ኑሮ እና ደም-ወዝ

Views: 117

ሰጥቶ የመቀበል ቀመርን ዋነኛ መርህ ባደረገች በምንኖርባት ዓለም፤ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ እልፍ አእላፍ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ያሳልፋል። እነዚህን የሕይወቱን ውጣ ውረዶች በማቅለል ብሎም ኑሮውን የተደላደለና ምቹ ከማድረግ አንፃር ገንዘብ የሚጫወተው ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም።

ሁሉም ሰው ገንዘብ ሊያገኝ የሚጥርባቸውና የሚያገኝባቸው መንገዶች ልዩ ልዩ ቢሆኑም፣ አዲስ ማለዳ ተቀጥሮ በመሥራት ወር ተጠብቆ ስለሚገኘው ክፍያ /ወይም ደም-ወዝ/ እንዲሁም ስለ ደሞዝተኛው የደሞዝ አጠቃቀም ባህል በጥቂቱም ቢሆን ዳሰሳ አድርጋለች።

በእያንዳንዱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን፣ የምንፈልገውን በምንፈልገው ጊዜና መጠን እንድናገኝ ገንዘብ የሞተሩን ድርሻ ይወስዳል። ታዲያ ሰዎችም የዓለምን የኑሮ ውጣ ውረዶች አልፎና አሸንፎ የተደላደለና ምቹ ሕይወትን ለመምራት በሚያደጉት የእለት ከእለት ጥረት ውስጥ ይህ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው ተብሎ የሚታመንበትን ገንዘብ ለማግኘት የማይቧጥጡት ዳገት፣ የማይንደረደሩት ቁልቁለት አይኖርም። ‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን…ቀበሮ ብታልም ጎሬዋን› እንዲሉ።

መቼም ደሞዝን ከወር እስከ ወር አብቃቅቶ ለመጠቀም የደሞዙ መጠንና የደሞዝተኛውን የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው። የአጠቃቀም ብልሀትና ጥበብም ሊታከልበት እንደሚገባ ግልፅ ነው። ካልሆነ ግን ለኪሳራ ይዳርጋል። እዚህ ጋር አንዲት ግጥም ጀባ ልበላችሁ፤ ርዕሱ ‹ጥሮ ግሮ ጠጣ› ይላል።

‹ደሃ ድህነቱን ፈጽሞ ይረሳ ዘንድ፣
አብዝቶ ይጠጣ ከመጠጥ ይዛመድ።
…ብሎ ቅዱስ ቃሉ ያዘዘው ይመስል፣
ያነጋል ወገኔ ጉበቱን ሲያቃጥል፣
የአንድ ወር ልፋቱ ደም-ወዙ ሲመጣ፣
በማግስቱ ባዶ…ጥሮ ግሮ ጠጣ።›

የኑሮ ውድነትና ደሞዝ
አሁን ላይ በአንድ የሥራ መስክ ላይ ብቻ ተሰማርቶ የሚገኝን ደመዝ ወር እስከ ወር አብቃቅቶ እና ቆጥቦ መጠቀም እጅግ ከባድ ፈተና መሆኑ ብዙዎቻችንን የሚያስማማ ጉዳይ ነው። በአንድ የመንግሥት ወይንም የግል መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ ሠራተኛ ጎን ለጎን ተጨማሪ ሌላ ገቢ ከሌለው በስተቀር ወሩን ሙሉ ያለመታከት ሠርቶ የሚያገኘውን ደሞዝ ቆጥቦ የልቡን ሊያሟላ ይከብደዋል።

ቤተሰብ መመሥረት፣ ቤት መሥራት፣ መኪና መግዛትና ሌሎች ቅንጦት የሚመስሉ ነገር ግን ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ንብረቶችን መሸመት ይቅርና የእለት ጉርሱን ችሎ፣ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ወሩን ሙሉ የተበደራትን ብድር ከፋፍሎ ሲጨርስ የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎቹን ለመሸፈን እስኪከብደው ድረስ በኪሱ ውስጥ የሚቀር ገንዘብ አይኖረውም።

