አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? (መዝ 38 (39) ÷ 7)

Views: 131

ተሾመ ፋታሁን የተግባቦት ባለሙያ እና አማካሪ ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱትን አገራዊ ኹነቶች እና ከዓለም አቀፍ መድረክም በታላቅ ከተሞች የተካሔዱትን የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በማስተሳሰር የግል ምልከታቸውን ሰጥተዋል። በጉዳዩ ላይ የዓለመ አቀፍ የአገረ መንግስትን ጉዳይ በሚመነለከት ሰፊ ትንተና የሚሰጡ ታላላቅ ግለሰቦችንም ለአብነት በማንሳት የጉዳዩ አካል እና መረጃውን ማጠናከሪያም አድርጓል።

የጥቁር ህይወት ቁብ አላት (#BlackLivesMatter)!ይህን መፈክር ብዙዎቻችን የፌስ ቡክ ፎቶ መታወቂያችን አድርገነዋል ወይም ተደርጎ አይተነው ወደን አጋርተነዋል።በተለይ ባሳለፍነው የግንቦት ወር መጨረሻ ጥቁሩ አሜሪካ ዊጆርጅ ፍሎይድ በአሰቃቂ ሁኔታ ዴሬክ ሚካኤልሾቨን በተባለ የሚኔያፖሊስ የፖሊስ አባል የፊጥኝ ታስሮና ተደፍጥጦ መተንፈስ አልቻልኩም (I can’t Breathe) እያለ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን ባጣበት ወቅት በዓለም ዙሪያ ብዙዎች (#BlackLivesMatter) ብለው የኮሮና ቫይረስን እንኳን ሳይፈሩ አደባባይ ወጥተው ተሰልፈውበታል ፣ከፖሊስ ጋር በመጋጨት ጭምር ዋጋ ከፍለውበታል።

#BlackLivesMatter የሚለው እንቅስቃሴ ለመጀመሪያ ጊዜ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ሆኖ አደባባይ የወጣው በየካቲት2012 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በወቅቱ የ17 ዓመት ወጣት የነበረውን የትሬይቮን ማርቲንን በአደባባይ በጥይት ተደብድቦ መገደል ተከትሎ ሲሆን፣ከዛን ጊዜ ጀምሮ የቀለም ዘረኝነትን ለመቃወም በተለይም ደግሞ ለጥቁሮች መብት ትግል እንደ ዋና መቀስቀሻ ሆኖ ጥቅም ላይ ይውላል።በያዝነውም ዓመት የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ (#BlackLivesMatter) በዓለም ዙሪያ በርካቶች ለብሰውታል ፣ፊታቸውን ተቀብተው ፣ቤት አንገባም ብለው ደጅ አድረውጮኸውበታል፣በማህበራዊ ሚዲያም ተጋርተው አጋርተውታል።የአንድ ሰው ክቡር ሕይወት አለአግባብ ማለፍ ግድ ብሎአቸው ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በርካቶች በዓለም ዙሪያ ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት ጮኸዋል፣አልቅሰዋል ተቀስቅሰው ቀስቅሰዋል።

እኔም ዛሬ በተለይ በዚህ ሳምንት « የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ »ሰኔ 22/ 2012 ምሽት በአዲስአበባ የተፈጸመውን የድምጻዊ አጫሉ (ሃጫሉ) ሁንዴሳን ግድያ ህልፈት አስታኮ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ በርካታ ከተሞች በተፈጠሩ ብጥብጦች በተለይ በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ የደረሱትን አሰቃቂ ኹነቶች ስመለከት ይህን ልል ወደድኩ (#EveryHumanLifeMatters) የማንም ይሁን የማን የክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት ግድ ሊለን ያሻል።መንግስት በድርጊቱ እጃቸው ይኖርበታል ያለቸውን ሰዎች ማሰር መቅጣት መጀመሩ እሰየው የሚያስብል ቢሆንም በአፍ ድርጊቱን ተከትሎ የጠፉ ክቡር የሰው ልጅ ህይወቶችን እና የንብረት ጥፋቶችን በቁጥር ካለማሳወቅ በላይ በሞቱ እነ እገሌም አሉበት የሚሉ ትርክቶችን (በኢመደበኛነት ቢሆንም እንኳ) መስማት ግን በተጎጂዎቹ ህመም ላይ ሌላ ህመም ነው።

