የሰሞኑ የወላይታ ዞን ኹነት እና የደቡብ ክልል ቀጣይ ፈተናዎች

Views: 262

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት ሲንከባለሉ ከቆዩ የረዥም ጊዜ በርካታ ጥያቄዎች መካከል የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ናቸው።በተለይም ከመጀመሪያው ጥናት ተደርጎባቸው እልባት ያላገኙ ጥያቄዎች ለዘመናት ሲንከባለሉ በመቆየታቸው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ችግር አፈታት ስልት ውስብስብ እንዳደረገው ይታመናል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወስጥ አሁን ላይ በርከት ያሉ ውስብስብ ችግሮች የተደቀኑ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን አመራሮችን እስር ተከትሎ በዞኑ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።ከሰሞኑ ሁከት የተፈጠረባት ወላይታ ዞን ትሁን እንጅ በጥቅሉ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አንስተው የፌደራል መንግስት እልባት ለመስጠት የተለያዩ አመራራዊና ህዝባዊ ምክክሮችን ማካሄዱ ይታወሳል።በክልሉ የተነሳውን የዞኖች የክልልነት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ጥናት አጥኝ ኮሚቴ በፌደራል መንግስት ተቋቁሞ ያጠናውን ጥናት በክልሉ ጥያቄ ላነሱ ዞኖች ለውይይት አቅርቦ በወላይታ ዞን በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን በወቅቱ በቀረበው የደቡብ ክልል መዋቅር ጥናት ላይ የተሳተፉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ፖለቲከኛ ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል፡፡

በደቡብ ክልል ከተነሱ የክልልነት ጥያቄዎች ውስጥ ግንባር ቀደም የነበረውና በቅድሚያ ጎልቶ የወጣው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ነበር።በዚሁ መሰረት ሲዳማ በፌደራል ምርጫ ቦርድ አማካኝነት በህዝብ ውሳኔ የክልልነት ጥያቄውን አስመልሶ ክልል መስርቶ በአሁኑ ጊዜ የክልሉን መዋቅር እያደራጀ ይገኛል።ይህን ተከትሎ ነበር የክልሉ መክር ቤት ጥያቄችንን ካለመለሰ ራሳችንን አግለናል በማለት የወላይታ ዞን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ምክር ቤት አባላት ከክልሉ ምክር ቤት አባልነት እራሳቸውን በማግለል ክልሉ ምክር ቤት የነበራቸውን መቀመጫ ትተው የወጡት።የብሔሩ ተወካይ አባላት ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ያገለሉበት ምክንያት የዎላይታ ሕዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያስችለኛል በሚል ላቀረበው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምክር ቤቱ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በማለት ነበር፡፡

የወላይታ ክልል ሲቋቋም የሚመራበት የሕገ-መንግሥት ረቂቅ ላይ ለመወያየት የተሰበሰቡ ባለሥልጣናት፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ከታሰሩ በኋላ በዞኑ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቢ፣ የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ የላጋ የተባለው የወጣቶች ንቅናቄ ተወካዮችን፣ የዎላይታ ሽማግሌዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና ምክትላቸው፣ እንዲሁም የንግድ ምክር ቤት ተወካዮችን ጨምሮ ወደ 28 ሰዎች መታሰራቸውን ተጠቁሟል።

የዞኑ ፖለቲከኞች እና የተለያዩ ማሕበረሰብ ተወካዮች መታሰራቸው ከተሰማ በኋላ ሶዶን ጨምሮ በተለያዩ የዎላይታ አካባቢዎች ተቃውሞ መነሳቱን የሚታወስ ነው።በተፈጠረው አለመረጋጋት የ16 ሰዎች ሂወት መጥፋቱ ተገልጿል፡፡