ይህን ስንል ታዲያ የኑሮ ፈተናው ከአንድ በላይ የሆኑ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ተቀጥረው ከፍተኛ ክፍያን የሚያገኙትን አይነካም ማለቴ አይደለም። በይበልጥ የፈተናው ገፈት እኚሁ በአንድ መሥሪያ ቤት ብቻ ተቀጥረው የሚያገኟትን ትንሽ ደሞዝ በማብቃቃት ኑሮቸውን ለመግፋት የሚታትሩት ሰዎች ላይ ይበረታል በማለት ነው።

አንድ ገጠመኝ እናንሳ። አንዴ ነው አሉ፣ አንድ የግል ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ሠራተኛ እንደ አጋጣሚ እድሉን አግኝቶ በአንድ ሆቴል ከአለቃው ጋር ምሳ እየበላ ነው። ምሳው ተበልቶ እንዳለቀ አለቃው ‹‹እንዴት ነው ተመቸህ ምን ይጨመር?›› ይለዋል፤ ሠራተኛው ቀበል አድርጎ ‹‹ደሞዝ! ደሞዝ ይጨመር›› በማለት የሆዱን ብሶት ሳያስበው አለቃው ፊት ዘረገፈው።

እንደረጃው ይለያያል እንጂ የአብዛኛው ደሞዝተኛ ፍላጎት ከዚህ አያልፍም። በሚሰራው ስራ ልምድ እና ብቃቱን በማሳደግ ደሞዙንም ሆነ የኑሮ ደረጃውን ማሳደግ ይሻል። ነገር ግን አሁን ገሀዱ ዓለም ሹክ እንደሚለን ከሆነ ምንም ያህል ደሞዛችን ቢያድግም በዛው ልክ ፍላጎታችን እና የዋጋ ግሽበቱም በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ነው።

ጌቱ አስማረ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ የሚሠራ ወጣት ነው። በትምህርት ቤቱ ከ2000 ጀምሮ እንዳገለገለ ይናገራል። በመጀመሪያ ሥራ ሲጀምር መነሻ ደመሞዙ 625 እንደነበር እና በአሁኑ ወቅት የተጣራ 5430 ብር እንደሚያገኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ አስታውሷል።

‹‹ነገር ግን›› ይላል ጌቱ ‹‹…ነገር ግን በአንፃራዊነት ሳየው ቀድሞ ሥራ ስጀምር የሚከፈለኝ ለኔ በጣም ትልቅ ገንዘብ ነበር። አሁን ከሚከፈለኝ እና ሥራ ስጀምር የሚከፈለኝ መካከል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ልዩነት ቢኖርም በኑሮ ውድነት ሳቢያ እንደውም ከቀድሞው ጊዜ በተለየ መልኩ አሁን አሁን ደሞዜን ከወር እስከ ወር አብቃቅቶ መጠቀሙ እጅግ እየከበደኝ መጥቷል።›› ሲል ይገልፃል።

‹‹በፊት ከነበረኝ ደሞዝ አኳያ የአሁኑ ደሞዝ ከፍተኛ ቢሆንም የገንዘቡ ቁጥር ጨመረ እንጂ ሌላ ለኔ የጠቀመኝ ነገር የለም።›› የምትለው ደግሞ ትዕግስት አሰፋ ናት። ትዕግስት እንደ ጌቱ ሁሉ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በፋይናንስ ሠራተኝነት እየሠራች የምትገኝ ሲሆን በድርጅቱ ውስጥ ሥራ ከጀመረች ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በድርጅቱም ከ200 ብር ደሞዝ ጀምራ በአሁን ወቅት የተጣራ የ6671 ብር ተከፋይ እንደሆነችም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ አንስታለች።

