የእለት ዜና

የአፍሮ ባሮ ሜትር ጥናትና ብዙዎች <አልተዋጥክልንም› ያሉት የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር

Views: 568

ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላም ግማሽ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩ እንዳልተዋጠላቸው የአፍሮ ባሮ ሜትር አፍሪካ ጥናት አመላክቷል።

በአፍሪካ አገራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ጥናትና ምርምር የሚያከናውነው አፍሮ ባሮ የተሰኘው ይኸው ተቋም ኢትዮጵያውያን ዜጎች በአገራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየትንና ፍላጎቶችን በመዳሰስ ያገኘውን ውጤት በያዝነው ሳምንት ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ይህ መረጃ ይፋ የሆነው።

በኢትዮጵያ ካለው ብዝኀነት የተነሳ ራሳቸውን የቻሉ የክልል መንግሥታት ያሉት የፌዴራሊዝም ዓይነት አሁንም ለዚህ አገር የተሻለ የመንግሥት ቅርጽ ነው የሚሉ በአንድ ወገን ይገኛሉ። በአንጻሩ ፌዴራሊዝም በጣም ከፋፋይና ለግጭቶች የሚዳርግ ስለሆነ የኢትዮጵያ የመንግሥት ቅርጽ ማእከላዊ መንግሥት በውሳኔ ሰጪነት የበለጠ ኃይል ወደሚኖረው አሃዳዊነት የመንግሥት ቅርጽ መለወጥ/መቀየር አለበት የሚሉ ሐሳቦች አሁንም ድረስ ይነሳሉ።

ኢትዮጵያዊያን ከአሃዳዊ መንግሥትነት ይልቅ በፌዴራሊዝም ስምምነት ቢኖራቸውም ብሔርን መሰረት ያድረግ ወይስ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን የሚለው ላይ ልዩነት እንዳላቸው ጥናቱ አሳይቷል። በአብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊ ኢትዮጵያዊያን ምልከታም የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር አሁን እንዳለው የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ የክልሎች አወቃቀር ይሁን ወይስ የአገሪቷን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መሠረት ያደረገ ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ መልስ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ኹለት ዓመታት የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በፌዴራሊዝሙ እጣ ፋንታ ላይ ሰፋፊ ውይይቶችና ክርክሮች ሲደረጉ ቆይቷል።
የመንግሥትና የግል ሚዲያዎችም በየበኩላቸው ፖለቲከኞች፣ ለምሁራንና ለሲቪክ ማኅበራት ‹ሕገ-መንግሥቱ ከፀደቀበት 1987 ጀምሮ እየተተገበረ ያለው ብሔር/ ኅብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝም እንዳለ ይቀጥል ወይስ ይሻሻል ነው ወይስ አሃዳዊ ወደ ሆነው የመንግሥት ስርዓት ይቀየር› በሚለው ላይ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች እያዘጋጁ ነው።

እንደ ዳሰሳ ግኝቱ ታድያ 61 በመቶዎቹ በኢትዮጵያ ከአሃዳዊ ይልቅ ፌዴራላዊ መንግሥት አወቃቀር እንዲኖር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የፌዴራል መንግሥት አወቃቀሩን በሚመለከት ኢትዮጵያዊያን በኹለት የተከፈለ ፍላጎት ወይም ምርጫ እንዳላቸውም አሳይቷል። በዚህም ግማሽ የሚሆኑት (49 በመቶዎቹ) በአገሪቷ ያለው ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝምና በእርሱ የተዋቀሩት ክልሎች እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸው እንደሆነ ሲገልፁ፣ በተመሳሳይ ድርሻ (ማለትም 48 በመቶዎቹ) የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ የክልሎች አወቃቀር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ቢያደርግ ይመርጣሉ።

54 በመቶ የሚሆኑ ኑሯቸውን በከተማ ያደረጉ የጥናቱ ተሳታፊዎች የክልሎች አወቃቀር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መሰረት ቢያደርግ እንደሚመርጡ ጥናቱ ያመላከተ ሲሆን፣ 44 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ እንደማይደግፉ አመላክተዋል።