በደቡብ ክልል የሚነሱ ጥያቄዎችና የወላይታ ዞን ሰሞናዊ ችግር መነሻ
በደቡብ ክልል በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሁከቶችና ጥፋቶች መነሻቸው ከመጀመሪያዎ የደቡብ ብሔርብሔረሰቦች ተብሎ በአንድ ሲጨፈለቅ መሆኑን የሚምኑ የክልሉን ፖሊተካ በቅርበት የሚከታተል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።እንደ ፖለቲከኛው ገለጻ “የደቡብ ክልል ፖለቲካ የተበላሽው ገና ከጥንስሱ ነው፡፡” በማለት በክልሉ አሁን ላይ በተለይም በወላይታ ዞን ለተፈጠረው ወቅታዊ ችግር እንደ ምክንያ ያስቀመጡት፡፡

ፖለቲከኛው አክለውም የደቡብ ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር ጥቂት ልሂቃን የተሰበሰቡበተ ህዝብን ያላሳተፈ አስላለፍ መኖሩ እንደሆነ ይገልጻሉ።በወላይታ ክልል አሁን ላይ ለተፈጠረው ችግርም መነሻው እራሱ መንግስት መሆኑን ፖለቲከኛው ሲገልጹ፣ በዞኑ አመራሮች ላይ የተደረገው ድንገተኛ እስር የአካባቢውን ህዝብ ለአመጽና ለተቃውሞ በመጋበዙ የሰው ሂወት እንድጠፋ ሆኗል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉን ‹ፖለቲካ በንቃት የሚከታተሉ ት የጋሞ ድሞክራሲያዊ ፓርት ሊቀመንበር ዳሮት ጉምአ የደቡብ ክልል ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ መነሻ ከሙባሉት ውስጥ የመልካም እተዳደር ችግር፣ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት፣ ፍትሐዊ ውክልና አለማግኘት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መሆኑን ያመንናሉ፡፡

ሌላኛው የኮተቤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ፌደራሊዝም መምህር አየነው ብርሀኑ(ደ/ር) የደቡብ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ በዋናነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ መሆኑን ያምናሉ።አያሌው(ደ/ር) እንደሚሉት ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ከሚነሱበት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር ክልል በመሆን የሚገኘውን የበጀት ድጎማ እንደ መነሻነት ያነሳሉ።እንደ አያሌው ገለጻ በዋናነት የኦኪኖሚ ተጠቃሚነት መሰረታዊ መነሻ ቢሆንም፣ ክልል በመሆን የስልጣን ፍለጋ ላይ መሰረት አድርው የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኛች ህዝቡን ወክለነዋል በማት በራሳቸው ፍላጎት የሚጓዙበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ ተወስኖ ሲዳማ ክልል ሆኖ መመስረቱ ችኮላ የታየበት መሆኑን የሚምነት አያሌው(ዶ/ር)፣ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በወቅቱ በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠሩ ውሳኔው በመታለለፉ በክልሉ ጥያቄ ያነሱ ዞኖችን ጥያቄ ለመመለስ አንዱ እንቅፋት እንደሚሆን አያሌው ያምናሉ።በወቅቱ መንግስት ውሳኔውን ጫና ላይ ሆኖ ቢወስነውም ሌሎች ውሳኔውን ተከትለው የሚመጡ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችል መታሰብ ነበረበት ሲሉ የቀድሞ የሲዳማ ክልልነት ውሳኔ ያስከተለውን ችግር አያሌው ጠቁመዋል፡፡

የወላይታ ዞን አመራሮች እስር አንደምታ
የወላይታ ዞን አመራሮች እራሳቸው ከክልል ምክር ቤት እግልለው ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም፣ የክልሉ ምንገስት ህገ ወጥ መሆነ አስራር በመሳተፍ ችግር ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ለእስር ተዳርገዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ አዲስ ማለዳኝ የጠየቁት የክልሉ ፖሊተከኛ የወላይታን የክልልነት ጥያቄ ህዝቡ የተስማማበት መሆኑን በመጠቆም፣ ዞኑ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ወስኖ ዋና መቀመጫውን ሶዶ ከተማ ለማድረግ መወሰኑን በማንሳት፣ ሰሞኑን መንግስት በዞኑ የፈጸመው ድርጊት ከህግ አግባብ ውጭ በሀይልና በአንባገነናዊ አስራር የሄደበት ሁኔታ መታየቱን ይገልጻሉ።ሁነቱን “ወላይታ ላይ የታየው ትንሸ ማሳያ ነው፡፡” የሚሉት ፖሊከኛው ወላይታ ላይ መንገስት የፈጸመው ተግባር መፈንቅለ መንገስት ነው ብላታል፡፡

