የእለት ዜና

የለውጥ ሐሳብ መነሻ ግለሰብ ወይስ ቡድን?

አዳዲስ ሐሳቦች፣ ፈጠራዎች፣ ግኝቶች ሁል ጊዜ ከግለሰባዊ ወደ ማኅበራዊ በሚደረግ ለውጥ የሚመጡ ኹነቶች ናቸው የሚሉት ፈቃዱ ዓለሙ፣ ስለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ለውጥ ከግለሰባዊ ነውጠኝነት የሚመነጨው በማለት ይሞግታሉ። አንድ ሰው ከራሱ አልፎ ተራማጅ የሚሆነው ከራሱ ምህዋር ወጥቶ ማሰብ ሲጀምር ነው በማለትም ተያያዥ ሐሳቦችን አጋርተዋል።

የዓለምን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ስናይ ግለሰቦችን ማእከል ያደረገ ሆኖ እናገኘዋልን። ስለለውጥ፣ ስለልማት፣ ስለነጻነት ስናስብ ዋና መዘወሪያው ግለሰባዊ ተራማጅነት ነው። ዶክተር ፈቃደ አዘዘ እንደሚሉት ብዙዎች እንደ አንድ ማሰብ፣ መልማት፣ መለወጥ የሚጀምሩት መጀመሪያ ‹ከሁሉም በፊት ግለሰቦች ራሳቸውን በመለወጥ፣ ከሁሉም በፊት ግለሰቦች ራሳቸውን በማልማት፣ ከሁሉም በፊት ግለሰቦች ራሳቸውን ነጻ በማውጣት ነው› ይላሉ። (መድበለ ጉባኤ፣ 2001 ዓ.ም፣ ገጽ 49)

በማኅበረ-ሥነ ባህሪ ጥናት የእያንዳንዱ ዜጋ እንቅስቃሴ፣ መብት፣ ሥነ አእምሯዊ እሳቤ ሲከበር የተራማጆች ቁጥር ከፍተኛ ይሆናል። ግለሰባዊ ነውጠኝነት ወይም ተራማጅነት ከሌለ ማኅበራዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ኪነ ጥበባዊ ልማት እንዲሁም የሂስ ባህል እያጠጠ ይመጣል። ሌላው የድርሰት ልማት ከተራማጅነት ጋር በጣም የተቆራኘ ነው። ብዙ የድርሰት ሥራዎች ከግል አልፎ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣት ይታወቃሉ።
እንደነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ እንደነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ እንደነ አቤ ጉበኛ፣ እንደነ በዓሉ ግርማ፣ እንደነ ሀዲስ አለማየሁ…የመሳሰሉትን ካየን የድርሰት ሥራዎቻቸውና አፈነጋገጣቸው ዘመኑን የቀደመ ነበር። ይሄም ብቻ ሳይሆን እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቡድን፣ ብሎም እንደ አገር በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘውጎች የለውጥ ዑደት መባጃ ነበሩ።

ማኅበራዊ አስተዋጽኦ
አዳዲስ ሐሳቦች፣ ፈጠራዎች፣ ግኝቶች ሁል ጊዜ ከግለሰባዊ ወደ ማኅበራዊ በሚደረግ መካኒካል ለውጥ የሚመጡ ኹነቶች ናቸው። ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ለውጥ ከግለሰባዊ ነውጠኝነት የሚመነጨው። እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ቡድን ኢኮኖሚ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ሥነ ልቡና፣ አካባቢ፣ ቤተ ሰብእ፣ በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶችና ቤተ እምነቶች ለተራማጀነት አስተሳሰብ የማኅበራዊ አስተዋጽኦ ምሰሶዎች ናቸው።

እነ ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ አልበርት አንስታይን፣ ካርል ማርክስ፣ ጄምስ ብሩስ፣ ናጅብ ማህፉዝ፣ ኑጉጊ ዋቲያንጎ፣ ማኦ፣ ቼጎቬራ፣ አብራሃም ሊንከን፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆነው የአረብ አብዮት እና ሌሎች እስከ አሁን ድረስ ያልተቋረጡ ማእበሎች ወይም ኹነቶች የሚያውጠነጥኑት በግለሰቦች ሐሳብ አመንጭነት ነው።
ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ አብዛኛው ማኀበራዊ ምሰሶዎች ግለሰባዊ ተራማጅነትን የሚያበረታቱ ሳይሆኑ ግለሰባዊ ንቃትን ወይም ነውጠኝነትን የሚያንኳስሱ ሆነው እናገኛቸዋለን። በተለይ ታሪኩ፣ ባህሉና ወጉ እንደ ቡድን መኩራራትን እንጅ እንደ ግለሰብ ተራማጅነትን አያበረታቱም። እያወቁ እንዳላወቁ መሆንን፣ ዝምታ መልካምነትን፣ ባህሉና ወጉ አይፈቅድም መባልን…እየሰማና እያየ ባደገ ማኅበረሰብ ውስጥ ግለሰባዊ ተራማጅነት እንደ ኋላ ቀር ወይም አፈንጋጭ ይቆጠራል። ደንቃራ ሆኖ መቆጠር ብቻ ሳይሆን “ነጠላ”፤ “ቆሞ ቀር” የሚል ፍርጃም አለው።