በታዋቂው የሰብአዊ መብት ታጋይ ኦባንግ ሜቶ የሚመራው « የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ » የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሥፍራው ድረስ በአካል በመሄድ ጥፋቶችን በማየትና « ከፈረሱ አፍ » እንዲሉ ተጎጂዎቹን በማናገር ላጠናቀረው ሪፖርት ክብረት ይስጥልን ማለት ያስፈልጋል ።በሪፖርቱ ላይ ዘርን፣ ሃይማኖትንና ዘር እናሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥፋቶች መከሰታቸው ተሰንዷል።በአንድ አገር ላይ አንዱ ባለቤት ሌላው ቤት አልባ ሆኖ ማየቱ ያሳዝናል።ኢትዮጵያ የማን ናት ? በአንድ አገር ላይስ እንደዚህ ዓይነት ነገር ማየቱ ማንን ይጠቅማል ? የሚሉ ጥያቄዎች በተቻለ ፍጥነት መልስ የሚሹ ይመስላሉ።

በአንድ አገር ስንት ዜግነት አለ ? አንድ ሰውስ አንድ ቦታ ላይ ስንት ዓመት ሲቆይ ነው በቦታው ዜግነት የሚያገኘው ? እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ በተለይ በሻሸመኔ ተወልደው ያደጉ፣ ያረጁ ያፈጁ፣ የኳሉ የዳሩ ሰዎች፣ በከተማዋ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኖሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል።የታዋቂው አትሌት ናባለሃብት ኃይሌ ገብረስላሴ ንብረት ወድሟል፤ የሰጠይጣን ጆሮ ይደፈንና በተለይ በወቅቱ አትሌቱ በዛአድሮ ቢሆን ምን ይሆን ነበር?

ተጎጂ ወገኖች እንደሚያምኑት ድርጊቱ ድንገቴ አይደለም።የቤት ቁጥርና የስም ዝርዝር የያዙ በባህላዊ መንገድ የታጠቁ በሃሰት ትርክት የተሞሉ ምክንያታዊነት የማያውቃቸው ወጣቶች በር እየቆጠሩ ድጋሚ ለራስ እንኳን ለማውራት የማይመች ድርጊት ፈጽመዋል።ድርጊት ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ማዋሉና መቅጣቱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ዛሬም ድረስ በአብያተ ክርስቲያናቱ ተጠልለው ያሉትን ሰዎች ወደ ቤት ንብረታቸው መመለስና ነገ ድርጊቱ እንደማይፈጸምባቸው ዋስትና መስጠት የመንግስት የቅድሚያ ቅድሚያ ቢሆን መልካም ነው።የሥነ-መንግስት ተመራማሪው ቶማስ ሆብስ እንደሚመክረው መንግስት የህዝቦችን ደህንነት ከመጠበቅ የሚቀድምበት ኃላፊነት ሊኖረው አይገባም።

ቢቆጡ የሚሰሙ ቢረግሙ የሚደርስላቸው አረጋውያን ባደጉበት፣ ተምረው ባስተማሩበት፣ በቀደሱና ባስቀደሱበት፣ ስጋ ወ ደሙ ወስደው በመነኮሱበት፣ አሳድገው በዳሩበት፤ ለእህል እንጂ ለሥራ ያልደረሱ ደቂቃን ወላጆቻቸውን ተነጥቀው ምክንያታዊ በሆኑ አብሮ መኖርን በሚያውቁ ወዳጅ ጎረቤቶቻቸው ቤት እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት አሁንም ድረስ ተጠልለው ይገኛሉ።

