የልጆች ደኅንነት የወላጆች ጉዳይ ነው!

Views: 159

ከሰሞኑ የትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ምዝገባ እንዲያከናውኑና የ2013 የትምህርት ዘመን ከተገቢው ጥንቃቄ ጋር እንደሚካሄድ አስታውቋል። ግዛቸው አበበም ይህን ነጥብ በማንሳት ‹አልተቸኮለም ወይ› በማለት ይጠይቃሉ። ወረርሽኙን በመስጋት የጥቂት ቀናት ኹነት የሆነው ምርጫ ተራዝሞ ዘላቂ የሆነና ተማሪዎች በየእለት በአንድ ስፋር የሚገናኙበት ትምህርት መከፈቱ አግባብ ነው ወይ ሲሉም ከተለያዩ የዓለም አገራት ተሞክሮዎች ጭምር በማንሳት ዕይታቸውንና ስጋታቸውን አካፍለዋል።

ለተወሰነ ጊዜ ‹ሸብ ረብ› ነው ሊባል የሚችል፣ ሰዎችን በተፈለገው መጠን በቦታና በጊዜ አራርቆ ቅስቀሳዎችን ማካሄድ፣ መመዝገብና ድምጽ እንዲሰጡ ማድረግን የሚያካትተውና ብዙም የማይከብደው ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። በአንጻሩ ተማሪዎችን ቢያንስ ለዐስር ወራት በየክፍሉ አስቀምጦ ጊዜ እንዲያሳልፉ የሚጠይቀው ትምህርት ሊጀመር ዳር ዳር እየተባለ ነው።
ምርጫ ማካሄድ እንደ አደገኛ ‹ኹነት› በመቆጠሩ፣ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ምርጫ ከወዲሁ እናካሂዳለን በሚሉ ወገኖች ላይ ምንነቱ ግልጽ ያልተደረገ ነገር ግን ‘የማያዳግም’ የተባለ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝተዋል።

እርግጥ ነው ጠቅላዩ ቆየት ብለው ምርጫ ተደረገ ተብሎ ጦርነት እንደማይከፈት፣ ነገር ግን ‘ችግር’ ሊፈጠር እንደሚችል ተናግረው፣ የኢሕአዴግ አካል ያልነበረ ቡድን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ ብቻ ነው ሲሉም ተሰምተዋል። ጠቅላዩ የተናገሩትን በቀጥታ ለማስቀመጥ ችግር የሚፈጠረው በትግራይ በሚካሄደው ምርጫ ሕወሐት ተሸንፎ አረና ወይም ሌላ ቡድን ካሸነፈ ነው። ያም ሆነ ይህ ጠቅላዩ በአማርኛም በትርግርኛም በሰጡት መግለጫ የማያዳግመው እርምጃ በመለሳለስ መቀየሩን መረዳት ቀላል ነው።

ለመሆኑ ምርጫ የሰዎችን መሰባሰብ ስለሚጠይቅ አደገኛ ነገር ነው ተብሎ መንግሥትን ለእርምጃ የሚያነሳሳ ከሆነ፣ ትምህርት እንደ ዋዛ ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናትንና ጎልማሶችን በክፍሎችና በግቢዎች ለወራት ማሰባሰብ እንዴት ነው ቀለል ተደርጎ የታየው?

‹ምርጫ› እና ‹ትምህርት›
ምርጫ ቢካሄድ እያንዳንዱ ግለሰብ ኹለት ኹለት ጊዜ ብቻ ወደተፈለገው ቦታ እንዲመጣ በማድረግ ነገሩን መቋጨት ይቻላል። አንዴ ለመመዝገብ ከዚያም ድምጽ ለመስጠት። ለእያንዳንዱ ሰው ኹለት የእጅ ጓንትና ኹለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመስጠት፣ እያንዳንዱ ሰው ለመፈረምና ድምጽ መስጫ ወረቀቱ ላይ በተዘጋጀው ቀለም/እስክርቢቶ ምልክት ለማሳረፍ ሲል የጋራ መጠቀሚያዎችን ከነካ በኋላ እጁን በአልኮል/ሳኒታይዘር እንዲያጸዳ በማድረግ ወይም እጁን በውኃና በሳሙና እንዲታጠብ በማድረግ ሂደቱን ከችግር ነጸ ለማድረግ ወይም የኮቪድ-19 አደጋን መቀነስ ይቻላል።

