ዛሬም የቀጠለው የሕገ መንግሥት ይሻሻልልን ጥያቄ!

Views: 63

አፍሮ ባሮ ሜትር የተሰጠ የጥናትና ምርምር ማእከል በሕግና ፌዴራሊዝም ጉዳዮች ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል። በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 69 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ይፈልጋሉ። ፍቃዱ ዓለሙ ይህን ነጥብ በማንሳት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከመግቢያው ጀምሮ ያሉበትን ሕጸጾችና እንዲቀየር ገፊ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ጠቅሰዋል።

መግቢያ
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ነገን እንዲህ ነው ብሎ ለመሞገት ያስቸግራል። ምክንያቱም በአገሪቱ የቆዩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ብሎም ሕገ መንግሥታዊ ችግሮች አገሪቱን በብዙ ተቃርኖዎች እንድትቆም አድርጓታል።

ሰሞኑን አፍሮ ባሮ ሜትር የጥናት እና ምርምር ተቋም ከፍሪደም ሀውስ ጋር በመተባበር በሕግ እና በፌዴራሊዝም ጉዳዮች ያካሄደውን ጥናት ለመገናኛ ብዙኀን ይፋ አድርጓል። በጥናቱ የሕገ መንግሥት መሻሻል ጉዳይ፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች ብዛት፣ አንቀጽ 39፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እና ሌሎች አሳቦች በጥናቱ ለተሳተፉ ዜጎች የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ።

በዚህ መሠረት 69 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ይፈልጋሉ። 18 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ሕገ መንግሥቱ ባለበት እንዲቀጥል ብለዋል። 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአዲስ እንዲተካ ይፈልጋሉ፤ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳተተው።

ቀድሞም ቢሆን ነባሩ ኢሕአዴግ ከመፍረሱ በፊትም ቢሆን ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል እንደሚችል ጥቂቶች ያምኑ ነበር። ዛሬም ቢሆን ከዚህ ጥናት በፊት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የለውጥ አቀንቃኙ ቡድን ‹ሕገ መንግሥት ይሻሻልልን› የሚል አሳብ በልዩ ልዩ መንገድ ሲያስተጋቡ እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንኳን በአንድ ወቅት ‹የሕገ መንግሥቱ ጉዳይ ለጥቂቶች ሲባል አይሻሻልም› ቢሉም ቅሉ ከዚህ ጥናት በፊትም ሆነ በኋላ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል እንዳለበት እርሳቸውም ያምናሉ። የሆነ ሆኖ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ሕጸፆችስ ምን ያህሉ ዜጋ በቅጡ ያውቃቸዋል የሚለው ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው። ስለሕገ መንግሥቱ ይሻሻል፣ አይሻሻል አጀንዳ ሲነሣ አብዛኛው ሕዝብ በቅድሚያ የሚያስበው አንቀጽ 39 በተመለከተ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን ብቻ ይመስለኛል።
የሕገ መንግሥቱ ሕጸፆች በጥቂቱ

የአንድ አገር ሕገ መንግሥት ዋነኛ ዓላማ በዜጎችና በመንግሥት መካከል የሚደረግ የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን ለማንም ግልጽ መሆን አለበት። ይህ ማለት የጋራ መግባቢያ ሰነድ (covenant) እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ዜጋ ሊያሳትፍ ይገባል። የኢትዮጵያ ሕገ መንገሥት ግን ከዚህ በተቃራኒ ለይስሙላ በአንድ ወቅት በተደረጉ የጓዳ የፖለቲካ ተወካዮች (ቡድኖች) ውይይቶች ሌላውን (በተለይም አማራውን) ያገለለ የስምምነት ሰነድ እንጂ አብዛኛውን ሕዝብ ያሳተፈ እንዳልነበረ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን አስታውሳለሁ።

በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ችግሩ የሚጀምረው ገና ከመግቢያው ነው። በሕገ መንግሥቱ መግቢያ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች….” በማለት ስንኩል አሳቡን ማተት ይጀምራል። ይህ አገባብ ከየትኛውም አገራት ሕገ መንግሥቶች የተለየ ነው።

ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት “እኛ የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች” ይላል። የብዙ ጥቁሮች፣ የነጮች እንዲሁም የላቲኖችና ኤሲያውያን መኖሪያ የሆነችው አሜሪካ እንኳን በሕገ መንግሥቷ “እኛ የአሜሪካ ሕዝብ (We the people of United States)” በማለት በየአገራቱ የሚኖሩ ሕዝቦችን “እኛ” ሲል በአክብሮትና ለመላው ሕዝቦች ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።
በነገራችን ላይ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማለት ምን ማለት ነው? ብሔር ማለት ዘሀገረ ቡልጋ፣ ዘሀገረ ጎንደር እንዲል ብሔር ማለት ሀገርን ያመለክታል። ብሔረሰብ ማለት ደግሞ በአንድ አገር /ክልል ውስጥ የሚኖሩ ልዩ ልዩ ቋንቋና ባህል ያላቸውን ነገዶች/ዜጎች ወይም ነዋሪዎችን ይገልጻል።

ታዲያ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ልክ እንደ ሌሎች አገራት በመግቢያው ላይ ‹እኛ› ከማለት ይልቅ ለምን ብሔር፣ ብሔርሰቦች ለማለት መረጠ? ከላይ የተገለጹትን ልዩ ልዩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቋንቋ እኛ ከማለት መነጣጠል ለምን ተፈለገ ከተባለ፣ ቀጥሎ የምንመለከተው አሳብ ይበልጥ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ዜጎችን የሚያይበት መነጽር ግልጽ ያደርጋል።

መምህርና የሕግ ጠበቃ ማሩ ባዘዘው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ችግሮችና መፍትሔዎቱ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 16 ላይ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ (Preamble) ከተጠቀሱ ሀረጎች መካከል ‹በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት…› የሚለውን አባባል ሕገ መንግሥቱ ከመውጣቱ በፊት (1987) ለነበረችው ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት እውቅና አለመስጠቱን የሚያመላክት እንደሆነ ያነሳሉ። ይህ ማለት እንደ አገር ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያልነበረች ነገር ግን በሥልጣን ላይ የነበሩ ቡድኖች መልካም ፈቃድ እንደገና አፍርሰው እንደሠሯት ለማመላከት አስበው ያደረጉት ነው።

ጸሐፊው አክለውም ‹የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን…› የሚለውን አገላለጽ ከአንቀጽ 39 ጋር እንደሚገናኝ እና አገላለጹ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውጭ በሌሎች አገራት እንደማይገኝ ያትታሉ። ከዚህ በመነሳት ነው ብዙዎቹ ሕገ መንግሥትን የአንድ ቡድን የቃል ኪዳን ሰነድ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡት። እዚህ ላይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በትግላችንና በከፈልነው መስእዋትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚለው አባባል በሕገ መንግሥቱ የአንድን ቡድን ዓላማ ለማስፈጸም እንደተደነገገ ያመለክታል።

ሌላው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ‹ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት ለማረም…› የሚለው አባባል እጅግ አደገኛ ነው። ይህ ሕገ መንግሥቱ ካዘላቸው ጥቂት ሕጸፆች መካከል አንዱና የጋራ እሴቶችን የሚያፈርስ፣ በተቃርኖ ቁስሎች ላይ በርበሬ እየረጩ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳሳ ሁል ጊዜ እያላዘኑ፤ እየተቋሰሉ እንዲኖሩ የሚያደርግ በቶሎ መወገድ ያለበት ሕጸጽ ነው።

