የራስን ዕድል በራስ መወሰን – በወላይታና በትግራይ!

Views: 189

የፖለቲካ አለመረጋጋት ሰላም የነሳት ኢትዮጵያ የጥያቄዎቿን መልስ አንድም በፈፌዴራል መንግሥቱ ላይ ያኖረች ይመስላል። ይልቁንም የራስን ዕድል በራስ መወሰንን በሚመለከት የሚነሱ ጥያቄዎች በተለይ በደቡብ ወላይታ እና በትግራይ ክልል አጀንዳ ሆነው ከቀረቡ ከራርመዋል። ግዛቸው አበበም የእነዚህ ኹለት ክልል ጥያቄዎች በተመሳሳይ መንገድ እየተስተናገደ እንዳልሆነ አንስተዋል። አልፎም በሚወሰድ እርምጃ አንዱ እያጠፋ ሲታለፍ፣ ሌላው ‹ወርቅ ላበደረ…› ሆኖበታል ሲሉ ያብራራሉ።

የፌዴራሉን መንግሥት ቅር ቢያሰኙም በትግራይና በወላይታ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። በትግራይ ምርጫ ማካሄድ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መገለጫ ነው በሚል ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ሸብ-ረብ መባል ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። በወላይታ ደግሞ ራስን በራስ ማስተዳደር የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አንዱ አካል ነው በሚል ክልል የመሆን ጥያቄ ቀርቦ ተጓዳኝ እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ከዓመት በላይ ዘልቋል።

የፌዴራሉ መንግሥት የትግራዩን ምርጫ ‹ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም› ብሎ ቢቃወመውም፣ የወላይታውን የክልልነት ጥያቄ ግን ግልጽ ባላደረገው ምክንያት መልስ እንዳያገኝ አድርጓል። ሕገ-መንግሥቱን ይጥሳል ያለውን የትግራዩን ምርጫ በሚመለከት ከዛቻ ያለፈ እርምጃ ሳይወስድ፣ በሕገ-መንግሥታዊነቱ ላይ ምንም ጥርጥር የሌለውን የወላይታዎችን ጥያቄ ግን በጉልበት ለማስቆም ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው።

በ1987 በወጣው ሕገ-መንግሥት መሰረት የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሲባል በአንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 መሰረት በማንኛውም ጊዜ ከነበሩበት ክልል ተለይቶ የራስን ክልል መመስርትን የሚያካትት ነው። በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት ደግሞ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የራስን አገር የመመስረት መብትን ማግኘትን የሚያጠቃልል ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች መንደሮች ወደ ምክትል ወረዳ፣ ምክትል ወረዳዎች ወደ ወረዳ፣ ወረዳዎች ወደ አውራጃ/ዞን፣ አውራጃዎች/ዞኖች ወደ ክልል ማደጋቸው በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ሲሠራበት የቆየና ተቀባይነት ያለው ነው። ጥያቄ ከሚያቀርበው ሕዝብ አልፎም አገርን በጥሩ መንገድ ለማስተዳደር የሚበጅ አሰራር ቢሆንም፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ መብት ተብሎ የተቀመጠው ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ራስን አገር መመስረት ይቻላል የሚለው ሐሳብ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ውስጥ ብቻ የሚገኝ ነው። እንጂ በየትኛውም አገር ሕገ-መንግሥት ውስጥ የማይገኝ እንደሆነ ይነገራል።

በአንድ ወቅት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት የትኛውም አገር ደፍሮ ያልሰጠውን ‘መብት’ የሰጠ ነው። ከኢትዮጵያ የመገንጠልና የራስን አገር የመመስረት መብት አላቸው የሚባሉት ብሔሮችና ብሔረሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቦች የሚባሉትም ጭምር ናቸው መባሉ፣ አገርን ያህል ነገር ማፍረስ ተቧድነው ለተነሱ ሰዎችም በቀላሉ የሚፈቀድ መብት ይመስላል። አገር እንዳይፈርስ ጦር እስከመማዘዝ የደረሰ ጥረት በሚደረግበት ዓለም ውስጥ አገርን በቀላሉ የማፍረስ መብትን የሰጠ ብቸኛው ሕገ-መንግሥት።