ታዲያ ይህን መሰሉን ከፍተኛ ወጭን የሚጠይቅ ነገር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች በየቀኑ ለበርካታ ወራት ማድረግ የሚያዛልቅና ሳይቋረጥ ምድረግ የሚቻል ነውን?
ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ይህን መሰል የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ የታሰበበት መሆኑን ገልጿል። ሆኖም በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሕክምና ተቋማት፣ የኮቪድ-19 ሕክምና ማእከላት የሆኑትን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ራሳቸውን መከላከል የሚችሉባቸው ቁሶችና ኬሚካሎች እጥረት እያማረሯቸው መሆኑ ይሰማል። በዚህ ሁኔታ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉንም ነገር ለተማሪዎች ለማሟላት ተዘጋጅቼአለሁ ማለቱ አጉል ድፍረትና ከወሬ የማያልፍ አለመሆኑ መረጋገጥ ያለበት ከወዲሁ ነው።

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ትምህርት ሚኒስቴት ትምህርት እንዲጀመር የፈለገው ለተማሪዎችና ለትምህርት አስቦ ነው ወይስ ለሌላ ዓላማ? የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ ኮቪድ-19 እየተስፋፋ ቢሆንም ተማሪዎች በየቤታቸው በመዋላቸው ለሥነ ልቦና ችግር ስለተዳረጉ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት መፈለጉን ነው የተናገሩት።

ከዚህ በፊት በአንዳንድ መገናኛ ብዙኀን ላይ ልጆች በየቤታቸው አርፈው ስላልተቀመጡና በየቦታው ተሰባስበው እየተጫወቱ ስለሚውሉ ትምህርት ቤት መዘጋቱ ትርጉም አልባ እየሆነ ነውና ትምህርት ቢጀመር ይሻላል የሚል ነገር መሰማቱ የሚረሳ አይደለም። ወይዘሮ ሐረጓ ከዚህ የተለየ ምክንያት ትምህርት እንዲጀመር መገፋፋቱን መናገራቸው ደግ ነገር ነው።

አልጋው፣ መመገቢያ ‘ጠረጴዛው’፣ ሞሰቡ፣ የእህል ጎተራ፣ የቅመሙ ጣሳ፣ ደብተሩ፣ ወላጆችና ልጆች አንድ ክፍል ብቻ ተጋርተው ለሚኖሩበት ቤተሰብ ጭምር ነውና ከቤት አትውጡ የሚለው መመሪያ የወጣው፣ ለሚሊዮኖች የሚሠራ አይደለም። ነገር ግን በዚህ ሰበብ ግቢአቸውን ዘግተው የተቀመጡትን ቤተሰቦች ጭምር ልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት ላኩ ማለት ፍትሐዊ አይደለምና፣ አሁን ትምህርት ይጀመር ሲባል ይህ ሰበብ የትምህርት ሚኒስቴርም ሰበብ ሆኖ አለመቅረቡ ጥሩ ነገር ነው።

ጥያቄ አጫሪ ኹኔታዎች
ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ የኮቪድ-19 የመከላከል ስርዓቶች በሚገባ ስለተመለዱ በትምህርት ቤቶች ችግር እንደማይኖር ለመግለጽ ሞክረዋል። በእርግጥ መግለጫቸው በምዝገባ ላይ ያተኮረና ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ እንደማይታወቅ፣ ትምህርት ሲጀመርም የሚተገበር የኮቪድ-19 መከላከያ ፕሮቶኮል ተዘጋጅቶ እንደሚተገበር ስለተናገሩ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በቅርቡ እንዲመጡ በማድረግ የተጠቀሰውን ሥነ ልቦና ጉዳት መቅረፍ እንዳልታሰበበት መረዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ ከነሐሴ 20/2012 ጀምሮ ምዝገባ በችኮላ እንዲጀመር የተፈቀደው ለምድን ነው ብሎ ለመጠየቅ በር የሚከፍት ነው።

የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ፣ ከሆቴሎች በባሰና በፈጠነ ሁኔታ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የተዘፈቁት የግል ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ይታወቃል። ወረርሽኙ መጋቢት 4/2012 ላይ ኢትዮጵያ መግባቱ ተነግሮ መጋቢት 7/2012 ወደ እኩለ ቀን አካባቢ ትምህርት ለ15 ቀናት መቋረጡ ተነግሮ እነሆ እንደተቋረጠ ስድስት ወራት ገደማ ተቆጥሯል።

ትምህርት ተዘግቶ አንድ ኹለት ወር እንደተቆጠረ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ለመምህራንና ለሠራተኞቻቸው ደሞዝ የመክፈል አቅም እንዳነሳቸው በመግለጽ ደሞዝ ላለመክፈል ወይም ከሠራተኞቻቸው ደሞዝ እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ቀንሰው ለመክፈል ማንገራገራቸው ተሰምቶ ነበር። በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቶቹ መምህራንና ሠራተኞች አቤቱታቸውን ይዘው ይመለከታቸዋል ባሏቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢሮዎች ገባ ወጣ ማለታቸው፣ መንግሥት የትምህርት ቤቶቹን ውሳኔ መቃወሙና ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት መድረሱም አይዘነጋም።

በመካከል አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያዎችን ከተማሪዎቻቸው ለመጠየቅ ዳር ዳር ማለታቸው ይታወሳል። አሁን ወራትን ያለ ገቢ ወይም በዝቅተኛ ገቢ ያሳለፉት ትምህርት ቤቶች በተለይም የተማሪዎችን ክፍያ በየወሩና በየሩብ ዓመቱ የሚሰበስቡ የነበሩት፣ በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መገመት ከባድ አይደለም።

ነሐሴ 20 ቀን 2012 ምዝገባ የሚጀመረው በሁሉም ትምህርት ቤቶች መሆኑ በትምህርት ሚኒስቴር የተነገረ ቢሆንም፣ ግንባር ቀደም ሆነው የተማሪዎቹን ምዝገባ እንዲጀምሩ የተፈለጉት የግል ትምህርት ቤቶች መሆናቸው እየተሰማ ነው። በተቀመጠው ዕለት ወደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ለምዝገባ የመጡ ተማሪዎች በማስታወቂያ ወይም በቴሌግራም ሌላ ጥሪ እስኪደረግላቸው እንዲጠባበቁ እየተነገራቸው ተመልሰዋል።

ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤቶች ከሚያስተምሩ ወላጆች ብዙዎቹ በጥሩ የሀብት ደረጀ ላይ የሚገኙና አስተማማኝ ገቢ ያላቸው ናቸው። እንዲሁም ልጆቻቸውን በግል መኪናቸው ወይም በኮንትራት ታክሲ በቀጥታ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት እንደሁም ከትምህርት ቤትም ወደ ቤት ማመላለስ የሚችሉ መሆናቸው በፌርማታዎችና በሕዝብ ማመላለሻዎች ውስጥ የሚፈጠር ቅርርብና ንክኪ ላይኖር ይችላል።

እነዚህ ወላጆች ጥራት ያለው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ጓንት ያለ ማቋረጥና በበቂ መጠን እየገዙ ለልጆቻው መስጠት የማይከብዳቸው፣ አልኮልና ሳኒታይዘርን የመሳሰሉ ንጽሕና መጠበቂያዎችን በበቂ መጠን ማቅረብ የሚችሉ ናቸው ተብሎ ይታመናል። እናም ከኮቪድ-19 አደጋ የመጠበቅ ዕድላቸው የሰፋ ሊሆን ይችላል። ትምህርት ሚኒስቴር የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በፌርማታወችና በሕዝብ መጓጓዠዎች ውስጥ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ወይም ሰዓታት ለንክኪና ለመተፋፈግ ተጋልጠው በርካታ ወራትን እንዴት በሰላም አንደሚያሳልፉ ያለው ነገር ባይኖርም፣ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ አስፈላጊዎቹን መከላከያዎች እንደሚያሟላ ተናግሯል።

ከየሕክምና ማእከላቱ የሚሰሙ እሮሮዎች ትምህርት ሚኒስቴር የሚናገውን መተግበሩ ይሳካለት ይሆን ብሎ መጠየቅን ተገቢነት ያለው ያደርገዋል። ለመሆኑ የአፍና አፍንጫ መከለያ ጭንብሎች፣ የእጅ ጓንት፣ ሳኒታይዘር፣ መማሪያ ክፍሎችንና ሌሎችንም ተማሪዎች የሚገለገሉባቸው መመገቢያ ቦታዎችን፣ ቤተ-መጽሐፍትን፣ መጸዳጃ ቤቶችን ወዘተ… ጸረ-ተሕዋስ ኬሚካል በመርጨት ትምህርት ቤቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ከኮቪድ-19 አደጋ ነጸ ማድረግ ይቻላልን?

