ከአቧራ ማስነሳት ከፍ፥ ከአውሎ ነፋስ ዝቅ ያለው የኢዜማ ጥናት ይፋ መደረግ

Views: 114

ከሳምንት በፊት ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሓዊ ዕደላ ጋር በተያያዘ የጥናት ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መስተጓጎሉ ይታወሳል።

ኢዜማ በወቅቱ መግለጫ መስጠት ባይችልም በቀጣዩ ሰኞ አስፈላጊ የተባሉ መስፈርቶችን አሟልቶና ፈቃድ አግኝቶ መግለጫውን እንደሚሰጥ አስታውቆ፥ መግለጫችን የተስተጓጎለበት እውነተኛ ሰበብ የጥናታቸውን ይዘት ፍራቻ መሆኑን እንረዳለን ሲሉ የፓርቲው ቃል አቀባይ ናትናኤል ፈለቀ ለመገናኛ ብዙኀን በዕለቱ ከፍ ባለ በራስ መተማመን ስሜት አስታውቀዋል። ብዙዎች ዜናውን የተቀበሉት በግርምት ሲሆን አንዳንዶች ባለማመን የቀድሞው የሕወሓት መር ኢሕአዴግ መንግሥት በየት በኩል ተመልሶ መጣ ሲሉ በድርጊቱ ተሳልቀዋል።

በነጋታው ከንቲባ አዳነች አበቤ ካቢኔያቸውን ሰብስበው የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደራቸው የ20/80 እና የ40/60 ቤት ያልደረሳቸውን ነገር ግን ፍላጎት እና አቅም ያላቸው ተመዝጋቢዎች በማኅበር ተደራጅተው የጋራ ቤት በራሳቸው ለመገንባት እንዲችሉ ከሊዝ ነፃ እና ሌሎች ግብዓቶችን ለማቅረብ አስተዳደራቸው መወሰኑን አስታውቀዋል። በርግጥ ሐሳቡ አዲስ ባይሆንም ብዙዎች ለቀጣዩ የኢዜማ መግለጫ የቅድሚያ የመልስ ምት ለመስጠትና የፓርቲውን መግለጫ ዋጋ ለማሳጣት ያለመ ነው ሲሉ የመንግሥት አካሄድን ኮንነዋል።

ሰኞ ቀን የተቆረጠለት የኢዜማ መግለጫ እንደቀዳሚው አርብ መንግሥት እንዳያካሂድ ለማስተጓጎል የሞከረ ቢሆንም፤ እድሜ ለቴክኖሎጂ በፌስቡክ ማኅበራዊ መድረክ በቀጥታ ለዓለም ደርሷል። በጠራራ ፀሐይ በተደራጀ መልኩ በከተማው የተፈጸመው መሬት ወረራ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላት ጭምር ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን በዋና ተዋናይነት የተሳተፉበት ነው የሚለው ጥናቱ፥ ናሙና ከተወሰደባቸው አምስት ክፍለ ከተሞች ብቻ 213 ሺሕ ዘጠን መቶ ካሬ ሜትር ያህል ስፋት ያለው ቦታ መወረራቸውን አረጋግጧል።

በተጨማሪም ጥናቱ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተገናኘ በግልጽ የታየው የመንግሥት አካላት ሕገ ወጥ ተግባርን ሲገልጽ ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጽሕፈት ቤት የተመዘገቡ ሁሉም ሠራተኞች ብዙ ሺሕ ቤቶች ታድሏቸዋል፤ መታወቂያም ያለምንም ቢሮክራሲ ታትሞ እንደተሰጣቸው ጥናቱ ጨምሮ አረጋግጧል። በሥመ አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ እንዲሁም በእግር ኳስ ደጋፊነት ለተሰባሰቡ ማኅበራት የንግድ ቤቶቹ መከፋፈላቸውን በተጨባጭ ማስረጃዎች ማረጋገጡን ገልጿል።

የቀድሞውን የከተማዋን ከንቲባ ታከለ ኡማን አስተዳደር እርቃኑን ባስቀረው መግለጫ ላይ ከተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እስከ ተርታው ሰው ድረስ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰምተዋል፤ ሙግቶችም ተካሂደዋል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ታከለ ኡማም በፌስቡክ ገፃቸው “በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ ይቻል ይሆናል እንጂ አገር አይገነባም – የፖለቲካ ትርፍ የለውም!!” በሚል ጽሁፋቸው በቀጥታና አንድ በአንድ ውንጀላዎችን በማንሳት ሳይሆን በደምሳሳው አስተባብለዋል።

ከንቲባው በሰጡት ምላሽ ላይም ይሁን ከዚህ ቀደም የሠሯቸው በመጥቀስ ከጎንዎት ነን በማለት ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ያሉትን ያክል፤ በማስረጃ የተደገፉትን የኢዜማ የጥናት ውጤቶች በተጨባጭ ማስተባበል ሳይችሉ የብሔር ካርታ በመሳብ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት መሞከራቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም ሲሉ በተቃራኒ የቆሙት ቅሬታቸውንም ንዴታቸውንም በአንድ ላይ ገልጸዋል።

ከታዋቂ ሰዎች “እስክንድር ባመነበትና በመሰለው ግልጽ አቅዋም ተመርኩዞ፣ ሽንጡን ገትሮ እምነቱን ማሰማቱ አንድ ነገር ነው፤ መስፍን ወልደማሪያም ስለቤት ማፍረስና ሰዎችን ማፈናቀል የጮኸው ለብቻው አንድ ነገር ነው፤ ኢዜማ ዝርዝር መረጃ ይዞ የገለጠውና ከስሜት ያወጣን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው!” በማለት ድምጻቸውን ያሰሙት ፕሮፌሰር መስፍን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምድሩን ሁሉ ትቶ በሰማይ ላይ ትላልቅ ፎቆች እያሠራልን ነው ሲሉም በስላቅ ሽንቁጠዋል።

በሌላ በኩል ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ይገናኝ አይገናኝ ባይታወቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “. . . ዴሞክራሲን ጽኑ መሰረት ላይ ለመትከል ብቻ ሳይሆን የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የወንድማማችነት እሴት እጅግ ወሳኝ ነው።” ሲሉ በኢዜማ መግለጫ ማግሥት በፎስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

የሆነው ሆኖ የኢዜማ ጥናት ይፋ መደረግ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ መስተጋብር የባሰ ያሳሳዋል ሲሉ ስጋታቸውን የገለለጹ በርካቶች ናቸው። አንዳንዶች ታከለ የሠሯቸው ብዙ መልካም ተግባራት ቢኖሩም ለጥፋታቸው ግን እሳቸውም ሆኑ አስተዳደራቸው ከተጠያቂነት ማምለጥ የለባቸውም፤ አሁኑኑ ከያዙት የፌደራል ሥልጣን መባረር እንዲሁም በወንጀል መጠየቅ አለባቸው ሲሉ ቁርጥ ያለ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ምን ይፈጠር ይሆን የሚለውን ጊዜ ሚዛን እንደሚመልሰው ግን ብዙዎች ሳይነጋገሩ የተግባቡበት ይመስላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com