በሹምሽሩ የደበዘዘው የጃዋር የፍርድ ቤት ውሎ

Views: 201

አንዳንድ ሳምንታት ከሌሎች በተለየ የመነጋገሪያ ጉዳዮች የሚበዙባቸው ይሆናሉ፤ ልክ እንደሰሞኑ። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ትኩረት የሳበው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሹምሽር መካሄዱ ነው። በተለይ ከብልጽግና ፓርቲ አባል ውጪ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆኖ መሾም በአዎንታዊነት የተወሰደ ሲሆን የለማ መገርሳ መተካት ደግሞ ተጠባቂ በመሆኑ አላስገረመም።

የታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ከንቲባነት መነሳትን በተመለከተ ብዙዎች ጉራማይሌ ምላሽ ሰጥተዋል። ከንቲባውን የሚደግፉትና ሥራቸውን የሚደንቁትን ከቦታቸው መነሳታቸውን በቅሬታ ቢፈጥርባቸውም ባሳረፏቸው መልካም አሻራ ይታወሳሉ ሲሉ ተጽናንተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መነሳታቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው፤ እንዲያውም የዘገየነው ሲሉ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና ዝንባሌ መበራከታቸውን ለመከራከሪያነት አቅርበዋል። ከዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለትምህርት በሚል ሰበብ ከንቲባውን ከሥልጣን ለማውረድ ያደረጉት ሙከራ በቄሮ ተቃውሞ መቅረቱንም አስታውሰዋል።

የአዳነች አበቤ ከንቲባ ሆኖ መሾምም እንዲሁ ጉራማይሌ አቀባበል አስተናግዷል። የሴትየዋን ቆራጥነት በመጥቀስ በአንድ በኩል በሙስና፣ በመሬት ወረራና በአገልግሎት መጓደል የተዘፈቀውን አስተዳደር ከአረንቋ ያወጡታል በሚሉ ተስፈኞች ድጋፍ አግኝቷል። ከከተማው ካቢኔ አባላት ጋር በተዋወቁበት መድረክ ላይ “ያቀድነውን ለማሳካት እና የሕዝብ አገልግሎት እርካታን ለመጨመር ቆርጠን መነሳት አለብን” በማለት አቅጣጫ ያስቀመጡበት መልዕክት እዚህ ላይ ተጠቃሽ ሆኗል። ብሔርተኛ በመሆናቸው ደግሞ ልክ የገቢዎች ሚኒስቴርን አድርገውታል እንደተባለው የከተማውን አስተዳደር በአንድ ብሔር ከላይ እስከ ታች እንዳያይጠረንፉት ሲሉ ስጋታቸውን ያስተጋቡም አሉ።

ሹምሽሩ በተለይ የሚኒስትሮቹ ሹመት ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀርብ መካሔዱ ጥያቄ አስነስቷል። አንዳንዶችም መከራከሪያቸውን ሕገ መንግሥት በማጣቀስ ጭምር ተከራክረዋል፤ የዐቢይ አምባገነንነት መገለጫ አድርገውም ወስደውታል።

ሌላው የዚህ ሳምንት መነጋገሪያ ጉዳይ በኹለት ቀናት ልዩነት ለኹለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው ጃዋር መሐመድ ሆኗል፤ አሁንም ድረስ ማነጋገሩን ቀጥሏል። በመጀመሪያው ቀን የፍርድ ቤቱ ውሎ ዐቃቤ ሕግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች ሊያሰማ በተዘጋጀበት ቅጽበት፥ ጃዋር በቀዳሚው ቀን ምሽት መታመማቸውን፣ እንቅልፍ ማጣታቸውንና ምንም ዓይነት ማስታገሻ አለመውሰዳቸውን በመጥቀስ ችሎቱን ለመከታተል እንደማይችሉ በመናገር ችሎት አቋርጠው ሲገቡና ሲወጡ እንደነበር በሰፊው ተዘግቧል።

በተጨማሪም ውጪ አገር የሚገኙ ባለቤታቸውንና ልጃቸውን በቪዲዮ እንዲያነጋግሩ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቀድላቸው አቤቱታቸውንም አሰምተዋል። ይህንን ድርጊታቸው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ተቃዋሚዎቻቸው በበጎ አልወሰዱትም። የፍርድ ቤት ሒደቱን ለማስተጓጎል ሆን ተብሎ የተሸረ በሴራ ነው ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ሌላ ብጥብጥ ማስነሻ መንገድ አድርገው የወሰዱትም አልጠፉም።

በኹለተኛ ቀን የፍርድ ቤት ውሏቸውም፥ ጃዋርን ጨምሮ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ እና ሸምሰዲን የተባሉት ተጠርጣሪዎች ከኮሮና ነፃ መሆናቸው በምርመራ መረጋገጡን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፍርድ ቤቱ ማስታወቁ ትኩረት አግኝቷል። የነጃዋር ደጋፊዎች ይህንን ከበሽታ ነፃ መሆን ውጤት በደስታ የተቀበሉት ሲሆን ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ “ኮሮና ፋራ ነው፤ የሚይዘውን አያውቅም” በማለት ጭምር በሰሙት የምርመራ ውጤት ተሳልቀዋል።

በዚሁ ቀን ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ጃዋር ውጪ አገር ከሚኖሩ ቤተሰቦቹ ጋር በቪዲዮ እንዲገናኝ ያስተላለፈው ትዕዛዝ መፈጸሙን አረጋግጧል። በዕለቱም ጃዋር የቤተሰብ ሐኪም እንዲያያቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ መፍቀዱን የተቃወሙት ዐቃቤ ሕግ፥ “እንደማንኛውም ታሳሪ ፖሊስ ያስመርምራቸው” በሚል የቀረበውን ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። አንዳንዶች “ለምን ምንሊክ ሆስፒታል ወስደው አያስመረምሩተም?” ሲሉ በሾርኔ የተናገሩት ለአንዳንዶች ፈገግታ ያጫረባቸውን ያክል ያናዳደቸውም አልጠፉም።

ኢቲቪ የፍርድ ቤት ውሎውን በዘገበበት ዜና፥ ጃዋር የበቀለ ገርባን ትከሻ ተደግፎ ከችሎት ሲወጣና ወደ መኪና ሲያመራ በሚሳየው ምስል መጠነኛ አካላዊ መክሳት እንዲሁም የድካም ገጽታ መታዘብ ተችሏል።

በዕለቱ ዐቃቤ ሕግ ለቅድመ ምርመራ የኹለት ምስክሮች ቃል ለፍርድ ቤት እንዳሰማ የታወቀ ሲሆን በቅርቡ ክስ እንደሚመሰርት ምክትል ዐቃቤ ሕጉ ፈቃዱ ፀጋ ለመገናኛ ብዙኀን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጃዋር ጠበቃዎች ቁጥር 11 መሆን በራሱ ሌላው አነጋጋሪ ርዕስ ከመሆን አላማለጠም። ባይረጋገጥም የጠበቃቸውን ብዛት እና አንዱ ከሌላው የሚያቀርቡት ሐሳብ የተለያየ በመሆኑ ችሎቱ፥ ሁሉንም በመወከል አንዳቸው ጠቅለል አድርገው መከራከሪያቸውን እንዲያቀርቡ ሐሳብ አቅርቦላቸዋል የሚል ሹክሹክታም ተሰምቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com