አገራትና ትምህርት ቤቶቻቸው – ከወረርሽኙ አንጻር
አንዳንድ አገራት በኮቪድ-19 ምክንያት የዘጉትን ትምህርት ለመጀመር የተነሳሱና ለተማሪዎቻቸው ጥሪ አድርገው ትምህርትም የጀመሩ ትምህርት ቤቶች ዜናዎች መሰማታቸው እርግጥ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ፈጥነው የጀመሩትን ትምህርት ለማቋረጥ የተገደዱ ትምህርት ቤቶች ዜናም ተሰምቷል።

ከዜጎቿ መካከል 19 ሺሕ ብቻ በኮቪድ-19 ተጠቅተውባትና ከእነሱም 310 ብቻ ለሕልፈት ተዳርገውባት ወረርሽኙን በመዋጋት ተጠቃሽና ተመስጋኝ አገር ለመሆን የበቃችው ደቡብ ኮርያ፣ ዘግታቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን ባለፉት ግንቦትና ሠኔ ወራት ቀስ በቀስ ከፍታ ነበር። ነገር ግን ትምህርቱ ሊቀጥል የቻለው እስከያዝነው ነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት ብቻ ነው።
ኮቪድ-19 እንደገና እያገረሸ በመምጣቱ ባለፉት ኹለት ሳምንታት ብቻ 200 የሚሆኑ መምህራንና ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ተገኝተዋል። መዋዕለ ሕጻናትን ጨምሮ ማናቸውም ትምህርት ቤቶች ተመልሰው እንዲዘጉም ተደርገዋል። በቅርብ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በዋና ከተማዋ እና ዙሪያዋ የኮሮና ቫይረስ ማገርሸቱም ታውቋል።

ለተወሰነ ጊዜ የደቡብ ኮርያ ትምህርት በርቀት፣ በበይነ መረብ እገዛ እንዲካሄድም መወሰኑ የተሰማው በዚሁ በያዝነው ሳምንት ነው። የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ተፈላጊውን መከላከያ አሟልቼ ትምህርት መስጠት እጀምራለሁ ያለውም በዚሁ በያዝነው ሳምንት ነው።

በዚህ በያዝነው ሳምንት ከወደ አሜሪካም የገጽ-ለገጽ ትምህርት በጀመሩ በአሜሪካ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥም ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ ቪኦኤና ቢቢሲ ላይ ተሰምቷል። ችግሩ ከታየባቸው የአሜሪካ ዩንቨርሲቲዎች በአንዱ ወደ 500 የሚሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች ሠራተኞች ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸዋል። ችግሩ ስጋት ካሳደረባቸው የአሜሪካ የትምህርት ተቋማት አንዳንዶቹ የገጽ-ለገጽ ትምህርቱን አቁመው በበይነ መረብ ስልት ብቻ ማስተማር ጀምረዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ ትምህርት በጀመሩ የአሜሪካ ዩንቨርሲቲዎች ላይ ባካሄደው ዳሰሳ ሁሉም በሚባል ደረጃ የኮቪድ-19 መዛመት ችግር ፈተና ደቅኖባቸዋል። ኒውዮርክ ታይምስ ‘Tracking Coronavirus Cases at U.S. Colleges and Universities’(Aug. 26, 2020) በሚል አርእስት ስር በካርታ ምስል አስደግፎ ከለቀቀው መረጃ ማየት እንደሚቻለው፣ በአሜሪካ አራቱም ማዕዘናት የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በዐስሮች ወይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ሆነው ተገኝተዋል።

