ስራ ያቆመው LTV ሰራተኞቹን አሰናበተ

Views: 597

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰራጩ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ የሆነው Ltv ባጋጠመው ኪሳራ ምክንያት መዘጋቱን ሠራተኞች አስታወቁ።
ሠራተኞች እንደሚናገሩት ሰኞ ሐምሌ 28/2012 በኪሳራ ምክንያት ስለመዘጋቱ የሚገልጽ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና መዘጋጃ እንዳልተነገራቸው የገለፁት ሠራተኞቹ ድንገት ሥራውን መቀጠል እንደማይችል እና የሦስት ወር ደሞዝ (ሥራ የማፈላለጊያ) እና የሥራ ልምድ በመስጠት ግንኙነታችን እንደተቋረጠ ነው የተነገረን ሲሉ አስታውቀዋል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ከተጀመረ አራት አመት ያስቆጠረ ሲሆን በስሩም በቋሚነት ተቀጥረው የሚሰሩ የነበሩት 40 የሚጠጉ ሰራተኞች እንደነበሩት ለማወቅ ተችሏል። ባለፉት አራት እና አምስት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ገቢው በመቀነሱ ላይ አንዳንድ ወሬዎች ሲነሱ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በግልፅ ለሰራተኞቹ የተነገረ ነገር እንደሌለ እና በተጠቀሰው ቀን ሲሄዱ ደብዳቤ ተዘጋጅቶ እንደጠበቃቸው የጣቢያው ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው በኤል ቲቪ አስተዳደር ክፍል ውስጥ ሰራተኛ የነበሩት ስም እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምንጭ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ ኤል ቲቪ በበጀት ምክንያት መቀጠል ባለመቻሉ እንደተዘጋ ገልፀው ፤ በዚህም ደብዳቤ ለሰራተኛ የተሰጠው ደግሞ ሀምሌ 28/ 2012 እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ኤል ቲቪ ስራ ከጀመረ አራት አመት የሆነው ቢሆንም እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ የሆነ ሂደት ታልፏል ብለዋል።
ይሄንንም ሰራተኛው ያውቃል፤ ሀሉንም ውሳኔ በስምምነት እንደተጠናቀቀም አንስተዋል። ከዚህ በኋላ ይመለሳል አይመለስም የሚለው ላይ ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

እንደሚታወሰው አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሮድካስተር ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሻው ወልደሚካኤል አናግራቸው በነበረበት ሰዓት ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጊዜ ወዲህ በተለይም በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ያጋጠመው የገቢ መቀነስ በፍጥነት በመጨመሩ፣ ተቋማቱ ሊቋቋሙት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አነስተው ነበር፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ የማኅበሩ አባል የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከዚህ በፊት ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ የሚሰበስቡት በቅድሚያ አገልግሎቱን ሰጥተው እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ሰዓት ግን የአየር ስዓት ሽያጭ እና የንግድ ተቋማት ማስታወቂያ ከመቆሙ ባሻገር ተቋማቱ ለሰጡት አገልግሎት እንኳን የሚገባቸውን ክፍያ መሰብሰብ አለመቻላቸውን ማንሳታቸውም የሚታወስ ነው።

የብሮድካስት ሚዲያ ዘርፉ አብዛኛውን ገቢውን የሚሰበስበው የአየር ስዓት በመሸጥ እና የንግድ ተቋማት ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ እንደሆነ የገለጹት እንደሻው፣ በአሁኑ ጊዜ የንግድ ሥራዎች በመቀዛቀዛቸው የብሮድካስት ሚዲያዎች ገቢ በእጅጉ መቀነሱን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ሚዲያዎች ችግሩን የሚቋቋሙበት እና ያጡትን ገቢ የሚያካክሱበት መንገድ መፍጠር አንዳልተቻለም እንደሻው ለአዲስ ማለዳ ጨምረው አንስተው ነበር፡፡

ነገር ግን የሚዲያዎቹ ችግሩን ተቋቁመው መቀጠል ለመንግሥትም ሆነ ለኅብረተሰቡ፣ በተለይም ስለኮሮና ቫይረስ መረጃ ለማድረስ አስፈላጊ በመሆናቸው፣ በሥራ ላይ የሚቆዩበትን አቅም ለማመቻቸት ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው ብለውም ነበር ።ከዚም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ እየታየ ያለው ችግርም እየከፋ በመምጣቱ እና አንዳንድ ጣቢያዎች እስከመዘጋት እንደደረሱ፣ አንዳንዶች ደግሞ የሠራተኛና የደሞዝ ቅነሳ እያደረጉ መሆኑን እንደሻው ያነሱ መሆኑ ሚታወስ ሲሆን በዚህም እስካሁን ኮሮና ቫይረስ ከመጣ በኋላ እስካሁን ኹለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተዘጉ ሲሆን Ltv ከ Jtv በመቀጠል ኹለተኛው የመዘጋት ዕጣ ያጋጠመው ጣቢያም ሆኗል ።

በተጨማሪም ከኢትዮጲያ ብሮድካስት ባለስልጣን ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ አዲስ ማለዳ ሙከራ ብታደርግም ሳይሣካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com