አራት ድርጅቶች ፓልም የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ እንዲያመረቱ ፈቃድ ተሰጣቸው

Views: 301

ፓልም የምግብ ዘይት ማምረት የሚያስችል ማሽነሪ እና አቅም አላቸው ተብለው የተለዩ አራት የአገር ውስጥ ድርጅቶች ፓልም የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ ፈቃድ ተሰጣቸው።
ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም ፓልም የምግብ ዘይት አምጥተው ሲያከፋፍሉ የነበሩ ሲሆን ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶቹም በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኙት ፌቬላ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እና ደብሊው ኤ የዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ደብረ ዘይት የሚገኘው አል ኢምፔክስ ዘይት ማምረቻ የተባሉት አራት ፋብሪካዎች ዘይቱን ለማምረት ፍቃድ እንደተሰጣቸወም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር የሆኑት አድማሱ ይፍሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ድርጅቶቹ የተመረጡት የፓልም ዘይት ለማምረት ያላቸው ብቃት ማሽነሪዎች አላቸው ወይ የሚሉትን መስፈርቶች በተመለከተ ድርጅቶች ተለይተው ፈቃድ እንደተሰጣቸው አድማሱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ድርጅቶችን ለመመልመል የትኞቹ ድርጅቶች የፓልም ዘይት ድፍድፉን ብቻ ከውጭ አገር በማስገባት አገር ውስጥ ማምረት የሚችሉት እነማናቸው ብሎ በመለየት እና መንግስት የፓልም ዘይትን እናስመጣት የነበረውን ዶላር ለበለሃብቶች በመስጠት እና ድፍድፉን እንዲያስመጡ በማድረግ ለማህበረሰቡ ዘይቱ እንዲታደል እና እንዲከፋፈል ውል ፈጽመናል ሲሉም አድማሱ አስረድተዋል።
በየወሩ መንግስት የሚፈልገው የፓልም ዘይት መጠን ወደ 73 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደ አገር የሚያስፈልግ በመሆኑ ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ እንዲያመርቱ ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለመሸፈን ከውጭ ማስገባቱንም እንደማይቆም አድማሱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ በከፊል እንዲያመርቱ የተፈቀደላቸው ምክንያት ሲያስረዱም የዶላር እጥረት መኖሩ ብቻ ሳይሆን ድርጅቶቹ የማምረት አቅማቸው ሙሉ በሙሉ የአገሪቱን ፍላጎት ለማማላት የማምረት አቅም ላይ ገና አለመድረሱ ነው ያሉት አድማሱ ፋብሪካዎቹ ግን በሙሉ አቅማቸው ሲሰሩ ከውጭ የሚመጣን ዘይት እናስቆማለን ሲሉ ተናግረዋል።

አድማሱ እንደሚያስረዱት ከሆነም ድርጅቶቹ አሁን የተሰጣቸው ፈቃድ የሙከራ ጊዜ ሲሆን ስራቸውንም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ስራቸውን እንዲጀምሩ ውል ፈጽመናል ብለዋል። በዚህም መሰረት ፈቃድ የተሰጣቸው ፋብሪካዎች ስራ ሲጀምሩ በዓመት 32 ሚሊዮን ሊትር የፓልም ዘይት እንደሚያመርቱ ይጠበቃል።

ዘይቱን ለግብዓትነት የሚጠቀሙበትን የዘይት ድፍድፍ ከውጪ ለማስመጣት ከብሄራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሬ ጥያቄ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ አግኝተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ዘይቱን በአገር ውስጥ በሚያመርቱበት ወቅት በእኛ በኩል የዋጋ ቁጥጥር እናደርጋለን ነው ያሉት።
ፋብሪካዎቹ ለማምረት አቅም እንዳላቸው አረጋግጠናም ብለዋል አድማሱ፡፡

ፓልም የምግብ ዘይት ለማምረት እና ወደ ዘርፉ መሰማራት የሚችል ማንኛውም የአገር ወስጥ ባለሃብት በዘርፉ የመሰማራት አቅም ካለው እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያስቀመጣው እንዲሁም አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን መስፈርት ካሟሉ ጨረታ መወዳደር እንደማያስፈልግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት ድጎማ በማድረግ ከውጪ እያስገባ ለኅብረተሰቡ ሲያሰራጭ የነበረው ፓልም የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ መሻሻሉና ፓልም የምግብ ዘይት መንግሥት የዋጋ፣ የአቅርቦት እና የስርጭት ቁጥጥር እያደረገባቸው ከሚገኙ መሠረታዊ ሸቀጦች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሆኖም ዘይቱ በውስጡ ካለው የስብ መጠን እና ከአስመጪዎች መረጣ ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ሲነሱ እንደነበርም የሚታወስ ሲሆን ይህንን ማሻሻሉን መግለጹም የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com