ዝምታ ምላሽ አይሆንም!

Views: 145

ኹለት ዓመት ተኩልን እንደ ቀልድ ፉት ያለው የለውጡ መንግስት አዲሱ ኃይል ከመባል ይልቅ ወደ ለውጡ ኃይል መባል ስያሜ ለመለወጥ አፍታ አልገጀበትም። ይኸው ኃይል ታዲያ ወደ መንበር በመጣበት በመጀመሪ ቀናት ላይ በርካታ ቃል የገባቸውን እና ሊያከናውናቸው እነሆ በደጅ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በይፋ ለሕዝብ ሲያሳውቅ በርካቶችንም ልብ በደስታ ጸሐይ ያሞቀ እና ለድጋፍም ያሰለፈ ጉዳይ ነበር።

ይኸው የለውጡ ኃይል ከዚህ ቀደም ተሰሩ ተባሉ ብልሹ አሰራሮችን አንድ ጊዜ በቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም ሲያሰራባቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በተለያዩ መድረኮች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥባቸው ሕዝብም ያለፈውን እየረገመ የወደፊቱን ለመያዝ ሲንደርደር እነሆ ዘመናት ተደራርበው 2012 ዓመትን ልንሰናበተው በደጅ ላይ እንገኛለን። ታዲያ ይህ አሳዳጅ እና ተሳዳጅ አይኖርም የተባለ ሕዝብ፣ ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድን እንፈጥራለን የተባለ ትውልድ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ኢ ፍትሀዊነት በዚህ መንግስት ውስጥ ግብኣተ መሬቱ ተፈጽሟል ሲባል ነበረው የዋሕ ሕዝብ አሁንም ለቅርብ ጉዳዮች ማብራሪያ ሽቶ በማንጋጠጥ ላይ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲያልፍም አይነካንም ከዚህ በኋላ በሚል የተሰጠባቸው እነዛ በርካታ መድረኮች ዛሬ ላይ ተመልሰን ልንገመግማቸው ብንደፍር የተሰራው ጉዳይ ምን ያህል እንደሆነ ራሳችን በራሳችን ልንገመግም የሚቻለን ይመስለኛል። ከሰኔ 23/2012 የሀጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ ለጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት እና የረጅም ዘመን የልፋት ውጤት የሆኑ ንብረቶች ሲወድሙ የዝምታው ጥልቀት ትዕግስትን በሚፈትን ደረጃ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይም ምላሽ ለመስጠት ችሎ ነበር። በእርግጥ ከተነሳው ግርግር ጋር ዕጃቸው አለበት የተባሉ አይነኬ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የመንግስትነት ቁመናውን ለማሳየት የሞከረበትን እርምጃ ሳይደነቅ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም።

ያለፈው አልፎ እንዲሁም ተድበስብሶ አልፎ አሁንም ደግሞ ቅርቡን እንኳን ብንወስድ በኤትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከኹለት ቀናት የመግለቻ የመስጠት መብቱ ከተነፈገ በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለቻ እና ለስድስት ሳምንታት ምርመራ አካሒጄበታለሁ ያለውን የአዲስ አበባ ጉዳይ በተመለከተ መንግስት ዝምታ ፍጹም ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን አዲስ ማለዳ በግልጽ ትረዳለች።

ፓርቲ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲነቱ አንጻር የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ውስጥ ሲደረግ ነበር ያላቸውን የሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን እና ኢ ፍትሀዊ የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ክፍፍል በሚመለከት በምስል እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ መረጃዎችን በማቅረብ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች በፌደራል መንግስቱ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ቅሬታን እንደፈጠረ በተለያ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የሚስተጋባ ጉዳይ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል።

ከዚህም በመነሳት ታዲያ ቀድሞው የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ነበሩት ኢንጅነር ታከለ ኡማ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የተደረገው ሁሉ መሰረተ ቢስ እደሆነ እና በልማት ሰበብ የተነሱትን አርሶ አደሮች ፍላጎት ማሟላት ቢያንስ ነው እጂ የሚበዛ እና ሕገ ወጥ ጉዳይ እንዳልሆነ አስቀምጠዋል።