51 በመቶ በገጠር የሚኖሩ ማለትም እምብዛም እንደ ከተማ የብሔር ስብጥር የሌላቸው ዜጎች፤ እየተተገበረ ያለው የብሔር ፌዴራሊዝም ቢቀጥል እንደሚፈልጉ አሳይቷል።
የአፍሮ ባሮ ሜትር ጥናቶች የሚካሄዱት በዋናነት በገፅ-ለገፅ ቃለ መጠይቅ ሲሆን፤ የጥናቱ መረጃ አሰባሰብ ሂደት የጥናቱ ተሳታፊዎች በመረጡት አካባቢያዊ ቋንቋ እና ወካይ የሆነ የናሙና መጠን በመመደብ እንደሆነ ሙሉ ተካ፣ የአፍሮ ባሮ ዋና ተመራማሪ ጥናቱን ባቀረቡበት ወቀት ገልፀዋል።

ጥናቱ የተካሄደው 2400 ቃለ-መጠይቆችን ዕድሜአቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በማሳተፍ ነው። መረጃውም ከታኅሳስ እስከ ጥር 2020 የተሰበሰበስ መሆኑን ሙሉ ተካ ተናግረዋል። የናሙናው መጠን በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተሠራና ወካይነት ያለው መሆኑ እና የስህተት ህዳጉ +/-2 መቶኛና የአስተማማኝነት ደረጃው 95 በመቶ እንደሆነ ዋና ተመራማሪው አስረድተዋል።

ከፌዴራል አወቃቀሩ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ እንደሚፈልጉ አዲሱ የአፍሮ ባሮ ሜትር የጥናት ውጤት አሳይቷል። አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎችም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሻሻል እንጂ በአዲስ መተካት እንደሌለበት ይስማማሉ።

ይህም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ያሉትን ፍላጎቶች ለማስታረቅና ለማካተት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ሕገ መንግሥቱ በሚሻሻልበት ወቅት የተርታው ኅብረተሰብ ሐሳብና ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መቼ ይሻሻል የሚለው ሐሳብ ላይ የተለያየ አቋም እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ጠቁሟል። ከጥናቱ ተሳታፊዎች 1/3ኛ የሚሆኑት ሕገ መንግሥቱ ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ አስቀድሞ ቢሻሻል ሲሉ፤ ተመሳሳይ ድርሻ ያላቸው (ማለትም 33 በመቶዎቹ) ደግሞ ምርጫው ተካሂዶ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቢሻሻል ብለዋል። ቀሪዎቹ 29 በመቶዎቹ ምርጫው ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢሻሻል ይመርጣሉ።

አብላጫዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን በኹለት የምርጫ ጊዜ ብቻ እንዲገደብና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን የሚያይ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ይሻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ከኅብረተሰቡ ጋር በተወያዩበት አንድ የሐዋሳው መድረክም ‹‹ማንም መሪ ቢሆን ከኹለት የሥልጣን ዘመን በላይ መምራት የለበትም›› ብለዋል። በዚህም ልጓም ያልተበጀለትን የጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ቆይታ በግልጽ መቃወማቸው ይታወሳል።

የሥልጣን ቆይታ ባልተገደበባት ኢትዮጵያ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለበት 1987 ወዲህ ላለፉት 25 ዓመታት፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ሳይጨምር ኹለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ብቻ መርተዋል። ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት 1987 ጀምሮ መለስ ዜናዊ በሞት እስከተለዩበት 2004 ድረስ ለ16 ዓመታት መርተዋታል። ይህ እንግዲህ በፕሬዝዳንትነት የመሩበትን አራት ዓመታትን ሳይጨምር ነው።

በእርግጥም የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባላቸው አገራት የሥልጣን ገድብ ማስቀመጥ ግድ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በአህጉራችን አፍሪካ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን አንቀፆች እንደ ተፈለጉ ሲሻሻሉ ይስተዋላል። በድምሩ ግን ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ እንደሚፈልጉ አዲሱ የአፍሮ ባሮ ሜትር የጥናት ውጤት አመላክቷል።