በ1985 የኤርትራውን ሪፈረንደም ለመከታተል በአገሪቱ በርካታ የዓለም ጋዜጠኞች ተገኝተው ነበረ። የሪፈረንደሙ ውጤት እንደታወቀ ጋዜጠኞቹ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ቃለ ምልልስ የማድረግ ዕድል አገኙ። ከጋዜጠኞቹም አንዱ ‹‹…. አዲሲቱ አገር ኤርትራ ተቃዋሚ ቡድኖች እንዲንቀሳቀሱ ትፈቅዳለች ወይ? በኢትዮጵያ እንደሚታየው በዘር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ቡድኖች እንዲኖሩስ ትፈቅዳላችሁ ወይ?›› ብሎ ጠየቃቸው።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ የጋዜጠኛውን ጥያቄ የመለሱት በጓዶቻቸው በእነ አቶ መለስ ድብቅ አስተሳሰብ ላይ እየተረማመዱና እያሾፉ ነበረ። ‘…በዘርና በሐይማኖት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የምትፈቅደው ልታፈርሰው የምትፈልገው አገርና ልታጫርሰው የምትሻው ሕዝብ ሲኖርህ ነው…’ የሚል መልስ ሰጡ።

በእርግጥ በዚህ ዓለም ላይ በማሕጸኗ በተገኙ ነገር ግን አምርረው በሚጠሏትና ሕልውናዋን በማይሹ ቡድኖች እጅ ውስጥ ገብታ አበሳዋን የመብላት ዕጣ የገጠማት የዓለማችን ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም። ኢትዮጵያ አንድነቷን ለመናድ፣ ሕዝቦቿን ለማናቆር፣ ታሪኳን ለማንቋሸሽ፣ ታላላቅና ታሪክ ሠሪ ገዥዎቿንና ጀግኖቿን ለማጥላላት የሚሯሯጡ ቡድኖች የሚራኮቱባት ከሆነች ሰነባብታለች። በአገራት ታሪክ እነዚህን መሰል ቡድኖች የተከሰቱት አገራቱ በቅኝ ገዥዎች እጅ ውስጥ በገቡበት ወይም ቅኝ ገዥዎች ከመጋረጃ ጀርባ ተደብቀው ለመግዛት ሲሉ ሥልጣን ላይ ያወጧቸው አገር በቀል ባንዳ አሻንጉሊቶች አገር እየመሩ ነው በሚባልበት ጊዜ ነው።

ሰሞነ ለውጥ የጥፋቱ መጀመሪያ
በ2010 በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ ሲባል በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው ሕዝብ አገሪቱ ሊያፈርሷትና ሊያወድሟት በሚፈልጉ በጠላቶቿ የምትገዛበት ጊዜ አከተመ የሚል ትልቅ ተስፋን ሰንቆ ነበር። የለውጡ መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለ27 ዓመታት ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ቃልና ወኔ ደግ ደጉን ሲናገሩ መሰማታቸው በጊዜው የነበረውን የመከፋፈል ስጋት መቅረፍ በመቻላቸውም ጭምር ነው።

ሠኔ 16/2010 በአዲሰ አበባ ተጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ በትልልቅና ትንንሽ ከተሞች የለውጡን መሪዎች ምስልና የድጋፍ መፈክሮችን አንግቦ በወጣ ሕዝብ የተሞሉ ሰልፎች የታዩት ለዚህ ነበረ። በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኘው ‘ኢትዮጵያ ወይም ሞት!’ ባይ ሕዝብ በዚህ ዓይነት የፌሽታ ዓለም ውስጥ ይግባ እንጅ በኢትዮጵያዊነታቸው የማያኑና ኢትዮጵያን መፈራረስ እንደሚገባት አገር አድርገው የሚያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ ‹ኢትዮጵያዊ ነን፣ ኢትዮጵያን እንወዳታለን› ከሚሉትም ጥቂት የማይባሉት ግለሰቦችና ቡድኖችም በሐዘንና በብስጭት ውስጥ ገብተው ሐሜት ከመንዛት ጀምሮ ሴራ እስከ መጎንጎን በደረሰ የክፋት ሥራ ተጠምደው ነበር።

