መንግሥት እና ፓርቲ እስከ ምን?

Views: 496

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አልረጋ ያለው የካቢኔ ሹም ሽረት እና ተደጋጋሚ መቀያየሮችን አስተናገዷል። ይሄ ሲነሳ በተለይም የጠቅላይ አቃቤ ህግ እና የመከላከያ ሚኒስተር መስርያ ቤቶች አራት እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሃላፊዎች ተፈራርቀውባቸዋል።

ለምሳሌ የመከላከያ ሚንስትርን ሹመት ብንወስድ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ሞቱማ መቃሳ፣ አይሻ መሃመድ ለማ መገርሳ፣ ቀነዓ ያደታ የተፈራረቁበት ሲሆኑ፤ የጠቅላይ አቃቤ ህጉን መስሪያ ቤት ደግሞ ጌታቸው አምባዬ፣ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ አዳነች አቤቤ፣ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አስተናግዳል። ኹነቱ ይሄንን ያክል ሹም ሽር ምን አመጣው አስብሏል? ከሰሞኑ አንጋጋሪ ሆነው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ዋናው እና ያልተጠበቀው ሁነት፤ ባለፉት ቅዳሜና እሁድ ለሁለት ቀናት ከተመሰረተ የመጀመሪያውን ኮንፌረንሱን ያካሄደው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ስብሰባውን ማጠናቀቁ እና እሱን ተከትሎ የመከላከያ ሚንስተር የሆኑትን ለማ መገርሳን ከብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጊዜያዊነት ማገዱ ነበር።

ለውሳኔ እንደ መንደርደርያ በዚሁ ኮንፌረንስ ተነስቶ ከተላለፉ ውሳኔዎች በትልቁ ትኩረት የሳበው ጉዳይም ከወራት በፊት በፓርቲው ተሳትፎአቸው እየደበዘዘ የመጣው፤ አሁን ሃገርን እያስተዳደረ ላለው የለውጥ መንግስት ስኬታማነት ግን የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል የሚባልላቸው፤ የመከላከያ ሚኒስቴሩ ለማ መገርሳ እና ሌሎች ሁለት የፓርቲው አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መታገድ ዋናው ነበር።

የኮንፍረንሱን መጠናቀቅን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ፍቃዱ ተሰማ ኮንፌረንሱ ፓርቲውንና ፓርቲው የሚያስተዳድረውን ክልል አጋጥሞታል በሚል እንደ ክፍተት ገመገማቸው ነበር ካሉት ጉዳይ አንደኛው የአመራሮች በኃላፊነታቸው ልክ አለመስራት መሆኑን ነበር።

በዚህም “በየደረጃው ያሉት አመራሮች ተጨባጭ ውጤት ከማስመዝገብ ይልቅ አውርተው የመኖር አዝማሚያ መስተዋሉ ተገምግሟል” የሚሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው በቅርቡ በክልሉ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ክፍተት አሳይተዋል የተባሉ ከ800 በላይ የወረዳ፣ እንዲሁም 117 የዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮችን ለማጥራት መታሰቡን አንስተውም ነበር።

መሰል ውሳኔ በታችኛው የአመራር እርከን ብቻ መቆም የለበትም የሚል ሃሳብ ከአባላቱ ተነስቷል ያሉት ፍቃዱ ተሰማ በተደረገው ግምገማ ለጊዜው ሶስት የድርጅቱ የበላይ አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታግደዋል። ከነዚህ መካከል አንደኛው የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትና የአሁኑ የመከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ መሆናቸውን አንስተው ነበር።

