የእለት ዜና

የግል ቢዝነስ ከመጀመራችን በፊት…

ብዙዎች በሌሎች ባለሀብቶችና ቀጣሪዎች ስር አልያም በመንግሥት ቤቶች ተቀጥረው ከመሥራት ይልቅ የግል ሥራ መሥራት አዋጭም ተመራጭም እንደሆነ ያስባሉ፤ ያምናሉም። አብርሐም ፀሐዬም ይህንኑ ሐሳብ አንስተው፣ እንዲህ ያለ የግል የንግድ ሥራ ለመጀመር ሐሳብና እቅድ ያላቸው ሰዎች ወደ ሥራው ጠልቀው ከመግባታቸው በፊት ትኩረት ሰጥተው ሊያጤኗቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦች አካፍለዋል።

ይህ ክፍለ ዘመን እንደመታደልም እንዳለመታደልም ሆኖ የሕይወት ሩጫው አድካሚ ሆኗል። በቅጥር ሥራ ላይ ያለንም ሆንን የመተዳደሪያ ገቢያችን እምብዛም ለሆነብን ሰዎች አል ያም ደግሞ ሥራም ሆነ ገቢ አለን ብለን ለማውራት የማንደፍር ሰዎች፣ አንድ ያቀድነው የገቢ ምንጭ ይኖራል። ይኸውም ቢያንስ ራሳችን የምንሠራው ወይም የምንመራው የንግድ ሥራ ሲሆን፣ ይህ የግል ሥራ እንዲኖረን በመፈለግ የምናሰላስለው ወይም የምናቅደው የቢዝነስና የንግድ ሥራ ውጥን አለ።

በመሆኑም ይህ የንግድ ሐሳባችን እንዲተገበርና ውጤታማ እንዲሆን ከፈለግን የውሳኔ ሰጪነት ብቃታችን ሊዳብር ይገባል። ብዙ ነገርን ልንመኝ እንችላለን። ትልቅና የተሳካለት የንግድ ሰው መሆን አንዱ ነው። ወይም ደግሞ መለስተኛ ገቢ ያለው መጠነኛና የተስተካከለ አኗኗርን የማሰብ፣ ከፍ ሲልም ደግሞ የተትረፈረፈ ሀብት ባለቤት ሆነን ለሌሎችም ጭምር የመርዳት ሕልም ሊኖረን ይችል ይሆናል።

ሥመ ጥር የንግድ ተቋማት ባለቤት የመሆን ውጥን አስቀምጠንም ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሐሳቦች ደግሞ በምን መልኩ ሊሳኩ እንደሚችሉ ማወቅና ወደ ውሳኔ መግባት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለይቶ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው። በተለይም ራስን የት ጋር እንዳለን መለየቱና ያለንን ዝግጁነት መመዘኑ የተሻለ ነው።

ስለሆነም ትልቅም ይሁን መለስተኛ የንግድ ሰው ለመሆን ለምናስብ በተለይም ጀማሪ ለሆንን ሰዎች መሠረታዊ እና ትኩረት መስጠት የሚገቡንን ጉዳዮች እንመልከት።

ምርጫዎችን ማጥበብ
ሰው ማለት የሚመርጠው ነገር ግራ እስኪገባው ድረስ በርካታ ግራ አጋቢ ምርጫዎች ውስጥ የተጣለ ምስኪን ፍጡር ነው። ፍላጎቱም በዛው መጠን የሚቀያየርና ብዙ ሊሆን ይችላል። በኹለት ዐይናችን ከኹለት በላይ፣ በኹለት ጆሮአችን ከኹለት ነገር በላይ እንድንሰማ ቢፈቀድም ሁሉም ግን አይጠቅምም የሚል መርህ አለ።

እዚህ ላይ ቆም ብለን ልንመለከትና ልናደምጥ በስተመጨረሻም የተሻለውን በመምረጥ ልንወስን ይገባል። ስለዚህም ያየውን ሁሉ የሚያባርር አንዱን አይዝምና በንግድ አካባቢ ካሉት በርካታ ምርጫዎች መካከል አበጥረን የተሻሉትን በመምረጥ ከኛ አቅምና ፍላጎት፣ እንዲሁም የአዋጭነትና የተፈላጊነት ደረጃውን በማመዛዘንና በመለየት የምንገባበትን የንግድ ዓይነት መወሰን ግድ ይላል።

አዋጭነት
አንድ ልብ ልንለው የሚያስፈልገው ጉዳይ የምናየው ሁሉ ወይም ዝናውን የምንሰማለት የንግድ ዓይነት በሙሉ ይሆነናል ማለት አይደለም። አዋጭነቱን ማስላት ግድ የሚሆንበት የመጀመሪያው የመረጃ ማሰሻ ቦታ ሊሆን ይገባል። ‹ለመሆኑ ይህ የምጀምረው ንግድ ምን ያህል አዋጪ ነው?› ብሎ ራስን መጠየቅ ለትክክለኛ እርምጃ ጅማሬ ነው።

ይኸውም ሊያተርፈን ከቻለ በምን ያህል መጠን፣ ኪሳራ የሚባለውስ እስከ የትኛው ዝቅታ ድረስ ይሆን? ለሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ከወዲሁ ተጨባጭ መልስ መፈለግ ይገባናልና ነው። ስለሆነም ያለበቂ መረጃ ዘው ላለማለት ሲባል ቀድሞ ዙሪያ ገባውን ለማጥናት መወሰን፣ ያንንም ተግባራዊ ማድረግ ተመራጭ ነው።