ኢትዮጵያን እንወዳለን እያሉ የለውጡን አመራሮች ገና ከጅምሩ የሚቃወሙት ግለሰቦችና ቡድኖች ትልቅ ቁጭት ‹ከኢሕአዴግ ውስጥ የወጡ ሰዎች ሥልጣኑን በአቋራጭ መልሰው ወሰዱት፣ ለእኛ የሰገደውን ሕዝብ የእነሱ ተከታይ አደረጉብን።› የሚል ዓይነት ነበር። በቅናት ከተንገበገቡት ‹ኢትዮጵያዊ ነን› ባዮች ውስጥ በአገር ቤት ይሁን በስደት የሚኖሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና አክቲቪስቶች ይገኙበታል። እና አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት፣ ‘የጠላቴ ጠላትን…’ ሆነ ‘እኔ ከሞትኩን…’ እየተረቱ ኢትዮጵያን የማውደም የረዥም ጊዜ ምኞት ካላቸው ጠላቶች ጎን ተሰለፉ።
ለውጡ ወደ ነውጥ እንዲቀየር ፈጥነው ተንኮል መሥራት ጀመሩ። ከዛም አሁን የእነዚህና የእነዚያ ወገኖች ግልጽና ስውር ደባዎች ስለበዙ ብቻ ሳይሆን የአመራሩ ዝርክርክነትና ደካማነት ከልክ ያለፈ በመሆኑ የአገሪቱ ሕልውናና የሚሊዮኖች የመኖር መብት አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ ጥሎታል።

ትግራይና ወላይታ – በፌዴራል መንግሥት ዐይን?
በደቡብ ኢትዮጵያ ብዙ አካባቢዎች ክልል የመሆን ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው። ጥያቄዎቹ የሚቀርቡት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 47 በማጣቀስ ነው። ጥያቄዎቹን ማፈንና በኃይል ደፍጥጦ ማለፍ በምንም ዓይነት መንገድ ተገቢ ያልሆነና ተቀባቀይነትም የሌለው አምባገነናዊ አካሄድ ነው።

በሌላ በኩል ጥያቄዎቹ ሊነሱ የሚገባበት ጊዜ ወይም ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠት የሚገባበት ጊዜ አሁን አይደለም የሚባል ከሆነ አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶች ተዘርዝረው መቀመጥና በግልጽም ተነግረው የጊዜ ቀጠሮ ተይዞላቸው፣ የሚተገበሩበት ዕቅድም ይፋ ሆኖ ከጥያቄ አቅራቢዎቹ ሕዝቦች ጋር መግባባት ተፈጥሮ እንዲዘገይ ማድረግ ተገቢ ነው። የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 47 ስህተት አለበት ወይም አዋጭ አይደለም የሚባል ከሆነም ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ውይይትና ውሳኔ አንቀጹ ይሻሻል ወይስ ባለበት ይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ አካሄድን ተከትሎ እልባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው።

ካልሆነ ‹ሕገ-መንግሥቱ አይቀየርም፣ እኔን ደስ ያላለኝ የሕገ-መንግሥት አንቀጽም አይተገበርም።› የሚባል ከሆነ ድንቁርና የሞላበት አምባገነናዊ አካሄድ ነውና በጊዜ ሊታረም ይገባዋል። እንዲህ የሚል ዓይነት አቋም የያዘ መስሎ የሚታየው የብልጽግና ቡድን በወላይታ ዞን ጉዳይ ጋር በተያያዘ የያዘው አቋምና እየወሰደው ያለው እርምጃ አሳሳቢ፣ ትዝብት ላይ የሚጥልና የወላይታን ሕዝብ ለተጨማሪ ተቃውሞዎች የሚያስነሳ መሆኑ ለአፍታም ቸል ሊባል አይገባም።

