የእለት ዜና

ወደ ውጪ ከተላኩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

በተጠናቀቀው በጀት አመት ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሆኑ ድርጅቶች ወደ ውጭ አገራት ከላኳቸው የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፊጤ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገልጸዋል።

ገቢው የተገኘው በበጀት አመቱ 11 ወራት ጊዜ ውስጥ በኢንስቲትዩቱ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግን ንዑስ ዘርፍ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የግል ድርጅቶች ሲሆን ወደ 30 የሚሆኑ መዳረሻ ሀገራት የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ (ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ) ምርቶችን በመላክ 37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም አስታውቋል።

እንደ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነም ገቢው የተገኘው ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ከሚያርግላቸው ከ 20 በላይ ከሚሆኑ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ኩባንያዎች ሲሆን ምርቶቻቸውን ወደ ጎረቤት አገራት፣ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቁል፡፡

ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች መካከልም ተሽከርካሪዎች፣ተንቀሳቃሽ የዕጅ ስልኮች፣ አልሙኒየም፣ ቆርቆሮ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ይገኙበታል ሲሉም አክለዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም በመሠረታዊ ብረታ ብረት በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች 14 ሚሊዮን 500 ሺህ ዶላር ለመላክ ታቅዶ 3 ሚሊዮን 409 ሺህ ዶላር መገኘቱን በመግለጽ ይህም በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ 41 ሚሊዮን 247 ሺህ ታቅዶ በአፈፃፀም 33 ሚሊዮን 593 ሺህ በላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ቀንሷል ያሉት ፊጤ፤ ቀደም ሲል የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩም ኢንዱስትሪዎቹ የአቅማቸውን ያህል አምርተው ለገበያ እያቀረቡ እንዳልነበረም በምክንያትነት ገልጸዋል።

እንዲሁም ለኩባንያዎቹ ምርት ግብአቶች ከውጭ አገራት የሚመጡ በመሆናቸው በተለያየ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ምርት ማምረት አለመቻሉን አመላክተዋል።
ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ወይም የወረርሽኙን ሁኔታ እየተቋቋሙ ምርቶቻቸውን እንዲያመርቱ እየተሰራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከላከላቸው አገራት መካከልም ኬንያ፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቱርክ አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጀርመን አሜሪካ፣ እስራኤል እና ሞሮኮ ተጠቃሾቹ ናቸው።

ኢንስቲትዩቱ በ2012 በጀት ዓመት በመሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ የምርት ዘርፎች ዕቅድ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ምርትችን ወደ ተለያዩ አገራት ለመላክ አቅዶ ማሳካት የቻለው ግን ከ 4 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑ ታውቐል፡፡

በተመሳሳይም በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርት ዘርፎች 45 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ወደ ተለያዩ የዓለም መዳረሻ ገበያ ለመላክ ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን ከ37ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በሁሉም የንዑስ ዘርፉ በበጀትአመቱ 60,841,607.44 ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ 40,360,795.20 ማሳካት የቻለ ሲሆን ይህም ከዕቅዱ 66.3375% መሆኑን እና የከባለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ14.6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ፊጤ ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!