ትዕግስት ሥራ በጀመረችበት ወቅት የነበራት ወርሃዊ ወጪና በአሁኑ ሰዓት የምታወጣውን ወጪ በማነፃፀር ስታስረዳ እንዲህ ትላለች ‹‹በእርግጥ የዛን ጊዜ በማገኛት 200 ብር እና አሁን በማገኘው ክፍያ መካከል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ልዩነት ያለ ቢሆንም፤ የዛን ጊዜዋ 200 ብር ግን ለኔ ትልቅ ዋጋ ነበራት። ምክንያቱም በዛን ጊዜ ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር የማወጣው ወጪና የማገኘው የብር መጠን የተመጣጠነ ነበር።

አሁን ግን የብሩ መጠን ቁጥር ብቻ ነው የሆነብኝ። እያንዳንዱ ነገር ጨምሯል፣ ያልጨመረ ነገር የለም። ስለዚህ ምናልባት ሲታይ በፊት ከነበረኝ ደሞዝ አኳያ የአሁኑ ደሞዝ ከፍተኛ ቢሆንም የገንዘቡ ቁጥር ጨመረ እንጂ ሌላ ለኔ የጠቀመኝ ነገር የለም።›› በማለት ከገጠመኟ አጣቅሳ ታስረዳለች።

የደሞዝ ወቅት እና ደሞዝተኛ
በአብዛኛው የደሞዝተኛ ቀን አቆጣጠር ስሌት መሰረት ደሞዝ ከወጣበት እለት አንስቶ በተከታታይ ባሉት አምስት ቀናት ገፋ ካለም ዐስር ቀናት ድረስ ያለው ጊዜ ለደሞዝተኛው የተለየ ወቅት ነው። በእነዚህ ቀናት ደስታ እና ፈንጠዝያው ልዩ ነው ብለው የሚምኑ አሉ። አካሄድ፣ አወራር ሰላምታ አሰጣጥ ሳይቀር በፈገግታ የታጀበበ ይሆናል ሲሉም ደሞዝ የተቀበለ ሰው በመጀመሪያ ሰሞን የሚያሳየውን ሁኔታ የሚገልጹ አሉ።

‹‹በየሄደበት ካልከፈልኩ ያበዛል። በየመንገዱ የሚያየውን ነገር ሁሉ ለመግዛት ልቡ ይከጅላል። ከዚህ በፊት በአውቶቢስ ይጠቀም ከነበረ የደሞዝ ሰሞን ታክሲ ያዘወትራል። መሸት ካለበት ወይ ደግሞ ከቤቱ እራቅ ካለም ኮንትራት ይጠራል። ባለፈው ወር የተበደራቸው ብድሮች ካሉም ያለ አንዳች ጭቅጭቅ ከነወለዳቸውም ቢሆን ይከፍላል።›› የሚሉ ሐሳቦችም ይታከላሉ።

ነገር ግን ይህ በዚህ እንደማይቀጥል ሁሉም ይስማማሉ። ከቀናት ወይንም ከአንድ ኹለት ሳምንታት በኋላ በኪሱም ሆነ በባንክ አካውንቱ ያለው ገንዘብ እየቀነሰ መሄዱን በድንገት ይረዳል። በዚህ ጊዜ ደሞዝተኛው የለመዳቸውን ነገሮች ሁሉ ቢያንስ በግማሽ መቀነስ ይጀምራል። እንደ ቀድሞው ቀደም ቀደም እያለ ወደ ኪሱ ከመግባት ይታቀባል። ወዳጅ ጓደኞቹ ጋር እንደወትሮው እግር ከማብዛት ይቆጠባል። በፌሽታው ጊዜ እንደ ድንገት ሆኖ ለሰው ገንዘብ ካበደረም ያንን ሰው በእግር በፈረስ ማስፈለግ ይጀምራል።

ይህ ወቅት ታዲያ የደሞዝተኛው የአርምሞ ወቅት ነው ይሉታል። ደሞዝ በወጣበት ሰሞን ያለአግባቡ ያጠፋቸውን ገንዘቦች በማሰላሰል ቁጭት ያበዛል። በሚቀጥለው ወር አልደግመውም የሚለውን ግዝቱን ይጀመራል። ከዛም የወሩ መገባደጃ አካባቢ ‹አበዳሪ ለዘላለም ይኑር› የሚል መፈክሩን አንግቦ ብድር ፍለጋ ወዲህ ወዲያ ሲል ይታያል።

