በዓል እና የመገናኛ ብዙኃን መሰናዶዎች

Views: 111

ኢትዮጵያዊያን ለበዓል ቀናት ያለን ስሜት ልዩ ነው። በተቻለን አቅም ሁሉ እለቱን በልዩ ስሜት፣ ደስታ እና በምቾት ማሳለፍ እንፈልጋለን። የዘወትር እንቅስቃሴዎችም ለበዓል እረፍት ስለሚወስዱ፣ እኛነታችን በሚያጎሉ ወግና ባህልን መሠረት ባደረጉ ስነ ስርዓቶች ታጅበን በዓላትን ከቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ ጎረቤት ጋር ሰብሰብ ብለን በማክበር ልምዳችንም እንታወቃለን።

በዓልን በልዩ ስሜት ከማክበር ጋር በተገናኘ ከበዓሉ አንድና ኹለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ቅድመ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። መኖሪያ ቤት ይፀዳል፣ አስፈላጊ ከሆነም ይታደሳል፣ አልባሳት ይታጠባሉ አዲስ የሚገዛም ከሆነ ይገዛል፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ይዘጋጃሉ፣ ጠላ ይጠመቃል፣ ድፎ ዳቦ ይደፋል፣ ዶሮ፣ በግ፣ በሬ የመሳሰሉ ለእርድ የሚቀርቡ እንስሳት ይገዛሉ። ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ እናት አባት ሁሉም በየፊናው ለበዓሉ የሚጠበቅበትን ዝግጅት ያደርጋል።

ታዲያ የእነዚህን የበዓል ዝግጅቶች ድባብ በማጉላትም ሆነ እለቱን ሞቅ ደመቅ ባለ ሁኔታ እንድናከበርው ለማድረግ ልዩ የበዓል ስሜትን መፍጠር የሚችሉ የተለያዩ መሰናዶዎችን በማዘጋጀትም የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በየፊናቸው ወዲህ ወዲያ ሲሉ ይሰነብታሉ።

እንደሚታወቀው በአገራችን የሚገኙ የተለያዩ የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከበዓል መዳረሻ ቀኖች ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት እለት ድረስ የተለያዩ በዓል በዓል የሚሸቱ ሙዚቃዎችና የአውዳመት መሰናዶዎችን አዘጋጅተው በማቅረብ እለቱን በልዩ ድምቀትና የደስታ ስሜት እንድንቀበለው የሚያደርጉት አስተዋፅዎ ይህ ነው የሚባል አይደለም። በተለይም የበዓሉ እለት የሚቀርቡ የመዝናኛ ዝግጅቶች እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶች በብዙዎቻችን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁና ለበዓሉ ድምቀት ተቀዳሚ ምርጫዎች ናቸው።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ልዩ የአውዳመት መሰናዶዎች ተብለው የሚተላለፉና የሚቀርቡ ዝግጅቶች ልዩ መሆናቸው እየቀረ፣ አሰልቺና አታካች እየሆኑ መምጣታቸውን በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል። የአዲስ ማለዳ ጥበብ እና ሕይወት መሰናዶዋ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አጠር ያለች ዳሰሳ አድርጋለች።

የበዓል ፕሮግራሞች ይዘት ተመሳሳይነት
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቴሌቭዥንም ሆነ የሬዲዮ ጣቢያዎች በቁጥር እየተበራከቱ መጥተዋል። የመበራከታቸውን ያህልም ወደ ተመልካቾቻቸው ይዘው የሚቀርቡት ዝግጅት በይዘትም ሆነ በጥራት በዛው ልክ ሊጨምር ይገባዋል። ነገር ግን ይህ እየሆነ አይደለም። በተለይም በበዓል ወቅቶች በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ለማለት በሚያስችል መልኩ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች የአቀራረብ እና ይዘት ተመሳሳይነት፣ በየበዓሉም የሚጋበዙት የጥበብ ባለሙያዎች፣ ኮሜዲያን እና ሌሎች እንግዶች ተደጋጋሚነት ብዙዎችን እያሰለቸ እንደሚገኝ ብዙዎች ይገልፃሉ።