ወታደራዊ እመቃና የጥይት ተኩስ መልስ ሊሆኑ አይችሉም። ሲዳማዎች በ1993 ከተካሄደባቸው የሎቄ ጭፍጨፋ ጀምሮ በዕለት 11/11/2011 እስከተከሰተው በወታደራዊ እርምጃ የማመቅ ሙከራ ብዙ ችግሮች ቢደርሱባቸውም፣ ክልል ከማግኘት ያገዳቸው ኃይል የለም።

በመላ ኢትዮጵያ ከችግር ነጻ የሆነ ቦታ አለ ባይባልም፣ ከላይ እንዳነሳነው በትግራይና በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በወላይታ የሚታየው በፌዴራሉ መንግሥትና በአካባቢዎቹ መስተዳደሮች መካከል የተከሰተው ውጥረት ግን ትኩረትን የሚስብ እየሆነ ነው። በወላይታና በትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በማስታከክ የተነሱ ጥያቄዎች ለፌዴራሉ መንግሥት የራስ ምታት ፈጥረውበታል። አስገራሚውና አሳፋሪው ነገር የፌደራሉ መንግሥት በኹለቱ አካበባቢዎች የተነሳበትን መገዳደር አንዱን በብረት እጅ ሌላውን በቅቤ እጅ ለመቆንጠጥ መሞከሩ ነው።

በ2012 መካሄድ የነበረበት አገራዊ ምርጫ የተራዘመው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሊከተል የሚችልን እልቂትን ለማስወገድ ነው ተብሏል። ይህ ክልከላ በትግራይ ክልል እንዳልሠራና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ሙሉ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ሕወሐት ጉዳዩን የራስን ዕድል በራስ እንደመወሰን አድርጎ እንደቆጠረው በማሳወቅ ብቻ ሳይሆን የታገልኩት ለዚህ ነው በሚል ድምዳሜ የመጣውን ሁሉ እንዳመጣጡ እመልሰዋለሁ የሚል አቋም ይዞ የምርጫ ዝግጅቶችን በአብዛኛው አጠናቅቆ ለድምጽ መስጫ የተቆረጠውን እለት (ጳጉሜ 4/ 2012) እየተጠባበቀ ነው።
የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ተቋቁሟል። የተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ምዝገባ፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ ቅስቀሳና የተወዳዳሪዎች ክርክሮች (በክልሉ በሚገኙ ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎች አማካኝነት) ተካሂደዋል።

በክርክራቸው የሚያነሷቸው ሐሳቦች ቀልብን የሚስቡ ዓይነት ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዶቹ የሚሰነዝሩት ሐሳብ እንደ እውነተኛ
ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለሚያዳምጣቸው አሳሳቢና አስደንጋጭ ናቸው። ልክ እንደ ሕወሐት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዳንዶቹ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ አገር፣ የግዛት አንድነት ወዘተ… ሲባል እንደ አሃዳዊ፣ እንደ ኋላ ቀርና እንደ ጨፍላቂ አባባል ይቆጥሩታል። እነሱ ለአንዲት ትግራይ፣ ለትግራይ ግዛት አንድነት፣ አንድ ለሆነ የትግራይ ሕዝብ፣ ለትግራይ ሉዓላዊነት እንደሚታገሉ ይናገራሉ።

‹አንቀጽ 39 የሕገ-መንግሥቱ መሰረት ነው፣ ሳይሸራረፍ የሕገ-መንግሥቱ አካል ሆኖ መኖር አለበት። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አገር ምልክት ነው› ሲሉ የሚሟገቱት እነዚህ ቡድኖችና ሕወሐት፣ ትግራይን ቢገነጥሉ በሕገ-መንግሥታቸው ይህን አንቀጽ ያካትቱት ይሆን? እነዚህን እና ሌሎች በነጻነት ከሚሰነዘሩ ሐሳቦች ውስጥ አንዳንዶቹን በማንሳት ነጻነቱን ሊነጠቅ ግርግር ከበዛበት ከወላይታዎች ሐሳብ ጋር ማነጻጸር ተገቢ ነው።