የአገራችን መንግሥታዊ አስተዳደር የሚመራው በሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገው የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ በውክልና ዴሞክራሲ መርህ (Representative Democracy) የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕግ አግባብ በሚያደርጉት ምርጫ አማካኝነት ብቻ ነው።

ነገር ግን የተቀመጠ ገደብ ባለመኖሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኹለት የምርጫ ጊዜ ብቻ አገልግሎ ሥልጣን እንዲያስረክቡ የሚፈልጉ ተሳታፊዎች 73 በመቶ ናቸው። ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን የሚከታተል ፍርድ ቤት ቢቋቋም ፍላጎታቸው የሆነው ደግሞ 55 በመቶ እንደሆኑ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል።

ባለፉት ኹለት ዓመታት ከአገር ውጪ የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር መግባትን ተከትሎ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የተለያዩ ድምፆች ይሰማሉ። በአገሪቷ በታየው ለውጥ እንዲሁ ሚዲያዎች ተስፋፍተዋል። በሕገ መንግሥቱ ላይ በተለያዩ አካላት የሚታዩ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ሚዲያዎች የፖለቲካ ምሁራንን በመጋበዝ ጠንከር ያሉ ክርክርና ሙግቶች እየተካሄዱ መሆኑን ጥናቱ አውስቷል።

በአንጻሩ 11 በመቶ የሚሆኑት ከነአካቴው ሕገ መንግሥቱ በአዲስ መተካት አለበት የሚል ሐሳብ አንፀባርቀዋል። 18 በመቶዎቹ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ አሁን ባለበት እንዲቀጥል ይሻሉ።
ታማኝ የሆኑ መረጃዎችን በዋናነት ዴሞክራሲ፣ አስተዳደርና የኑሮ ጥራት ላይ በማሰባሰብ የካበተ ልምድ አለኝ የሚለው አፍሮ ባሮ ሜትር፣ አፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረገ ገለልተኛ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም ነው። በአጠቃላይም በ38 የአፍሪካ አገራት ላይ ከ1999 እስከ 2018 ጥናቶችን መሥራቱን ጨምሮ አስታውቋል።

በተጨማሪም ተቋሙ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን መስጠቱን በተመለከተ፣ ከምክር ቤቱ ውጪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን የሚከታተል ፍርድ ቤት ይቋቋም ወይስ እንደነበት ይቀጥል የሚለውንም ጥናቱ ለመዳሰስ ችሏል።

አንቀጽ 39 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ዋስትና የሚሰጥ እንዲሁም የራስን ክልል የማዋቀር መብት የሚያረጋግጥ መሆኑን በመጥቀስ አንቀጹ በሕገ መንግሥቱ እንዲቆይ የሚፈልጉት 50 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ነው ጥናቱ ይፋ ያደረገው።

በዚህ መሠረት ይፋ የሆነውን የሪፖርቱን ግኝቶችን አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፓርላማው፣ ከአስፈጻሚው፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ከለጋሽ አገሮች፣ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ቀጣይ ውይይቶችን እንደሚያዘጋጁም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የፌዴራል ዴሞክራሲ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሰረት ተግባራዊ አለመደረጉ እና እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲተገበር ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው የፌዴራልና የክልሎች ተዋረዳዊ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት አካላት የጎንዮሻዊ የሥልጣን ክፍፍል ድንጋጌዎችና መርሆዎች በትክክል መተግበር አለመቻል ሩብ ከፍለ ዘመን አስቆጥሮም ግማሽ የሚደርሱ ኢትዮያውያን ሊዋጥላቸው አልቻለም። ምናአልባትም በየጊዜው እየጨመሩ የመጡት ግጭቶ ገፊ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

እንዲሁም ኅብረ ብሔራዊው፣ ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራሊዝም በትክክል ሥራ ላይ እንዲውል የራስ አስተዳደርና የጥቂቶች እንዲሁም የዜጎች የግል መብቶች ተጣጥመው መተግበር ይኖርባቸዋል። ይህን ለመተግበር አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችን ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው።

እንዲሁም የፌዴራላዊ ሥርዓቱን ተቀባይነት ባላቸው የዴሞክራሲ መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ መተግበር፣ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ጠለቅ ያለ የማሳወቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com