በእርግጥ አብዛኛው ኢትዮጵያ ታሪክ የተዛባ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለው ጥናት ይፈልጋል። ይሁንና ያለፈው ታሪኮቻችን የተዛቡ ቢሆኑም ባይሆኑም እንኳ ያለፈን ታሪክ መማሪያ ማድረግ ሲቻል በየጊዜው ቁስል ያለበትም የሌለበትም ጉዳዩን እያነሳ አገሪቱ ወደማትወጣበት አዘቅት ገፍቶ ላለፉት 30 ዓመታት እንዳትረጋጋ አድርጓታል። እዚህ ላይ መምህርና የሕግ ጠበቃ አቶ ማሩ ባዘዘው እንደሚሉት፣ ያለፈን ታሪክ መቀየር አንችልም። ነገር ግን እንደ ሩዋንዳ፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ እንደ ጀርመን እና መሰል አገራት ካለፈው ታሪክ በመማር ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለውን ማቆየትና ማስተማር እንጂ በየጊዜው ማቋሰል እንደ መማር አይቆጠርም።

ሕወሓት/ኢሕአዴግ አገሪቱን መምራት ሲጀምር አቆጥቁጦ የነበረው የብሔር-ፖለቲካ በመንግሥት አስተዳደር እንደ ሥርዓት በመተከሉ ምክንያት ዛሬ ላይ ለደረስንበት ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓትና በማንነት ላይ የተመሠረቱ ጥቃቶች ብዙ ሺሕ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች በገዛ ወገኖቻቸው፣ ተወልደው ባደጉበት ቀዬና አካባቢ እንዲሰደዱና ቤት ንብረታቸው እንዲወድም ሆኗል።

ይህ ክስተት ዛሬም አላባራም። ሰዎች በያዙት የፖለቲካ አመለካከት ይጠቃሉ። በማንነታቻው ምክንያት ይገፋሉ፣ በማንነታቸው ምክንያት ይሞታሉ፣ ብሎም በአገር ደረጃ ሰላምና መረጋጋት እንቅፋቱ ይሄው በማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ዲስኩር ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ዮናስ አሸኔ በአንድ አውደ ጥናት ላይ ‹በጽንፈኛ ብሔርተኞች መካከል በሚደረግ የፖለቲካ ፉክክር አገረ መንግሥቱን እና ተቋማቱን ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ በበላይነት ለመቆጣጠር፤ አብዛኛውን ሕዝብ በማግለለ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን በልማትና በእኩልነት ጥያቄዎች ስም ፖለቲካውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ሽኩቻ አገሪቱ ተረጋግታ ወደ ልማት እንዳትጓዝ እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል› በማለት የወቅቱን የኢትዮጵያን የብሔር ፖለቲካ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጠውታል።

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች አገር ነች። ወርቅዮ ባህሎችና አስተማሪ የሆኑ የሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች አሏት። በተመሳሳይ ብዙ ሺሕ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቱባ ባህልና ታሪክ ያሏት ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ በባህላዊ የቃል እንጅ በጹሑፍ ያልተመዘገቡ ናቸው፣ የተሟሉ አይደሉም።

በዚህ ምክንያት ልክ እንደ ሌሎቹ አገራት በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በመጥፎም ሆነ በበጎ ያለፍናቸው ታሪኮቻችንና ማንነቶቻችን ዛሬ በሐሰት ትርክትና በበሬ ወለደ መረጃዎች አማካኝነት በአገራችን ውስጥ የጎሳ ፖለቲካን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ሰፍኗል። በዚህም ምክንያት አልፎ አልፎ እየተከሰተ ላለው ሃይማኖታዊ ግጭቶችም መንስኤ ሆነዋል። ዛሬም በተቃርኖ ትርክት የተሞሉ የፖለቲካ አሰላለፎች ይህን ሕገ መንግሥት ተራ ሰነድ እንዲሆን ያደርጉታል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በአፍሪቃ ኅብረት የስብሰባ አዳራሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶችን በማጥበብ የጋራ ስምምነት በማድረግ አገርን ከመበታተን ለማደን መልካም ነገርን ያለመ ውውይት ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ዛሬም ድረስ እንደ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ዓይነት ምሁራን ሳይቀር በትምህርት ባገኙት እውቀት ነገሮችን ከመመርመር ይልቅ ይህን ትርክት እንዳለ በመቀበል ሕዝቡና ተከታዮቻቸው በእንዲህ ዓይነት ማመንዠክ እድሜ ልካቸውን ሲጮሁ እንዲኖሩ መንገዱን አሰፉት እንጂ ማጥበብ እንዳልቻሉ ትልቅ ማሳያ ነው።