አጥፊዎቹን መቅጣት አንድ ነገር ሆኖ ተጎጂዎቹን ዋስትና ሰጥቶ ወደ ኑሮአቸው መመለስ የቅድሚያ ቅድሚያ ነው፣ አልያ ግን ጥቅምት ላይ በመጠኑ ጀምሮ ሰኔ ላይ በዓይነትም በብዛትም አድጎ የመጣው ይህ ጥፋት ለሦስተኛ፣ ለአራተኛ ጊዜ ላለመደገሙ ማንም ዋስትና የለውም፣ ዜጎች ዓይናቸው እያየ እህት ወንድማቸው፣ እናት አባታቸው በአደባባይ በአሰቃቂ ሁኔታ ሞተውባቸው፣ ለዓመታት ያፈሩት ንብረት ፊታቸው ዶግ አመድ ሆኖ እያዩ፣ ህጻናት የወላጆቻቸውን ሞት እያስታወሱ በስጋት ውስጥ ይገኛሉ፣ ጥፋቱን መመለስ ባይቻልም እንዳይደገም ማድረግ ግን ይቻላል።

ነዋሪዎቹ አሁንም ድረስ የተመሳሳይ ጥቃት ስጋት መሆናቸውን ሪፖርቱ ይናገራል።የሕግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋና ሥራው እንዲሆን ይለምናሉ፣ የሚፈራና የሚከበር መንግስት ለችግሩ ዋና መፍትሔ ነው።የዜጎች በአገራቸው ሰርተው ንብረት የማፍራት መብት ሊከበር ያስፈልጋል።ጥፋተኞችን በሙሉ አግኝቶ አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እነሱን ከማስተማሩ ባሻገር ነገ ለሌላ ጥፋት የተዘጋጀውንም ለማስጠንቀቅ ያግዛል።መንግስት ዝምታውን ሰብሮ በተለይ ደግሞ በገለልተኛ አጣሪ ቡድን የጥቃቱ መጠን አጣርቶ ውጤቱን ቢገልጽ ለብዙ ነገሮች መፍትሔ ይሆናል።

ሪፖርቱ እንደሚያጥተው ሮጠው የጠገቡ አሩግ አባቶችና እናቶች ለዘመናት ያፈሩት ንብረት የእሳት ራት ሆኗል፤ አዛውንቱም ያለጧሪ ቀርተዋል።የነዚህን አሩግ አዛውንት ቤትና ንብረት መመለስ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖር በእጅጉ ይረዳል።በሃተታው እንደቀረበው የጸጥታ ኃይሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የድርጊቱ ተሳታፊ ነበሩ፤ እንዚህንም ለይቶ ለህግ ማቅረብና ከአቀናባሪዎቹ ጋር አብረው ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ቢቻል ለሁላችንም ይጠቅማል ካልሆነ ግን ሁላችንም ከተጎጂዎቹ ጋር አሁንስ ተስፋችን ማን ነው ከማለት ውጭ ምርጫ የለንም።