የጽህፈት ቤት ኃላፊው ፍቃዱ ተሰማ ለማ መገርሳ ከማዕከላዊ ኮሚቴው የታገዱበትን ምክኒያት ሲያስረዱም፤ “ጓድ ለማ በአንድ ወቅት ሃሳባቸውን በሚዲያ መግለጻቸው ይታወሳል። ያንን ተከትሎ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ እሳቸውም ተሳስቻለሁ ብለው ይቅርታ ጠይቀው ነበር። ከዚያም በአመራርነታቸው እንዲቀጥሉ ተደረገ። ይሁንና በብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም ኃላፊነቱን ሰጥቶአቸው የነበረውን አካል ወክለው ድምጽ እንዲያሰሙ ቢጠየቁም ያን አላከበሩም። ይህ ደግሞ በፓርቲው መተዳደሪያ አሰራር ክልክል በመሆኑ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ጉዳዩን ካዩት በኋላ እኚ ሰው ምንም እንኳ አገራዊ ለውጥ በማምጣት ሂደት ውስጥ ትልቅ ክብር የሚገባቸው ቢሆኑም፤ ማንም ከፓርቲውና ከኦሮሞ ህዝብ በላይ ባለመሆኑ፣ በዚህ ኮንፌረንስ ላይም እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ተጠይቀው መሳተፍ ባለመቻላቸው፣ ሃሳባቸውንም ዴሞክራሳዊ በሆነ መንግድ ወደ መድረክ ለማቅረብ ፈቃደንነትን ባለማሳየታቸው፣ ለጊዜው ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታግደዋል” በማለት ተናግረዋል።

ከዛም ጓድ ለማ እንደ ክፍተት የተነሳባቸውን ነጥቦች ለማስተካከል ፈቃደኛ ሲሆኑ ወደ የፓርቲው አመራርነት መመለስ እንደሚችሉ ውሳኔ ላይ መደረሱም ተነስቶ ነበር። ከዛም በተጨማሪ ኮንፌረንሱ የፓርቲው ውስጣዊ ችግር ነው ብሎ የገመገመው ሌላው ጉዳይ የአመራሮቹ የተለያዩ ቦታዎችን መርገጥ ነው ማለቱ ሲሆን ችግሩ በየአመራር እርከኑ በሰፊው የተስተዋለ መሆኑ ተጠቁሞ ነበር። ሌላው በየደረጃው ያሉ አመራሮች ይታሙበታል የተባለው የሌብነት ጉዳይ እንዲለዩና ማስተካከያ እንዲደረግበትም አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል። ውሳኔዎቹ የተላለፉትም በመገፋፋት ስሜት ሳይሆን የፓርቲው አሰራርና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በማሰብ ነው ሲሉም አስረድተዋል ፍቃዱ ተሰማ አንስተው ነበር።

ይህ ኮንፈረንስ በተደረገ ከቀናት በኋላ ነሃሴ 12/2012 ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ (ዶር) የተለያዩ የስልጣን ድልድሎችን እና ማስተካከያዎችን አድርገዋል። በዚህም ድልድል ውስጥ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስተር የነበሩት ለማ መገርሳ ከስላጣናቸው ተነስተው በእርሳቸው ቦታ ቀንዓ ያዳታ( ዶ/ር) የቀድሞው የፖሊስ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት የመነበሩት እንደተኳቸው ተገለፀ።

እንደሚታወሰው የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት ለማ መገርሳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 34ኛውን መደበኛ ስብሰባ ባካሄደበት ዕለት ክቡር ለማ መገርሳን የመከላከያ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ሲሆን ፤ ምክር ቤቱ ሹመቱን ባጸደቀበት ዕለት እንደተገለፀው ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መን ግሥትን በብቃት በመምራታቸው ለበለጠ ኃላፊነት ተሹመዋል ሲል አንስቶ ነበር።

የክልሉ መንግሥት የነበሩት ለማ መገርሳ በአዳማ ከተማ የሽኝት ፕሮግራም ባካሄደበት ዕለት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ ለማ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በርካታ ለውጦች ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በዛም ምክንያት ለከፍተኛ ኃላፊነት ተሹመዋል›› ብለው ነበር።

የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስቴር ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ ጉደያ ቢላ በሚባል ወረዳ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትም ህርታቸውንንም በዚያው ቦታ ተከታትለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በፖለቲካል ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ግንኙንት የባችለር ዲግሪ እና የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ለተወሰኑ ዓመታት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት አቶ ለማ፤ በክልሉ ፀጥታ እና ሠላም በማስፈን እንዲሁም በሌሎች በርካታ ሥራዎች በሚገባ አገልግለዋል።

ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ያበረከቱትን ውጤታማ ሥራ ምክንያት በማድረግም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል።
እንደሚታወሰው የብልፅግና ፓርቲዎች አንድ ላይ ጥምረት በፈጠሩበት ጊዜ ብዙ ቅሬታዎች የተነሱበት ቢሆን ዐቢይ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባደረጉት ንግግር የኢሕአዴግ ውህደትን የተቃወሙ ወገኖች በስም ባይጠቅሱም መልስ ሰጥተው ነበር። ኢሕአዴግ «ባለፉት አመታት የታመመ ድርጅት ነው» ያሉት ዐቢይ ግንባሩን በእንቁላል መስለው «በጊዜ ባንሰብረው ኖሮ ሕይወት ሊወጣው በፍጹም አይቻለውም» ብለውም ነበር ።

ነገር ግን የኢሕአዴግ ውህደት ከግንባሩ መሥራች ህወሓት ባሻገር ከኦዲፒ ምክትል ሊቀ-መንበር እና የመከላከያ ምኒስትር ለማ መገርሳ የጠነከረ ትችት ገጥሞት ነበር በሰዓቱ ይሄንን ከእርሳቸው መስማት ደግሞ አብዛኛው። ለማ ከወራት በፊት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የኢሕአዴን የህብረተሰብ ክፍል ድንዳጤ እና ጥርጣሬ ውስጥ ከቶት ነበር። ለማ በዋናነት በሰዓቱ ሲያነሱት የነበረው ስለ ውህደቱ «ትክክል አይደለም፤ ትክክል ቢሆን እንኳ ጊዜው አይደለም» ሲሉ ተቃውመው ነበር። የጠቅላይ ምኒስትሩ የቅርብ አጋር የሆኑት ለማ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከኦሮሞ ሕዝብ ተቀብሏል ያሉትን ጥያቄ ሳይመልስ ውህደት መፈጸም «እምነት ማጉደል ይሆናል» በማለት ተናግረው ነበር።

ከዛም በተጨማሪ «ይኸን ፓርቲ ማዋሀድ ጊዜው አይደለም። ብዙ አደጋ አለው» ሲሉ ማስጠንቀቂያ ጭምር ሰጥተው ነበር ። ለማ «የሽግግር» ባሉት ጊዜ የአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ከኢሕአዴግ ውህደት በፊት ቅድሚያ ሊሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ለማስተወስ ሞክረው ነበር። «የእኛ ፕሮግራም ኢትዮጵያን የሚያሻግር መሆኑን ካመናችሁ እና ጥያቄ ካቀረባችሁ፤ አሁን አገር በመምራት ላይ ካለን ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎች ድርጅቶች ከእኛ ጋር በመሆን ለመታገል ፍላጎት ካላቸው እንደከዚህ ቀደሙ በራችን ዝግ ያልሆነ መሆኑን እና በመደራደር ማንም ድርጅት ከእኛ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን እንዲያሻግር ፍላጎት ያለን መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።» ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ታድያ ይሄ ሁሉ ክርክር እና መመላለስ ነበረው የብልፅግና ፓርቲ ውህደት ቀደምት የሚባሉትን እና ለመጣው ለውጥ ተብሎ እየተጠራ ላለው መንስት እንደ ዋና መሳርያ ሱጠቀሱ የነበሩ ጓዶችን እርምጃዬን ካደናቀፍክ እና እኔ በሄድኩት ልክ መሄድ ካልቻልክ መቀነስህ አይቀርም የሚል ይመስላል።

የቀድሞ መከላከያ ሚኒስቴር የነበሩት ለማ መገርሳ ከፓርቲው የስራ አስፈፃሚነት ከታገዱ በኃላም ከተሰጣቸው ሃላፊነት እንዲነሱ እና በዕርሳቸው ቦታ ተተኪ እንዲኖር ተደርጓል።

ፓርቲን እና መንግስትን ምን ያገናኛቸዋል ምንስ ያለያያቸዋል?
ይህንንም አስመልክቶ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ሳይንስ እና የፌደራሊዝም ምሁራኖች የተለያየ ማብራሪያ ሰጥተውበት ነበር ።
የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግስቴ(ደ/ር) ፓርቲ እና መንግስት የሚገናኙባቸው እና የሚለያዩባቸው ሂደቶች አሉ። እርግጥ ነው በምንመለከተው ሁኔታ ፓርቲን እና መንግስትን ለያይተን ማሰብ አንችልም። በመጀመርያ አንድ ፓርቲ ተመስርቶ ተደራጅቶ ፕሮግራም እና ሪዮተ አለም ነድሮ ሲንቀሳቀስ የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ ነው። ወደ ተግባር ለመግባት እን እራሱ ባቀደው መሰረት የራሱን ፕሮግራም ለማስፈፀም ብሎም አባላቱን እና ደጋፊዎቹን ለመጥቀም ይንቀሳቀሳል።