ይህን ሕግ መንግሥት (ሰነድ) ያዘጋጁት ወገኖችና ነገን የተሻለ እንዳይሆን ሁልጊዜ በተቃርኖ ትርክት እያቋሰሉ፤ እየበጠበጡ መኖር የሚፈልጉ ኃይሎች ከሕገ መንግሥት ይሻሻልን በተቃራኒ ቆመው ከጉዳቱ ይልቅ ጠቃሚ ሲሉ አድምጠናቸዋል። ዛሬም እንዲህ ዓይነት ድምፆች አሉ።

በተቃርኖ የተሞላው የፌደራሊዝም ሥርዓት አተካከልና መሠረታዊ ችግሮቹ
ኢትዮጵያ የምትከተለው የመንግሥት ሥርዓት ፌዴራሊዝም በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ የተቃኘው በዚሁ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ ነው። የፌዴራሊዝም ሥርዓት በዋናነት ሥልጣንን በማእከላዊ መንግሥት አካላት መካከል በማከፋፈል (Division of Power) የየአካባቢው ማኅበረሰብ የሥልጣን በአካባቢው ጉዳይ ላይ እንዲወስን ትልቅ አስተዋጽዖ አለው።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 መሠረት የፌዴራል ሥርዓቱ በክልሎች የተዋቀረ ሆኖ በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋና ማንነት ላይ እንዲሆን ያትታል። እዚህ ላይ ፌዴራሊዝም የተቀላጠፈ አስተዳደር እንዲኖር የሚያደርግ ቢሆንም፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን በተቃርኖ የሞላ ያደረገው ምክንያት ክልሎች የተዋቀሩበት የቋንቋና ማንነት ጉዳይ ነው።

መምህርና የሕግ ጠበቃ አቶ ማሩ ባዘዘው ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ገጽ 24 ላይ የአንዳንድ ክልሎች አወቃቀር አኗኗራቸውንና አሰፋፈራቸውን በመተው ቅይጥ ማንነትና አኗኗር ያላቸውን ሕዝቦች በቋንቋና በማንነታቸው ብቻ ለይቶ ከአንዱ ወደ አንዱ በማካለላቸው ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ። ለምሳሌ በወልቃይት፣ ጠገዴና ራያ አካባቢዎች የሚሰሙ የመብት ጥያቄዎች መነሻ ችግሮች ይኸው አከላለል ጉዳይ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ።

በተጨማሪም በአንዳንድ ክልሎች ላሉ ጥቂቶች (Minorites) ምንም ትኩረት አይሰጥም። የቡድኖች መብት የጥቂቶችን ዴሞክራሲያዊ መብት ያፍናል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የተለያየ ብሔር ያላቸው ጥቂቶች አሉ። እነዚህም ብዙ ጊዜ መብታቸውና ፍላጎታቸው ሲከበር አይታይም። ይባስ ብሎ በአንዳንድ ክልሎች የሚገኙ እነዚህ ጥቂቶችች በራሳቸው ቋንቋ ምንም ዓይነት የመንግሥት አገልግሎት ማግኘት አይችሉም ሲሉ አቶ ማሩ ባዘዘው የፌዴራሊዝሙን አተካከልና ውስብስብ ችግሮች በስፋት ይዳስሳሉ።