የወላይታ ሕዝብ ራሴን በራሴ ለማስተዳደር ክልል የመሆን መብት ማግኘት አለብኝ ብሎ ወስኖ ሕገ-መንግሥቱ የሚጠይቃቸውን ጉዳዮች አሟልቶ ጥያቄውን አቅርቧል። መልስ ግን አላገኘም። በተገቢው ጊዜ መልስ ባለመገኘቱ ወላይታ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። የሕዝባቸውን ጥያቄ ይዘው ገዥውን ቡድን ለመጋፈጥ ቆርጠው የተነሱት በደቡብ ክልል ምክር ቤት የወላይታ ሕዝብ ወኪሎች ምክር ቤቱና የክልሉ መንግሥት የሕዝባችንን ጥያቄ መመለስ ድጋፍ የማይሰጥ ከሆነ በምክር ቤቱ ውስጥ ምን እንሠራለን ብለው ጥለውት ከወጡ ወራት ተቆጥረዋል።
የወላይታ ዞን አመራሮችና የዞኑ ብልጽግና ቡድን ከፍተኛ አመራሮችም ከወላይታ ሕዝብ በላይ የሆነ አለቅነትን አንቀበልም፣ የሕዝቡን ጥያቄ ከማስመለስ የበለጠ ኃላፊነትና ስራም የለብንም ብለው ጽኑ አቋም ይዘዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱን ተከትሎ “የጨረባ ምርጫ በሚያካሂዱ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” ብለው ዝተዋል። ሆኖም በትግራይ ክልል በመካሄድ ላይ ያለውን ሞቅ ያለ የምርጫ እንቅስቃሴ ለማስቆም ያደረጉት አንዳች ነገር የለም።

በተቃራኒው የወላይታ ወጣቶች ክልላችንን በራሳችን እናውጃለን የሚል እንቅስቃሴ ለመጀመር ዳር ዳር በማለታቸው ዞኑ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር እንዲገባ ተደርጓል። ግጭት ተከስቶም ብዙዎች ለእስራት ተዳርገዋል። በጥይት የሞቱና የቆሰሉ ዜጎችም አሉ። የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ቡድኖች በወላይታ የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ተመጣጣኝ ያልሆነ ነው ሲሉ ፈርጀውታል።

የትግራይ መገናኛ ብዙኀን ነጋ ጠባ የብልጽግና ቡድንን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹የአዲስ አበባው አምባገነን›፣ ‹አሃዳዊው ቡድን›፣ ‹ንጉሥ ነኝ ባዩ ገዥ› ወዘተ… በሚሉ ቅጽል ሥሞች እየጠሩ ውግዘት ከማውረዱ ጎን ለጎን የምርጫ ቅስቀሳና ምርጫውን ለማቆም የሚመጣን ማንኛውንም ኃይል ለመፋለም የትግራይ ሕዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው። በወላይታ ደግሞ ‘ወጌታ ኤፍኤም’ የክልልነት ጥያቄን፣ የወላይታ ሕዝብ አስተያየቶችን እንዲሁም በወላይታ ዞን ላይ እየደረሱ ያሉ ተጽዕኖዎችን ወዘተ… የሚመለከቱ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው።

የወላይታው ወጌታ ኤፍ.ኤም. ለተወሰኑ ቀናት በወታደሮች ቁጥጥር ስር ገብቶ ሥራ ለማቆም የተገደደ ሲሆን፣ በትግራይ የሚገኙ ሚዲያዎችን ደግሞ ከሳተላይት በማውረድ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። የመቀሌውን ፋና ኤፍ.ኤም. በሚመለከትም ከጥበቃዎች ውጭ ያሉ ሠራተኞቹ በሙሉ ወደ አዲሰ አበባ መዛወራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመላክ፣ በተዘዋዋሪ መቀሌ ከቀሩ ደሞዝ እንደማያገኙና ከሥራ እንደለቀቁ በመንገር የመዘጋት እርምጃ ተወስዶበታል።