ከዛም አለፍ ሲል ስልጣኑን መረከቡን ካረጋገጠ በኋላ የተረከበውን ቦታዎች የራሱን ፕሮግራም እና እቅድ የሚያስፈጽሙለትን ሰዎች( አባላቶች) በእነርሱ ቦታዎችን ሊመድብ (ሊሾም) ይችላል ይላሉ። ከዛ ባለፈ ግን የመንገስት ሰራተኞች (ሲቪል ሰርቫንት) የሚባሉት የሚይዙት ይሆናል ብለዋል። ይሄም ይሁን እንጂ የሚሉት ሲሳያ የገዢውን ፓርቲ ሃሳብ እና ፕሮግራም ግን በዛው ልክ ማስፈጸም ግዴታ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ይሄን አላስፈፅምም የሚል ከሆን ግን ከስራው እንዲወጣ ወይንም እንዲለቅ ሊደረግ ይችላል ይላሉ። ማለትም ይህን ተፈፃሚ የሚያደርጉበት በህጉ መሰረት ( በዲሲፒሊን) በስነምግባር ጥሰት ተገምግሞ ሊባረሩ ይችላል። ነገር ግን የሚሉት ሲሳይ አሜሪካን ሀገር እንደ ምሳሌ አንስተው አንድ ፓርቲ አሸንፎ ወደ ስልጣን ሲመጣ አስከ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ቦታዎችን መንግስት ከነበረው ፓርቲን ያገለግሉ ከነበሩት አባላት ተነስተው በአዲሱ ፓርቲ ሸዋሚዎች ይተካሉ። እኛ ሀገር ላይ ግን አንድ ፓርቲ አሽንፎ ወደ ስልጣን ሲመጣ ሊይዛቸው የሚገቡ ቦታዎች ተብለው አልተለዩም ቁጥራቸውም አይታወቅም። ግን ቢያንስ ሚኒስትሮች፣ ምክትል ሚኒስቴሮች ፣ ዳይሬክተሮች ፣ ምክትል ዋና ዳሬክተሮች እየተባለ ነው ቦታው የሚያዘው።

ይሄም ቢሆን ግን የፓርቲው ስራ እና የመንግስት ስራ ይለያያል። ፓርቲውን እየመሩ የሚቀጥሉ የፖለቲካ አመራሮች ይኖራል፤ አብዛኞቹ የአሸናፊ ፓርቲ አመራሮች ወደ መንግስት ሃላፊነት ይመጣሉ።

በአሸናፊ ፓርቲ እና በመንግስት መካከል ጥርት ያለ ልዩነት አልተቀመጠም ያሉት ሲሳይ፤ ይሄም ሆኖ አንዳንዴ ፓርቲው እና የመንግሰት መደበላለቅ ካለ ችግር ይፈጠራል። የሚያመጣውም ተፅዕኖ ሲናገሩ፤ ፓርቲው ራሱን ስራዎች መስራት ሲገባው ተደበላለቀ ስርዓት ፣ ወገንተኝነት እና ስህተቶች የበዙበት ስራ ለመስራት ይጋብዘዋል።

መሆን ያለበት የሚሉት ሲሳይ ብቃት ያላቸውን እና በፓርቲው ላይ ለውጥ ያመጡልኛል ብሎ የሚስባቸውን አስገምግሞ በፓርቲው ስራ ላይ ቦታ መስጠት ከዛም ባሻገር ያለውን የመንግስት ስራ ደግሞ ቀድሞም የነበሩ ሰዎችም ይሁኑ አዳዲስ ሰዎች ከፓርቲው ጋር አለማገናኘት መልካም ነው ይላሉ።
ደመቀ አቺሶ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ እና የውጭ ግንኙነት መምህር የሆኑት በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያታቸውን እንደሰጡን ከሆነ አብዛኛውን ሃሳብ ከ ሲሳይ መንግስቴ ( ዶ/ር) ጋር ይጋራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com