አሁን አሁን በዓል በመጣ ቁጥር የሚተላለፉ የቴሌቭዥን እና የሬዲዮ ፕሮግራሞች እጅግ አሰልቺና ተደጋጋሚ በመሆናቸው እንደ ወትሮው ሁሉ በናፍቆት የሚጠብቃቸው ሳይሆን እንዲሁ ጠዋት ላይ ብቻ እቤት ውስጥ በሚኖረው ጊዜ ጣቢያዎችን እየቀያየረ የሚመለከታቸው መሆኑን የሚገልፀው ዮናስ ሰለሞን ነው። ዮናስ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ በዓላት ሲመጡ ያለውን ስሜትና በዓሉን አስታከው የሚተላለፉ የመገናኛ ብዙኃን መሰናዶዎችን በተመለከተ ያለውን ሐሳብ አካፍሏል።

‹‹ዓመት በዓሎች ለኔ ደስ የሚል ስሜት ይሰጡኛል›› ይላል ዮናስ ስለበዓል ያለውን ስሜት ሲያስረዳ ‹‹ዓመት በዓል ሲዳረስ ጀምሮ በየቦታው የሚከፈቱ የአውዳመት ሙዚቃዎች ይስቡኛል። በተለይም የበዓሉ እለት ቤተሰብ ተሰብስቦ እየተበላ እና እየተጠጣ በሳቅ በጨዋታ የማሳልፈው ጊዜ እጅግ ይናፍቀኛል።››

‹‹ነገር ግን አሁን አሁን…›› በማለት ሐሳቡን ይቀጥላል ዮናስ፣ ‹‹ነገር ግን አሁን አሁን የበዓሉ እለት በቴሌቭዝን የሚተላለፉ ዝግጅቶችን ለማየት ስከፍት ምንም የሚያስደስት ነገር አላገኝም። ያው ባለፈው በዓል ያየኹት አርቲስት እና ኮሜዲያን በአሁኑም ቁጭ ብሎ ኢንተርቪው ሲደረግ ይታያል። ሌላ ጣቢያ ብትቀይርም ያንኑ ሰው በዛም ጣቢያ ሌላ ነገር ሲሠራ ልታየው ትችላለህ። ስለዚህ ከባለፈው በዓል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፕሮግራም እንደሆነ ስለምገምት በየመገናኛ ብዙኃኖቹ የሚተላለፉት የበአል መሰናዶዎች ትኩረቴን መሳብ አቁመዋል።›› በማለት እንደ በፊት ጊዜው ሁሉ የበዓል መሰናዶዎችን በጉጉት መጠበቅና መከታተል ማቆሙን ይገልፃል።

‹‹እኔ አሁን በዋናነት ፊልም ባለሙያ ነኝ። የመጀመሪያ የበዓል ፕሮግራማችንን ስንሠራም ይሄ የይዘት እና የአቀራረብ ተመሳሳይነት ልክ አለመሆኑን እና እንደዚህ እንደማይሠራ ለማሳየት ነው የሠራነው።›› የሚለው ደግሞ የብሬ ማን ፊልም ፕሮዳክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብርሀኔ ጌታቸው ነው። ዝም ብሎ ሲወራ እና በተግባር ሲሠራ ስለሚለያይ ከኋላ ሆኖ ልክ አይደለም ከማለት ሠርቶ ማሳየት ይሻላል በማለት የመጀመሪያ ፕሮግራሙን መሥራቱንም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ አጫውቶናል።

‹‹የመጀመሪያ ነው ሊባል በሚችል ደረጃ እኛ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ ሰዎች በእለቱ ሌላ ፕሮግራም ላይ ሄደው መሥራት፤ ሌላው ቢቀር መግለጫ እንኳን ቢሆን በእለቱ መስጠት እንደማይችሉ ብዙ ስምምነቶችን አድርገን ነው ቀረፃ የምንጀምረው።›› በማለትም የበዓል ፕሮግራሞች ተመሳሳይነትና በየመገናኛ ብዙኀኑ የሚጋበዙ ሰዎችን ተደጋጋሚነት ለማስቀረት በፕሮዳክሽኑ በኩል እየሠራ ያለውን ሥራ ያስረዳል።

የፕሮግራም ይዘት እና የአቀራረብ ስልቱ ተመሳሳይት ከየት የመጣ ነው? በማለት አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄም ብርሀኔ ሲመልስ ‹‹አንደኛ የፈጠራ ችሎታ አለመኖር ነው። ምን አልባትም አንድ ተመሳሳይ የሆነ አዳራሽ ውስጥ ሰው ትጠራለህ፣ ከዛ የሆን ቢራ ስፖንስር ያደርግሃል፤ እሱን እየጠጡ በመዝፈን ወይ በመቀለድ የተገደበ ነው።