የክልሉ መንግሥት እና የሕወሐት ንብረት የሆኑት የሬዲዮ ጣቢያዎችና ቴሌቪዥን ማሰራጫዎች ግን እንደ ወጌታ ኤፍ.ኤም. ወረራ አልተካሄደባቸውም። የአየር ስርጭታቸውም አልተገታም። እንዲያውም መንግሥት ምርጫ መካሄድ የለበትም ብሎ በመዛት ላይ ቢሆንም ትግራይ የሚገኘው ሰሜን ዕዝ አመራሮች ከትግራይ ጸጥታ ኃይሎች አመራሮች ጋር ተሰብስበው ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ መስማማታቸውን በትግራይ መገናኛ ብዙኀንና በድምጸ ወያነ ቴሌቪዝንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ሲነገር ሰንብቷል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በተለያዩ ጊዜያት እየተሰበሰበ ክልሉ የራሱን ምርጫ እንዲያካሂድና ክልሉ የራሱን የምርጫ ኮሚሸን እንዲያቋቁም ሲወስን፣ የፌዴራሉ መንግሥት ያላየና ያልሰማ መስሎ አልፎታል። የትግራይ ክልል ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ብዙ እርምጃዎችን መውሰዱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ በመጻፍ ‘አቁሙ’ ለማለት ሞክሮ አልተሳካለትም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የምርጫውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለማስቆም ወይም ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች እየመረመረ መሆኑን አሳውቋል። የትግራይ ክልል ደግሞ በየዕለቱ “መረጻ መግለጺ መሰል አርሰ ውሳነ እዩ” (ምርጫ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መገለጫ ነው) የሚለውን አዲስ መዝሙር ነጋ ጠባ በየሚዲያዎቹ እያሰማ በጀመረው ሥራ ቀጥሏል።

የሕዝብ ግፊት የበረታባቸው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪዎችና የዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት አመራሮች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት መሪዎች ግፊቱን ረገብ ለማድረግ ያስችላል ያሉትን ነገር ለማድረግ ተሰብስበው እያሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል። የታሰሩት አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት መሪዎች በከፍተኛ ገንዘብ በተተመነለት ዋስትና ከእስር ወጡ ቢባልም የዞኑ አመራሮች ከሥራ ውጭ ሆነው ፍርድ ቤት ለመቅረብ ወደ ሐዋሳ የመመላለስ ዕጣ እየጠበቃቸው ነው።

የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ለማካሄድ መንቀሳቀስ መጀመሩንና የጠቅላዩን መዛት ተከትሎ የሽምግልና ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ መሄዱ ይታወሳል። ቡድኑ ‹‹መቀሌ ሄጄ ሥራዬን አሳክቼ ተመለስኩ›› ቢልም ከወደ መቀሌ ቤተ-መንግሥት ይፋ የወጡ ወሬዎች ‹‹ማሸማገል የሚገባችሁ ሕወሐትንና ብልጽግናን ወይም ዐብይንና ደብረጽዮንን ብቻ አይደለም፣ ሁሉንም ቅር ያላቸውን ወገኖች ሲሸማገሉ ነው ለአገር የሚበጀው …›› ብለው መክረው እንደመለሷቸው የሚገልጹ ናቸው።

እንዲያውም የትግራይ ምክትል ፕሬዝደንት ‹‹አገራዊ መድረክ ማዘጋጀት እንጂ ከሕወሐት ጋር በድብቅ የሚደረግ ውይይትን አንቀበልም›› ማለታቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ተናግሯል። ነገር ግን ይህ ከአዲሰ አበባ ተነስቶ መቀሌ ለመድረስ የተጣደፈ የሽማግሌዎች ቡድን ወደ መቀሌ ለመሄድ የጓጓውን ያህል የትም ለመሄድ ሲነሳሳ አልታየም። ለምን? ሌላው ቢቀር ከፍተኛ ችግር ውስጥ

