የእለት ዜና

ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከግል ተቋራጮች ጋር አብሮ ለመስራት ልየታ ጀመረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለደንበኞቹ ፍትሀዊ ተደራሽነትን ያረጋገጠና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከማድረስ አንጻር ሁሉንም ስራዎች በራሱ አቅም ብቻ ለመሸፈን ከመጣር ይልቅ የሶስተኛ ወገን ወይንም የግል ተቋራጮችን ለማስገባት የሚሰሩ ስራዎችን በመለየት ላይ እንደሚገኘ አስታወቀ።

ይህም የተነገረው ተቋሙ ያለፈውን በጀት አፈፃፀምና የ2013 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት ባሳለፍነው ሀሙስ ነሐሴ 21/2012 በሒልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በመግለጫው ላይም የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሽፈራው ተድላ እንደገለፁት በአሁኑ ሰአት እጅግ እየተስፋፋ የሚገኘውን የተቋሙን የአገልግሎት ስራዎች በተቋሙ ብቻ ለመሸፈን በመሞከር የደንበኞችን እርካታ ማረጋገጥ አይቻልም። ስለዚህ የሶስተኛ ወገን (outsoursing) ስራዎችን በመለየት በአገሪቱ ያሉ የግል ተቋራጮችም በዚህ ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በ2012 የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩና በቀጣይም ይህ ሄደት ተጠናክሮ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል።

ይህንንም በሶስተኛ ወገን ላይ የሚሰራ ስራ ለመቆጣጠር የሚያስችል ውል አለ ያሉት ስራ አስፈፃሚው በውል ስምምነቱ መሰረት የሶስተኛ ወገን ወይንም ተቋራጭ ሆኖ የሚገባ አካልን የምንቆጣጠርበት እና የምናስተዳድርበት ስርአት ስላለ በዛ መሰረት ይከናወናል ብለዋል።

ነገር ግን እነዚህ በሶስተኛ ወገን የሚሰሩ ሰዎችም ይሁኑ ሌሎች አካላት ከደንበኞች ጋር ትክክለኛ ያልሆነ ግንኙነትን በመፍጠር ተፅእኖ ያሳርፋሉ የሚል ስጋት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መፈጠሩን ተረድተናል ያሉት ሽፈራው፤ የሶስተኛ ወገን ሰራተኛም መስለውም ይሁን ከሶስተኛ ወገን ጋር ንዑስ ተቋራጭ የነበሩ ሰዎች ስራቸውን ሲያቋርጡ ተመልሰው ማህበረሰቡን ለማጭበርበር የሚሰሩበት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

‹‹ይህን ለመከላከል ህብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት አገልግሎቱን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደመሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች የራሳቸው መታወቂያ አላቸው። በመሆኑ ማህበረሰቡ መታወቂያ መጠየቅ ይችላል ከዛ ውጪ የሆነ ጥያቄ ከመጣ ደንበኞቻችን በአካባቢው ለሚገኝ የፖሊስ አካል እና ለተቀዋሙ ቢሮውም ቢሆን በቀጥታ ሪፖርት በማድረግ ይሄን ወንጀል መከላከል እንችላለን።›› ሲሉ ስራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ2011 በጀት አመት ጀምሮ አጠቃላይ የተቋማዊ ማሻሻያ ስራዎችን የጀመረ ሲሆን ለደንበኞች እንዴት የተሻለ አገልግሎት ወደሚሰጥበት ቁመና መምጣት ይችላል፣ እንዲሁም እንዲሁም ለዚህ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ስራዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ከአደረጃጀት ከሰው ሀይል ከአሰራር ጀምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውም በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

ተቋሙ በአጠቃላይ ስራቹን በሶስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ላይ አጠንንክሮ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን እነዚህም የትኩረት መስኮች በተቋሙ ያልተማከለ አደረጃጀትና አሰራርን መተግበር፣ ስራዎችን በሶስተኛ ወገን ማሰራትና ተቋሙን በቴክኖሎጂ በማዘመን የቋሙን አሴት ዲጂታላይዝድ ማድረግ እንደሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል ባሳለፍነው የ2012 በጀት አመት ተቋሙ ለ1 ሚሊዮን ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማድረስ አቅዶ የነበረ ሲሆን የእቅዱን 16.87 በመቶ ወይንም ለ ከ168 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ማድረስ መቻሉን ሽፈራው አስታውቀዋል።

በዚሁም በተገባደደው በጀት አመት የሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መልሶ ግንባታን ጨምሮ 405 ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ላይ የፕሮጀክት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከእቅዱም ውስጥ 325 የሚሆኑ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የኤሌትሪክ አቅርቦቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መደረግ መቻሉ ተገልጿል።

ተቋሙ በ2012 ከሀይል ሽያጭ 23.75 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ሲሆን የእቅዱን 80 በመቶ በማሳካት 11.06 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት አመቱ በእቅድ ይዞት ከነበረው 25.38 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 14.97 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 59 በመቶ ማሳካት መቻሉም ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!