ዞኑ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ችግሮች መንገግስት ሀላፊነት እንደሚወስድ ተጠያቂ እንደሚሆን አስቀድሞ መግለጹን ያነሱት ፖለቲከኛው፣ ዞኑ ከክልሉ ምክር ቤት ራሱን ያገለለው ምርጫ ስለሌለውና ጥያው ስላልተመለስ ነው ብለዋል።ፖሌከኛው አክለውም “ስብሰባ ላይ ባሉበት የታሰሩ አመራሮች አስር ቤት እያሉ መንግስት ሹም ሽረት አድረጓል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።ሁኔታውም አንባገነናዊ ነው ብለዋል፡፡

ወላይታ ላይ አሁን የተፈጸመው ተግባር በክልሉ ጥያቄ ላነሱ ዞኖች እንደማሳያነት እና የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉም ፖለቲከኛው ገልጸውታል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ በዞኑ መንገስት እየወሰደ ካለው ተመጠጣኝ ያልሆነ የሀይል እርምጃ እንድቆጠብ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታውሳል፡፡

የደቡብ ክልል ቀጣይ ፈተናዎች
በደቡብ ክልል እስካሁን ከ12 በላይ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በአንፃሩ መንግስት የደቡብ ክልልን እስከ አራት ክልል ድረስ ለማደራጀት የክልሉን ህዝብ ፍላጎት አጥኝ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ እንደነበር የሚታወቅ ነው።ነገር ግን በክልሉ የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎች የፌደራል መንግስት ክልሉን እንደ አዲስ በአራት ክልል ለመደራጀት ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ ዞኖች አለመስማማታውን እየገለጹ ይገኛሉ።መንገስት የሲዳማ ክልልነትን ቸኩሎ በመወሰኑ የሌሎችን ጥያቄ በቀላሉ ለመመለስ አስቸጋሪና ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል የፌደራሊዝምና የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አያሌው(ዶ/ር) ይገልጻሉ።አያሌው አክለውም በደቡብ ክልል አሁን የሚታየው ዝንባሌ ክልል በመሆን የሚገኙ ጥቅሞችን ለማግኘት ለውጥ ሳይጠፋ ለመጠቀም ያለመ የሚመስል ሲሉ ገልጸውታል።ከዚያም ሲሻገር አሁን የሚታየው ለውጥ ቢቀለበስ እንኳን ክልል ሆኘ ልጠብቅ የሚል አይነት ቅኝት ያለው ይመስላል ሲሉ አክለዋል።ይሄ ደግሞ የሀገርን የወደፊት እድገት እንደሚፈታተን አያሌው ያምናሉ፡፡

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል የወደፊት ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ ተብለቀው ከሚታሰቡ ጉዳዮች አንዱ የቀድሞው የደቡብ ክልል መቀመጫ የሆነችው ሀዋሳ የወደፊት እጣ ፋንታ ነው።ሀዋሳ ሲዳማ እራሱን በክልል ካደራጀ ወድህ የሲዳማ ክልል እና ደቡብ ክልል መቀመጫ ሆናለች።አሁነ ላይ ሀዋሳ የደቡብ ክልልና የሲዳማ ክልል የጋራ መቀመጫ ነች።የደቡብ ክልል እስከ ቀጣይ አስር አመት ድረስ መቀመጫውን ሀዋሳ እንዳደርግ አቅጣጫ እንደተያዘም ተጠቁሟል፡፡