እንደ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ተሰናባቹ እና የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ሳይሆኑ የሚመለከተው የመንግስት አካል ወደ ሕዝብ በመቅረብ ተፈጠረ ስለተባለው ጉዳይ ጥልቅ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባዋል። ከዕለት ጉርሱ ነጥቆ ነገ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ጥሪት አስተላልፋለሁ ያለው ተስፈኛ ነዋሪ የቆጠብከው መኖሪያ ቤት ውሃ በልቶታል እና ከዚህ በኋላ መኖሪያ ቤትህን ለማግኘት ባትደክም ይሻልሃል አይነት አንደምታ ያለው ጉዳይ ከተፎካካሪ ፓርቲ ሲደርሰው መንግስት ተገቢ ነው ያለው ምላሽ ግን ለመስጠት ደክሞ ነበር። በዚህ ጉዳይ መንግስት አስቸኳይ ምላሽ እና ተደረገ የተባለውም ጉዳይ በእርግጥም ተደርጎ ከሆነ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የተከፋውን እና ፍትህ የተነጠቀውን ሕዝብ መካስ እንዳለበት አዲስ ማለዳ በሚገባ ታምናለች። ይህ ካልሆነ ግን አሁንም በሕዝብ እና በመንግስት መካከል የሚኖረው አለመተማመን ሰፊ ልዩነት እንደሚያሳይ እና አንድ ጊዜ ያጡትን አመኔታ መልሶ ለማግኘትም ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል መንግስት ሊገነዘበው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ይህ ብቻ ሳይሆን በቅር ከአዲስ አበባ መስተዳደር ዘንድ የተሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤትን በሚመለከት ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ባለ እድለኛ ያልሆኑ ሰዎች በማኅበር ተደራጅተው መገንባት የሚችሉበት አካሔድ ተግባራዊ እንደሚደረግ መነገሩ ደግሞ ከዚኤማ ወገን ለወጣው መግለጫ እና ጥናታዊ ግኝት ማስረገጫ የሚመስልበት ጉዳይ ሰፊ በመሆኑ መንግስት ይህንንም በሚመለከት ተገቢውን ማብራሪያ መስጠት በይደር የሚያቆየው ጉዳይ እንዳልሆነ ሊገነዘብ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

አንዱ በስፋት ተጠቅሟል፤ ሌላው ደግሞ በሚገባ ተበድሏል በሚል በስፋት ወሬዎች ሲናፈሱ እና ከመንግስትም ወገን ማስተባበያም ሆነ ማብራሪያ በተገቢው እና በአሳማኝ መንገድ አለመሰተታቸው ደግሞ ጉዳዩን በሕዝብ ዘንድ በማጽናት እና የጉዳዩን ትክክለኛነተ ከማረጋገጥ የዘለለ ፋይዳ ስለማይኖረው ዝምታው ይብቃ ፤ መንግስትም ይህን ጉዳይ ችላ እንዳይለው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በልማት ሰበብ ተፈናቅለው እና ከበቂ በታች በሆነ ካሳ ከዘመናት ቀያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች እና ሕይወታቸው ሰቆቃ ሆነባቸው አርሶ አደሮች በእርግጥም ተጠቃሚ ቢሆኑ የሚከፋው ዜጋ እንደማይኖር እሙን ነው። ነገር ግን ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጠው በድህነት እየማቀቀ ለመኖሪያ ቤት በሚቆጥበው ደሀው ሕዝብ ገንዘብ መሆኑን ግን አንደኛው መከራከሪያ ሲሆን በእርግጥስ ቤቶች ተላልፈውላቸዋል ተባሉ አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆችስ እንደተባሉት እነርሱ ናቸው ወይ የሚለው ጉዳይ በእርግጥም ማብራሪያ እና ማረጋገጫ እንደሚያሸው ሊታወቅ ይገባል።

በኦሮሞ አርሶ አደሮች ግሩም የስብዕና እና የስነ ምግባር ልክ ይህ ተላለፈላቸው የተባለው መኖሪያ ያለ አግባብ ነው ተብለው ቢሰሙት በእርግጥ ተረጋግተው በተሰጣቸው መኖሪያ ቤት እንደማይኖሩ እርግጥ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ያልፉበትን የሚመኙ አርሶ አደሮች ኦሮሞ ሕዝብ እንደሌለው ቀሪው ሕዝብም መንግስትም ሆነ የሰሞኑ የመግለጫው ባለቤቱቹም በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በመሆኑን ከቀድሞው ምክትል ከንቲባ በኩል ደሀውን የኦሮሞ አርሶ አደር ቤት ተላልፎለታል በሚል ማምለጫ ለመፈለግ መሞከር ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ከመክተት ያለለፈ ምንም ፋይዳ ስለማይኖረው ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን አቋሟን ትገልጻለች።

ይህ ጉዳይ ግን በግልጽ ካልተብራራ እና መንግስታዊ መግለጫዎች ካተሰጡበት አሁንም ጉዳዩ በይደር ቆይቶ የነገ ከፍተኛ የቤት ስራ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል። ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ›› ነው እና ተረቱ ከወዲሁ ከስር ከስር ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት እና መንግስት ወደ ሕዝብ ከመቼውም ይልቅ በመቅረብ ትርታውን ካላዳመጠ በጥቅም ተሳስረው በከበቡት አዳማቂዎች ጭብጨባ ተሸውዶ ነገውን እንዳያበላሽ እና ታሪኩን እንዳያጎድፍ አዲስ ማለዳ ምክሯን ትለግሳለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com