በተጨማሪም ሌላው ጉዳይ ደግሞ የስነ ስርዓት ጉዳይ ነው። እራሱ የምትጠራው አርቲስት ‹እዚህ ቦታ ቀርቤያለሁ ስለዚህ በእለቱ አምስት ስድስት ቴሌቭዥን ላይ መቅረብ የለብኝም!› ብሎ የራሱንም ክብር ማስጠበቅ አለመቻል ነው። ግን ደግሞ እንደውም ከሆነ ጊዜ በኋላ ተጀምሮ ሊሆን ይችላል እንጂ ክፍያም ብዙ አልነበረውም። ለብር ነው አርቲስቶቹ የሚበዙት እንዳይባልም።›› በማለት ያስረዳል።

‹‹እንደ አገር አንድ ነገር ትለምድና እሱን እየተቀባበልክ የመሄድ ልምድ አለ። አንዱ ዳቦ ቤት ከከፈተ ጎረቤቱም ዳቦ ቤት እንደሚከፍተው ማለት ነው።›› የሚለው ብርሀኔ ነገር ግን ይሄ ጉዳይ የእነሱን የበዓል ዝግጅቶች እንደማይመለከትም ያስረዳል።

‹‹እኛ ሙሉ ለሙሉ ይሄን የተመሳሳይነት ችግር ለማስተካከል ነው ፕሮግራሙን እራሱ የጀመርነው። እነቴዎድሮስ ታደሰን ከአሜሪካ ድረስ አስመጥተን በትልልቅ አርቲስቶች ሙሉ ዝግጅቶችን አድርገን የሠራን በመሆኑ ከተመሳሳይ ፕሮግራሞች ለመለየት የራሳችንን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል።›› ይላል።

አዲስ ሐሳብ ባለሞያን ከማምጣት አንፃር
መቼም ዓመት በዓል ሲመጣ በቴሌቭዥን መስኮትም ይሁን በሬዲዮ ጣቢያዎች በሚተላለፉ የበዓል መሰናዶዎች ላይ የተለመዱ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ዘፈን ስለዘፈኑ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖና ተቀባይነት ከፍተኛ ስለሆነ፣ ወይንም ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የሚያወሯቸው ቀልድ እና ገጠመኞች ህብረተሰቡን ሊያዝናና ይችላል ተብሎ ታስቦም ሊሆን ይችላል። ብቻ የበዓሉ አድማቂ እንዲሆኑ ታስብው ይጋበዛሉ።

ችግሩ ያለው ከመጋበዛቸው ሳይሆን በየበዓሉ እና በየመገናኛ ብዙኃኑ መደጋገማቸው ነው። ይህም አርቲስቶቹን፣ ዝግጅቱንም ሆነ የዝግጅቱን አቅራቢዎች ሳንወድ በግዳችን እንድንሰለቻቸውና ምነው እኛ ብቻ ነን የበዓል አክባሪዎች አሉ! እንድንል ይገፋፉናል።

‹‹መጋበዝ የሚገባቸው አዳዲስና ጎበዝ የጥበብ ባለሙያዎች ብዙ አሉ እኮ›› የሚለው ዮናስ ነው። አክሎም ‹‹ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የማስታወቂያ ደርጅቶች እና የፕሮዳክሽን ባለሙያዎች ስለበዙ ሚዲያውም እድሉን ለእነሱ ይሰጣል። እነሱ ደግሞ የሚፈልጉትን ሰው ብቻ ጠርተው እኛን ሲያደነቁሩን ይውላሉ። እታች ያሉትና በጣም አዝናኝ የሆኑ መሰናዶዎችን ወደ ሕዝቡ ይዘው መቅረብ የሚፈልጉትን ወጣቶች አይደገፉም።

ፕሮግራሙን ከሚመሩት ጀምሮ እንግዳ ሆነው እስከሚቀርቡት እና የሚታደሙትም ጭምር በመተዋወቅ እና በጥቅም እንጂ ሕዝቡ ምን ይፈልጋል ተብሎ የሚመረጡ አይደሉም። ይሄንንም እነሱ የቀለዱበትን ፕሮግራም ይዘው መሄጃ የላቸውም እና ይመለከቱናል በማለት በየመገናኛ ብዙኃኑ ይቀርባሉ።

