የቢሊዮነሩ ዋረን ባፌት ዘመን አይሽሬ የንግድ ምክሮች

Views: 272

ገንዘብን ንግድ ላይ ማዋል ሮኬት እንደማስወንጨፍ ባይከብድም ቀላል አለመሆኑን ግን እንወቅ ይላሉ፤ ዋረን ባፌት። በንግድ ሥራ ላይ ስኬታማ መሆን የቻሉ ሰው ናቸው። በሄዱበት መንገድ የቀናቸውና የተሳካላቸው ሰዎች ደግሞ በዛው መንገድ ሊሄዱ ለወደዱ ለተከታዮቻቸው መንገድ የሚያቀኑ ናቸውና፣ አብርሐም ፀሐዬ የእኚህን የቢሊዮነር ልምድና ምክር አውስተዋል።

‹‹ቢያንስ ለቀጣይ ዐስር ዓመታት ይዘህ ልትሠራው የማታምንበትን ንግድ ለዐስር ደቂቃ እንኳን አታስበው››
ዋረን ባፌት።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር አሁን ባለንበት በወርሃ ነሐሴ 1930 ላይ የተወለዱትና ከዓለማችን ምርጥ ዐስር ግንባር ቀደም ቢሊዮነሮች መካከል አንዱ የሆኑት አሜሪካዊው አዛውንት ዋረን ባፌት፣ ያላቸው የንግድ ሐሳብ አሁን አዲሱ ዘመን እያመነበት እስካለው ውጤታማ የንግድ ስርዓት ድረስ የተሻለና ተቀባይነት ያለው ነው።
ሰውየው የንግድ ሥራንም ሆነ ትምህርትን አሃዱ ያሉት በዐስራዎቹ የዕድሜ ክልላቸው ነው። ይህም ልምድና ዕውቀታቸውን ተፈላጊ አድርጎታል። የሚከተሉት ምክሮቻቸውም ብዙዎች እንደ መመሪያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ገንዘብህን የምታውቀው ንግድ ላይ አውል
በማታውቀውና በቅጡ ባልገባህ ንግድ ላይ ገንዘብህን ለማፍሰስ አትሞክር። ሌሎች የሠሩትና ያተረፉበት አልያም እነርሱ የተሳካላቸው ንግድ ለአንተም ይሆናል ማለት አይደለም። ይህንን ጉዳይ ሲያጠነክሩትም ልትሠራበት የፈለከውን ንግድ ለሌሎች የማስረዳት ብቃት ላይ እስከምትደርስ ድረስ እንዳትጀምረው።
የሥራው አካሄድ ካልገባህ ተወው። ትተህም ወደምታውቀው ተሸጋገር። በአጠቃላይ ነገ የት እንደሚያደርስህ መተንበይ የማትችለውን ንግድ በአጉል ድፍረት አትጀምር።

በጥራት ላይ አትደራደር
ለንግድ ሥራዎችህ ጥራት ሊጨምሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ገንዘብ ለማውጣት ራስህን አታቅብ ወይም ወደኋላ አትበል። ጥራት ወጪ ሳይሆን ገቢ ነው። የሚያስወጣው ገንዘብ አነስተኛ ነው በሚል የሚጀመር ሥራ አደጋ ሊኖረው ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ጥራት ላይ ትኩረት ባለመስጠት የሚከሰት መሆኑ ነው።
ለጥራት በጀት ያልመደበ ንግድ በኪሳራ የመደምደም ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። ጥራት ጥቅም ነው፣ ጥራት ትርፍ ነው፣ ጥራት ዘላቂ ንግድ ነው። ጥራትን አስቀድም። ስለሆነም ለጥራት የገንዘብ በጀት መድብ።

ዘላቂነት
አንዴ እገባበታለሁ ብለህ ለምትወስነው ንግድ እስከመጨረሻው እንደምትዘልቅበት አምነህበት ይሁን። ራሳችንን ከተራ ግዢና ሽያጭ ንግድ አውጥተን ጥራት ባለው ሥራ ላይ በመሣተፍ ዘላቂና አዋጪ ንግድ መመሥረት እንችላለን። ይህ ውሳኔ ውጤታማ ንግድን እንዴት በዘላቂነት ይዘን መሄድ እንችላለን ብለው ለሚሰጉ መልስ ይሆናል።

ሥራህ እና ንግድህ የተለያየና የተበታተነ አይሁን
ንግድህን ስታቅድ ዘላቂነቱን፣ ልትቆጣጠረው ስለመቻልህ፣ የገንዘብ ወጪና ትርፋማነቱ አዋጪ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሁን። ሥራህ፣ ውሎህ፣ ሐሳብህ ልትጀምር ከምትፈልገው ንግድ ውጪ ሆኖ ሳለ ልሥራ ብሎ መነሳት ገና ከመነሻው እንደማያሸንፉ አምኖ የመሮጥ ያህል ነው።
በደንብ በምናውቀውና በሚገባ በምንቆጣጠረው ንግድ ላይ ጊዜያችንና ተግባራችን ይዋል። ንግድ ወደን ልንሠራው የምንችለው እንጂ በይሆናል የምንገባበት ሊሆን አይገባውም።

አብዛኞቹ የምንሰማቸው መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ ስለማድረግ
ሁሉም ዜና ዜና አይደለም ወይም አይጠቅምም። የምትሠማውን መረጃ ሁሉ ተከትለህ አትሂድ። በመገናኛ ብዙኀንም ሆነ በሌላ መስመር የምንሰማቸው መረጃዎች የራሳቸው የጀርባ ዓላማን ያነገቡ ሊሆኑም ይችላሉና አስተውል። ዋረን ባፌት ሲናገሩ ‹‹ሌሎች ሰዎች 80 ከመቶ የሚሆነው ውጤትህ የሚመጣው 20 በመቶ ከሚሆነው ውጤታማ ሥራህ ነው ይላሉ። እኔ ደግሞ የምልህ ሁሉም መረጃ መረጃ አይደለም።

