ምርጥ የንግድ ሰው ለመሆን

Views: 180

አንድ ሰው የንግድ ሰው መሆኑ ብቻ በቂ እንዳይደለ እና ምርጥ ንግድ ሰው የሚለው ጉዳይ ደግሞ በዋናነት ሊጤን የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አብረሐም ፀሐየ በሚገባ አንስተው እና ከዚህ በፊት የንግድ መጀመርን ጥበብ ያካፈሉንን ሀሳብ በድጋሚ በማካተት ምርጥ የንግድ ሰው ምን መምሰል እንዳለበት ለማሳየት ሞክረዋል

የሁሉም ነገር ስኬት ሚስጥር አለው፤ ብልሆች ደግሞ ይደርሱበታል፡፡ እርስዎ ከወደንግዱ ላይ ለመሰማራት ሲያስቡ ከራስዎ ጋር ሊነጋገሩ የሚገባዎት ጉዳይ ይኖራል ይህ ከራስ ጋር የሚደረግ ንግግር ለንግድ የሚያበቃ ስብዕና አለኝ ወይ? የሚለው ነው፡፡ ወደንግዱ ዓለም ለመሰማራትም ቁርጠኛ ከሆኑ ቀጣዮቹ ነጥቦች የሚስጥሩ ጠቋሚ መንገዶች ናቸው፡፡

ጊዜ ገንዘብ በመሆኑ በሚገባ ማስተዳደር
በሃብት ስኬት ላይ የደረሱ ሰዎች እንደሚሉት ሃብታም ሰው ሃብቱን በጊዜ ላይ ያፈሳል፡፡ ደሃው ደግሞ ጊዜውን ገንዘቡ ላይ ያፈሳል፡፡ እነዚህ በሁለት ተለያዩ ሰዎች መካከል ያሉ አንኳር ልዩነቶች ናቸው፡፡ በአጭሩ ነቅሰን ብናየው ሃብታም በተገቢው ጊዜ ግሮሠሪ ሲከፍት ፣ ጊዜው ከንቱ የሆነበት ደግሞ ግሮሠሪ ሄዶ ጊዜውን ለመሰዋት እንደሚቀመጠው ማለት ነው፡፡ ነገሮችን በተገቢው ጊዜ የማቀድና የመከወን ልማድ የስኬታማነትህን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል፡፡
ለራስህ ጠንካራ አመለካከት ይኑርህ

ውሳኔዎችህ ሌሎች በሚሉህና ሲያደርጉ ባየኸው ላይ ብቻ መመርኮዝ የለበትም፡፡ ይህ ጥገኝነትንና አሉታዊ ተፅእኖን ይፈጥራል፡፡ የሌሎች ሰዎችን አስተያየት ሙሉ ለሙሉ ከመቀበል ይልቅ በሐሣብ ግብዓትነቱ መጠቀም ይመረጣል፡፡ በተለይ ስለሚያጋጥምህ ወይም ሊያጋጥምህ ስለሚችለው ውድቀት ለሚተነብዩልህ ሰዎች ቦታ አትስጥ፡፡ ራስህን መመዘን ያለብህ በማንነትህ ልክ እንጂ ከሌሎች ጋር ተፎካክረህና ተነፃፅረህ ሊሆን አይገባም፡፡ ውድቀት ሲደርስብህ ሀዘንህን ሊካፈል የሚመጣው ሰው ብዛት በተሳካልህ ጊዜ ተደስቶ ከሚመጣው ሰው ብዛት ይልቅ ከፍ ያለ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ ቢሆንም ግን በውድቀት ጠሪ ሰዎች አትሸበር፡፡ የራስህ ጠንካራ አመለካከት ስር የሰደደ የጥንካሬህና የዘላቂነትህ ምንጭ ስለሆነ ለማንነትህ ጥሩ ምልከታ ይኑርህ፡፡

