በኦሮሚያ የተከሰተው ግርግር በሐዋሳ ቤት አስወደደ

Views: 397

በሐዋሳ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ግጭት እና ኹከት ተከትሎ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ ሸሽተው በመግባታቸው የቤት ኪራይ እና የቤት ግዢ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳየ።

በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት የተፈጠረውን ኹከት እና ረብሻ ምክንያት በማድረግ ከሻሸመኔ እና ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ተፈናቅለው በርከት ያሉ ሰዎች ወደ ከተማዋ በመግባታቸው የቤት ኪራይ በአንድ ክፍል ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ ብር ልዩነት ማሳየቱን የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

እንደ ምንጮች ገለፃ ከሆነ በሐዋሳ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎች አዳዲስ መንደር እየሆኑ እንደሆነ ገልፀው፤ አብዛኛውን በሚባል ሁኔታ ከሻሸመኔ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ሐዋሳ መግባታቸው ታውቋል። በዛም ምክንያት ባለፉት ኹለት ሳምንታት በኪራይ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለውጥ ቢያሳይም፣ ሦስተኛው ሳምንት ላይ ለሚገቡ ሰዎች ምንም አይነት የሚከራይም የሚሸጥም መኖሪያ እንደሌለ እየተገለፀ እንደሆነ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሐዋሳ የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩት ከሆነ ከፍተኛና ድንገተኛ የኑሮ ውድነት እንደሚያሰጋቸው እና በከተማዋ የሰላም ችግር ሊፈጠር ይችላል ብለው እንደሚገምቱም ነው የተናገሩት።

ምንጮች ጨምረው እንዳሉት ወደ አዲስ አበባ መውጫ ጥቁር ውሃን ጨምሮ እንደ ዲያስፖራ ሰፈር ያሉ ሰፈሮች ሙሉ ግቢ ለመራየት በፊት ከነበረው ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን እና ከዚህ ቀደም ከ 6 ሺሕ እስከ 8 ሺሕ ብር ይከራይ እንደነበር አንስተዋል።

አያይዘውም እንዳነሱት ከዚህ ቀደም ሐዋሳ ላይ በነበረው ግጭት እና ግርግር ሰዎችም ቤቶችን ሸጠው የመሄድ ነገር እንደነበር እና ቤቶችም ተፈላጊነታቸው ቀንሶ የመሸጫ ዋጋቸው መቀነስ አሳይቶ ነበር።

አሁን ግን እንደ አዲስ የገዢዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እና ተፈላጊነቱ እጅግ መናር እየታየበት እንደሆነም ተናግረዋል። አክለውም አሁን በጣም ተፈላጊነቱ ብሶ የኪራዩም የግዢም ቤቶች ተሸጠው አልቀው የለም እየተባሉ እንደሆነ እንደሚታዘቡ አስረድተዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ምርጫ እና ማማረጫ ቦታ ስለሌላቸው በተባሉት ዋጋ እየገዙም ሆነ እየተከራዩ እየገቡ ነውም ብለዋል። ከዛም በተጨማሪ የተለያየ ዓይነት ሽኩቻ እና አለመግባባቶች እንዳሉ፣ ነገር ግን ከሻሸመኔ ከመጡት ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዋሳ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የኖሩት ሰዎች እንደ ሻሸመኔ አይነት ችግር ይፈጠራል ብለው እንደሚሰጉ የሚነሱ ጭምጭምታዎች አሉ ብለዋል።

በተያያዘም የተለያዩ መከላከያንና ልዩ ኃይሎችንም ጨምሮ በከተማው ላይ እንደተበተኑ እና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ምንጮቻችን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደሚታወሰው ሐዋሳ ከተማ የተለያዩ ጥያቄዎችን ስታስተናግድ መቆየቷ እና ከዛም ባለፈ ኢትዮጵያ ለውጡን ካስተናገደች በኋላ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ በተጋጋለ መልኩ በመነሳቱ ምክንያት የሐዋሳን ከተማ ጨምሮ ከ2010 እስከ 11/11/2011 ድረስ ለጥያቄው መልስ ይሰጠን በሚል ከፍተኛ የሆነ ቀውስን አስተናግዳ ነበር። ከዛም ኅዳር 10 ቀን 2012 ሲዳማ በድምፅ ብልጫ ክልል የመሆን ጥያቄዋ እስከተከበረበት ዕለት ድረስ ከፍተኛ ቀውስ ብሎም ከሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ተፈናቃይ እንደነበር ይታወሳል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ እነዚህን እና ሌሎች ከሐዋሳ ሰላም ጋር ብሎም ኅብረተሰቡ ስለሚያነሳቸው ቅሬታዎች አንስታ መልስ እንዲሰጠን ለማድረግ በተደጋጋሚ ለሐዋሳ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብትሞክርም፣ ማግኘት አልቻለችም።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com