የተከዜ የብረት ድልድይ በጎርፍ ተወሰደ

Views: 507

 

የተከዜ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ ምክንያት የነዋሪዎች እንቅስቃሴ መገደቡን የስሃላ ሰየምት ወረዳ አስታወቀ።

ችግሩ በየዓመቱ ለሦስት እና ለአራት ወራት የሚዘልቅ መሆኑን የጠቀሰው ወረዳው፤ ከፊሉ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም ጠይቋል።

የስሀላ ሰየምት ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  ጋሻው በደረሰው ችግር ፤ትራንስፖርት በጊዜያዊነት  በመቋረጡና የፈረሰውን ድልድይ በዘላቂነት ለመሥራት ወራትን የሚጠይቅ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በደረሰው ችግር ከ39 ሺ በላይ በሚሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎችም መስተጋብራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርም ጋሻው ገልጸዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን እሸቱ በበኩላቸው በተከዜ የኃይል ማመንጫ ውሃ ምክንያት ለሰመጠው የብረት ድልድይ ተለዋጭ የኮንክሪት ድልድይ እንዲሠራ አስተዳደሩ በየዓመቱ ለክልልና ለፌዴራል መንግሥታት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ አሁንም ለችግር መጋለጣቸውን አመላክተዋል።

ሠው ሠራሽ ኃይቁን አቋርጦ የተሠራው የብረት ድልድይ በውሀ በመሞላቱ ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ሳምንት የሆነው ቢሆንም ችግሩን ለመቀነስ ካለፉት ከቅዳሜና እሁድ ጀምሮ ትራንስፖርቱን በየብስ እና በጀልባ በመቀባበል ማስቀጠላቸውንም አብመድ ዘግቧል።

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com