ነገር ግን ሀዋሳ ከ56 በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች ሀብት የፈሰሰባትና የደቡብ ክልል ህዝቦችን ሀብት የያዘች ከተማ ነች።የደቡብ ህዝቦች ተዋህደው የሚኖሩባት ከተማ ነች።የፌደራሊዝመና የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ እንደሚሉት የደቡብ ጉዳይ ውስብስብና በጥንቃቄ መመራት ያበት ስለመሆኑ አትኩሮት ተናግረዋል፡፡

የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ፖለቲከኛ በበኩላቸው የሀዋሳ ጉዳይ ሀዋሳን ማዕከል አድርጎ የተመሰረተው ሲዳማ ክልል ሲመሰረት አብሮ መታሰብ የነበረበት ጉዳይ እንደነበር ያነሳሉ።ነገር ግን ሀዋሳ ጉዳይ አንዴት ይሁን የሚለውን ጉዳይ መንገስት መግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም ብለዋል።በመሆኑም ህዝቡ ጥያቄ ሲነሳ ያኔ የሀዋሳን እጣ ፋንታ የሲዳማን ክልልነት የወሰነው አካል ይመልሰዋል።እንደት ይመልሰዋል የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል ሲሉም ፖለቲከኛው አክለዋል፡፡

እንደ ፖለቲከኛው ገለጻ የሀዋሳ ጉዳይ ሀዋሳ ላይ የተከማቸው የክልሉ ህዝብ ሀብት ጉዳይ ይልቅ ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ ሀዋሳ ላይ ተዋልዶና ተዋህዶ የሚኖረው ህዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ መሆኑን ጠቁመዋል።ብሔርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት እስካልቀረ ሰድረስ የሀዋሳ ኗሪዎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ፖለቲከኛው አበክረው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታትና የሀገር ሰላም ለመፍጠር መፍትሔዎቹ
የፌደራል ስርዓት በየጊዜው ተለዋዋጭ መሆን እንዳለበት እንደሚታመን የሚገልጹት የፌደራሊዝም መምህሩ አያሌው(ዶ/ር) የክልል ምስረታ አንዱ የፌራሊዝም ስርዓት መሆኑን በማንሳት፣ ክልል ምስረታ እንደ ትልቅ ነገር መወሰድ የለበትም ይላሉ፡፡

በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የክልል ምስረታ ህጋዊ ማእቀፍ እንዳለውና ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉት የሚጠቁመት አያሌው(ዶ/ር) ከቅድመ ሁኔታውቹ መካከል ዋናኛው በቂ ራስን ማስተዳደር የሚስችል ተፈጥሯዊ የኢኮኖሚ ምንጭ መኖር ሲሆን፣ ሌሎችም የህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።በኢትዮጵያም ለሚነሱ የክልልነትና የማንነት ጥያቄዎች ህጋዊ መስረት ያላቸው ቅድመ ሆኔታዎችን መስረት ባደረገ አካሄድ መመለስ አለባቸው ይላሉ ፌደራሊዝም መምህሩ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች የሚመሰረቱበት ሁኔታ ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አያሌው፣ ማንነትና መሰረት አድርገው የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች እስካልቀሩ ድረስ በሀገር እድገት ላይ እንቅፋት መሆናቸው አይቀርም በማለት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች ጉዳት አያሌው አመላክተዋል።

በሌሎች ሀገሮች የክልልነትና የማንነት ጥያቄ የፖለቲካ ጉዳይ እንዳልሆነ ያነሱት አያሌው(ዶ/ር)፣ የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች የሚመለሱት ገለልተኛ የሆነ አካል ተቋቁሞና በሙያተኞች የሚሰራ ስራ መሆኑን አንስተዋል።ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄን ለመተግበር ህገ መንግስታዊ ክፍተት እንዳለ አያሌው ያምናሉ።ለዚህም በህገ መንገስቱ የሚታዩ መሰረታዊ ቸግሮችን አጥንቶ ህገ መንግታዊ መሻሻያ አንዱ የመፍትሔ አማራች መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለዱት ፖለቲከኛ በበኩላቸው የደቡብን ክልል ፖለቲካ ለመቃርና ችግሮችን ለመፍታት በወታደራዊ ሀይል የሚመለስ ጥያቄ አንደሌለ በማንሳት፣ መፍትሔው ያለ ምንም ማመናታት ስልጣንንና የግል ፍላጎትን መሰረት አድረገው ከሚንቀሳቀሱ ህዝብን ወክለናል ከሚሉ ፖለቲከኛች ይልቅ የህዝቡን ፍላጎት አዳምጦ ያለ ምንም ማመናታታ የህዝብን ጥያቄ መመለስ ነው ይላሉ፡፡