እውነቴን ነው የምለው! አሁን አሁን የቴሌቭዥን የበዓል ፕሮግራሞችን ከማይ ከቤት ወጥቼ ከጓደኞቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ እየበለጠብኝ መጥቷል። እንደ ድሮው ከቤተሰብ ጋር ተሰብስቦ የበዓል መሰናዶዎችን እየተመለከቱ በዓልን በቤት ውስጥ የማሳለፍ ልምዴን ሁሉ ነው እንድጠላው ያደጉኝ።›› በማለት ትንሽ ምሬት ባዘሉ ቃላቶች ሐሳቡን ይገልፃል፤ ዮናስ።

‹‹አንደኛ አሁን ያለው የፕሮግራም አቀራረብ ልምድ ለሌሎች እድልን አይሰጥም። የሆነ አንድ ይወደዳል ተብሎ የሚትገመት ሰው አምስት ስድስት ቦታ ላይ እየተጠራ ሲቀርብ ሌሎቹ ሊወደዱ የሚችሉ፤ ከዛ በላይ አቅም ያላቸው ሰዎች እድል ያጣሉ።›› የሚለው ደግሞ ብርሀኔ ነው።

‹‹ከዛም በላይ ግን…›› በማለትም ብርሀኔ ሐሳቡን ይቀጥላል ‹‹ከዛ በላይ ግን ተመልካቹን ሰው በጣም ማሰላቸት ነው። አንድ ቲቪ ላይ ስትከፍት የሆነ ሰውዬ ተመሳሳይ ነገር እያደረገ፣ አንዱ ጋርም ስትከፍት ወይ እንቁላል ይዞ እየሮጠ፤ እንደዚህ እንደዚህ አይነት ነገር ሲሆን ተመልካች ይሰለቻል። ትልቁ ነገር ደግሞ አምጥተህስ ያንን ሰው ምን እንዲያደርግ እያደረከው ነው ያለኸው ነው? ያለውን አቅም ለወጣቶች እንዲያሸጋግር እያደረክ ነው ወይስ እንዲያዝናና ነው?›› ብርሀኔ የሚያነሳው ሐሳብ ነው።

ከታዘበው በመነሳት አንድ አጋጣሚ ሲጠቅስም፣ በአንድ መሰናዶ ላይ አዘጋጆቹ የአገራችን ትልቅ የሚባል የሙዚቃ ባለሙያ አንድ ፕሮግራም ላይ ጠርተው ገመድ ያስዘልሉታል። ‹‹ታዲያ አሁን ይሄ ምንድን ነው? በዛ ሰው ገመድ በመዝለል እንደ አገር ሆነ እንደ ተረካቢ ትውልድም የሚያመጣው ለውጥ አለ?።›› በማለት መልሶ ይጠይቃል።

‹‹የእኛን ልምድ ብነግርህ እኛ ጋር መጥተው እና የበዓል ፕሮግራማችን ላይ ተሳትፈው እና ከትልልቆቹ ጋር ልምድን ተካፍለው በአሁኑ ሰዓት ውጤታማ የሆኑ አርቲስቶች አሉ። እነ ራሄል ጌቱ፣ ዘቢባ ግርማን ልትወስድ ትችላለህ። በዛች በአንድ ፕሮግራም ያገኙት ልምድ እና ሐሳብ ብቻቸውን ወጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በዛ ላይ ደግሞ ወጣቶችን ብቻ ከማሳተፍ ሳይሆን ትላልቆችንም ብዙ ልምድ እና አቅም ኖሯቸው ሰው የማያስታውሳቸው ሰዎች አሉ። ስለዚህ ይህ አካሄድ ለእነሱ እድል አይሰጠም።››

የመሰናዶዎችና መሰናጃ ስፍራቸው?
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ወግ፣ ባህል እና ስርዓቶች ባለቤት አገር ናት። እነዚህ ወግ እና ስርዓቶች ደግሞ በየአካባቢው በሚገኙ የአኗኗር ዘይቤዎች ይገለፃሉ። ታዲያ ዓመት በዓል ሲመጣ እነዚህን አካባቢዎችን በመድረስ የበዓል አከባበር ስነስርዓታቸው ምን ይመስላል የሚለውን ለማኅበረሰቡ ማድረሱ ከማዝናናቱም በተጨማሪ ተመልካቹ በየአካባቢው ያለው የበዓል አከባበር ስነስርዓት ምን ይመስላል የሚለውን እንዲገነዘብ ያደርገዋል።