‹‹ደሞዝ ማለት ለኔ ሠላሳ ቀን ሙሉ ሳስበው የምኖርና ከአሁን አሁን ደረሰ እያልኩ በጉጉት የምጠብቀው ነገር ሆኗል።›› ይላል፣ ጌቱ። ከመቼው ደሞዙ መጥቶ ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ነገሮች አሟላለሁ በማለት እንደሚቸኩልም ያስረዳል። ‹‹የቤት ኪራይ አለ፣ የምትበላው አለ፣ የምትለብሰው አለ፣ መታመም አለ፣ ዘመድ ቤተሰብ መጠየቅ አለ። ሌላው ቢቀር እንኳን ከቦታ ወደ ቦታ ስትዘዋወር ገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ያንን ገንዘብ በማሰብ ወሩን ሙሉ እጨርሳለው። ያቺ የደሞዝ ቀን ለኔ የፌሽታ ቀን ብትሆንም በንጋታው ግን ያው መልሼ መቆዘም ነው። ወሩን ሙሉ ሰቀቀን።›› በማለት ወሩን ሙሉ ሠርቶ የሚያገኘው ገቢ ወሩን ሙሉ ከሚያወጣው ወጪ ጋር አለመመጣጠኑን ያስረዳል።

ደሞዝ የተቀበለ ቀን ትኩረቱ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት እንደሆነ የሚያወሳው ጌቱ ‹‹አሁን ቤት ኪራይ የለብኝም። ቤት ኪራይ መክፈል አቅቶኝ ወደ ቤተሰብ ቤት ገብቻለሁ። ስለዚህ የደሞዝ ቀን ዋናው የማተኩረው ምግብ እና ምግብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው። ሌላ ነገር አይታሰብም። ልብስ የሚለበሰው እንደው አልበላም አልጠጣም ብለህ እቁብ መጣል ከቻልክ ነው።›› ሲል በፈገግታ ይገልጻል።

ትዕግስት በበኩሏ ‹‹ደሞዝ እንደተቀበልኩኝ ምንድን ነው የማደርገው የሚለውን የራሴ ፕሮግራም አለኝ።›› ትላለች። ስለዚህ እቅዷ ስትገልጽም፤ ‹‹ለወር ለትራንስፖርት የሚሆነኝን ብር አስቀድሜ አስቀምጣለሁ። ምክንያቱም በትራንስፖርት ካልተመላለስኩኝ በስተቀር ሥራ መሥራት እንደማልችል አውቃለሁ። የቤት ወጪ ለቀለብ፣ ለመብራት፣ ለውሃ ለስልክ የሚያስፈልጉትን ሁሉ ነገሮች ደምሬ የማገኛትን ደሞዝ እከፋፍላታለሁ።

ያው ተቀማጭ ብር ባይተርፈኝም ያለኝን ገንዘብ በአግባቡ ከወር እስከ ወር አብቃቅቼ ለመጠቀም ጥረት አደርጋለሁ። ግን እንደዚህም ሆኖ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥመኝ ብዙ ጊዜ ለራሴ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ወደጎን በመተው ለቤቴ እና ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ቅድሚያ እሰጣለሁ።›› ስትል ከደሞዝ አጠቃቀም ልምዷ ታካፍላለች።