ግምገማ
አንድን ውሳኔ ለመወሰን ምን ያህል ጊዜ ሊወስድብን ይገባል? የምንወስነው ውሳኔስ በሕይወታችን ላይ የምንፈልገውን ያህል ተጠቃሚነት ማምጣት ይችላል ወይ? በእነዚህ ኹለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አዋጭ የምንለውን የግል ሥራ ከመረጥን በኋላ ወደ ድርጊት የመሸጋገር ቆራጥ ውሳኔ ይጠበቅብናል።

የቸኮለም የዘገየም ኹለቱም ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ መሆኑ እሙን ነው። ስለዚህም ዐስር ቀን የሚፈልገውን በዐስር ዓመት እያዘገየን፣ ወይም ደግሞ ‹ቁጭ ከምልና ብሩ ከሚጠፋ ልሥራበት› በሚል ያልተገባና ኋላ ቀር አካሄድ ከመመራት ይልቅ ጥርት ያለና ወቅቱን የጠበቀ ግምገማ ያስፈልጋል።

የምንሰማራበት ንግድ ቀላል ወይም ከባድ ውሳኔ እንደሚሻ መለየት
የምንሰማራበት የንግድ ሥራ አንዳንድ ጊዜ ቴሌቪዥኝ ከፍቶ የማየት ያህል ቀላል ሊሆን ይችላል። አዲስ ነገር ፈጥሮ፣ አዲስ መሠረት ጥሎ “ሀ” ብሎ የመጀመር ያህል ጠንከር ያለና ፈተና ያለበት ሊሆንም ይችላል።

ቅለቱንና ክብደቱን የመመዘን አስተውሎት ያስፈልገናል። ይህንን ቀድሞ መለየት ከራሳችን የመሥራት ፍላጎትና ከሥራው ጋር አብሮ ለመቆየት ያለንን ጽናት ለመለካት ያስችለናል።

አንዲት ካልሲ ለመግዛት አስራ ስድስት ሱቅ የሚዞር ዓይነት ሰው ከሆንን የጊዜ ዋጋ አልገባንም፤ የውሳኔም ሰው አይደለንም ማለት ነው። ከባዱንም ጉዳይ ያለበቂ ዝግጅት በስሜታዊነት ፈጥኖ መጀመር አጉል መስዋእትነት ይሆናል። ስለሆነም አመዛዝኖና በተገቢው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወስኖ ወደ ሥራ አለመግባት በኋለኛው ዕድሜ ላይ ‹ወይኔ ያን ጊዜ ብጀምረው ኖሮ…› ከሚል ፀፀት አያድንም።

ምርጫችን የተጠና ውሳኔ ይፈልጋል
ወደ ግል ሥራ የመግባት ውሳኔ አዋጭነቱ፣ ምርጫዎቹ፣ ክብደትና ቅለቱን፣ እንዲሁም የሚፈጀውን ጊዜ መወሰን ያስፈልጋል ካልን እንዴት የሚለው ጥያቄም ወሳኝ ነው። ምንጊዜም ወሳኙ ጥያቄ ቢኖር ‹እንዴት?› የሚለው ነው። ትልቁ መልስም ይህንኑ እንዴት የሚለውን ጥያቄ መመለስ መቻል ነው።

ስለሆነም ልንጀምረው የፈለግነውን ንግድ ያውቃሉ ከምንላቸው ሰዎች መፈለግ የተሻለ ይሆናል። በጓደኛ ዙሪያ፣ ዘመድም ይሁን የሥራ ባልደረባ ጋር በመጠጋትና በመወያየት አልያም በጉዳዩ ላይ የሥራ ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች የማማከር ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢም ብልህነትም ነው።
ተጨባጭ ውጤት ያለው ጥናት ያስፈልጋል። ንግድ በስሜት የሚገባበት አይደለም። የስማ በለው ጥናት አልያም አጉል ድፍረት ከሆነም ራሳችንን ለኪሣራ አመቻቸን ማለት ነው። በተረፈ ይሄ ንግድ እንደሚያዋጣ አጎቴ ነግሮኛል፤ ጎረቤቴ ወይም ጓደኛዬ መክሮኛል እያልን ውሉ ባልተያዘ ሁኔታ ላይ ተመስርተን እንሥራ ካልን ከወዲሁ ውድቀትን ለማስተናገድ እንደወሰንን ማወቅ ይኖርብናል።

ውሳኔያችን በተጣራ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ
ልንጀምር ያሰብነውን ንግድ ስናጠና እያገኘን ያለነው መረጃ ተጨባጭ፣ የተሻለና እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንለይ። መረጃውን በመገምገም ከእኛ ሐሳብና ፍላጎት እንዲሁም ወደ ድርጊት ለመሸጋገር በሚያስችለን ደረጃ ላይ የሚያደርሰን ስለመሆኑ እርግጠኛ ከሆንን፣ ጥሩ የራስ መተማመንን ይፈጥርልናል። በዚህም ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንደሚያደርሰን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች አብዛኞቻችን ወደምንፈልገውና ወደሚያዋጣ የግል ሥራ ላይ ለመሰማራት ስናቅድ ከውሳኔ በፊት ልናስተውላቸው የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችና የማመላከቻ መንገዶች ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com