ነገር ግን አሁን አሁን እነዚህ አካባቢዎች ከአንዳንድ በጣት ከሚቆጠሩ የበዓል መሰናዶዎች ውጪ እምብዛም ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲዳሰሱ አይስተዋልም። የአብዛኞቹ አዘጋጆች የቀረፃ ትኩረት በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በሚገኙ የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል።

‹‹እኛ ይሄንን እንደ ችግር ይዘን ብዙዎቹን ፕሮግራሞቻችንን አርባምንጭ፣ ቢሾፍቱ ጎንደር እና ሌሎች ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች ወጥተን ነው የሠራናቸው።›› የሚለው ብርሀኔ፣ ነገር ግን ትልቁ ችግር በዚህ ሥራ ላይ የበጀት ችግር እንደሆነም ይገልፃል።

‹‹በዚህ ጉዳይ አሁን ብዙ ፕሮዲውሰሮችን ወይም ፕሮዳክሽኖችን አልወቅስም። ምክንያቱም ሥራው በጣም ከፍተኛ በጀት ይጠይቃል። እዚህ ጋር አሁን የእኔን የአርባ ምንጭ ወይንም የደብረዘይት ልምዴን ባነሳ አንዳንድ አካሎች ሐሳቡን ስለወደዱትና ፕሮግራማችንን ስፖንሰር ስላደረጉት ነው እንጂ፤ በግሌ እዛ ሄጄ ልሥራ ብል በብዙ መቶ ሺሕ ብሮች ወጪ ይጠይቃል። ስለዚህ ዋንኛው ችግር የበጀት ነው።›› ይላል።

‹‹ከከተማ ወጣ ተብለው የሚሠሩ ፕሮግራሞች ከሚተላለፈው ከሙዚቃ ወይንም ፕሮግራም በላይ አገርን የማስተዋወቅና ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ብዙ ቱሪስቶችን የመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው።›› የሚለው ብርሀኔ ‹‹ነገር ግን ዋነኛው ችግር የበጀት ችግር ነው። እዚሁ ቅርብ አካባቢ ያለምንም ችግር አስፈቅዶ መሥራትና 50 እና 60 አባላት ያሉት ፕሮዳክሽን ይዞ ክፍለ አገር ድረስ ሄዶ መሥራት በተለይ ብዙዎቹ የማይተባበሩ ከሆነ በጣም ከባድ ነው።›› ሲልም የፕሮዳክሽኖች አቅም ማነስ በተለያዩ ክልል እና አካባቢዎች ፕሮግራሞቹን እንዳይሠሩ ተግዳሮት መሆኑን ያነሳል።

በቀጣይ የበዓል ፕሮግራሞች ምን ይምሰሉ?
‹‹ከዚህ በፊት ጄ ቲቪ ስርጭቱን ሳያቋርጥ በጆሲ /ዮሴፍ በቀለ/ የሚቀርቡ የነበሩ ፕሮግራሞች በጣም ነበር ደስ የሚሉኝ።›› በማለት ዮናስ ትውስታውን ለአዲስ ማለዳ እንዲህ ያጋራል።
‹‹የበዓል ጊዜ በጄ ቲቪ የሚታዩና ሰውን መርዳት ላይ ትኩረት ያደረጉት መሰናዶዎች በጣም ይስቡኝ ነበር። የበዓል ቀን ከቤተሰብ ጋር ተሰብስበን የእሱን ዝግጅቶች እያየን ማልቀስ ነበር። ማልቀስ ስል ታዲያ ሰው በመረዳቱና በበዓል ቀን ደስተኛ ሆኖ በመታየቱ የሚሰማውን ስሜት በማሰብ በሚሰማን ደስታ ነበር የምናለቅስው። የደስታ እንባ ማለት ነው። አሁን ግን ስርጭቱም ተቋረጠ መልሰን እንግዲህ አርቲስቶቻችንን በየሚዲያው እንደጉድ ልናያቸው ነው።›› የሚለው ዮናስ ቀጣይ የበዓል መሰናዶዎችም መሰል በጎ ሥራዎች የሚሠሩባቸው፣ ያልታዩ እና እምቅ አቅም ያላቸው ግለሰቦች የሚወጡባቸውና ከሳቅ ከጨዋታም ባለፈ ቁም ነገር የሚተላለፍባቸው ይሆኑ ዘንድ ተስፋ እንደሚያደርግ ይገልፃል።

