የሕወሃት ክልላዊ ምርጫ ቀጣዩ ሰሜናዊ የፖለቲካ ትኩሳት

Views: 299

ከሰሞኑ ከወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን እና ከሕገ መንግስቱ አካሔድ ውጪ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ምርጫን ከማድረግ አያግደንም በተባለበት አካሔድ በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ እና ሽር ጉድ እየተስተዋለ መሆኑ ዕሙን ነው። ይህንንም ጉዳይ ፍቃዱ አለሙ ታሪካዊ ዳራውን የተከተለ ጽሑፍ ከወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚታየውን ፖለቲካ ትኩሳት ለጋዜጣ ይሆን ዘንድ አስማምቶ አካፍሎናል።

መንደርደሪያ
ከገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ጀምሮ እስከ ዋለልኝ መኮንን ድረስ በኢትዮጵያ የነበረው የማንነት ፖለቲካል ጥያቄ በዋናነት በመደብ ጭቆና ላይ ያተኮረ ነበር።በወቅቱ አገረ መንግሥቱን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግና ተቋማቱ ብሔሮችንና ህዝቦችን መስለው ለህዝቦች ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻል ያለመ ነበር።

ኢትዮጵያ ፖለቲካ የወለደው የማንነት መብት ጥያቄ ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ዝቅ ብሎ ወደ ከፍለ ብሔር ወርዶ ዛሬም ድረስ የግጭቶች ሁሉ መነሻ ይሄው የማነንት ጥያቄ ነው።ሕወሃት/ኢህአዴግ ሀገሪቱን መምራት ሲጀምር ቀደም ሲል አቆጥቁጦ የነበረው የብሄር-ፖለቲካ በመንግሥት አስተዳደር እንደ ሥርዓት በመተከሉ ምክንያት ዛሬ ላይ ለደረስንበት ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓት መነሾው ይሄው የማንነት ፖለቲካ ነው።እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የብዙ ብሄረሰቦች ሀገር ነች።ወርቅዮ ባህሎችና አስተማሪ የሆኑ የሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች አሏት።

በተመሳሳይ ብዙ ሺሕ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቱባ ባህልና ታሪክ ያሏት ቢሆኑም አብዛኞቹ በባህላዊ የቃል እንጅ በጹሑፍ ያልተመዘገቡ እና የተሟሉ አይደሉም።በዚህ ምክንያት ልክ እንደ ሌሎቹ ሀገራት በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በመጥፎም ሆነ በበጎ ያለፍናቸው ታሪኮቻችንና ማንነቶቻችን ዛሬ በሐሰት ትርክትና በሬ ወለደ መረጃዎች አማካኝነት በሀገራችን ውስጥ የጎሳ ፖለቲካን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት በመስፈኑ የጎሳ ግጭትና መፈናቀል አልፎ አልፎ እየተከሰተ ላለው ሃይማኖታዊ ግጭቶችም መንስኤ ሆነዋል፡፡

ይህ ክስተት ዛሬም አላባራም።ባለፉት ኹለት ዓመታት ከተከሰቱ ግጭቶች በተለየ ሁኔታ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ድግያን ተትሎ የተፈጠረው እጅግ አሳፋሪና ዘግናኝ ብሔር ተኮር ግድያ፣ ዘረፋና ቃጠሎ ብሎም ማፈናቀል ከፍተኛ ክልላዊና ሀገራዊ ውድመት አስከትሏል።

ይህን ኹነት ስናስብ ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ብዙ አዎንታዊ የፖለቲካ መሻሻሎች እንደነበሩ ማመን ያስፈልጋል።የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ የነበረው እውነታ እንደሚያሳየው ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በታየው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የማንነት/ብሄር-ተኮር ፖለቲካል ዲስኩር መስፋፋት ታይቷል።

ሰዎች በያዙት የፖለቲካ አመለካከት ይጠቃሉ፣ በማንነታቻው ምክንያት ይገፋሉ፣ በማንነታቸው ምክንያት ይሞታሉ ብሎም በሀገር ደረጃ ሰላምና መረጋጋት እንቅፋቱ ይሄው በማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ዲስኩር ነው።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በአንድ በኩል ዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርኝ ከፍተኛ አማካኝት እየደረሰ ባለው ኢኮኖሚያዊ ጫና በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ጥናት ከሆነ ከፍተኛ ቁጥር (50%) ያለው አምራች ዜጋ ከሥራ መፈናቀል በሌላ በኩል እዛም እዚህም በሚነሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች ሀገሪቱን ከባድ ውጥረት ውስጥ ከቷታል።በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ፖለቲካዊ ትኩሳት በተገቢው ሁኔታ አለመፈተሽና ገና ያልተጠናቀቁ የቤት ሥራዎች ያሉበት ክልል መሆኑ።በደቡብ ክልል የወላይታ ክልል እንሁን ጥያቄ እና ሌሎች ገና ያልጠሩ ብዙ ትኩሳቶች ያሉባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