ወደገባው ወደ ወላይታ ዞን ለመሄድ ትንሽም ፍላጎት ያላሳየው ለምን ይሆን?
የወላይታ ዞኑ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ሶልያና አዲሎ ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የወላይታ ሕዝብ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንዳለ፣ በዞኑ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቆሙንና ዞኑ መንግሥት አለ ሊባል በማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አሳውቀዋል። አክለውም የደቡብ ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በወላይታ ዞን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ቀጭን እገዳ በመጣሉ የዞኑ ሥራ መሽመድመዱንና ሕዝቡ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ መግባቱን አሳውቀዋል።

በዞኑ ላይ ያረበበውን ጥቁር ደመና ለመግፈፍ የወላይታ አገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት መሪዎችን ያካተተ ቡድን ነሐሴ 13 እና 14 2012 የክልሉን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ወደ ሐዋሳ ከተማ አቅንቶ ነበር። ቡድኑ እህ ብሎ የሚሰማው ቀርቶ ሊያየው የሚፈልግ አንድም የክልል ባለሥልጣን አጥቶ ተንከራትቶ ተመልሷል።

የዞኑን አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቢን ጨምሮ የዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች መታሰራቸውና ከሥራ ውጭ መደረጋቸው አልበቃ ብሎ፣ የክልልነት ጥያቄው ሕዝብ ሳይሆን ሥልጣን የጠማቸው የጥቂት ካድሬዎችና ፖለቲከኞች ጥያቄ ነው የሚል ውንጀላንና ማሸማቀቂያን ለመጋፈጥ ተገድደዋል። ለአንዳንዱ ታሳሪ መቶ ሺህ ብር በጠቅላላው ወደ ኹለት ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ ሲጠየቅ፣ ከነፋስ ፈጥኖ የተጠየቀውን ብር ቆጥሮ ያስረከበላቸው ሕዝብ ግን በግንባር ተሰልፈው መከራን ለመቀበል ቆርጠው የተነሱ መሪዎቹን ሊተዋቸው አልፈቀደም።

በሐዋሳ የተሞከረው የሽምግልና ሙከራ በክልሉ መንግሥት ችላ መባሉን ተከትሎ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። በዚህ ስብሰባም ሕዝቡ ከመሪዎቹ ጎን መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በሚቀርቡ ጥያቄዎችንና የአቋም መግለጫ አዘጋጅተዋል።

በዚህም ያካተቷቸው ሐሳቦች ሲጨመቁ ‹የወላይታ ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ነው፣ የክልልነት ጥያቄ ማቅረብ ወንጀል ከሆነ ሁሉም የወላይታ ሕዝብ ወንጀለኛ ነው። በወላይታ ዞን ለተካሄዱት ግድያዎች ተጠያቂና ኃላፊነት የሚወስድ አካል ይኑር። የወላይታ አመራሮችን ሥልጣን የጠማቸውና የክልል ባለሥልጣን ለመሆን ሲሉ የሕዝብ ያልሆነን የክልልነት ጥያቄ የሕዝብ አስመስለው አራምደዋል እያሉ ሥም ያጠፉ በመገናኛ ብዙኀን ይቅርታ ይጠይቁ›› ወዘተ…. የሚል አንድምታ ያለው ነው።

በወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ስለቀረበ ብቻ የመከራ ዶፍ እየወረደ ነው። በትግራይ ሕወሐት ምርጫ ማካሄድ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አንዱ ክፍል ነውና የፌደራል መንግሥት አያገባውም ብሎ ወደ ምርጫ ሥራዎች ገብቶ ብዙ ሲራመድ ከልካይ አልሄደበትም።

ሕወሐት ተደመርኩ ብሎ አያውቅም። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የብልጽግና መንገድም የውድመትና የመደህየት ጉዞ ነው ብሎ በማጣጣል በራሱ መንገድ ቀጥሏል። በአንጻሩ የወላይታ ሕዝብ ተደመር ሲባል ተደመርኩ ብሎ፣ ብልጽግና ሲባል እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ተቀብሎ ነው የክልልነት ጥያቄ ያነሳው። እናም ምላሹ ‘ወርቅ ላበደረ ተጠር’ ሆነበት።