መበደር ካለብህ ብድርህ የተመጠነ ይሁን
በክሬዲት ካርዶችና በተለያዩ ብድሮች መኖር ሃብታም አያደርግም ወይም የተሳካለት የንግድ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ቢቻልህ ሰባራ ሳንቲም አትበደር፡፡ መበደር አስፈላጊ ከሆነ ግን ከአበዳሪዎችህ ጋር መክፈል በምትችለው የወለድ መጠንና የመክፈያ ጊዜ ላይ በደንብ አስብበት፡፡ በተገቢው መልኩ ተወያይተህ ተስማማ ወይም ተደራደር፡፡ ምክንያቱም ዕዳህን መክፈል ስለመቻልህ ከመበደርህ በፊት ዕርግጠኛ ልትሆንበት የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከተበደርክ በኋላ የተበደርከው ገንዘብ ሌላ ገንዘብ ሊያመጣ የሚችል ስለመሆኑ ተገቢ ስሌት ሊኖርህ ይገባል፡፡ አለበለዚያ እንደብድር ለራስ ምታት የሚዳርግ ህመም አለመኖሩን አውቀህ መግባትህን እንዳትዘነጋ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ብድር ንግድህን ሊያቀላጥፍ የሚችል ጥሩ የኢንቨስትመንት አማራጭ እስከሆነ ድረስ መበደር አይከፋም፡፡

ምን ያህል የፅናት ሰው ነህ
በንግድ ህይወት ውስጥ ትላልቅ ሃብታሞችን ጨምሮ የማሸነፍያ አንዱ መንገድ ፅናት ነው፡፡ የትጋትና የፅናት ባለቤት ሆኖ መገኘት ደግሞ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡ የተሳካለት የንግድ ሰው ሆኖ ለመገኘት ወይም ለመውጣት ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይፍጅ! ፅናት ይኑረን ፡፡ ፅናት በትዕግስት እንድናሸነፍ የሚያግዘን መሳሪያ ነው፡፡ (ብዙ ሰዎች ከስኬት መንገዳቸው ቀድመው የሚወጡት የያዙት ጉዳይ መቼ በስኬት እንደሚጠናቀቅ ትክክለኛ የጊዜ ስሌት ስለሌላቸው ነው) ግብ ላይ ለመድረስ ልክ እንደሚገነባ ህንፃ ጊዜ ይፈልጋል፡፡

አንድ ትልቅ ህንፃ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሰባት ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህንንም እንደዚያ ማሰብ ነው፡፡ ይህን ንግድ ብጀምረው እስኪሣካ ድረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅ ይሆን? ምናልባትም ሰባት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ግን በቃ አልተሳካም ብለው ሁለተኛና ሶስተኛ ወይም ደግሞ ስድስተኛ ዓመት ላይ ያቋርጡታል፡፡ የያዝነው ስራ በታለመለት ጊዜ እንዲያልቅ ፅናት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡

የአስተዳደር ክህሎትን ማጎልበት
የአንድ ንግድ ሥራ ባለቤትና መሪ ላቋቋመው ሥራ በሥሩ ያሉትን ሰዎችና ሌሎች ሃብቶች በአግባቡ ለመምራት ዕቅዶችን የመንደፍና ያንን ለማሳካትም የመሪነቱን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ሠራተኛ መቅጠር የማዘዝ ጥምን ለመቁረጥ ሳይሆን አንድ ሰራተኛ ከሥራው ጋር ተዋህዶ የንግድ ስራውን የማገዝ ኃላፊነት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ የንግዱ ባለቤት ኃላፊነት የሥራ ቡድን መፍጠር ፣ ማነቃቃትና ማበረታታት ነው፡፡ የሞራል ማነሳሻ ክፍያዎችን በመዘርጋትና በመሣሠሉት ብልህና በሳል የአመራር ክህሎቶች መጠቀም መቻል ነው፡፡ ጥሩ የአስተዳደር ክህሎት አለው የሚባለው የስራ መሪ በተለይ የቡድን ስሜቶች አንዳይረበሹ ገንቢ የሆኑ ከባቢ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርበታል፡፡ ይህ ተገቢነትም ብልህነትም ነው፡፡