በቤተ ሰብእም ሆነ በአካባቢ ልጆች ጭምትና ራሳቸውን ሳይሆን ሌሎችን ተከታይ ሆነው እንዲያድጉ በሚመከርበት አገር ተራማጅነት ጋጠወጥነት ነው። የቤተ ሰብእና የአካባቢ ባህሎቻችን፣ ወጎቻችን ጥሩ የመሆናቸውን ያህል በተራማጅነት እሳቤ ካየናቸው ደንቃራነታቸው ያይላል።

አኩሪ ታሪክ ያለው ማኅበረሰብ ግለሰባዊ ተራማጅነትን ያበረታታል። ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ ታሪካችን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ከፍ ያደረጋትን ያህል በአገር ውስጥ ተራማጅና ለውጠኛ ትውልድ ሳይሆን በታሪኩ የሚኮሰምን ትውልድ እንዲፈጠር አድርጓል።

በትምህርት ዘርፍ የተሻለ ተራማጅ ትውልድ ተፈጥሮ ነበር ወይስ የዘመን ብልጭታ?፣ ለሚለው ጥያቄ ጥናትን መሠረት ያደረገ አመክንዮ ማቅረብ የግድ ይላል። ቢሆንም በኢትዮጵያ ታሪክ ከባህላዊ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ውጭ በዘመናዊ ትምህርት የመጣ ተራማጅነት ብለን ልንጠቅስ የምንችለው በ1960ዎችና በ1997 የተከናወኑ ዋቢ ኹነቶች ናቸው።

ይሄም በትምህርት ብቻ ሳይሆን በንባብ የታዘለ ቢባል ማጋነን አይሆንም። የአገራችን የትምህርት ፖሊሲና ሥርዓተ-ትምህርት ተራማጅነትን ወይም ንቁና ጠያቂ ትውልድን የሚያበረታታ ነው ወይ? መልሱን አሁንም ለአንባቢያን መተው ይቀላል።

በዚህ ዙሪያ አንድ የተረጋገጠ እውነት ያለው፣ በትምህርት ቤቶች የሚታየው የመምህርና የተማሪ ግንኙነት ተራማጅነትን ወይም ሐሳብን እስከ ጥግ የማቅረብና የመሞገት ባህል ደካማ እንደሆነ ማሳያ ነው። በትምህርት የሚገኝ ተራማጅነት አዳዲስ ሐሳቦችን የሚቀበልና የሚሞክር፣ በራሱ የሚተማመንና ለፍትሕና ለነጻነት መተግበር ዘብ የሚቆም ትውልድ እንዲፈጠር እድል ይከፍታል።

ሌላው በኢኮኖሚ ያልዳበረ ወይም ያልጠነከረ ማኅበራሰብ ውስጥ ግለሰባዊ ሐሳብ አመንጭነት ወይም ለውጠኝነት ይከስማል። በእርግጥ ከኢኮኖሚ ይልቅ ሥነ ልቡናዊ ጥንካሬ ለግለሰባዊ ለውጠኝነት ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ በባለአእምሮ ሰዎች ዘንድ ይታመናል። በድምሩ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተራማጅነት እንቅስቃሴ ጎልቶ እንዲታይ ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚ የዳበሩ ኃያላን አገራትና የግለሰቦች ተራማጅነት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል። የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትልልቅ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎች ውጤቶች የተገኙት በወጣት ተራማጅ ግለሰቦች አማካኝነት ነው። በአገራት መካከልም የጥንካሬ መለኪያ ከሚባሉት መካከል ኢኮኖሚ ዋና ምሰሶ ነው።

ልክ እንደ አገራት ሁሉ ሰዎች ከቀን ፍጆታና ፍላጎት ባለፈ ማሰብና መመራመር የሚጀምሩት ከዕለት ልብስና ከዕለት ጉርስ ሐሳብ ነጻ ሲሆኑ ነው። ኢኮኖሚያና ሥነ ልቡናዊ አስተሳሰቦች የሰው ልጆችን አንደበት ወይም አእምሮ የማሠር ከፍተኛ ልእልና አላቸው። አንድ ሰው ከራሱ አልፎ ተራማጅ የሚሆነው ከራሱ ምህዋር ወጥቶ ማሰብ ሲጀምር ነው።