የሕወሓት ባህሪና ክልላዊ ምርጫ
ሀገራችን አሁን ባለችበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ሕወሓት በትግራይ ክልል ምርጫ ካላካሄድኩ ሞቼ እገኛለሁ በሚል እብሪት አቋሙ ዛሬም ቀጥሏል።ምን አልባትም ቀጣዩ ሰሜናዊ የፖለቲካ ትኩሳት የሚሆነው በትግራይ ክልል የሚካሄደው ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የክልል ምርጫ ሊሆን ይችላል።ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 06/2012 ዓ.ም ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝት ለምርጫ የተመዘገቡ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስድስት የግል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ መጀመራቸውን የክልሉ የምርጫ ኮሚሽነር ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።ነገር ግን ይህ ምርጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

ምክንያቱም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም አካሂደዋለሁ ያለውን ሀገራ ምርጫ አራዝሟልና ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ ወረርሽኝ የሚያሳድረው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጫና ለሕወሓት ምኑም አይደለም።ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ያወጣው ጥናት እንደሚለው ከሆነ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ (ክፉኛ) የገቢ ማሽቆልቆል ከታየባቸው ወይም በቀጣይ ስድስት ወራት የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ክፉኛ የረሀብ ችጋር ሊጋለጡ ከሚችሉ አምስት የክልል ከተሞች መካከል የትግራይ ክልል አንዱ ብሏል።
ሕወሓት ግን ለትግራይ ክልል ህዝብ እንዲህ ሲል ባለፈው ባስተላለፈው መልዕክት “ኮሮና ቫይረስን፣ የበረሃ አንበጣንና የአሜሪካ ባርኖስን በመመከት ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ በግንቦት 20 የተጎናጸፍካቸውን ዘርፈ ብዙ ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ተረባረብ” ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

ይሁንና ሕወሓት ግን ባለፉት 27 ዓመታት በዚች ሀገር ላይ በፈጸመው ጥፋት ከመጸጸት ይልቅ ክልሉ ላይ መሽጎ ዛሬም ለይስሙላ ምርጫ አካሂዳለሁ በሚል ነውጠኛና አጥፊነት ባህሪው ቀጥሏል።ሕወሓት ድሮም ቢሆን ሀገር፤ሰው አሳስቦት አያውቅም።እንዲያውም ሕወሓት የክልሉን ሕዝብ ሲደልል ምርጫው የትግራይን ብሔራዊ መግባባት ይፈጥራል ሲል ተደምጧል።እውነታው ግን ይህ ሳይሆን እዚች ሀገር ላይ ራሱ በፈጠረው ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በገባው ቅራኔ መግባባት እንደማይፈልግ ስለሚያውቀው ካፈርኩ አይመልሰኝ ሆኖበት ነው።ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር አስበው ወደ ክልሉ የሄዱ የሀገር ሽማግሌዎችን አሳብ ሳይቀበል ቀርቷል።የሚገርመው ደግሞ አሁን ያለውን የመንግስት አስተዳደር እንደተበዳይ ሆኖ የፌደራል መንግሥቱን ሲኮንን ይደመጣል።የሆነ ሆኖ በክልሉ የሚደረገው፡-

ምርጫ(ው) የትግራይን ብሔራዊ መግባባት ይፈጥራል ሲል ምን ማለቱ ነው?
ሕወሓት እዚች ሀገር ላይ የፈጠረው የማንነት ፖለቲካ ዲስኩር፣ ሽብር፣ ግድያ እና ዝርፊያ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ይህን ባህሪውን ጠንቅቆ ያውቀዋል።ተዋግቸለታለሁ በሚለው የትግራይ ሕዝብ ሳይቀር ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ እየዘረፈ ለሕዘቡ ግን አንዳች ነገር ሳያደርግ ቁማር ሲጫወት እንደነበርም ይታወቃል፡፡