ከአላባማ ዩንቨርሲቲ በአንደኛው ግቢ ከ970 በላይ የኮቪድ 19 ተጠቂዎች መመዝገባቸው ከፍተኛው ነው። የትምህርት ተቋማቱ የወቅቱ ቴክኖሎጂና የአሜሪካና የአሜሪካውያን ሀብት ደረጃ የሚፈቅደውን የመከላከል አቅም ሁሉ እየተጠቀሙ በኮቪድ-19 ምክንያት ከሚጋረጠው ችግር ማምለጥ ስላልቻሉ፣ ኒውዮርክ ታይምስ ጉዳዩን ትምህርትን ዳግም የመጀመር ፈተና አድርጎ ነው የተመለከተው።

በኢትዮጵያ የተማሪዎች ምዝገባ እንዲጀመር የተፈለገው የትምህርት ቤቶችን የገንዘብ ችግር መቅረፍን ታሳቢ በማድረግ ብቻ ሊሆን ይችላል። ምንም ዓይነት ሙያዊ ውይይት ከሚመለከታቸው የጤናው ዘርፍ ሰዎች ጋር ሳይደረግ፣ ሰብአዊ ትርፉና ኪሳራው ሳይሰላ የገንዘብ ችግርን ብቻ በመመልከት ትምህርት የመጀመር ዳር ዳርታ መታየቱ ከማንም በላይ ወላጆችን ሊያሳስብ ይገባል። አዎ! ከትምህርት ቤቶቹም ሆነ ከመንግሥት በላይ ወላጆችን ሊያሳስብ ይገባል። ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ውሳኔዎች የሚያልፉትና ችላ የሚባሉት ከሙያዊ ግምገማዎች በመነሳት ከመሆን ይልቅ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ግፋ ሲልም ወሳኙ እኔ ነኝ ከሚል የግብዝነት መንፈስ በመንደርደር ሊሆን እንደማይገባ ማስተዋል ተገቢ ነው።

መነሻና መድረሻን በማስተዋል!
እነዚህን ከመሳሰሉ ተገቢ ያልሆኑ መነሻዎች በመነሳት የተቀመጡ በርካታ ውሳኔዎች አገራችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ሥራቸው የኮቪድ-19 ተጠቂዎችን፣ ሟቾችን እና አገጋሚዎችን ቁጥር በየዕለቱ መዘግብ፤ ከዚም አለፍ ሲል ቁጥሮችን ወደ መቶኛ በመቀየር ማስፈራሪያዎችን መንዛት ብቻ የሆነ ይመስላል።

በመገናኛ ብዙኀን ጭምር የተለያዩ አካላት አነጋጋሪ፣ አጠያያቂና አሳሳቢ ነገሮችን ሲሰነዝሩ እነዚህ የመንግሥት አካላት በዝምታ ማየታቸው የተለመደ ነገር ነው። ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አትሌቶችንና አሠልጣኞቻቸውን ሆቴል ሰብስቤ ካላሠለጠንኩ ብሎ ድርቅ ሲል የተባለ ነገር አልነበረም። አሁን ደግሞ ስፖርት ተዳከመ በሚል ሽፋን ከከረንቡላ ጨዋታ ጀምሮ በሜዳ ላይ እስከሚካሄድ የማስ ስፖርት እንደገና እንዲጀመር በኢቲቪ ላይ ውትወታ በተደጋጋሚ ሲሰማ የተባለ ነገር የለም።

ኮቪድ-19 ገባ በተባለ ከማግስቱ ጀምሮ ሰዎች ማስክ ፍለጋ ሲሯሯጡ ባለሙያ የተባሉ ሰዎች በመገናኛ ብዙኀን ላይ እየቀረቡ ማስክ ማድረግ የሚገባቸው ሐኪሞች፣ ታማሚዎችና አስታማሚዎች ብቻ ናቸው ሲሉ ነበር። ቆየት ብሎ ደግሞ ማስክ ማድረግ ግዴታ ሆኖ ማስክ ያላደረጉ ሰዎች በአደባባይ በፖሊሰ ዱላ ሲነረቱና ታፍሰው ሲታሰሩ አይተናል። አንድ ሰሞን N-95 ማስክ የሐኪሞች ነውና ለምን ሕዝቡ ይጠቀምበታል እየተባለ ሕዝብ ለሐኪሞች ምቀኛ የሆነ የሚያስመስሉ ወሬዎች በመገናኛ ብዙኀን ላይ ሲነዙ ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በእነዚሁ መገናኛ ብዙኀን N-94 ማስክ ሐኪሞችም ሆኑ ሌላው ሕዝብ ሊጠቀምበት አይገባም። ብናኝ ለመከላከል ብቻ ነው ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው ሲባል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ሕዝብ ግራ እንዳይጋባ በማሰብ ያሉት ነገር የለም። የፖለቲካ ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎች፣ ንቅናቄዎችና የመሳሰሉት በብልጽግና ፓርቲ ሲካሄዱ፣ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያላዩ መስለው በማለፍ ላይ ናቸው።

