የእለት ዜና

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአውቶሞቲቭ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለውን ኢኮኖሚ ስርዓት ታሳቢ በማድረግ የገቢ ምርትን ለመተካት በመታሰቡ አዲስ አውቶሞቲቭ ፖሊሲ ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲዋን በአሁኑ ወቅት እያሻሻለች የምትገኝ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የአውቶሞቲቭ ንዑስ ዘርፍ ፖሊሲ በማርቀቅ ሂደት ላይ ትገኛለች። የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲው ከወጪ ምርት (export promotion) ወደ ገቢ ምርት መተካት (import substitution) የሚቀየር ሲሆን አዲሱ የአውቶሞቲቭ ፖሊሲም በዚሁ ቅኝት መሰረት በንግድና ኢዱስትሪ ሚኒስቴር እና በኢንቨስትመንት ኮሚሽን እየተዘጋጀ እንደሚገኝ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና የኬሚካል ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ዮሀንስ ድንቃየሁ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የአውቶሞቲቭ ፖሊሲ እሳካሁን ድረስ ያልነበራት ሲሆን ይህም ማቆጥቆጥ የጀመረውን የዘርፉን እድገት ወደፊት እንዳይራመድ እና ከውጪ ከሚመጡት ያለቀላቸው የተሸከርካሪና ምህንድስና ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ እንዳይሆን አድርጎትእንደቆየም ተጠቅሷል።

አዲሱ ፖሊሲ አውቶሞቢሎችን፣ ባሶችን እንዲሁም የኮንስትራክሽንና የግብርና ተሸከርካሪዎችን በአገር ውስጥ የማምረት እድልን ከመፍጠሩም ባሻገር እራሱን የቻለ የመለዋወጫ እቃዎች ኢንዱስትሪ ፓርክም ማቋቋም አላማው ማድረጉን ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።

በዚህም ትላልቅ አለም አቀፍ የመኪና አምራቾች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ፋብሪካቸውን እንዲተክሉ የሚደረግ ሲሆን በመጪውም 2013 የጃፓኑ ቶዮታና የደቡብ ኮሪያው ዴዎ ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ እቅድ መያዙን የብረታ ብረት ኢንደስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ደረጄ አስፋው ተናግረዋል።

ከዚሁም ጋር ተያይዞ ለረጅም ጊዜያት በተሸከርካሪ አስመጪነት ስራ ውስጥ የቆዩ እንደ አምቼ ያሉ ድርጅቶችም ወደ ማምረት ሂደት ውስጥ እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የመኪና ፋብሪካዎች ወደ ገበያው መግባት የጀመሩ ቢሆንም በአገሪቱ ያለው ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ተሸከርካሪ ከውጪ የሚመጣ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ተሸከርካሪዎች ያሉ ሲሆን በአገሪቱ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ የግንባታ ማሽነሪዎች ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የሚገኘው የተሸከርካሪ ገበያ ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ቢሆንም ዘርፉ ለአገር ውስጥ አምራቾች ምቹ የሆነ ሁኔታን ሳይፈጥር መቆየቱ ይታወቃል።

በባለፉት 10 ዓመታት አገሪቱ የብረታ ብረት ውጤቶችን ከውጪ አገራት ለማስገባት 53.5 ቢሊዮን ዶላር ያወጣች ሲሆን ከዚህም ውስጥ 5 በመቶው ወይንም 3 ቢሊዮን ዶላር ለተሸከርካሪ፣ 31 በመቶ ወይንም 17 ቢሊዮን ለማሽነሪዎች እንዲሁም 54 በመቶው ወይንም 29 ቢሊዮን ዶላር ለመሰረታዊ የብረት ውጤቶች አውላለች ያሉት ደግሞ በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት የእቅድ እና ህዝብ ግንኑነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጥላሁን አባይ ናቸው።

ኢንስቲዩቱ ባሳለፍነው ሐሙስ ነሐሴ 21/2012 ያለፈውን የ5 አመት አፈፃፀም ገምግሞ የቀጣይ 10 አመታት እቅዱን ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ነው ይህ የተነገረው። በአጠቃላይ ዘርፉ በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት እጅግ ዝቅተኛ አፈፃፀም እያሳየ በመሆኑ በቀጣይ ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብ የመፍትሄ ሀሳቦች በአምራች ማህበራት በኩል እየተዘጋጁ መሆኑም ተገልጿል።

በአፍሪካ ውስጥ የአውቶሞቲቭ ፖሊሲ ያላቸው አገራት በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን በዚህ ዘርፍ ውጤታማ እየሆኑ ያሉት እንደ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ በአዲሱ የአስር ዓመት የልማት እቅድ መሰረት በ2022 እ.ኢ.አ ከአፍሪካ የኢንዱስትሪ አምራች አገራት ተርታ ውስጥ የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ ያቀደች ቢሆንም እስከዛሬ የአውቶሞቲቭ ዘርፍ ፖሊሲ ሳይኖራት ቆይቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!