‹‹ጉዳዩ የፈጠራ አቅምን ከማጎልበት ጋር የተያያዘ ነው።›› የሚለው ደግሞ ብርሀኔ ነው። ‹‹አሁን በሐሳብ ማመካኘት አይቻልም። ስለ በጀት ስለ ማቴሪያል ልናወራ እንችላለን፤ ከሌሎች ጋር አንፎካከርም ልንልም እንችላለህ። ሐሳብን ግን ምንም የሚገድብ ነገር የለም። እራሳችን ልንፈጥረው የምንችለው ነገር ነው። ወይንም ደግሞ የሚያማክሩንም ሰዎች ካሉ ሊሰጡን የሚችሉት ነገር ነው።
አንድ ቦታ ተሰብስቦ የሆነ ነገር ስለተደረገ እኛም ያንን ማድረግ የለብንም። ስለዚህ የበዓል ፕሮግራም ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት ፕሮግራም ልንሠራ ስናስብ የመጀመሪያ ጥያቄያችን መሆን ያለበት በዚህ የአንድ ሰኣት ወይንም የኹለት ሰዓት ፕሮግራም ላይ ምንድን ነው ላስተላልፍ የምፈልገው? በማለት እራሳችንን መጠየቅ አለብን።

ምንድን ነው ዓላማው? ማዝናናት ሊሆን ይችላል፣ ከአንዱ ትውልድ ወደ አንዱ ትውልድ የሙያ ቅብብል ለማድረግ ይሆናል ወይስ ደግሞ የሆነን ሰው የሕይወት ልምድ በመጠየቅ ለተመልካች ልናካፍል ይሆናል። ሰው አይቶት ሲጨርስ ምንድን ነው ይዞ የሚወጣው ብለን ጠይቀን ከተነሳን በጣም ቀላል ነው።››

ሌሎቹ ባልሠሩበት አቅጣጫ ምን ፈጥሬ ልምጣ ብለን ማሰብም ወሳኝ ነው የሚለው ብርሀኔ ይሄን ስናስብ መልሱን እናገኛለን፣ ብዙ ነገሮቹም የሚመሳሰሉ አይሆኑም ይላል። ‹‹አንድ ፕሮግራም ላይ አንዱ የሆነ እንቁላል ይዞ ካልተሯሯጠና አንተ ደግሞ ጀበና አስይዘህ የምታሯሩጥ ከሆነ ምንድን ነው በዛ መሯሯጥ ውስጥ ለአገርም ሆነ ወጣቱ ላይ የምታመጣው ለውጥ? ይሄንን እራስህን ከጠየቅክ ይገባሀል። ለውጥ አለው እንኳን ብለህ ብታስብ ተሠርቶበታል። ሰለዚህ አንተ ደግሞ የራስህን ሐሳብ ይዘህ ለመነሳት ትሞክራለህ ማለት ነው።››

በ2013 ዘመን መለወጫ ምን እንጠብቅ?
ዘንድሮ በተለይም ከፋሲካ በዓል ወዲህ ያሉ በዓሎች እንደወትሮው ሁሉ በልዩ ድምቀት እና የአውዳመት ግርግር የሚከበሩ አይደሉም። የኮሮና ወረርሽኝ ከንክኪና ከጥግግት እራሳችን እንድንጠብቅና የቀድሞውን የበዓል ልምዳችንን ሁሉ እንድንቀንስ እያስገደደን ይገኛል።

ወረርሽኙ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ የተከበሩትን አብዛኞቹን የአንድነት በዓላትን በተናጥል ከቤተሰብ ጋር ብቻ በመሆን ያከበርናቸው ሲሆን፣ የ2013 የአዲስ ዓመት መግቢያም በዚሁ መልኩ የመከበሩ ጉዳይ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ታዲያ ይህን በቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ብቻ እንድናሳልፈው የተገደድነውን በዓል ልዩ ድባብ ሰጥተው የቀደመውን ጊዜ እያስታወሱ የአሁኑን አስከፊ ወቅትም እያስረሱ በተስፋና ደስ በሚል ስሜት መጪውን ዓመት እንድንቀበለው የማድረግ ከፋተኛ ሥራም ከመገናኛ ብዙኃን ይጠበቃል።