ከአንድ በላይ የገቢ ምንጭ መዘርጋት
በአንድ ስራ ላይ ብቻ ጥገኛ አለመሆን ጥሩ ነው፡፡ በሌሎች ተያያዥ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ከድንገተኛ ውድቀት ከመታደጉም በላይ ዋንኛውን ንግድ ሊደጉምና ሊያሳድግ የሚችል የገንዘብ ምንጭም መሆን ይችላል፡፡ ዓለም አሁን እያሳየች ያለችው የተለዋዋጭነት ባህሪም የያዝነውን ንግድ ባለበት የመቆየት ህልውናውን የሚፈትንበት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም ከአንድ ይልቅ ሁለት የገቢ ምንጭ ቢኖር ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ ዕድሜዋን ታረዝማለች እንደሚባለው ነው፡፡

ምርጫዎችን ማጥበብ
ሰው ማለት የሚመርጠው ነገር ግራ እስኪገባው ድረስ በርካታ ግራ አጋቢ ምርጫዎች ውስጥ የተጣለ ምስኪን ፍጡር ነው። ፍላጎቱም በዛው መጠን የሚቀያየርና ብዙ ሊሆን ይችላል። በኹለት ዐይናችን ከኹለት በላይ፣ በኹለት ጆሮአችን ከኹለት ነገር በላይ እንድንሰማ ቢፈቀድም ሁሉም ግን አይጠቅምም የሚል መርህ አለ።
እዚህ ላይ ቆም ብለን ልንመለከትና ልናደምጥ በስተመጨረሻም የተሻለውን በመምረጥ ልንወስን ይገባል። ስለዚህም ያየውን ሁሉ የሚያባርር አንዱን አይዝምና በንግድ አካባቢ ካሉት በርካታ ምርጫዎች መካከል አበጥረን የተሻሉትን በመምረጥ ከኛ አቅምና ፍላጎት፣ እንዲሁም የአዋጭነትና የተፈላጊነት ደረጃውን በማመዛዘንና በመለየት የምንገባበትን የንግድ ዓይነት መወሰን ግድ ይላል።

አዋጭነት
አንድ ልብ ልንለው የሚያስፈልገው ጉዳይ የምናየው ሁሉ ወይም ዝናውን የምንሰማለት የንግድ ዓይነት በሙሉ ይሆነናል ማለት አይደለም። አዋጭነቱን ማስላት ግድ የሚሆንበት የመጀመሪያው የመረጃ ማሰሻ ቦታ ሊሆን ይገባል። ‹ለመሆኑ ይህ የምጀምረው ንግድ ምን ያህል አዋጪ ነው?› ብሎ ራስን መጠየቅ ለትክክለኛ እርምጃ ጅማሬ ነው።

ይኸውም ሊያተርፈን ከቻለ በምን ያህል መጠን፣ ኪሳራ የሚባለውስ እስከ የትኛው ዝቅታ ድረስ ይሆን? ለሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ከወዲሁ ተጨባጭ መልስ መፈለግ ይገባናልና ነው። ስለሆነም ያለበቂ መረጃ ዘው ላለማለት ሲባል ቀድሞ ዙሪያ ገባውን ለማጥናት መወሰን፣ ያንንም ተግባራዊ ማድረግ ተመራጭ ነው።

ግምገማ
አንድን ውሳኔ ለመወሰን ምን ያህል ጊዜ ሊወስድብን ይገባል? የምንወስነው ውሳኔስ በሕይወታችን ላይ የምንፈልገውን ያህል ተጠቃሚነት ማምጣት ይችላል ወይ? በእነዚህ ኹለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አዋጭ የምንለውን የግል ሥራ ከመረጥን በኋላ ወደ ድርጊት የመሸጋገር ቆራጥ ውሳኔ ይጠበቅብናል።

የቸኮለም የዘገየም ኹለቱም ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ መሆኑ እሙን ነው። ስለዚህም ዐስር ቀን የሚፈልገውን በዐስር ዓመት እያዘገየን፣ ወይም ደግሞ ‹ቁጭ ከምልና ብሩ ከሚጠፋ ልሥራበት› በሚል ያልተገባና ኋላ ቀር አካሄድ ከመመራት ይልቅ ጥርት ያለና ወቅቱን የጠበቀ ግምገማ ያስፈልጋል።

