የእለት ዜና

የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ሊፈቀድ ነው

የሲሚንቶ እጥረትን ለማሻሻል እና እያደገ የመጣውን የሲሚንቶ ፍላጎት ከግንዛቤ በማስገባት የአዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንቶችን የሚከለክለውን ህግ መንግስት ሊያነሳ መሆኑ ታወቀ።

ረቂቅ የማሻሻያ ደንብ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ለንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት እና በቅርቡም በሚወጣው አዲስ የኢንቨስትመንት ደንብ ላይ እንዲካተት እየተሰራ መሆኑንም በኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብዓት የኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲቲዩሽን የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ጥናት እና ቴክኖሎጂ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ስመኝ ደጉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከጥቂት አመታት በፊት በአገር ውስጥ የሲሚንቶ ምርት እራስዋን የቻለችው ኢትዮጵያ ከኹለት አመታት ወዲህ ግን የሲሚንቶ እጥረትና የሲሚንቶ ዋጋ ግሽበት ሲፈታተናት መቆየቱ ይታወቃል። የመብራት አቅርቦት በፈረቃ መሆን፣ የፋብሪካዎች የመለዋወጫ እቃ እጥረት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ምርቱን የማጓጓዣ ትራንስፖርት እጥረት የሲሚንቶ ገበያውን ለስግብግ አከፋፋዮች አጋልጦት መቆየቱን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ከባለፈው ወር ጀምሮ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋን ጣልቃ በመግባት መወሰን የጀመረ ሲሆን አምስት የመንግስት የልማት ድርጅቶችም የሲሚንቶ ገበያውን እንዲቀላቀሉ አድርጓል። ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሲሚንቶ ኢንደስትሪዎችን ቁጥር እና የማምረት አቅም ማብዛት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።
በተለያዩ የቴክኖሎጂ እክሎች ምክንያት ከምርት የወጡ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ስመኝ በአሁኑ ሰአት በአጠቃላይ 14 ፋብሪካዎች በሲሚንቶ ምርት ስራ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ የሲሚንቶ ባህሪ ሁለት አይነት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ከእነዚህም ውስጥ አስር የሚሆኑት የክሊንከር የሚያመርቱ ሲሆኑ 4ቱ ደግሞ ክሊንከር እየገዙ የሚፈጩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የእነዚህ ፋብሪካዎች አጠቃላይ የማምረት አቅም 17.2 ሚሊየን ቶን በአመት ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ግን 8.4 ሚሊየን ቶን ምርት ብቻ እያቀረቡ ሲሆን ይህም የአጠቃላይ አቅማቸውን 57.8% ብቻ ነው።

የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት 10 ሚሊዮን ቶን ሲሆን ነገርግን በ10 አመቱ የልማት እቅድ ውስጥ በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል።
የኢንቨስትመንት ደንቡ ሲሻሻል ቀደም ብለው የማስፋፊያ ኢንቫስትመንት ለጠየቁት ለደርባና ለዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ፍቃድ የሚሰጥ ሲሆን ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ፍቃድ መስጠቱ እንደሚቀጥል ስመኝ ገልፀዋል።

ደርባ እና ዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው 2.5 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያላቸው ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በጥቅሉ ሁለቱ ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክታቸው 5 ሚሊየን ቶን የማምረት አቅምን ለማግኘትና ለማስፋፋት አብዛኛውን እቅዶቻቸውን ገና ከመጀመሪው ስራ ሲጀምሩ አያይዘው የሰሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

መንግስት የኢንቨስትመንቱን ደንቡን አሻሽሎ እንዲሁም አጠቃላይ የኢቨስትመንት ፖሊሲዎችን ከልሶ ማጠቃለያ ሲሰራ በቀጥታ ወደስራ እንዲገቡና ሌሎችም ይህን መሰል ሀሳብ ያላቸው ፋብሪካዎች ወደስራ እንዲገቡ ችግሩ እየተለየና የማሻሻያ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይህም የማስፋፊያ ፕሮጀክት የፋበሪካዎቹን የማምረት አቅም በሁለት እጥፍ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህንንም የማምረት አቅም መቶ በመቶ ማሳካት ባይቻልም አንድም ቀን እና ሰአት ሳይቆም አመቱን ሙሉ ማምረት ከተቻለ የእቅዱን ከ80 እስከ 85 በመቶ ማሳካት እንደሚቻልም አስታውቀዋል
ከሁሉም በፊት የአገር ውስጥ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገር ውስጥ ገበያ ሲሚንቶን በብዛት ለማቅረብ እየተሰራ ስለሆነ የሲሚንቶ ኢንፖርት አለመጀመሩን አስታውቀዉ ሁሉም ፋብሪካዎች ደረጃውን የጠበቀ ምርትን እንዲያመርቱ ለማድረግ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com