ከአዲሰ አበባ ዳርቻዎች የሚገኙ ሆቴሎችና ጭፈራ ቤቶች በሰዎች ብዛት ከመጨናነቅ አልፈው ጭፈራ የመጀመር ዳር ዳርታዎችን ሲያሳዩም ተቆጭ ያላቸው አይመስሉም። ትግራይ ውስጥ መቀሌን ጨምሮ ወደ ሰባት በሚሆኑ ከተሞች በጎዳናዎችና በስቴዲዮም ሕዝብ ታዳሚ በሆነበት የጦርና የጦር መሣሪያ ትርኢት ሲካሄድ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ አባይ ግድብ በውኃ ሞላ በሚል ለግማሽ ቀን ያህል የአደባባይና የጎዳና ጭፈራ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሉት ነገር የለም።

በዚያ የጭፈራ ወቅት ሰዎች በሚኒባሶችና በጭነት መኪኖች ከልክ በላይ ታጭቀው በከፍተኛ ጩኸትና ፉጨት የተቀላቀለበት መዝሙር ሲያሰሙ ጉዳዩ እንደ ንቅናቄና የድል መግለጫ ተደርጎ በሚዲያዎች ተዘገበ እንጂ ሊከተል ስለሚችለው አደጋ የተጨነቀ ፖለቲከኛ ይሁን ከፍተኛ የጤናው ዘርፍ ባለስልጣን አልታየም። አሁን ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት እጀምራለሁ ሲል እነዚሁ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ተመልካች ብቻ ለመሆን የተዘጋጁ ይመስላል።

የኢትዮጵያ ትምህርት እንደ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ይቅር ባይባልም መቸኮል ግን አይገባም። ግልጽ ባልሆነ ወይም ተገቢ ባልሆነ ዓላማ በመነዳትና ባለማስተዋል ተደናብሮም ትምህርት መጀመርም ተገቢ አይደለም። ሩስያን የመሳሰሉ አገራት በተናጠል በሚያካሂዱትና በሳይንሳዊ ሙከራ ጥሩ ውጤት እያመጡ ነው የሚሏቸውን ክትባቶች እንዲሁም በዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ ወደ ግምገማ የደረሱ ክትባቶችን ውጤት መጠባበቅ፣ የእነዚህን መጨረሻ ሠይቶና ሰምቶ ትምህርትን መጀመር የመሳሰሉ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ ነው።

የመፍትሔ ጭላጭል ከሌለ ማለትም ኮቪድ-19ኝን በክትባት መከላከልን ወይም በፍቱን መድኃኒት ማከምን በሚመለከት ተስፋ ሰጭ ነገር ቢታጣ እንኳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆችንና ጎልማሶችን በዘፈቀደ ትምህርት አስጀምሮ ለአደጋ ከማጋለጡ በፊት በተቻለ መጠን አደጋው ዝቅተኛ የሚሆንባቸውን አዋጭና ከአገር ዓቅም አንጻር ዘላቂ የሆኑ ስልቶችን መንደፍ ተገቢ ነው።
አካሄዱ ከፍተኛ ችግር ወይም በቀጥተኛ አገላለጽ እልቂትን ሊያስከትል የሚችል ነውና ከማንም በላይ ወላጆች ለልጆቻቸው ማሰብና መወሰን ይገባቸዋል። ትምህርት የሰሐራ በረሀን በመከራ አቋርጦ፣ የሊቢያን አራጆችን በአጋጣሚ አምልጦ፣ የሜድትራኒያን ባሕርን በማይረባ ታንኳ ተሻግሮ አውሮፓ በመድረስ ሕይወትን ለማቃናት የማሰብን ያህል ጥቂት ዕድለኞች ብቻ የሚያሳኩት ጉዞ መሆን የለበትም።
ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com