‹‹በዘንድሮው በጣም ከባድ ነው። ለምን ብንል አሁን ጊዜውም የኮሮና ወረርሽኝ ከቤት የሚያስቀምጥ እንደመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደውም በአሁኑ በጣም የተለዩ እና የሚያዝናኑ ፕሮግራሞችን የመገናኛ ብዙኃኖች ማዘጋጀት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ሰዉ ቤቱ ተከቶ ነዋ የሚያከብረው! እንደ ድሮው ልውጣ ዘመድ ልጠይቅ ከወዳጅ ጓደኞች ጋር ላሳልፍ ቢል በሽታውም አይፈቅድለትም። ሰዉም ቢሆን እንደ ድሮው በደስታ መንፈስ እጁን ከፍቶ አይቀበለውም።

ስለሆነም ያለው አማራጭ እቤቱ ሆኖ ማሳለፍ በመሆኑ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የሆነ የማዝናናትና የበዓሉን ድባብ የማምጣት ሥራ ይጠበቅባቸዋል።›› በማለት ዮናስ ሰለሞን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና የፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢዎች ያለባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን በማሳሰብ ሐሳቡን ይቋጫል።

በእኛ በኩል ትልቅ ፕሮዳክሽን ሠርተናል በአሁኑም አዲስ አመት ይተላለፋል የሚለው ደግሞ የብሬ ማን ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጁ ብርሀኔ ጌታቸው ነው። ‹‹ፕሮግራሙም በጣም የምንወደው እና የምናከብረው ይልማ ገብረአብን የምናከብርበት፣ የእርሱ ሥራ የሆኑ ዘፈኖች ብቻ የሚዘፈኑበት፣ ትልልቅ አርቲስቶች እነ ሰርፀ ፍሬስብሐት፣ የትነበርሽ ንጉሤ፣ እነፀሐዬ ዮሐንስ፣ እነግርማ ተፈራ እና ጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ የተገኙበት ትልቅ ፕሮግራም ሠርተን እናቀርባለን። የሚገርመው ግን ቀድሞ ተቀርፆ በኮሮናው ተፅእኖ ምክንያት የቆየ መሰናዶ ነው።

ከዛ ግን እኛ ከዚህ በፊት በእያንዳንዱ ፕሮግራማችን ላይ ስለ አይምሮ ሕመም እንሠራለን። ላለፉት አምስት ዓመታት እኔ የአዕምሮ ሕመም ላይ ሠርቻለሁ። ስለዚህ የአዕምሮ ሕመም ላይ አሁን ልንሠራ አሰብንና ቀረፃ ሰናደርግ እንዴት አስቸጋሪ እንደነበር ለመግለፅ ይከብዳል። በየዓመቱ በዓል ሲመጣ ይጠብቁናል። ወደ ዐስር ሺሕ የሚሆኑ የአፍ መሸፈኛ ጭንብሎች ስፖንሰር ተደርገን ይዘን ሄደን ነበር። እንደድሮው እንደፈለግን ተቆጣጥረን መሥራት ግን አልቻልንም።

አንደኛ ለፕሮዳክሽን ቀረፃም ከባድ ነው። ምክንያቱም እንዳትሰጥም እንዳትቀበልም በሽታው ከባድ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ ጥቂት የሆኑ ታማሚዎችን ብቻ ይዘን በምንችለው ጥንቃቄ በማድረግ ለመሥራት ሞክረናል። ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። ኮሮና በአጠቃላይ እንደ አገር ጎድቶናል። ይሄንን የመዝናኛ ዘርፍም በጣም ጎድቶታል።›› ሲል ብርሀኔ የኮሮና ተፅዕኖ በፕሮግራሞቸው ላይ ያሳረፈውን ጫና ጨምሮ ያስረዳል።

‹‹አሁን ሌሎች ፕሮዳክሽኖች በእኛ ደረጃ ይሥሩ አይደለም። ምክንያቱም የስፖንሰርና የበጀትም እጥረት ሊኖር ይችላል።›› የሚለው ብርሀኔ ‹‹ሐሳብ ግን ከሌለ ባይሠሩ ይሻላል። እናንተም እንደ አዲስ ማለዳ ይሄ የመዝናኛ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያገኝ ማሳሰብ ይገባችኋል። መንግሥት ይህ ዘርፍ የሚያመጣው ተፅዕኖና የሚያመጣው ለውጥ ከፍተኛ እንደመሆኑ ሊደግፈው ይገባል። የአቅም ድጋፍ ካገኘ ሰዉ መፍጠር ይችላል።›› ሲል በማሳሰብ አደራም ሰጥቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com