እንደውም 99 በመቶ የሚሆነው በጤናማ መንገድ የመጣ ውጤታማ ንግድ በአግባቡ ተሰላስሎና ተስተውሎ በጥንቃቄ በተመረጠ አንድ በመቶ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተወሰነ ነው እልሃለሁ።›› ብለዋል። በዚህ ላይም ሲያክሉ የሰማኸውንና ያነበብከውን መረጃ በአስተውሎት መበለት መቻልህን አትዘንጋ ብለዋል።

አቅልለህ አትመልከት
ቢሊዮነሩ ዋረን ባፌት አታካብድ በሚለው ንግግር የሚስማሙ አይመስሉም። ገንዘብን ንግድ ላይ ማዋል ሮኬት እንደማስወንጨፍ ባይከብድም ቀላል አለመሆኑን ግን እንወቅ ይላሉ። ይህን ካሉ በኋላም የንግድ ሥራን ቀላል ነው የሚል ነጋዴ የያዘው ንግድ እርባና ቢስ መሆኑን አልጠራጠርም ብለው ይጨምራሉ።
ዋረን ባፌት ምክንያቱን ሲጠቅሱም ንግድ ማለት የማሳመን ጥበብ ነው። ይህ የማሳመን ጥበብ ደግሞ ዕውቀት ነው። ማርክ ትዌይን እንደሚለው ሰዎችን ማሳመን እንደማሞኘት የቀለለ ጥበብ አይደለም። ይህንንም ሲል ንግድ ጥበብ ነው ማለት ነው በማለት ይደመድማሉ።

ገንዘብን እና እሴትን መለየት
ወደገበያ ድርሻ የሚገቡ የንግድ ሰዎች ስለሚሳተፉበት የንግድ ዓይነት ሊያውቋቸው የሚገቡ ኹለት ነገሮች አሉ።
አንዱ ንግድ ጊዜያዊ የገንዘብ ጥቅሙ ከፍ ያለ ሲሆን፣
ኹለት በምርቱና አገልግሎቱ ጥሩ ሥም ይዞ የሚቀጥል ነው።

አንዳንዶች ገንዘብ ላይ ብቻ አተኩረው በመግባት ከጊዜ በኋላ የመክሰም አደጋ ውስጥ ይገባሉ። ከዚህ በላይ ግን ንግዱ ያቀረበው ምርትና አገልግሎት ተፈላጊነትን የሚያመጣ መልካም ስም ለተከታታይ ጊዜ ወጥ አድርጎ ቢገነባ የተፈለገውን ሁሉ ማግኘት ያስችላል።

የስኬት ጉዞዎች አሰልቺና ድብርታም መሆናቸውን መረዳት
እንደምሳሌ ብንወስድ የገበያ ድርሻን መግዛት ማለት ፈጥኖ ሀብትን የማግኛ አቋራጭ ዘዴ አይደለም ይላሉ ዋረን ቡፌት። ይልቁንም ቀስ እያለ የሚጓዝ፣ በሂደት ከፍ እያለ የሚነሳ፣ የተረጋጋ የሀብት ስሪትና ዕድገት ነው። አንዳንዴ ድንገት በአጋጣሚ የተተኮሱ ነጋዴዎችን ዐይተን አንታለል።
ይህ ዓይነቱ ክስተት የሚያጋጥመን ከውቅያኖስ ውሃ ውስጥ በጭልፋ የመጭለፍ ያህል ነው። ትክክለኛ የንግድ ስርዓት የማይወክሉትን ምሳሌ አታድርጉ። እነዚህ ሰዎች ያልሆነ መንገድ ተጠቅመውም ነውና። ቀሰስተኛና አሰልቺ የሚመስለውን የንግድ መንገድ በትዕግስት የጨረሰ ተጓዥ ከጥሩ መዳረሻ ላይ ማረፉ አይቀርም ይላሉ።

በአነስተኛ ዋጋ ማምረትን አነስተኛ ወጪ መጠቀምን አለመርሳት
ብዙውን ጊዜ ትልቅ አደጋን አላስፈላጊ በሆነ ሁኔታ መጋፈጥ አግባብ አይደለም። በስሜት መመራትም እንዲሁ። ከአቅማችን በላይ በሆነ ሥራ ለይ መግባትም ለኪሳራ ይዳርገናል። ጥናት ላይ ሳይመሰረቱ ያልተገባና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ትርፍን አመጣለሁ ብሎ መሟሟት ሞኝነት ነው። በተቻለ መጠን የመጨረሻው አነስተኛ ወጪን በጥራት አስደግፎ መጠቀም ላይ መትጋት ይኖርብናል። ለዚህም ብዙ በር ማንኳኳትን ይጠይቅ ይሆናል። መፍትሄው ደግሞ ማንኳኳቱ ላይ መትጋት ነው።

አድምጥ
የምታምንባቸውንና የምታውቃቸውን ሰዎች አድምጥ። በቅርጫት ውስጥ ያስቀመጥከው እንቁላል አንዳይሰበር ከአንተ በላይ የሚጨነቅና የሚጠነቀቅ አይኖርም። የራስህ ንግድም ዋና ተጨናቂው አንተ ነህ። እናም ሁነኛ ሰው ከመፈለግ፣ ከመጠየቅና ከማድመጥ አትቦዝን። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ጥሩ የሆነ የመግባባት ባህሪን ገንባ። ይህም ነገሮችን ወደ አንተ የምትስብበት ማግኔት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com