ሌላኛው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖር፣ ሀብትና ንብረት የማፍራት መብት በጽሑፍ እንጂ በተግባር የለም።
ብዙ የሕግ ምሁራንና የፖለቲካ ሳይንስ አጥኝዎች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እጅግ አስቂኝ ጉዳይ አድሏዊነቱ ነው። ክልል የመሆን ፍላጎትን ብንወስድ ለሁሉም እኩል መብት አይሰጥም ወይም አድሏዊ ነው። ለምሳሌ የሀረሪ ክልል አወቃቀር የሚያሳየው በክልሉ ያሉ ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ነው። ነገር ግን የሲዳማ ክልል ከዚህ ቀደም ክልል ከመሆኑ በፊት የክልል እንሁን ጥያቄው ቢያንስ ላለፉት 27 ዓመታት ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

ይህ የሚያሳው አቶ ማሩ ባዘዘው እንደሚሉት፣ ፌዴራሊዝሙ አድሏዊና እንዲያም ሲል በፌዴራል መንግሥት መልካም ፈቃድ እንደነበር ማሳያ ነው።
ሌላው የአገሪቱን ሕግ መንግሥት መነሻ በማድረግ የክልሎች ሕገ መንግሥት ሲታይ እጅግ አሳፋሪና የፌዴራሊዝሙ ሥርዓት የይስሙላ እንደነበር ያመላክታል። ለምሳሌ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን ሕገ መንግሥት በክልሎቹ እውቅና የተሰጣቸው በክልሎቹ የተወለዱ ብቻ ናቸው። ይህ ማለት ሌሎች ኢትዮጵያውያንን እንደ መጤ ያየቸዋል ማለት ነው።

ስለዚህ በአፍሮ ባሮ ሜትር የጥናት እና ምርምር ተቋም መሠረት ሕገ መንግሥቱ ይሻሻልልን ያሉት 69 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች አመለካከት ላቅ ያለ ተቀባይነት እንዳለው አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ሕገ መንግሥቱን በፍጥነት ማሻሻል የሚያስፈልግበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ ፈራርስ ማየት የሚፈልጉ ጽንፈኛ/ ጎጠኛ ኃይሎች በቶሎ እርማቸውን እንዲያወጡ ነው። በመሠረቱ የፌዴራሊዝም ትልቁ ጥቅም ልዩ ልዩ ፍላጎትና አመለካከት ያላቸው ማኅበረሰቦች ልዩነታቸውን አቻችለው ወይም አጣጥመው በተባበረ ክንድ/ሕብረት አንድ ሆነው እንዲኖሩ የሚያግዝ ስልት ነበር።

ስንተባበር እንደምንቆም፤ ስንለያይ ግን እንደምንወድቅ ጽንፈኛ ቡድኖች ጠፍቷቸው አይመስለኝም። ከዚህ በተቃራኒው የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለው በመሠረታዊነት ከፌዴራሊዝም ጽንሰ አሳብ ጋር አብሮ አይሄድም።

በተጨማሪም የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ማለት ቀኝ ተገዥና ቅኝ ገዢ እንደነበር ያሳያል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን ቅኝ አልተገዙም። እንዲሁም አንዱ ሌላውን ቅኝ የገዛበት ዘመንና ወር ከቶም የትም አልተጻፈም።

በአጠቃለይ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ (preamble) ጀምሮ የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር፣ የክልሎች አመሠራረት ከቋንቋና ማንነት አሰፋፈር ውጭ እንዲሆን ማድረግን፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖር፣ እንዲሁም ሀብትና ንብረት የማፍራት፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን፣ የባንዲራ፣ የፌዴራል /መንግሥት የሥራ ቋንቋዎችን እና ሌሎች መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልግ፣ ሁሉንም ማኅበረሰብ ወይም ዜጋ ያሳተፈ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ እዚች አገር ላይ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የትኛውም ሥልጣንና ኃይል ያለው ሁሉ ማሰብ አለበት።
ፍቃዱ ዓለሙ ጋዜጠኛ እና የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው esmbefe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com