአንጻሩ ነገሩ ከባድ እንደነበርና በጣም እንደፈተናቸው የገለጸው በፍቃዱ ነው። ‹‹ለእኛ በአጠቃላይ ሕይወታችን ነው የተቋረጠው ማለት ይቻላል። ቢሆንም ግን በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ እንረዳለን። በወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የኢንተርኔት መዘጋት ያስገኛቸውን ጥቅሞች በጣም በሚገባ ሁኔታ እንረዳለን፤ መዘጋቱንም እንደግፋለንም።›› ብሏል።

ኢንተርኔት መዘጋቱ ለአገር ሰላም አስተዋጽኦ ቢኖረውም እንደ ሥራ እና እንደ ባለሙያ ግን ምን ያህል ከባድ እንደነበር በፍቃዱ ያነሳል። በተለይም መረጃ የሚያደርሱት፣ የሚለዋወጡትና የሚነጋገሩት አልፎም ክዋኔዎችን የሚያሳውቁት በኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በተያያዘ መንገድ ነበር። ‹‹ነገር ግን…›› አለ፣ ‹‹ነገር ግን ከእኛ ከግለሰቦች ወይንም ከተወሰኑ ቡድኖች አገር ትበልጣለች።››

ቀጥሎ የተናገረውም ቃል በቃል እንዲህ ሲል ነው፤ ‹‹እኛም ነገሮች ተረጋግተው ሥራችንን እንድንሠራ በመጀመሪያ አገርና ሕዝብ ሰላም መሆን አለበት። የፀጥታ እና የደኅንነቱ ጉዳይ አስተማማኝ ሊሆን ይገባል።››

ጌታቸው በተመሳሳይ በዚሁ ጉዳይ ላይ ዕይታውን ለአዲስ ማለዳ ሲያካፍል እንደ በፍቃዱ ሁሉ ከአገር የማይበልጡ ጉዳዮች አሉ ብሏል። ኢንተርኔትን ለሥራ የሚጠቀሙ ሰዎች ተጎድተዋል፣ ግን በድምሩ አገር ስለምትቀድም በጉዳዩ ላይ ማማረር እንደማይኖርም ነው ያነሳው። ያለው አማራጭም ኢንተርኔቱ እስኪከፈት ድረስ መልካም ነገሮችን እየሠሩ ጉዳቱን አብሮ በመቃወም መታገል ነው ብሏል።

ምክንያቱን ሲያስረዳ እንዲህ አለ፤ ‹‹እንድንሻገር አገር መትረፍ አለባት፣ እንድንሻገር ትውልድ መኖር አለበት። ትምህርት ቤቶቻችንን የሚያፈርስ ትውልድ፣ የሀይማኖት ተቋማትን፣ ሰውንም በቁም የሚያቃጥል፣ ቤተ-መጽሐፍትንና የኽክምና ተቋማትን የሚያወድም ትውልድ ከፈጠርን፣ ሁላችንም ሥራ አለብን ማለት ነው።››

ቀጠለ፣ ‹‹ፌስ ቡክ የመጣው ለመልካም ነገር ነው። ዛሬ ግን በመልካምነቱ ሳይሆን በአጥፊነቱ የሚጠቀሙት ሰዎች ከበዙ ሁላችንም ተባብረን መቃወም አለብን። ይህንንም የምንታገለው ሜዳውን ከፍተውልን ነው እንጂ ዘግተውት አይደለም። ይሄ መንግሥትን የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉዳይ ሳይሆን ሕይወትን የማዳን፣ አገርን የማስቀጠል ጉዳይ ነው።››

ወረርሽኙን ከመከላከል አንጻር
‹‹ብዙዎች የኪነጥበብ መድረኮችን አስፈላጊነት በደንብ የተገነዘቡበት ወቅት ነው ብዬ አስባለሁ።›› ይላል በፍቃዱ። ይህንንም ያለው ከኹለት ነገሮች አንፃር እንደሆነ ያስረዳል። አንደኛ በኮቪድ 19 አንፃር ስንመለከተው ሰዎች አንድ ቦታ ላይ ተሰብስበው የኪነ-ጥበብ ዝግጅት መታደም እንደማይችሉ መረዳታቸው፣ ማኅበራዊ ግንኙነትም በመታጎሉ ጭምር የሚደርሰው የሥነልቦና ጫና ነው። በተያያዘም በየመድረኩ የሚተላለፉ መልእክቶች ምን ያህል ቁም ነገር እንደነበራቸው ማመላከቱ ነው።

ኹለተኛ ብሎ ያነሳው ነጥብ ደግሞ በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተከሰተው ሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ እነዚህ መድረኮች በጣም ትልቅ ጥቆማዎች የሚሰጡ እንደነበሩ ነው። ‹‹ለምሳሌ በእኛ መድረክ ላይ በሕግ አምላክ የሚል ምሽት ነበረን። በዛ መድረክ ላይ ሲቀርቡ የነበሩ መልእክቶች አሁን እየተከሰተ ያለውን ነገር የሚያጠይቅ ነው። በወቅቱ እርምጃዎች አለመወሰዳቸውንም ጭምር። ስለ አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሰብከናል። አንድ ባለመሆናችን ምን ያህል ዋጋ እየከፈልን እንደምንገኘኝ ይኸው አሁን መመልከት እየቻልን ነው።›› ብሏልም።