በትግራይ ‘ሳልሳይ ወያነ ትግራይ’ የሚባለው በትግራይ ምርጫ ለመፎካከር የተሰለፈ ቡድን ትግራይ ክልል በመሆን መገደብ የለባትም፣ የኢራቅ ኩርዶችን የመሰለ ‘ሉዓላዊ አገር አከል ፌዴሬሽን’ መሆን ይገባታል ብሎ የሚከራከርና በምርጫው ካሸነፈ ይህን ለማሳካት ቃል እየገባ ነው። ለፌዴራል መንግሥትም በርካታ ወሳኝ ሥልጣኖችን የሚያሸክሙ አንቀጽ 51ን የመሳሰሉ የሕገ-መንግሥቱ ከፍሎ እንዲሻሻሉ ማድረግ ግንባር ቀደም ሥራው እንደሆነ አሳውቆ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ወላይታዎች የኢትዮጵያ አስራ አንደኛ ክልል ለመሆን ነው የሚጣደፉት። ይሁን እንጅ የደቡብ ክልል መንግሥትና የፌዴራሉ መንግሥት ጥያቄአቸውን አገርን የሚያናጋ፣ የሕዝቦችን አንድነት የሚጎዳ፣ የምታምረውን ትንሽ ኢትዮጵያ (ደቡብ ክልልን) የሚያፈርስ ቅብጠት አድርገው እያዩባቸው ነው። ከወደ ትግራይ ደግሞ ወደ ምርጫ የገባው ሌላ ድርጅት ‘ውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት)’ (የትግራይ ነጻነት ድርጅት) ሕዝብ ከመረጠው ሳይውል ሳያድር የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 4 የሚሰጠውን መብት ተጠቅሞ በሕዝብ ውሳኔ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ተናግሯል።

ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየቷ ጉዳት እንጅ ጥቅም አላተረፈላትም ይላል። ትግራይን በሁለገብ መንገድ ማሳደግ የሚቻለውም ነጻና ሉዐላዊ አገር በማድረግ፣ ትግራይ በራሷ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብት ራሷ ብቻ ተጠቃሚ እንድትሆን በማስቻል፣ ከአዲስ አበባው አሃዳዊና አምባገነን አገዛዝ በማላቀቅ ብቻ ነው እያለ በመቀስቀስ ላይ ነው። ራሱንም ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመለየት ብቻ የተመሰረተና ይህ ሐሳቡ ሲሳካ የሚፈርስ ወይም ወደ ኹለትና ሦስት ፓርቲዎች ሊበታተን የሚችል ቡድን መሆኑን ይገልጻል።

ው.ና.ት. በተሳሳተ መንገድ ብሔረሰቦችን ጨፍልቃ የተገነባችው ኢትዮጵያ ከመፍረስ ውጭ ዕድል የላትም ከማለት አልፎ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ስለሚኖረው ዝምድና ማሰብን ጊዜን እንደ ማባከን አድርጎ የሚቆጥር ቡድን ነው። ትግራይ ሕያውና ሃብታም ሆና እንድትኖር ኢትዮጵያ መጥፋት አለባት እስከ ማለት የደረሰ ድርጅት ነው። አጼያዊ ኤምፓየሮች ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍተዋል የሚለው ው.ና.ት. ኢትዮጵያም ከመጥፋት ውጭ አማራጭ ስለሌላት አብሮ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለጉርብትናም ዕድል የላትም ባይ ነው።

አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አካባቢያዊና ለሳሆ (ለኢሮብ) ሕዝብ ወኪል ለመሆን የተነሳ ፓርቲ ይሁን እንጅ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ኤርትራን ጨምሮ ከሁሉም ጎረቤት አገራት ጋር በሰላም አብሮ መኖር ለትግራይ ሕዝብ ጠቃሚ ነው የሚል ግልጽ አቋም ያለው ብቸኛው ተወዳዳሪ ቡድን ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com