በዘመናት መተሳሰብ እናአብሮነት የተገነባው የማኅበረሰብ መሰረት እና አዕማድ በእኛ ዘመን እንዲፈርስም ልንፈቅድለት አይገባም። በተለይም ደግሞ ጭቃ አቡክተው አድገው ውሃ በተራጩበት ወንዝ በራሳቸው ባልንጀሮች ተደፍቀው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሲደረጉ መታዘብ ዕጅግ የሚሰቀጥጥት ተግባር እንደሚሆን ሊታጣ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ። ተስፋችንን አሁንስ በምን ላይ ልናድርግ እና ልንሆነ ነው ሚቻለን? ደፋ ቀና ብለን ባቀናነው እና በከፈልነው ግብር ልጆቻችን ይጠበቁልናል ብለን በገዛነው ጠመንጃ ለአጥፊዎች ድጋፍ እየተደረገ ጠፊዎችን ድራሽ ማጥፋት እንዴት ያለ ሞራል ልዕልና ውስጥ እንዳለን የሚያጠያይቅ ጉዳይ ነው። በዚህ ብቻ ሳይበቃን ከዛሬ ነገ ያፈቅናትን እና የሞትንላትን ነጻነት እና ብርሓን እናያለን ብለን ስንናፍቅ ጭራሽ ወደ ከበደው ጽልመት መንደርደራችን ነጋችንን እንድነፈራ እና እንድንጠራጠር አድርጎናል። አሁንስ ተስፋችን ማነው? በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የቁረጠው ፍለጠውን ፖለቲካ በሚያራምዱ ባለስልጣናት ወይስ በዝምታቸው ውስጥ ነገዋን አስፈሪ ኢትዮጵያ በሚጠባበቁ ጭቁን የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ነው?

የዘመናት አንድነት እና አዕማድ ሲፈራርሱ በዳር ሆኖ መመልከት ሙሉ በሙሉ ወደ ፍርስራሽ በተቀየረበት ወቅት ግን የዳር ተመልካች ሳይን የመሐል ላይ ተዋናይ ሳይወደድ በግድ የሚገባበት አንደኛው ምእራፍ መሆኑን ሊጤን የሚገባበት ጉዳይ ነው። እንጠይቃለን፤ መቼስ መጠየቅ አይከብደን። ተስፋችን ማነው? ይህን ደፍሮ ሚመልስልን አሁንም እያገኘን አይመስልም። በተለያዩ አካባቢዎች ሹማምንት በስሟ ምን እንደሚሰሩ የማታውቅ ምስኪን ሴት ፣ በአደባባይ ስለሴት ልጆች መብት የሚሟገቱ ቅንጡ መሰብሰቢያ አዳራሾችን የሚያሞቁ ተሟጋቾች ባሉባት አገር አሁንም በየጤሻው ትገደላለች ከባሰም ተደፍራ ትገደላለች። ታዲያ በዚህ ወቅት ምን የሚታይ ይመስላችኋል? የመንግስት ቸልተኝነት እና ዝግመታዊ ውሳኔ አሰጣጥ አካሔድ ነው በይፋ የሚታየው።

ከመቼውም ባለፈ መንግስት እንዲህ አይነት አካሔድ እንዲራመድ አይፈቀድለት። መሪን እኛው እንደምንፈጥረወ ማወቅ አሁን አይደለም በሚገባ የምንረዳው ጉዳይ። ይህን እና ሌሎች ጉዳዮችን አሁንም እያነሳን መንግስት ይድረስልን ለሚሉት ፍጥነቱ ከንፋስ በላቀ ሁኔታ ሊከሰት ይገባልም። አልሔድንም እንጂ ጉዟችን እኮ በአሰቃቂነታቸው አለም ዳግመኛ እንዳያነሳቸው ከተማለላቸው አሰቃቂ ዓለም ላይ ፍጅቶች እና ዕልቂቶች መንደር ነበር። ግን አሁንም የሽ ዘመን አብሮነት በሽራፊ አመታት አይበጠስምና ተያይዘን አለን።

ስናጋድል፣ ስናዘምም እና ስንገዳገድ አንዱ በአንዱ ላይ እየተዛዘለ መኖሩ ግድ ሆኖበታል። ይህ መተዛዘን እና የመደጋገፍ ጉዳይ የምርጫ ወይም የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን ሕልውና ጉዳይ ከሆነ ኹለት ድፍን አመታትን ተሸግረን ወደ ሦስተኛው እየተንደረደርን ነው። አሁንም አጥብቀን እንጠይቅ አሁንስ ተስፋችን ማነው?
teshomefantahun@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com