ይህን ባህሪውን ጠንቅቆ የሚያቀውና በዚህ ምክንያት ያኮረፈውን ወጣትና ሕዝብ ዛሬም በማይመስሉ የቃላት ድለላ የጥፋቱ ተባባሪ አድርጎ የነገን ተስፋ ለማጨለም በጉያው ለመሸጎጥ የውሸት ፊሽካ ሲነፋ ይውላል።ይህቺ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ የሚናገራት በውጭ ሲታይ መልካም የሚመስል ነገር ግን በውስጥ ሲታይ የበደለውን ሕዝብ (በስሙ ሲነገድበት የነበረውን ሕዝብ) ለመደለል እየተጠቀመባት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕወሓት አሮጌ ፖለቲከኞች ከለውጡ በኋላ ከሕዝቡ የዘረፉትን ሰብስበው ወደ መቀሌ ከመሸጉ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የሚሰነዝሩት ወቀሳ ቅቡልነት ለማግኘት ሕዝቡን ተባባሪ ለማድረግ አልመው ስለተነሡ ነው።በክልሉ መገናኛ ብዙሃን አማካኝት በየቀኑ የሚነዙት የጦር ስበቃ ጤናማ አይደለም።ሕወሓት ከትግራይ ክልል ሕዝብ ጋር ብሄራዊ መግባባት የምር አስቦ ከሆነ በመጀመሪያ ለምርጫ ከመጣደፉ በፊት የክልሉ ሕዝብ ለሚያነሣቸው የልማት ጥያቄዎች ማስቀደም ነበረበት።የክልሉ ሕዝብ ዛሬም ድረስ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የለውም።በኪቪድ ምክንያት ከሥራቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አዳዲስ የሥራ እድል መፍጠር ነበረበት።በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ጥናት መሠረት በክልሉ በኮቪድ አማካኝነት ገቢያቸው በእጅጉ ያሽቆለቆሉ የትግራይ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚቀይርበትን ዜዴ ከምርጫ በፊት ማሰብ ነበረበት።በምርጫ ስም ዛሬም የክልሉን ሕዝቡ በብሔራዊ መግባባት ስም ይደልላል፡፡

ሌላው የሕወሓት ልሳን የሆነው ወይን መጽሔት ትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ በማካሄድ ‘ዲ ፋክቶ ስቴት’ ለመሆን ወደ የሚያስችለውን ‘ቁመና’ (status) ለመገንባት ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ቢቢሲ አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ወይን መጽሔት “እንደ ሀገር ሊያጋጥም ከሚችለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በተነጻጻሪ የተሻለ እና መንግሥታዊ መዋቅርን (Institutions) የገነባ እንዲሁም ራሱን ችሎ የቆመ መንግሥት (De facto state) ለመመስረት የሚያስችል ሥራዎች ማሳለጥ ተገቢ ነው” በሚል በስፋት ማስበበቧን በተመሳሳይ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ይህ ሁሉ ታዲያ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ሕዝብ ዘንድና ሕወሓት ያጣውን ሕጋዊ የቅቡልነት እጦት (Legitimacy crisis) መላ የትግራይ ህዝብን በማሳተፍ ወይም የትግራይን ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሎ በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ሙሉ እምነት ለማግኘት ሲል ምርጫው የትግራይን ብሔራዊ መግባባት ይፈጥራል ይላል፡፡

ሀገረ መንግሰቱን እና ተቋማቱን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ በበላይነት ተቆጣጥሮ ሲያበቃ አብዛኛውን ሕዝብ ያገለለ ነገር ግን ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን የጠቀመ፤ በልማትና በእኩልንነት ጥያቄዎች ስም ዛሬም በክልሉ ፖለቲካውን ለመቆጣጠር የሚደርገው ሩጫ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የመሃል ሀገር ቋፍ ወደ ሰሜናዊ ቋፍ እንዳይወስዳት ያሰጋል።የፌደራል መንግሥቱ ምን አልባትም ይህን ሰሜን ፖለቲካ በሰላም መንገድ የማይፈታው ከሆነ ችግሩ ተደራራቢ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ከባድ አይሆንም፡፡

ምርጫው ይደረጋል ነገር ግን ከምርጫው በኋላ የሚፈጠረው ውስብስብ ችግር አሳሳቢ ነውና የፌደራል መንግሥት አማራጭ ያላቸውን የሰላም መንገድ በሙሉ እስከመጨረሻው ተጠቅሞ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ቢሞከር መልካም ነው። ከምርጫው ማግስት ምን ይፈጠር ይሆን? የትግራይ የምርጫ ውጤት በአጠቃላዩ ሀገራዊ ፖለቲካና የመንግሥት ሥርዓት የሚፈጥረው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል አብረን እናያለን፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com