ፖለቲካዊ ወይም መንግሥታዊ አስተዋጽኦ
ከርእዮት ዓለም መፈንጠቅ ቀደም ብሎ በነበረው የዓለም መንግሥታት የፖለቲካ ሥርዓት የገዥውን ወይም መደብን ማእከል ያደረገ ነውጠኝነት እንጅ ግለሰብን ማእከል ያደረገ አልነበረም። ይሁን እንጅ በሰው ልጅ የነጻነት ትግል ውስጥ የፖለቲካ ርእዮት/ አብዮት ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ ተራማጆችን በመፈልፈል የሚያኽለው የለም። እንደነ አንቶኒዮ ዲ ቲሬሲ፣ ካርል ማርክስ፣ ልዊስ አልዙስር፣ ማኦ፣ ቼጎቬራ፣ ፊደል ካስትሮ፣ እና የመሳሰሉ ተራማጆችን ርእዮተ-ዓለም የወለዳቻቸው ነውጠኞች ናቸው።

በተቃራኒው የፖለቲካ ርእዮት ብዙ ተራማጆችን የማፍራቱን ያህል ከማኅበረ-ሥነ ልቡናዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ርእዮት ለግለሰባዊ ተራማጅነት ደንቃራ የለም። በተለይ ከቅኝ ግዛት ቅሪት ያልተላቀቀው አብዛኛው የአፍሪቃ አገራት የአስተዳደር ሥርዓት ለነጻነት በሚደረገው ትግል ተራማጅ ግለሰቦችን በመዋጥ ሌሎችን አድርባይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በመሠረቱ ግለሰባዊ ለውጠኝነት መንግሥታት እንደ ሚከተሉት ርእዮተ ዓለምና ባህርያት እንዲወሰን ከሚያደርጉት ሰቃዥ ምክንያች ከላይ ያነሣነው የአፍሪቃ አስተዳደር ሥርዓት ይጠቀሳል።

ነጻና ዲሞክራት በሆኑ አገሮች ነውጠኝነትና ተራማጅነት እንደ አጋዥ የስኬት አጋጣሚ ሲወሰድ ፈላጭና ቆራጭ የሆነ የአገዛዝ ሥርዓት በሚከተሉ አገራት ለውጠኝነትና ተራማጅነት እንደ ባላጋራ ወይም ጠላት ይታያሉ። በኹለተኛው መንገድ አፍሪቃ እንደ አኅጉር የምትታወቅበት የጥላሸት ሥሟ ነው።

አፍሪቃ እንደ አጠቃለይ የብዙ ነገሮች ቤተ ሙከራ በመሆኗ ከተራማጅነትና ለውጠኝነት ጋር በተያያዘ ብዙ አደናጋሪና ውጥንቅጡ የጠፋ ኹነቶችን እንመለከትባታለን። ኢትዮጵያም ከዚህ ልክፍት አላመለጠችም። ፖለቲካ እንደ ኮረንቲ በሚቆጠርባት ኢትዮጵያ የፖለቲካ ርእዮት ወይም የመንግሥታቱ ሥርዓት ለውጠኝነትን ወይም ተራማጅነትን እንደ ባላጋራ ስለሚፈርጅ ፖለቲካዊ አስተዋጾው እርባና ቢስ ነው ማለት ይቻላል።

ምክንያቱም መንግሥታት የዜጎችን ወይም የግለሰቦችን መብት ሲያከብሩ ነው አፈንጋጭነት ወይም ተራማጅነት ከጠላትነት ይልቅ አጋዥ መሆናቸው የሚታመነው። መደማመጥ፣ መከባበር፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን የአገር ጠላት እንደሆኑ የሚቆጥር ሥርዓት፣ ሐሳብን በሐሳብ መሞገት ሳይሆን መፈራረጅን ባህል ባደረገ አገር ለውጠኝትንና ተራማጀነትን ሾከፍ የበዛበት ሲቃ እንዲሆን ያደርገዋል።

ግለሰባዊ ተስፋ-ቢስነት እየተስፋፋ የሚመጣው ሥነ-ልቡናዊና ፖለቲካዊ ምሰሶዎች የዜጎችን ልብ መስለብ ሲጀምሩ ነው። በአገሩ ፖለቲካ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሌለው ዜጋ፣ ግለሰቦች አሳቦቻቸውን ወይም በአገራቸው ጉዳይ ላይ ይሄ ይጎዳል ይሄ ይጠቅማል ካላሉና የኔነት ስሜት ከሌላቸው ምክንያተ ውጤቱ የፖለቲካ ንቅዘት ነው። ያም ሆነ ይኽ በዚህ ጥሎ ማለፍ በሆነበት ዘመን በኢኮኖሚያችን፣ በፖለቲካችን፣ በልማታችን፣ በነጻነታችን፣ በታሪካችን ላይ የሚሠለጥኑ ተራማጅ ነውጠኞች ያስፈልጉናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com