ደሞዝተኛና ብድር
‹‹አብዛኛውን ጊዜ የኔ ደሞዝ ሳይመጣ ነው የሚያልቀው።›› ያለው ጌቱ አንድ ገጠመኙን ለአዲስ ማለዳ አጫውቷታል። እንዲህ ሲል፤ ‹‹የሆነ ጊዜ ደሞዝ ለመቀበል ወረፋ ይዤ የእኔ ተራ ደርሶ ልቀበል ስሄድ ደሞዝ ሊኖረኝ ቀርቶ ጭራሽ ሀምሳ ብር ዕዳ አለብህ የተባልኩትን አልረሳውም። ለካ ደሞዜ በተለያዩ የብድርና የመሥሪያ ቤት ማኅበራት ክፍያዎች ተከፋፍሎ አልቋል። እነዛ ሁሉ ተደማምረው እንደውም ሀምሳ ብር እዳ እንዳለኝ ተነገረኝ። እናም ሀምሳዋን ብር ከጓደኞች ተበድሬ የከፈልኩበትና ባዶ እጄን ወደ ቤቴ የገባሁበት ጊዜ ትዝ ይለኛል።›› በማለት ያስታውሳል።
‹‹ደሞዝ እንደተቀበልኩኝ የመጀመሪያ ሳምንታት ብዙ አልቸገርም። ነገር ግን በዛው ልክ ደሞዝ ለመቀበል አንድ ሳምንት ሲቀር ደግሞ የገንዘብ እጥረት ይገጥመኛል።›› የምትለው ትዕግስት ናት።

‹‹ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር የማገኘው ደሞዝ በቂ አይደለም። ነገር ግን ገቢዬ ከፍተኛ ነው ብዬ ባስብ እንኳን ወጪዬ የዛኑ ያክል በመሆኑ የተመጣጠነ አይደልም። ስለዚህ ካለው የአገሪቷ ሁኔታ አንፃር የትራንስፖርት ወጪ ይታወቃል። ኹለትና ሦስት ታክሲ ነው የምጠቀመው፣ የምግብ ፍጆታ አለ፣ እድር እቁብ የማህበር መዋጮ ይኖራል። እነዚህ እነዚህ ተደማምረው ወደ ወሩ መጨረሻ አካባቢ የገንዘብ አቅሜን ስለሚያሟጥጡት አንዳንድ ጊዜ አበዳሪ መፈለጌ የማይቀር ነው።›› ብላለች።

ኮሮና እና ደሞዝ
አሁን አሁን የኮሮና ወረርሽኝ በደሞዝተኛው ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ እያደረሰ የሚገኘው ሁለንተናዊ ጫና እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። በኢትዮጵያ ቢያንስ እስከ 2.5 ሚሊዮን ሰዎችን ኮቪድ-19 ሥራ አጥ ሊያደርግ እንደሚችል ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በአንድ ጥናታቸው ላይ አመላክተዋል።

ፕሮፌሰሩ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች በመንግሥት ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ገልፀው፤ በወረርሽኙ ሳቢያ የመንግሥት ሠራተኛው ከሥራው ይፈናቀላል ተብሎ እንደማይጠበቅም ይገልፃሉ። በሌላ በኩል 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን በግል ሴክተሩ ውስጥ ተቀጥረው እንደሚሠሩ ጠቁመው፤ ከእነሱም ውስጥ ግማሽ ያክሉን ወረርሽኙ ከሥራ ገበታቸው ሊያፈናቅላቸው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።
በሌላ በኩል 3.1 ሚሊዮን ሰዎች በግል ሥራ ውስጥ ራሳቸውን ቀጥረው እንደሚያስተዳድሩ የገለፁት ፕሮፌሰሩ፣ እነርሱም ኮቪድ 19 በሚያስከትለው ጫና ምክንያት ሥራቸውን በቀላሉ ሊያጡ እንደሚችሉ አስቀምጠዋል።

‹‹የኮሮና ችግር ዘርፈ ብዙ ነው። ማኅበራዊ፣ ሥነልቦናዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አጋጥመውናል።›› የሚለው ጌቱ ይሄንንም ሲያብራራ እንዲህ ይቀጥላል። ‹‹ማኅበራዊ ችግሩን ስናይ የሰው ልጅ ባይበላም ባይጠጣም ከጎኑ ሰው ካለ፣ አብሮ ከተጫወተ ከተደሰተ፣ ያለውን ከተካፈለ ፍቅርን ከተለዋወጠ ይህ ራሱን የቻለ ተስፋ ይሰጠዋል። አሁን አብዛኛው ሰው ከዚህ ተገልሏል። አይገናኝም አብሮ አያወራም። ይሄ በራሱ ወደ ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ ይከተዋል። በዛ ላይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግር ተደርቦበታል።›› ብሏል።