ፖለቲከኛው አክለውም ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ በሚለው የአያሌው(ደ/ር) ሀሳብ ተጋርተው የብሔር ክልል ካልጠፋ ችግሩ አያፈታም ብለዋል።
በሌላ በኩል የዞኖችን ክልል መሆን የሚስገኘው ጥቅምና ጉዳት ሲመዘን የቱ ያመዝናል የሚለው ጉዳይ ሌላኛው አጠያየቂ ጉዳይ ሲሆን፣ የፌደራሊዝም መመህሩ አያሌው(ዶ/ር) እንደሚሉት ክልል መሆን ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ያምናሉ።ክልል የመሆን ዋናው መነሻ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደመሆኑ መጠን ክልሎች በበዙ ቁጥር የፌደራል መንግስቱ የኢኮኖሚ እና የአመራር አቅም እንደሚዳከም አያሌው ይገልጻሉ።ስለሆነም የክልልነት ጥያቄ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የፌደራል መንግስቱንና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሌላኛው የመፍትሔ መንገድ መሆኑን አያሌው ይጠቁማሉ፡፡

አንድ የክልልነት ጥያቄ ያቀረበ ዞን ክልል ሆኖ ቢደራጅ የሚገኘው ጥቀም የበጀት ድጎማ፣ በፌደራል ስርዓቱ ላይ ውክልና ማግኘት፣ በማንነትንና ባህል አስጠብቆ መቀጠልና የስራ እድል የሚሉት መሆናቸውን ያለሱት አያሌው(ዶ/ር)፣ በአንፃሩ ክልል መሆን የሚኖረው ጉዳት የፌደራል ስርዓቱ አንደሚፈተን አያሌው ያምናሉ፣ በተጨማሪም ሀገር ኢኮኖሚ ውድቀትና ቀውስ እንደሚስከትል አያሌው ገልጸዋል፡፡

የዎላይታ ዞን ክልል ቢሆን የሚገኘው ጥቅም ካለው ተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ ሀብት አንፃር አጥጋቢ እንዳልሆነ በብዙዎች የሚነሳ ጉዳይ ነው።አያሌው በዚህ ጉዳይ ወላይታ ካለው ተፈጥሯዊ ሀብት አንፃር ብቻውን ክልል ሆኖ ቢደራጅ ጥቅሙ የጎላ ሊሆን እንማይችል አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሰሞኑ በወላይታ ዞን የተፈጠረውን አለመረጋጋት በህግ አግባብ ብቻ እንደሚፈታው የደቡብ ክልል አስታውቋል።መንግስት በአካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ በህግ አግባብ ብቻ የሚፈታው እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብም ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሰላምና ደህንነቱን ሊጠበቅ ይገባል ተብሏል በመግለጫ፡፡

ሌላኛው በዞኑ የተፈጠረው ችግር በማስመልከት መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢሶዴፓ) በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሰው የዞኑ አመራር እና ሕዝብ በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መልስ በሰላማዊ አግባብ ሊሰጠው ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡
ኢሶዴፓ ባወጣው መግለጫ በዞኑ ለተነሳው ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄውን በማንገብ ምላሽ ለመሻት የተንቀሳቀሱትን የወላይታ ዞን አመራር አካላትን እና በጉዳዩ ሳቢያ የታሰሩትን ሁሉ በመፍታት፣ ለተከሰተው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲፈልግ አሳስቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com