የምንሰማራበት ንግድ ቀላል ወይም ከባድ ውሳኔ እንደሚሻ መለየት
የምንሰማራበት የንግድ ሥራ አንዳንድ ጊዜ ቴሌቪዥኝ ከፍቶ የማየት ያህል ቀላል ሊሆን ይችላል። አዲስ ነገር ፈጥሮ፣ አዲስ መሠረት ጥሎ “ሀ” ብሎ የመጀመር ያህል ጠንከር ያለና ፈተና ያለበት ሊሆንም ይችላል። ቅለቱንና ክብደቱን የመመዘን አስተውሎት ያስፈልገናል። ይህንን ቀድሞ መለየት ከራሳችን የመሥራት ፍላጎትና ከሥራው ጋር አብሮ ለመቆየት ያለንን ጽናት ለመለካት ያስችለናል።

አንዲት ካልሲ ለመግዛት አስራ ስድስት ሱቅ የሚዞር ዓይነት ሰው ከሆንን የጊዜ ዋጋ አልገባንም፤ የውሳኔም ሰው አይደለንም ማለት ነው። ከባዱንም ጉዳይ ያለበቂ ዝግጅት በስሜታዊነት ፈጥኖ መጀመር አጉል መስዋእትነት ይሆናል። ስለሆነም አመዛዝኖና በተገቢው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወስኖ ወደ ሥራ አለመግባት በኋለኛው ዕድሜ ላይ ‹ወይኔ ያን ጊዜ ብጀምረው ኖሮ…› ከሚል ፀፀት አያድንም።

ምርጫችን የተጠና ውሳኔ ይፈልጋል
ወደ ግል ሥራ የመግባት ውሳኔ አዋጭነቱ፣ ምርጫዎቹ፣ ክብደትና ቅለቱን፣ እንዲሁም የሚፈጀውን ጊዜ መወሰን ያስፈልጋል ካልን እንዴት የሚለው ጥያቄም ወሳኝ ነው። ምንጊዜም ወሳኙ ጥያቄ ቢኖር ‹እንዴት?› የሚለው ነው። ትልቁ መልስም ይህንኑ እንዴት የሚለውን ጥያቄ መመለስ መቻል ነው።

ስለሆነም ልንጀምረው የፈለግነውን ንግድ ያውቃሉ ከምንላቸው ሰዎች መፈለግ የተሻለ ይሆናል። በጓደኛ ዙሪያ፣ ዘመድም ይሁን የሥራ ባልደረባ ጋር በመጠጋትና በመወያየት አልያም በጉዳዩ ላይ የሥራ ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች የማማከር ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢም ብልህነትም ነው።

ተጨባጭ ውጤት ያለው ጥናት ያስፈልጋል። ንግድ በስሜት የሚገባበት አይደለም። የስማ በለው ጥናት አልያም አጉል ድፍረት ከሆነም ራሳችንን ለኪሣራ አመቻቸን ማለት ነው። በተረፈ ይሄ ንግድ እንደሚያዋጣ አጎቴ ነግሮኛል፤ ጎረቤቴ ወይም ጓደኛዬ መክሮኛል እያልን ውሉ ባልተያዘ ሁኔታ ላይ ተመስርተን እንሥራ ካልን ከወዲሁ ውድቀትን ለማስተናገድ እንደወሰንን ማወቅ ይኖርብናል።

ውሳኔያችን በተጣራ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ
ልንጀምር ያሰብነውን ንግድ ስናጠና እያገኘን ያለነው መረጃ ተጨባጭ፣ የተሻለና እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንለይ። መረጃውን በመገምገም ከእኛ ሐሳብና ፍላጎት እንዲሁም ወደ ድርጊት ለመሸጋገር በሚያስችለን ደረጃ ላይ የሚያደርሰን ስለመሆኑ እርግጠኛ ከሆንን፣ ጥሩ የራስ መተማመንን ይፈጥርልናል። በዚህም ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንደሚያደርሰን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች አብዛኞቻችን ወደምንፈልገውና ወደሚያዋጣ የግል ሥራ ላይ ለመሰማራት ስናቅድ ከውሳኔ በፊት ልናስተውላቸው የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችና የማመላከቻ መንገዶች ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com