ያላት የትራንስፖርት አማራጭ ታክሲ እንደሆነ የምትናገረው ትዕግስት፣ ‹‹በታክሲ ስጠቀም ደግሞ እንደሚታወቀው አሁን ትራንስፖርት ላይ ለአንድ ሰው ይከፈል የነበረው በኹለት ሰው እየታሰበ እንዲከፈል ተደርጓል። በፊት ከማወጣው ወጪ በእጥፍ በመጨመሩ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጌአለሁ።›› ስትል ወረርሽኙ እያደረሰባት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ትገልፃለች።

በኮሮና ምክንያት አንዳንድ የግል መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ቀንሰዋል። ለምሳሌ የትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይ አበል እንዲሁም ሌሎች መሰል ጥቅማጥቅሞችን ለሠራተኞቻቸው ከመስጠት ታቅበዋል። ይህም በሠራተኞቹ ላይ እያደረሰ ያለው የኢኮኖሚ መዛባት ቀላል የሚባል አይደለም።

እንደ መምህር ተጨማሪ ሰዓቶችን በማስተማርና በማስጠናት የሚያገኘው ገንዘብ እንደነበር የሚያወሳው ጌቱ፣ ያም የተለያዩ ወጪዎቹን ለመሸፈን ይረዳው እንደነበር አልደበቀም። ‹‹አሁን በኮሮና ምክንያት ሁሉም ሰው ጥግግትንና ንክኪን በመፍራት ማንንም በአስጠኚነት አይቀጥርም። ያም ባለመኖሩ ምክንያት ራሴን ማኖር አልቻልኩም።›› በማለት ያስረዳል።

በርከት ያሉ አባላት የሚገኙበት ቤተሰብ ያለው ሰው ነገሩ ምን ያህል እንደሚከብደው ለተመልካች ትቶታል፣ ጌቱ። ‹‹ብዙ ጓደኞቼ ተከራይተው ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለቀው እንደገና ተመልሰው ጥገኝነት በመጠየቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ገብተዋል። ስለዚህ ኮሮና በሠራተኞች ላይ ምን ያህል ቀውስ እንዳስከተለ ከዚህ በመነሳት መገመት ይቻላል።›› ሲልም በቀደመው ችግር ላይ ወረርሽኘኙ ምን ያህል ተጨማሪ ፈተና እንደሆነ ያስረዳል።

ከኮሮና ወረርሽኝ መግባት በኋላ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል በሚለው ሐሳብ ብዙዎች ይስማማሉ። በአንጻሩ ደግሞ ደሞዝ በግማሽ የቀነሰባቸው አሉ። ‹‹በአስማት ነው እየኖርን ያለነው። አሁን አሁን እንደውም ሸገር ዳቦ መምጣቱ ጥሩ ነው። በውሃ እየነከርክም ቢሆን እሱን እንመገባለን።›› ሲል ቀልድ ቢጤ ጣል አድርጎ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማሳየት ይመሞክራል።

ጌቱ በመጨረሻ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፤ ‹‹መንግሥት በአንድ በኩል የዜጎችን የምግብ ዋስትና አረጋግጫለሁ ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙኀኑ መብላት አቅቶት ፆሙን የሚያድር ነው። የሰው ዐይን የሚገርፈው ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ለም ናት፣ ሀብታምና የብዙ ሺሕ ዓመት ታሪክ ባለቤት ናት እንላለን። ይሁን እንጂ በልተን ማደር ካልቻልን ስለሆዳችን ብቻ የምንጨነቅ ስለሚሆን እንዴት ነው እኛ ስለሰላም፣ ስለ ልማት የምናስብበት ጭንቅላት የሚኖረን?››

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com