በኮቪድ 19 ጫና ለደረሰባቸው ሆቴሎች የብድር መሰጠት ጀመረ

Views: 135

ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የገበያ መቀዛቀዝ የታየበትን የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ለመደገፍ ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው የብድር አገልግሎትን አንዳንድ ሆቴሎች መጠቀም መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር አስታወቀ።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል ብርሀኑ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በማኅበሩ ስር ካሉ 153 ሆቴሎች ውስጥ 131 የሚሆኑት ብድር አገልግሎቱን ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር የ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር ከብሔራዊ ባንክ መጠየቁን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሆቴሎቹን ለመደገፍ ከዚህ በፊት የ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የብድር ድጋፍ አቀርባለሁ ብሎ እንደነበር ያስታወሱት ዳንኤል፣ የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር የብድር አገልግሎቱን ለጠየቁ ሆቴሎች ብድሩ ለአንድ ዓመት እንዲሰጣቸው መጠየቁን አስታውቀዋል። ነገር ግን አሁን እየተሰጠ ያለው የብድር አገልግሎት የ6 ወር ስለሆነ 1 ነጥብ 1 ቢለየን ብር እንዲሰጥ ተጠይቆ፣ ለአንዳንድ ሆቴሎች ገንዘቡ እየተሰጠ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከ131 ሆቴሎች ውስጥ ምን ያህሉ ሆቴሎች ብድሩን እንደወሰዱ እና ምን ያህሉ ደግሞ እንደቀሩ ገና ጥናት እየተሠራ እንደሚገኝ የገለፁት ዳንኤል፣ ጥቂት ሆቴሎች ግን ብድሩን መውሰድ መጀመራቸውንም ጨምረው ጠቅሰዋል።

የብድሩ ዓላማ ለሆቴሎች ሠራተኛ ደሞዝ እና ሥራ ማስኬጃነት እንዲያገለግል ነው ያሉት ዳንኤል፣ ይህም የሚሰጠው ገንዘብ ሆቴሎቹ ለሠራተኛ ስንት ይከፍላሉ የሚለውን የደሞዝ መክፈያ መዝገባቸው ታይቶ እና በስድስት ወር ተባዝቶ እንዲሁም አማካኝ የወር ወጪያቸው ታይቶ እና ተሰልቶ እንደሆነም ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት ብድር የነበረባቸው ሆቴሎች አሁን ባለው ወቅታዊ የኮቪድ 19 ሁኔታ ምክንያት ብድሩን መክፈል ስለማይችሉ በልዩ ሁኔታ ባንኮች ደንበኞቻቸውን የመያዝ ስርአት በመዘርጋት፣ ወለድ በመቀነስ እና የእፎይታ ጊዜን በመስጠት የሆቴሎቹን የመክፈያ ጊዜን ያራዝማሉ ብለው እንደሚያስቡ ዳንኤል አያይዘው አንስተዋል። ቢሆንም የሆቴሎቹ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ሳይፈናቀሉ መቀጠል ስላለባቸው፣ መገልገያ እቃዎች መበላሸት ስለሌለባቸውና ጥገናም ስለሚያስፈልጋቸው ለእነዚህ ጉዳዮች የሚውል ደግሞ ብድር ይወስዳሉ ብለዋል።

በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራ እና የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር የሚሳተፍበት የምርመራ ቡድን ደንብ እና ስርአቱን እንዲሁም አዋጁን ከማስፈፀም አንፃር እነዚህን ሆቴሎች የሚቆጣጠር የምርመራ ቡድን መቋቋሙን ያነሱት ዳንኤል፣ ቡድኑ ባካሄደው ምርመራ ሆቴሎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሠሯቸው ስህተቶች ነበሩ፣ እነዚህን ስህተቶች እንዲያስተካክሉም ተነግሯቸው ያስተካከሉ መኖራቸውን ገልፀዋል።

አሁን ደግሞ ከዚህ ከባንክ ብድር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይኸው የምርመራው ቡድን እያየና ምክረ ሐሳብ እየሰጠበት ይገኛል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች በወረርሽኙ ምክንያት ከባድ ጫና ውስጥ መግባታቸውን እና ጫናውን ተቋቁመው እንዲሁም የተፈጠረውን አስቸጋሪ ጊዜ ሠራተኞቻቸውን እንደያዙ መቀጠል እንደሚቸግራቸው በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

በተለይም ደግሞ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የተካተተውን የሠራተኛ ቅነሳ ክልከላ ወደ ጎን በማድረግም ሠራተኞቻቸውን የቀነሱ ሆቴሎች በአዲስ አበባ የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ውስጥ መኖራቸውንም አዲስ ማለዳ በቀዳሚ ዕትሞቿ በስፋት መዘገቧም የሚታወስ ነው።
የሆቴል ሠራተኞችም ከሥራ ገበታቸው መቀነሳቸውን ተከትሎ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች መዳረጋቸውም መዘገቡ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com