በድምሩም እነዚህ የኪነጥበብ ምሽቶች በጠቅላላው ሰዎቸ የሚዝናኑባቸው ብቻ ሳይሆን የሚማሩባቸውም ሐሳቦች የሚቀርቡባቸው እንደነበሩ መገንዘብ የተቻለበት ወቅት ነው ባይ ነው፤ በፍቃዱ። አክሎም ሲናገር ‹‹ስለሆነም አሁን ነገሮች እየተረጋጉ ሲመጡና በተለየም የኢንተርኔት አገልግሎት ሲጀመር ባለን አማራጭ ሁሉ ስለኮቪድ 19ኝም ይሁን በአገሪቷ ስለገጠመን ችግር በተመለከተ፣ አልፎም የጤና ዘርፍ አካላት የሚልኳቸው መልእክቶች ተግባራዊ የሚሆንበት እና ሕዝባችን ከኮቪድም ከፀጥታ ስጋትም ነፃ የሚሆንበትን መርሀ ግብሮች ለመዘርጋት ዝግጅቶችን አጠናቀናል።›› ሲል ይደመድማል።

ምሥራቅ በበኩሏ እንደግለሰብ የተባለችውን በመስማትና በመተግበር ላይ እንደምትገኝ በመናገር ጀምራለች። ‹‹የሕክምና ባለሙያዎች የሚሉትን በጠቅላላ እኔና ቤተሰቦቼ በተቻለ መጠን እያከበርን እና እራሳችንን እየጠበቅን እንገኛለን።›› ስትል ገልጻለች።

‹‹ነገር ግን እኔ ብቻ መሸሸጌና እኔ ብቻ ቤት ውስጥ መዋሌ ለውጥን አያመጣም።›› የምትለው ምሥራቅ፣ ሰውን ከቤት አትውጣ ማለት በተለይ በእለት ገቢ ለሚተዳደር ከባድ መሆኑን አውስታለች። አሁን ላይ ግን ቢያንስ አስቀድሞ የነበሩ የጥንቃቄ ተግባራት መዘንጋታቸውን በማውሳትም አስጊ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል ስትል ስጋቷንም ጭምር አካፍላለች።

‹‹ይህንን ለማስተካከል ሚድያ የራሱን ከፍተኛ ጫና ማድረግ አለበት። ሰዉ ስለበሽታው ግንዛቤ ሳይኖረው ቀርቶ አይደለም። ሁሉም ሰው ያውቃል። ግን ተግባር ላይ አያውለውም። ስለዚህ አስገዳጅ ነገር መኖር አለበት።›› ስትል ቁጥጥርና ክትትል እንዲጠብቅ፣ ያለምክንያት ከቤት የሚወጡ ሰዎች ካሉም ወረርሽኙን ለመግተት ሲባል በቤታቸው እንዲቆዩ ቢደረግ ስትል ምክረ ሐሳብ ሰጥታለች።

ጌታቸውም አለ፤ ‹‹እስከ አሁንም እየሠራን ያለነው በአባይ እና በኮሮና ጉዳይ ላይ ነው። ሁልጊዜም የተለያዩ መልእክቶችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለማስተላለፍ ጥረት እያደረግን ነው።››

ከበፊቱ ይልቅ አሁን ነበር ይበልጥ ማስተማር የሚገባው ያለው ጌታቸው፣ እጆችን መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅና መሰል ተግባራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ በነቂስ መሥሪያውና መቀስቀሻው ጊዜ አሁን ነበርም ብሏል። እንደ ኪነ-ጥበብ ባለሞያና እንደ ጋዜጠኛም ከኃላፊነት አንርቅም ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲል ተናግሯል።

በመጨረሻ ምሥራቅ መልእክቷን ስታስተላልፍ፣ እነዚህን አገራዊ ሥራዎች በጥበብ አማካኝነት ለመደገፍ ጥበባዊ ክዋኔዎች በተገኘወ አውድ አሁንም ሊደገፉ ይገባል ብላለች። አያይዛም አለች፤ ‹‹የኪነጥበብ ነው አገርን የሚለውጥ፣ ማኀበረሰቡን የሚያነቃቃ ነው። እናም እነዚህ ፕሮግራሞች እንዳይቋጡ መደገፍ ቢችሉ ተመልካች እንኳ ባይኖረው በተለያየ መንገድ በሚዲያው መጥተው እንዲተላለፉ ቢደረግ ሰውን ማንቃት ይቻላል። አሁን ግን ብዙ ሰው ድንዛዜ ውስጥ ነው ያለው ብዬ አስባለሁ።››

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com